የእውቀት ዛፍ – የልጆች ትምህርታዊ ዝግጅት

ሠላም ልጆች እንዴት ናችሁ? አዲስ ዓመት ሊገባ ጥቂት ቀናት ብቻ ናቸው የቀሩት። እና ለአዲስ ዓመት ምን ለማድረግ አቀዳችሁ? በትምህርታችሁ ጥሩ ውጤት ያመጣችሁ የበለጠ ለመጠንከር፤ ደከም ያላችሁ ካላችሁ ደግሞ ለማሻሻል እንዳቀዳችሁ ምንም ጥርጥር የለኝም። ልጆች እናንተን እውቀት ለማስጨበጥ የመገናኛ ብዙኃን (ሚዲያ)፣ ለምሳሌ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣ፣ ሬዲዮ እና ሌሎችም ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ታውቃላችሁ አይደል? ከዚህ ቀደምስ “ትምህርት በሬዲዮ” ተብሎ የተለያዩ የትምህርት አይነቶች በሬዲዮ ይሰጡ እንደነበርስ ሰምታችሁ፤ ወይም ወላጆቻችሁ ነግረዋችሁ ያውቃል? “በሚገባ!” አላችሁ ልጆች? ጎበዞች። ስለዚህም መገናኛ ብዙኃን ከብዙ ሰዎች ጋር በተለያዩ አማራጮች ስለሚደርሱ እናንተን ጨምሮ ሌላውን ማኅበረሰብ ለማስተማር ትልቅ ኃላፊነት እና አቅም አላቸው።

ልጆች፣ አሁን አሁን ልብ ብላችሁ ካስተዋላችሁ ደግሞ ለእናንተ የሚሆኑ የተለያዩ የልጆች የቴሌቪዥን ዝግጅት እንደ አማራጭ እየቀረቡ ናቸው። ይህ በጣም መበረታታት ያለበት ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ ያሉት በቂ ናቸው ተብሎ ግን አይታመንም። ዛሬ ግን አንድ አዲስ ትምህርታዊ የቴሌቪዥን ዝግጅት እናስታውቃችኋለን።

ልጆችን ማዕከል አድርገው ከሚሰሩ ማዕከላት መካከል “ኑ ጭቃ እናቡካ የልጅነት ማዕከል” አንዱ ሲሆን፤ በማዕከሉ ልጆች እንዴት እንጀራ እንደሚጋገር፣ እንዴት ጥጥ መፍተል እንደሚቻል፣ ሥዕል እንዲስሉ፣ ጭቃ እያቦኩ የሸክላ ውጤቶችን እንዲሰሩ በማጫወት እና በማዝናናት ብዙ ነገሮችን እንዲማሩ ይደረጋል።

አሁን ደግሞ በምን መጣ መሰላችሁ? ሕፃናትና ልጆች በቀላሉ ትምህርት እንዲገባቸው እና ፊደሎችን በቀላሉ መጻፍ እንዲችሉ በተግባር የተደገፈ ትምህርታዊ ዝግጅት ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራውን ጨርሶ በአዲስ ዓመት ለእይታ እንደሚበቃ ተነግሯል። ትምህርታዊ ዝግጅቱም የሚቀርበው በካናል ፕላስ፣ በድክድክ የልጆች ቻናል ነው። ዝግጅቱ በሁሉት የሀገራችን ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ “የእውቀት ዛፍ” የተሰኘ ስያሜ ሲኖረው፤ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ደግሞ “ኦዳ ቦሩምሳ” የተሰኘ ትምህርታዊ ዝግጅት እንደሚቀርብ የዝግጅቱ ፕሮዲውሰር አቶ ዮሴፍ ወልደአማኑኤል ገልጸዋል።

ልጆች እውቀት የሚገበዩበት አዲስ የትምህርት ፕሮግራም ለማስጀመር በሚገባ ተዘጋጅተናል ያሉት አቶ ዮሴፍ፤ ከልጆች በተጨማሪም ወላጆች (ሁሉም ሰው) በሚገባ እንዲመለከተው አድርገው ማዘጋጀታቸውን፤ በዝግጅቱም ወላጆች፣ ተማሪዎችና መምህራን የተሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል።

ልጆች “የቄስ ትምህርት” ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? እንደ አሁኑ የመንግሥትም ይሁን የግል ትምህርት ቤቶች ከመስፋፋታቸው በፊት፣ በዘመኑ የነበሩ ሕፃናት ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ሀ ሁ . . . እያሉ (ፊደል እየቆጠሩ) በዛፍ ጥላ ስር ሆነው፣ ከየኔታ (መምህር) እግር ሥር ቁጭ ብለው ይማሩ ነበር። ስለዚህም የቄስ ትምህርት እንዳይረሳ በማሰብ በእውቀት ዛፍ ትምህርታዊ ዝግጅት ላይ ልጆች ከዛፍ ጥላ ሥር ቁጭ ብለው ፊደሎችን እንዲማሩ ይደረጋል። ወላጆችም አስተማሪ ከመቅጠር ይልቅ ይህንን ትምህርታዊ ዝግጅት በማሳየት ልጆቻቸውን ለማስተማር እንደሚያግዛቸው አዘጋጆቹ ይገልጻሉ። አዝናኝ በሆነ መልኩ፣ ማለትም በሙዚቃ (መዝሙር) የተለያዩ እንስሳትን ይዞ በመቅረብ እና ዛፍ ላይ የተሰቀሉ ፊደሎችን በማውረድ ስያሜያቸውን፣ እንዲሁም እንዴት መጻፍ እንዳለባቸው በቀላሉ እንዲማሩ እንደሚረዳቸው አቶ ዮሴፍ ገልጸዋል።

ዕድሜያቸው ከሦስት እስከ አስር ዓመት ላሉ ሕፃናት ታስቦ የተዘጋጀው “የእውቀት ዛፍ” ዘወትር ቅዳሜ እና እሁድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ በካናል ፕላስ ድክድክ ቻናል የሚቀርብ ሲሆን፤ የአፋን ኦሮሞው “ኦዳ ቦሩምሳ” ትምርታዊ ዝግጅት ደግሞ በጦጴ ቻናል ዘወትር ቅዳሜ እና እሁድ በተመሳሳይ ሰዓት ከመስከረም 05 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለዕይታ ይበቃል።

ስለዚህም ልጆች አጋጣሚው እና ሁኔታዎች አመቺ ከሆኑላችሁ እናንተን ሊያስተምሩ የሚችሉ፤ ብሎም እውቀት ልታገኙበት የምትችሉባቸውን ትምህርታዊ ቴሌቪዥን ዝግጅቶች ከመምረጥ እና ከመከታተል በተጨማሪ፣ አጋዥ መጻሕፍትን በማንበብ በትምህርታችሁ ጎበዝ እንድትሆኑ ይረዳችኋል። የእረፍት ጊዜያችሁንም ዘና ፈታ ብላችሁ እንድታሳልፉ ያደርጋችኋል።

 እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You