የክልሉ ቱሪዝም እንዲያንሰራራ – ተስፋ ሰጪ ጅምሮች

ኢትዮጵያ የቀደምት ዘመን ስልጣኔ ተምሳሌት፣ የራስ ባህል፣ ማንነት እንዲሁም ሉዓላዊ ግዛት ያላት ጥንታዊ ሀገር ነች። ለዘመናት የራሷን ሀገረ መንግሥት መስርታ በቀኝ ገዢ እጅ ሳትወድቅ አሁን ላይ ከመድረሷም ባሻገር የብዝሀ ባህል፣ ሕዝብ፣ ቋንቋ ብሎም የጥበብና እውቀት መፍለቂያ ምንጭ እንደሆነች የታሪክ መዛግብትና የዓለማችን ጸሐፍት ይመሰክሩላታል። እነዚህን መገለጫዎች እንድትይዝ ካስቻሏት የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ደግሞ የትግራይ ክልል አንዱ ነው።

የትግራይ ክልል በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሃብቶች የታደለ አካባቢ ነው። ጥንታዊ ቤተ መቅደሶች፣ የአክሱም ጥንታዊ ሃውልቶች፣ ከ4ኛው እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን እንደተሰሩ የሚነገርላቸው ከ120 በላይ የሚሆኑ ከአለት ድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩ ውቅር አብያተ ክርስትያናትና ገዳማት እንዲሁም ሌሎች በርካታ ታሪካዊና አርኪኦሎጂካዊ ስፍራዎች የሚገኙበት የኢትዮጵያ ክፍል ነው።

ክልሉ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግዙፍ ድርሻ ቢኖረውም፣ በሰሜኑ ክፍል የተካሄደውን ጦርነትና የሰላም እጦት ተከትሎ ተቀዛቅዞ ቆይቷል። በአካባቢው ሲካሄድ የነበረው ጦርነት እንዲቆምና ሰላም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ስምምነት መደረሱ ይታወሳል፤ ይህን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባሮች በሰላም በኩል መሻሻሎች እየታዩ መምጣቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲያንሰራራ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችም የዚህ ስምምነት አካል ናቸው። ከሰሞኑ በክልሉ የተካሄደ አንድ መድረክም ይህንኑ ጉዳይ የሚያጠናክር ሆኖ አግኝተነዋል። የቱሪዝም ዘርፉን በበላይነት የሚመራው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በትግራይ ክልል የቱሪዝም ትግበራዎችን ዳግም ለማስጀመርና ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ለመግባት ሥራዎች መጀመራቸው ተጠቁሟል፤ ሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮቹን ወደ አካባቢው መላኩን ተመልክቷል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ግርማ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን አመራሮች በመቀሌ በመገኘት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ እና ከክልሉ የባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል። በክልሉ የቱሪዝም፣ የቅርስ እና ፓርኮች ሀብቶች ልማት፣ ፕሮሞሽን አሁናዊ ሁኔታ እና በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ በመወያየት በየደረጃው በሚሰሩ ተግባራት ዙሪያ መግባባት ላይ የደረሱ ሲሆን፣ በመቐለ ከተማ የሚገኘውንም የአጼ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት ጉብኝት አድርገዋል።

ይህንንም ተከትሎ የቱሪዝም ሚኒስቴር በትግራይ ክልል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ግጭት ምክንያት ቆሞ የነበረውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዳግም ለማስጀመርና ለማነቃቃት የሚያስችል ስልጠና መስጠቱን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ክፍል አስታውቋል።

በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አፅብሃ ገብረ እግዚአብሔር ጦርነቱ ከቆመ በኋላ እንደዚህ አይነት መድረክ ሲዘጋጅ ይህ የመጀመሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህ መድረክ ለዘርፉ በርካታ ብዙ ፋይዳ ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ጠቁመዋል። ቱሪዝም ሚኒስቴር በዚህ ወቅት ይህንን የስልጠና መድረክ በማዘጋጀቱና ከክልሉ ጎን በመሆኑ አክብሮትና ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

ሌላው በስልጠና መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በግጭቱ ምክንያት የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ እንደነበር አስታውሰዋል። ተቋርጦ የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዳግም እንዲያንሰራራ እና እንዲንቃቃ ለማድረግ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቱሪዝም ዘርፎች ላይ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እንደሚሰጥ ተናግረዋል። ህልውናቸውን በቱሪዝም ዘርፍ ላይ አድርገው ይኖሩ ለነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይህ መድረክ ወሳኝ መሆኑንም ነው ያመለከቱት፤ ከነሐሴ 16 ጀምሮ የሚከበሩትን የአሸንዳ በዓላት በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ቱሪስቶች እንዲጎበኙዋቸው ለማድረግ ክልሉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እና የማስተዋወቅ ሥራ እንዲሰራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በትግራይ ክልል ለቱሪዝም ባለሙያዎች ዘርፉ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን፣ ስልጠናዎቹ በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ስትራቴጂክ አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ደርበው፣ አቶ ይስፋልኝ ሀብቴ የፕሮሞሽን መሪ ስራ አስፈፃሚ እንዲሁም አቶ መቅደላ መሰጠታቸው ተገልጿል። ስልጠናው በዋናነትም የተቀዛቀዘውን የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ማነቃቃት፣ ከመልሶ ግንባታ፣ ከመዳረሻ ልማትና ከቅርሶች ጥገና ጋር የተያያዙ ነጥቦች የተነሱበት ነበር። በተጨማሪ ስልጠናው በቱሪዝም ሚኒስቴር ባለሙያዎች እና በዩኒቨርሲቲ ምሁራን በቱሪዝም መሠረተ ልማት፣ የቱሪዝም ግብይቱን ዲጅታላይዝ በሆነ መንገድ በቴክኖሎጂ በመታገዝ መዳረሻዎችን ከማስተዋወቅ አንፃር፣ የቅርስ ጥገና እና የአገልግሎት ፈላጊዎች የብቃት አሰጣጥ ሁኔታን እና መመሪያዎቹን የተመለከቱ ሀሳቦች ተነስተውበታል።

የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው የቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዓለማየሁ ጌታቸው በመድረኩ መልካም ውጤት መመዝገቡን ገልጸውልናል። በተለይ ተሳታፊዎቹ በስልጠናው ወቅት የሰጡትን አስተያየት መሠረት አድርገው ሲገልፁ፣ ስልጠናው እንዳስደሰታቸው እና የተዳከመውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል ሲሉ አቶ ዓለማየሁ ተናግረዋል። በዘርፉ ተሰማርተው ኑሮአቸውን የሚመሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ሥራቸው ለመመለስ እንደሚያስችላቸው ነው ያስታወቁት።

“የክልሉ የቱሪዝም እንቅስቃሴ በኮቪድ ወረርሽኝና በጦርነት ምክንያት ቆሞ ነበር” የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚው፤ በዚህ ምክንያት የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃትና የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀምና በይፋ ሥራዎችን ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ይናገራሉ። በመጀመሪያ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ (የተበላሹ) የመዳረሻ ቦታዎችና የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪው እንዲያገግምና ወደ ሥራ የሚገቡበትን መንገድ ለመፈለግ የውይይት እና የስልጠና መድረክ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ይናገራሉ።

ሥራ አስፈፃሚው፤ በዘርፉ ከወደመው ሃብትና ከቆመው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ውጭ በሰው ሀብቱ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ አርፏል ይላሉ፡፡ ይህን በማነቃቀት ላይም መሥራት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። በተለየ ከሥራ ውጭ ሆኖ የቆየው የሰው ኃይልን ማነቃቃት እንዲሁም ሙያዊ ስልጠና መስጠት ማስፈለጉን አንስተዋል። በዚህ ምክንያት ይህ ሥራ በቅድመ ትግበራ ሥራው ላይ መካተቱን ይናገራሉ። ከዚህ መነሻ 450 የሚደርሱ የቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ባለሙያዎችን፣ የሆቴል ባለቤቶችን፣ ሥራ አስኪያጆች፣ የቱር ኦፕሬተር ባለቤቶችንና አስጎብኚዎችን እንዲሁም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን ያካተተ ስልጠና መሰጠቱን ይገልፃሉ።

ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት፤ ወደዚህ ትግበራ ከመገባቱ በፊት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ተቋም የሆነው የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን እና የትግራይ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ በመሆን ቡድን አዋቅሮ በቅርሶቹ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የደረሱ ጉዳቶችን ለመለየት ተችሏል። አንዳንዶቹ በቀጥታ በጦርነቱ ምክንያት የደረሱ ጉዳቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የባለሙያ ክትትል ባለማግኘታቸው ምክንያት የደረሱ ናቸው። እነዚህን ጉዳቶች ከመለየት ባሻገር በቂ ጥገናና እንክብካቤ የሚደረግበትን መፍትሔ ለማስቀመጥ ከስልጠናው ጎን ለጎን ውይይትና ምክክር እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የቅርስ ጥገና ሥራው ከፍተኛ ወጪን እንደሚጠይቅ የሚናገሩት ሥራ አስፈፃሚው፤ ከዚህ ባሻገር የሰው ኃይልና ሰፊ ጊዜን የሚጠይቅ መሆኑን ይናገራሉ። ይህንን አሟልቶ ወደ ትግበራ ለመግባት ከዩኒቨርሲቲዎች (አክሱም፣መቀሌ) እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎችም በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጨማሪ የፋይናንስ አቅምን ለማጠናከር የድጋፍ ማፈላለግና የፋይናንስ ምንጭ ልየታዎች መደረጋቸውን ይገልፃሉ።

“ከቅርስ ጥገና እና እንክብካቤ በተጓዳኝ ወደ ክልሉ የቱሪስት ፍሰቱን ለማስጀመር እየሰራን ነው” የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስፈፃሚው፤ የውጪ ጎብኚዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዛት ወደ ክልሉ እንዲሄዱ ማድረግ ባይቻል እንኳን፤ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምርና ዘርፉ መነቃቃት እንዲችል ለማድረግ ልዩ ልዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተግባር ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።

ሥራ አስፈፃሚው እንደሚሉት፤ የክልሉንና የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ግንኙነት እና የሥራ ክፍፍል በጠበቀ ሁኔታ ለማስኬድ የሚያስችሉ ተግባራት ተጀምረዋል። በተለይ በክልሉ በፌዴራል ደረጃ የሚተገበሩ እንደ ሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የሆቴሎች፣ የቱር ኦፕሬተሮች እና አስጎብኚዎች ፈቃድና ደረጃ መስጠት ጋር ተያይዞ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ኃላፊነቱን ለመወጣትና ግንኙነቱን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በተለይ የውጪ ግንኙነቶችን በማድረግ የትግራይ ክልል የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚጠቅም ፕሮጀክቶችን ለማስጀመርም በተመሳሳይ እየተሰራ ነው።

“በትግራይ ክልል የቱሪዝም ዘርፉ እየተነቃቃ ነው። ከልዩ ልዩ አካባቢዎችም ወደ ክልሉ የሚገቡ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች አሉ” የሚሉት ሥራ አስፈፃሚው ይህን በጎ ጅምር ማስፋት ላይ በጋራ ለመሥራት የተጀመሩት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። በቅርቡ በክልሉ በድምቀት የተከበረው የአሽንዳ የሴቶችና ልጃገረዶች በዓል ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ልዩ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል። በተለይ በዲጂታል ሚዲያው ክልሉ ላይ ያለውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ፣ የበዓሉን ድምቀትና ሥርዓት አስመልክቶ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ዳግም ዘርፉን ለማነቃቃት እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን እንዲጨምሩ የሚያግዝ እንደሆነ ይናገራሉ።

ሥራ አስፈፃሚው የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ከሚደረገው ጥረቶች መካከል አንዱ የማህበራትን አቅም መገንባት እንደሆነ ተናግረዋል። በተለይ በአስጎብኚነት፣ በቱር ኦፕሬተርነትና በቱሪዝም ምርት አቅራቢነት ላይ የተሰማሩ እና በማህበራት የተደራጁ አካላት የክልሉን ቱሪዝም ቀድሞ ከነበረበትም በተሻለ መልኩ እንዲነቃቃ ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ የውይይት መድረኮችና የልማት ሥራዎች እነሱን መሠረት አድርገው እየተቀረጸና ወደ ተግባር እየተለወጡ መሆኑን አስረድተዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው የሰሜኑ ክፍል ጦርነት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የቱሪዝም ዘርፉ ቆሞ ነበር። በተለይ በትግራይ ክልል የመዳረሻ ሥፍራዎች በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ቱሪዝምን መሠረት አድርገው የእለት ጉርሳቸውን የሚያገኙ ዜጎች ሥራ አጥ ሆነው ቆይተዋል። ሆቴሎች፣ ቱር ኦፕሬተሮችና መሰል የዘርፉ አንቀሳቃሾች ሥራቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል።

ይህ ለሁለት ዓመታት ቢዘልቅም በፕሪቶሪያው ስምምነት የቱሪዝም ዘርፉ ዳግም ወደ ማንሰራራት እየመጣ ይመስላል። ይህን ጅምር መሬት ላይ ለማውረድ የፌዴራልና የክልሉ ቱሪዝም ዘርፍ አመራሮች የያዙትን ርብርብ አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You