ካዳስተር የመሬት ይዞታን መሠረት ያደረገ የመሬት መረጃ ሥርዓት ነው፡፡ የሚደራጁት መረጃዎች በዋናነት ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡ አንደኛው የካርታ መረጃ (spatial data) የሚባለው ሲሆን፣ የይዞታውን መገኛ ቦታ፣ ወሰኑን፣ ስፋቱንና ቅርፁን፣ አጎራባች ይዞታዎችን እና አዋሳኝ መንገዶችን የሚያሳይ ነው፡፡
ሁለተኛው ገላጭ መረጃ (non-spatial data) በመባል የሚታወቀው ሲሆን፤ የባለይዞታውን ማንነት (ስም፣ አድራሻ፣ ጾታ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ ወዘተ) የሚያሳየው ነው፡፡ በይዞታው ላይ ያለው መብት፣ ክልከላና ኃላፊነት፣ የቦታው አገልግሎትና ደረጃ ወዘተ እንደ ካዳስተር ዓይነቱ ተዘርዝረው የሚያዙ መረጃዎችን ያካትታልም፡፡ እነዚህ ሁለት የመረጃ ዓይነቶች በልዩ የይዞታ መለያ ኮድ እንዲገናኙ ይደረጋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የሕጋዊ ካዳስተር ዝርጋታ ተግባራዊ መሆን በርካታ ፋይዳዎች አሉት፡፡ አንዱ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋለውን የተወሳሰበ ችግር በመሰረታዊነት እንደሚፈታ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዘርፉ የግብይት ሥርዓቱን ቀላል፣ ግልፅ፣ ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል። በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይም የራሱን አውንታዊ ሚና ይጫወታል፡፡
በዘርፉ በመረጃ አያያዝ ጉድለት የነበረውን ችግር ተጠቅመው ጥቂቶች አላግባብ የሚበለፅጉበትንና ሕጋዊ ባለይዞታዎች ለተለያዩ ጉዳቶች ይዳርጉ የነበረበትን የአሰራር ችግርም ይፈታል፡፡ በክልልም ሆነ በፌደራል ደረጃ በዘመናዊ መንገድ የሚደራጀው የከተማ መሬት ይዞታ መረጃ አዳዲስ ፖሊሲዎችን፣ አሰራሮችንና ሕጎችን ለማመንጨት የተሻለ ግብዓት ሆኖም ያገለግላል፡፡
የከተማ አስተዳደሮች የሚያስተዳድሩትን መሬት ቆጥረው እንዲያውቁ፣ የትኛውን መሬት ለየትኛው አገልግሎት ማዋል እንዳለባቸው አቅደው እንዲሰሩና በተገቢው መንገድ እንዲያስተዳድሩ ከፍተኛ እገዛ ያደርግላቸዋል፡፡ ከተሞች ከመሬት ሃብታቸው መሰብሰብ የሚገባቸውን ግብርና ኪራይ በተገቢው መንገድ በመሰብሰብ ለከተማው የመሠረተ-ልማት ግንባታ በማዋል ከተሞች በሥርዓቱ እንዲያድጉም ማድረግ ያስችላል፡፡ የከተማው ነዋሪም የልማቱ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
የካዳስተር ሥርዓቱ በሚፈጥረው የመረጃ ምልዑነት በከተማ መሬት ይዞታ የሚስተዋለውን በዜጎች መካከል የሚፈጠረውን ክርክር ይቀንሳልም፡፡ በዚህ ምክንያት የሚጠፋውን ገንዘብና ጊዜ ይታደጋል፤ የፍትህ መጓደልንም ይቀነሳል፡፡ ማንኛውም ዜጋ በከተማ መሬት ይዞታ ዘርፍ ማግኘት የሚፈልገውን መረጃ ብዙ ውጣውረድ ሳይገጥመው በቀላሉ እንዲያገኝም ያደርጋል፡፡
በከተሞች ደረጃ ሕጋዊ ካዳስተርን መገንባት ከተቻለ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች በከተሞቹ ላይ እምነት ስለሚያሳድሩ ሃብታቸውን ልማት ላይ ያውላሉ፤ በዚህም ነዋሪው ተጠቃሚ ይሆናል፣ ከተሞች ያድጋሉ፤ ሳቢም ይሆናሉ፡፡ ይሁንና ዘመናዊ የመሬት መረጃ አያያዝና ምዝገባ ካዳስተር ሥርዓት የመዘርጋት አፈጻጸም ዝቅተኛ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ በከተማ መሬት የካዳስተር ምዝገባም እንዲሁ በሀገር ደረጃ አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ አንጻርም የከተሞች የመሬት አስተዳደርን የማዘመን ሥራ ገና በጅምር ላይ ይገኛል።
ከዚህ አኳያም አንዳንድ ከተሞች ምሳሌ መሆን በሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሆኑ መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ከተሞች ውጤታማ ትግበራ እያስመለከቱም ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከተሞች መካከልም 54ሺህ301 ሄክታር ስፋት ያላትና በስድስት ክፍለ ከተሞችና 19 ወረዳዎች የተዋቀረችው አዳማ ከተማ ትጠቀሳለች፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ የ2016 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማ ከተማ ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የስምጥ ሸለቆዋ እንቁ አዳማ ከተማ በተለይ የ2015 የመሬት ሪፎርም ሥራ አፈፃፀም በምርጥ ተሞክሮነት ቀርቧል፡፡
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሐይሉ ጀልዴ በመድረኩ ተገኝተው በከተማዋ ካዳስተርን ለመተግበር የተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሔዎችን እንዲሁም በአፈጻጸሙ የተገኙ ውጤቶችና ተሞክሮዎችን በሚመለከት ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፣ እኛም ይህን ተሞክሮ በሚከተለው መልክ አሰናድተን አቅርበነዋል፡፡
የዝግጅት ምዕራፍ
ካዳስተርን ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ አመራር፣ በጀት እና ብዙ ባለሙያ መኖርን የግድ ይላል፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ በዝግጅት ምዕራፍ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ዕቅድ እና አስፈፃሚ አካላትን የማዘጋጀት፣ ግንዛቤን የመፍጠር፣ ተጨማሪ ክፍሎች የማዘጋጀት፣ ለሥራው አስፈላጊ ሎጂስቲክ በተቻለ መጠን የማሟላትና የሰው ኃይል የማዘጋጀትና የማሰማራት እንዲሁም የመቆጣጠር ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በሥራ ሰዓት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ሃሳብ ማቅረብና መግባባት ላይ መድረስም አንዱ ተግባር ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊትም ጭምር የሚሰራ ሠራተኛ መፍጠር የተቻለበት ነው፡፡ በሳምንት ሁሉም ቀናት ለ24 ሰዓት ለመሥራት ከስምምነት ላይ የተደረሰበትን እድል የፈጠረም ነው፡፡ በአጠቃላይ ለካዳስተር ሥራ ምቹ ሁኔታዎችን የፈጠሩ ተግባራት የተከናወኑበት እንደሆነ መውሰድ ይቻላል፡፡
ከዚህ ባሻገር የከተማዋ አመራር፣ ከስድስት ክፍለ ከተሞችና 19 ወረዳዎች እንዲሁም ከመሬት ሴክተር ባለሙያዎች፣ በጎ ፈቃደኞች፤ ማህበራትና በሁሉም ክፍለ ከተማና ወረዳዎች ከሚገኙ የማህበረሰቦች ክፍሎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይትና ግምገማ የተለዩ ችግሮች
ካዳስተርን ተግባራዊ በማድረግ ሂደት በተደረገ ውይይትና ግምገማ ችግሮች ተለይተዋል፡፡ በተለይም የከተማው የመሬት መረጃ እና ፋይል አያያዝ ችግር ያለበት መሆኑ ታይቷል፡፡ በዚህ የተነሳም የባለጉዳዮች ምልልስ ጎልቶ እንደሚስተዋል መመልከት ተችሏል፡፡ ነባር ይዞታዎችን ሕጋዊ አድርጎ አለመጨረስ፤ በሕጋዊ ካዳስተር ላይ በአመራሩ፤ በባለሙያና በሕዝብ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ የቀደመው አመራር በቁርጠኝነት መሬትን በብቃትና በሙሉ አቅም አለመምራት፣ ያለውን የሰው ኃይል በእኩልነት ያለመጠቀም፣ የዋና መሥሪያ ቤት፣ ክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ ሥልጣንና ሚናዎች ክፍፍል አለመኖር፣ የሕዝቡን የመሬት ጥያቄና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ዝግጁ አለመሆን፣ ከከተማው መሬት ላይ የሚገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑ የሚሉት ከተለዩ ችግሮች መካከል ናቸው፡፡
የመፍትሔ አቅጣጫዎች
በከተማ፣ ክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ ያለው የሥራና የሰው ኃይል ሚና ተለይቶ ተሰጥቷል፡፡ በዚህም 28 ሠራተኞች ወደ ወረዳ እንዲወርዱ፣ በአጠቃላይ ከ436 ሰዎች በሥራው እንዲሳተፉ ተደርገዋል፡፡ የካዳስተር ሥራ ልዩ ዕቅዶች ተዘጋጅቶለታል፡፡ ካዳስተር በክፍለ ከተማ ደረጃ እንዲሰራና ሁሉም አመራር ባለቤት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የመሠረተ ልማት ሥራ ቀድሞ መሥራት እንዳለበትና በተለይም በርካቶች ካዳስተርን በተንሸዋረረ እይታ የሚመለከቱበት እይታን ለመቀልበስ ችግሩን የሚመጥን የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በስፋት ተሰርቷል፡፡
ቅድመ ዝግጅቶቹን በማጠናቀቅ በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለመግባትም የሥራ ቦታ ለሠራተኞችና ለደንበኛው ምቹ የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ለካዳስተር ሥራ ተጨማሪ ክፍሎች ተሰርተዋል፡፡ ሁሉም የከተማው የወረዳዎች እና ክፍለ ከተማዎች የተናጠል መዝገብ ቤት እንዲኖራቸው በማበረታታት የመዝገብ አያያዝ ተሻሽሏል።
ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ገለልተኛ ቢሮ እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ እንደ ፍርድ ቤት፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ኮንስትራክሽንና ሥራ ዕድል ፈጠራን የመሰሉ ጽህፈት ቤቶች ከአስተባባሪ ዘርፎች ጋር በመግባባት እንዲሰሩ ሆኗል። በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚከናወኑ ቁልፍ ተግባራት እና የእለት ተእለት ተግባራት ተለይተዋል። በአጠቃላይ የሥራ ቦታዎች በከተማው ዋና መሥሪያ ቤት፣ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ ምቹ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
በአፈፃፀም ምዕራፍ
የመሬት ማስረጃዎችን ዲጂታል ማድረግ እና የመሬት ማስረጃዎች ቆጠራ ረገድ በተከናወኑ ተግባራት 117 ሺህ488 የሚሆን የመሬት ፋይል ዲጂታላይዝ ማድረግ ተችሏል፡፡ የሲስተም አገልግሎት ከከተማ እስከ ወረዳ ተግባራዊ ተደርጓል። በ2015 ዓ.ም ሕጋዊ ካዳስተር አፈጻጸም ቅየሳና ማካለል ረገድ በእያንዳንዳቸው 18 ሺህ 500 ታቅዶ 32 ሺህ 057 ማከናወን ተችሏል፡፡
በይዞታ ማረጋገጥ ረገድ 17 ሺህ 500 ታቅዶ አፈፃፀሙ 39 ሺህ 722 ሆኗል፡፡ በርክክብ የታቀደው ደግሞ 17 ሺህ 500 ሲሆን፤ አፈፃፀሙ 36 ሺህ 909 መሆን ችሏል። ወደ ሲስተም የገባው ሲታይ ደግሞ 13 ሺህ125 ታቅዶ አፈፃፀሙ 37 ሺህ 505 ነው፡፡ እንዲሁም የካዳስተር ካርታ 13 ሺህ125 ታቅዶ 21 ሺህ 536 መፈፀም ተችሏል። አሁን ላይ የታቀደው ሥራ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ተጠናቋል፡፡
ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮም በአዳማ ከተማ የመሬት አገልግሎት በካዳስተር ብቻ እንዲሰጥ ውሳኔ ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ ማለት ግን ቀሪ ሥራዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ለአብነት በካዳስተሩ ካልገቡት መካከል ሕገ ወጥ ግንባታ፤ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዙ መሬቶችና አዲስ የገቡ ከተሞች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና ተመዝግበው ግን የሚቀመጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ወጪ እና ገቢ
የውጤታማ የካዳስተር አገልግሎት መተግበር የራሱን ገቢም ያመጣል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት ሰላሳ ሚሊዮን ብር በመመደብ 53 ሚሊዮን ብር ለማስገባት እቅድ ተይዞ ነበር። ይሁንና በውጤታማ አፈፃፀም 151 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡፡
አሰራሩ ከገቢ ባሻገር ሕግን በማስፈን ረገድ በተለይም ከአስርና ሃያ ዓመታት በላይ ያለግባብ የተያዙና የተቀመጡ መሬቶችን ማጋለጥ አስችሏል፡፡ በዚሁ መሠረት በትርፍነት ተይዘው የተገኙ ቦታዎች ወደ ሲስተም እንዲገቡ ተደርጓል። የገቡትም 31 ሄክታር፤ በሂደት ላይ ያሉ 40 ሄክታር ለይቶ ማወቅ ተችላል፡፡ ይህ ስኬት የተለያዩ ተግባራትና ውሳኔዎች ድምር ውጤት ነው፡፡ የካዳስተር ሥራ የሚደግፍ አካል ከከንቲባ ፅህፈት ቤት እና ከፓርቲው ከመመደብ ጀምሮ ሥራው በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ደረጃ እንዲወርድ ተደርጓል፡፡ ሥራን ቆጥሮ መስጠትና ቆጥሮ መረከብ እንዲሁም ሥራውን ለማደናቀፍ የሞከሩ አመራሮችንና ባለሙያዎችን ከቦታው የማንሳት ውሳኔም ተላልፏል፡፡፡
ክትትልና ድጋፍ
የሥራውን ሁኔታ ለመፈተሽ እና በቦታው ላይ አስተያየት ለመስጠት በየጊዜው ምልከታና የሥራ ግምገማ ተካሂዷል፤ ግብረ-መልስም ተሰጥቷል፡፡ በተለይ የሲስተም ችግሮች ባጋጠሙ ቁጥር ከSMART አዳማ ጽህፈት ቤት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ኢንሳ /INSA/ ጋር በመሥራት የማስተካከል ሥራ ተከናወኗል፡፡ በእያንዳንዱ ሥራ የተከሰቱት ችግሮች ወዲያውኑ እንዲፈቱ ሆነዋል፡፡
የባለድርሻ አካላትና የሕዝብ ድጋፍ
ወደ ሥር በመግባት ሂደት ለካዳስተር ሥራ ውጤታማነት የፌዴራልና ክልል ተቋማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡ ባለሙያዎችን ማሰልጠንን ጨምሮ የተለያዩ ግብዓቶችንና መሠረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከልም የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኦሮሚያ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን፣ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ይጠቀሳሉ፡፡
ለካዳስተር ሥራ በሚያግዙ ዕቃዎች ዝግጅት፣ በሎጂስቲክ ረገድ የማህበረሰብ ተሳትፎ ከፍተኛ የሚባል አቅም የፈጠረ ነበር፡፡ በተለይ በዜግነት አገልግሎት የነበረው የሕዝብ ተሳትፎ በገንዘብ ሲተመን 66 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በሰው ኃይል አበርክቶም ከ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ይሆናል፡፡
የተለያዩ ተቋማትና ከተሞች እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮች የአዳማን የመሬት ካዳስተር ሥራ ለመቃኘትና ልምድ ለመውሰድ ተደጋጋሚ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ የኦሮሚያ መሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጉታ ላቾሬና የልዑካን ቡድናቸው እና የሸገር ከተማ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የከተማ ልማትና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በአዳማ ከተማ የመሬት ካዳስተር ሥራን እንዴት መደገፍ እንዳለበት በአካል በመገኘት ጭምር ምልከታ አድርገዋል፡፡
የተገኙ ልምዶችና ውጤቶች
ለመሥራት ቁርጠኝነት ካለ እንደሚቻል፣ የበጀት እጥረት መሥራት እንደማይከለክል ትምህርት ተወስዶበታል፡፡ የከተማዋ ገቢ በ2014 በጀት ዓመት ሦስት ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2015 በጀት ዓመት ግን አምስት ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እስከ ሰኔ 30 ድረስ አምስት ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህ ማለት በተሰራው ሥራ የአዳማ ከተማ ገቢ ጨምሯል፡፡ በሳምንቱ ሁሉም ቀናት 24 ሰዓት በመሥራት የሥራ ባህል ለማሻሻል እንደሚቻል እድል ተገኝቶበታል፡፡ አገልግሎት ለማዘመን በር ከፋች መሆኑ በተጨባጭ ማረጋገጥ አስችሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር በካዳስተር ሥራ ውስጥ ብዙ ተተኪ መሪዎች ተፈጥረዋል፡፡
ያጋጠሙ ፈተናዎች
የመረጃ ጥራት ችግር፣ በካርታ ላይ ሌላ ካርታ ያላቸው ቦታዎች መኖሩ፣ ሕገ ወጥ ግንባታ ውስጥ ለውስጥ መፈጠሩና በብሎክ ብቻ ተወስኖ መሥራት፣ በሕግ የተያዙ ዕግዶች ቶሎ መፍትሔ አላማግኘት፣ የቁርጠኝነት ችግር፣ ያለው ሕግ አንዳንድ ነገሮች ላይ የማያሰራ መሆኑ ግንባር ቀደም ፈተና ሆነው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በቀጣይ ዓመት
በ2016 በጀት ዓመት ከከተማዋ ገቢ 13 ነጥብ 02 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዳል፡፡ በ2016 ዓ.ም ሌላኛው የሚሰራው ሥራ ከ2015 ዓ.ም የተንከባለሉ ቀሪ ሥራዎን መጨረስ እና አዋሽና ወንጂን ጨምሮ ካዳስተርን ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል፡፡ ገቢን ማሳደግ ወሳኝ ሥራ ሆኖ የተለየ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱም 583 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዳል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2015