ፊርማና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ፣
መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ።
(ቃል-ግጥም)
“መተማመን” እንደ ቃሉ አጠራር ወይም በሶስት ጎልተው በሚሰሙ የአንድ ፊደል ዘርና የከንፈር ድምፅ (“መ”) ላይ እንደ መመስረቱ ቀላል አይደለም። የሰው ዘር ባለበት ሁሉ ያለ፤ ምንም አይነት መልክአምድራዊ ሁኔታዎች የማይገድቡት፤ ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ ወዘተርፈ የማይለይ “ግዙፍ”፣ ሰው ተኮር ጽንሰ-ሃሳብ ነው።
ከላይ በመግቢያ ቃል-ግጥማችን ለመመልከት እንደሞከርነው፤ ወይም ቃል-ግጥሙ እንዳረገዘው ጥልቅ እሳቤ ከሆነ ከማንኛውም ማረጋገጫ፣ ፊርማም ሆነ ሰነድ የሚበልጠው፤ ያለ አቻም በብቸኝነት የሚቆመው “መተማመን” ብቻ ነው። ሌላው ሁሉ ተሰብስቦ ቢደመር “መተማመን”ን አያክልም ማለት ነው – እንደ ቃል-ግጥሙ ድምዳሜ።
በፈለፈልነው ቁጥር ከቃል-ግጥሙ የምናወጣቸው፤ ወይም የምንረዳቸው በርካታ ሚዛን የሚደፉ አስተሳሰቦችን ቢሆንም፤ የተወሰኑትን እንኳን እንመልከት ብንል፣ ወዳጅነት ከሚፀናባቸው፤ አብሮነት ከሚገነባባቸው ሁሉ ዋናው “መተማመን” ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በሙሉ ፋይዳ ቢስ፤ ወይም፣ “ተቀዳጅ” እና ተጣይ ሆነው ነው የምናገኛቸው። ያ ባይሆን ኖሮ “ብቻ” እዛ ውስጥ ገብቶ፣ ተገቢ ቦታውንም ይዞና “መተማመን”ን አፅንቶ ባላገኘነውም፤ የቃል-ግጥሙ ዋልታና ማገር ሆኖም ባላቆመው ነበር። (እዚህ ላይ “የማይተማመን ጓደኛ በየወንዙ ይማማላል” የሚለውንም ምሳሌያዊ አነጋገር (ሀገራዊ ፍልስፍና) እዚህ ጋ አካቶ ቃል-ግጥሙን ማወፈር ይቻላል።)
በመጽሐፍ ቅዱስ ለማመን ሶስት አካላት ባሉት አንድ አምላክ ማመን ግድ የሚል መሆኑ የእምነቱ ተከታዮች የተቀበሉት ሲሆን፤ ይህ በሌሎች ሃይማኖቶችም ተመሳሳይ ስለመሆኑ ከእለት ተእለት ማህበራዊ ሕይወትና አኗኗር መረዳት ይቻላልና እዚህ ሰፋ አድርጎ መሄዱ ብዙም ስያስፈልግ ወደ “ፊርማና ወረቀት … “።
ፊርማና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ፣
መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ።
በአንጓው መሠረት “ፊርማ” እና “ወረቀት” ሰው ሰራሽ እና ዘመን አመጣሽ ማሰሪያ-ማስተሳሰሪያዎች፤ የብልጣብልጥ ተግባርና መሸዋወጃ እንጂ መንፈሳዊም ሆነ ህሊናዊ ልእልናን ተችረው ወዳጅነትን ያፀኑ፤ አብሮነትን ያዳብሩ፤ ፍትህና ርትእን ያሰፍኑ ዘንድ ማዕረጉ የላቸውም። በቃል-ግጥሙ “መተማመን” እንጂ “መፈራረም” ዋጋ ቢስ ሲሆን፤ ወረቀትም ያው ሆኖ ነው የምናገኘው።
እንደ ቃል-ግጥሙ ለወዳጅነት ተፈጥሯዊው ልብ እንጂ፣ ከሱው የሚመነጨውና “ብቻ”ውን በቂ መሆኑ የተመሰከረለት “መተማመን” እንጂ የወረቀት ክምር ቤት አይሰራም። የፊርማ ጋጋታ ወንዝ አያሻግርም። ባይሆን ኖሮ “ፊርማ”ም ሆነ ወረቀት በ“ብቻ” አማካኝነት ባልተገፈተሩና ከወዳጅነት ጨዋታ ውጭ ባልሆኑም ነበር።
ይህን ቃል-ግጥም በዚህ “ዘመናዊ” እየተባለ በሚቆላመጠው ዓለም የበለጠ ተአማኒነት ያለው ሆኖ የምናገኘው፤ በ“ብቻ” አማካኝነት “ወረቀት” እና “ፊርማ” ከወዳጅነት ጨዋታው ውጭ ሆነው እየተመለከትን መሆኑ ሲሆን፤ ለዚህም ማረጋገጫችን ፊርማዎችና ወረቀቶች በየቀኑ እየተቀዳደዱ ሲጣሉና የትም ሲቀሩ ብቻ ሳይሆን፤ መተማመን ጠፍቶ ዓለም በየሰዓቱ ወደ እቶን እየሄደች በማየት ላይ መሆናችን ነው።
ፊርማና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ፣
መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ።
የሚለውን ዘመን ተሻጋሪ ቃል-ግጥም (ስሟን የዘነጋኋት ድምፃዊት ቃል ግጥሙን ወደ ዜማ አምጥታዋለች) ምን ያህል ትክክል መሆኑን የምናረጋግጠው፤ የቀድሞው የቃል-ግጥሙ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ምን ያህል አርቆ አሳቢና መጪውን ተንባይ መሆኑን የምንገነዘበው በዚህች፣ በዛሬዋ ዓለም ምን ያህል ፊርማዎች ገና ቀለማቸው ሳይደርቅ ሲካዱና ምን ያህል የፊርማ ወረቀቶች እየተበጫጨቁ ወደ “ጋርቤጅ” ሲወረወሩ እያየን መሆኑን ልብ ስንል ነው።
ፊርማና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ፣
መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ።
በተለይ በዚህ በዘመናዊ ተብዬው ዓለም (“ድሮ የሠርግ መኪና ጡሩምባ ነበር በብዛት የሚሰማው፤ ዘንድሮ ግን ያለ መቋረጥ የሚሰማው የአምቡላንስ መኪና ጡሩምባ ነው”፤” ድሮ ጠዋት ጠዋት በየሱቁ የሚወርሰው ዳቦ፣ ዛሬ – ጫት”፤ “ድሮ ከማንም ቀድሞ በየበሩ ከተፍ የሚለው ወተት – ዛሬ ድራፍት” – – – የሚለው ዘመናዊውን ዓለም ከሚገልፁት መካከል ጥቂቶቹ መሆን ይችላሉ) አብዝተን ከምንመለከታቸው፤ አዝወትረን ከምንሰማቸው… ዜና-ዘገባዎች መካከል ሰፊውን የአየር ሰዓትና የገጾች ብዛት ይዘው ከምናገኛቸው የዓለም ሁነቶች መካከል ቀዳሚዎቹ የፊርማዎች መሻር-መካድና የወረቀቶች (የስምምነቶች ማለትም እንችላለን) መቀደድና መቀዳደድ ናቸው።
(በአዲስ አበባ ከጋብቻው ቁጥር የፍቺው ቁጥር መብለጡ የሚያሳየን ምን እንደ ሆነ ማንም ያውቀዋል። የዓለማችን የጦርነቶች ቁጥር እየጨመረ የመሄዱን ምክንያት ህሊናችን ከነምክንያቱ አሳምሮ ይገነዘበዋል። በዓለማችን የሰላም ቀጣናዎች እየቀነሱ፤ የግጭት ቀጣናዎች እየጨመሩ የመሄዳቸው ጉዳይ የመተማመን መጥፋት ማሳያዎች እንጂ ሌላ ምንም ሊሆኑ አይችሉም። ለዚህ ደግሞ እየደገመና ተደጋግሞ ፊርማና ወረቀት ከሚቀዳደድባት ደ/ሱዳን በላይ ማሳያ የለምና ይህንን በቅንፍ አስቀምጠን ማለፍ የሚከለክለን ካለ አሁንም የመተማመን ችግር አለ ማለት ነው።)
ፊርማና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ፣
መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ።
ፈረንጆች “ማይ ቦዲ” እንደሚሉት፣ “ወዳጅ” ማለት የልብ ሰው (ደራሲው እውቅ ሥራቸውን “ወዳጄ ልቤ” ሲሉ እንደ ሰየሙት ሁሉ) ሲሆን ደረጃውም ከ“ጓደኛ”ነት ይልቃል። አንድ ሰው አንድን ሰው “ወዳጄ” ካለው የሁለቱ ግንኙነት ከተራ ትውውቅ የዘለለ፤ ከጓደኝነትም የላቀ፤ በከፍተኛ መተማመን ላይ የተመሰረተ ሰብዓዊ ተግባቦት ደረጃ ላይ የደረሰ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ወዳጄ!!! (በሀገራችን ላይ፣ ሀገራትም “ወዳጅ” እንዳላቸው ከ“ወዳጅ ሀገር(ራት) – – -” መረዳት ይገባል።
(ከዜማና ግጥምም ባለፈ፤ ከ”ወዳጄ” እና “My body” በዘለለ መተማመን በፍልስፍናውም ዘርፍ (Philosophical Dimensions of Trust) በሚገባ ተገላብጦ የተፈተሸ፣ የተመረመረ፣ ትርጉሙ፣ ጽንሰ-ሀሳባዊ ብያኔው (Conceptual Nature of Trust)፣ ጥቅሙ (Trustworthiness)፣ ዋጋው (Value of Trust)፣ ከአስተሳሰብ አኳያ (Mental Attitude)፣ ሥነ እውቅታዊ ይዞታው (Epistemology of Trust) ሁሉ የተብጠለጠለ፤ ወደፊትም በዚሁ ብቻ ሳይሆን (የበለጠ እያስፈለገ ከመሄዱ አኳያ) እየተገላበጠ የሚታይ ጉዳይ ነው። (እያንዳንዳቸውን በተመለከተ የተለያዩ ፈላስፎችን አመለካከትና ትንታኔ፤ እንዲሁም፣ ለበለጠ ግንዛቤ “Stanford Encyclopedia of Philosophy”ን መመልከት በጣም ጠቃሚ ነው – ኦንላየን ላይም ይገኛል።)
የእምነት ተግባር የሆነው መተማመን ብዙ ጊዜ ከሚስተዋልባቸው አካላት መካከል በንግድ ሸሪኮች፣ በትዳር አጋሮች፣ በጓደኛሞች፣ በፖለቲከኞች፣ በሕዝብና መንግሥት፤ በከሳሽ/ተከሳሽ እና በጠበቃ ወዘተ መካከል ሲሆን፤ በሀገራት መካከልም ችግሩ ሲከሰት ይስተዋላል።
ለምሳሌ ያህልም በሀገራት መካከል መተማመን ሲኖር በሰላም አብሮ መኖር ይመጣል። መተማመን ካለ ያለፈ ቁርሾን መርሳት ይመጣል (ለምሳሌ ሩዋንዳ)። መተማመን በሚኖርበት ጊዜ “ይቅር ለእግዚአብሔር” መባባሉ ቀላል ይሆናል። ጉዳዩን የበለጠ ለመረዳት፣ ወደ ኮሪያ እንዝለቅ።
በአንድ ወቅት እሳትና ጭድ የነበሩትንና በእርስ በርስ ጦርነት የተቆራቆሱትን ሁለቱን ኮሪያዎች ወስደን ብንመለከት ከፊርማና ወረቀት ይልቅ መተማመን ተገቢውን ስፍራ ይዞ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ … ፋይዳ ኖሮት፤ ሰላምን አስፍኖ እንመለከታለን።
የሁለቱ ጦርነት (1950 እስከ 1953) ከቆመ ወዲህ በሁለቱ መካከል ያለው ሰላማዊ ኑሮ በብዙዎች በምሳሌነት ይጠቀሳል፤ የ”መተማመን” ማሳያም ሆኖ ይነገርለታል። በተለይ የደቡብ ኮሪያ በዚህ ደረጃ መመንደግ ብዙዎችን ድንቅ ያስባለ ሲሆን፤ ሰሜን ኮሪያም፣ በተለይ በጦር መሳሪያ የምትታማ አይደለችም ነው የሚባለው። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ሁለቱም ያንን ሁሉ ረስተው በመልካም ጉርብትና መኖር በመቻላቸው ሲሆን፤ ለዚህም ያለ ምንም ፊርማና ውል፣ ያለ ምንም ሶስተኛ ወገን አስታራቂነት፤ በመተማመን ላይ ብቻ የተመሰረተ፤ በመካከላቸው ምንም አይነት ግጭት የሌለበትና ሊኖርበትም የማይገባ “የሰላም ቀጣና” እንዲኖር መስማማታቸው ነው። (ዝርዝሩ ብዙ በመሆኑ ከተገቢ ምንጮች ማየት ይቻላል።)
ከላይ እየተመለከትን እንደመጣነው፣ መተማመን (Trust) ወደ ውጭ ብቻ የሚመለከት ፅንሰ-ሀሳብ አይደለም፤ ራስን፣ ውስጥንም ይመለከታል። ባይሆን ኖሮ “በራስ መተማመን”፤ “በራሱ የሚተማመን / የማይተማመን” ወዘተ የመሳሰሉት አገላለጾች በእለት ተእለት ሕይወትና አኗኗራችን ውስጥ ተደጋግመው ባልተሰሙ ነበር።
መተማመን ከምስጢር አያያዝ፣ ከመልካም ሥነ ምግባር፣ ከመልካም አስተዳደር፣ ከሕግና ሥርዓት፤ ጉርብትናና ቤተሰባዊነት… ጋር የማያሻማ፣ ጥብቅ ግንኙነት ያለው እንደ መሆኑ መጠን፤ ሁሉም ልክ የሚሆነው መተማመን ሲኖር እንደሆነ ማንም ከሕይወት ተሞክሮ የሚገነዘበው ጉዳይ ነው።
መተማመን ኃላፊነትን ከመውሰድ፣ ኃላፊነትን ከመሸከም፣ ከግል (ቡድን) ውሳኔ ሰጪነትና ተቀባይነት፤ የፈቃደኛ ልብ ባለቤት፤ እውነተኛ ከመሆን፣ ጤናማ ሕይወትን ከመመራት፣ ከሀገር ፍቅር፣ የሕዝብ አገልጋይነት፣ ሠላማዊ ሕይወትን ከመኖር፤ ብቸኛና ተጠራጣሪ (Isolated and suspicious) ሆኖ ካለመኖር ጋር ሁሉ የሚገናኝ ሲሆን፤ መተማመን ለማንም ይሁን ለማን፤ በማንኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም ዘርፍና ክፍል እጅጉን ያስፈልጋል ማለት ነው።
መተማመን ከራስም አልፎ ሌላኛውን ወገን እስከማመን ድረስ የሚዘልቅ፤ ከመታመን የሚመጣ አእምሯዊ ሁኔታ ሲሆን፣ ካለመታመን መተማመን በፍፁም ሊገኝ አይችልም። መታመን ደግሞ እንደ እንቁላል ወይም ብርጭቆ ነው፤ ከእጅ ካመለጠና ከወደቀ ተመልሶ ንብረት አይሆንም።
የመተማመን አለመኖር መነሻው አለማመንና አለመተማመን ሲሆን፣ የአለመተማመን ምንጩ ደግሞ ስር የሰደደ የመተማመን ፍርሀት (pistanthrophobia) ነው። ይህም ወደፊት አደጋ ሊያደርስብኝ ይችላል፤ ሊክደኝ ይችላል… ከሚል ስጋት የሚመነጭ ፍርሀት። (“እመን እንጂ አትፍራ”ን እዚህ ጋ አምጥቶ ከዚህ አይነቱ ፎቢያ መገላገል ይቻላል የሚሉ አሉ።)
ካገላበጥናቸው የምሁራን ሥራዎች መረዳት እንደቻልነው፣ መተማመን ሥነ ልቦናዊ ነው፤ መተማመን ማህበራዊ ነው፤ መተማመን አእምሯዊ ሂደት ነው፤ መተማመን ራስን ከሌላው ሰው (አካል) ጋር ማስማማት ነው፤ መተማመን ራስንም ሌላውንም ማመን ነው። መተማመን የግጭት በርን ዘግቶ የሰላም በርን መክፈት ነው። መተማመን ከራስ አልፎ ለሌላውም ማሰብ ነው። መተማመን የጋርዮሽ ተግባር ሲሆን በተናጠል ማመን እንጂ መተማመን የለም። መተማመን የፍቅር ሁሉ፣ የሰላም ሁሉ፣ የሰብዓዊ ተግባራት ሁሉ፣ የእምነት ሁሉ… እምብርት ሲሆን፤ ፋይዳውም ለሁሉም ነው። ከኢኮኖሚ አኳያም ቢሆን “መተማመን” ጥቅሙ ቀላል አይደለም ለዚህ ደግሞ “trust fund” የሚለው ጥሩ ማሳያ ነው።
ፊርማና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ፣
መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ።
ይህ (ካስፈለገ ቃል-ግጥሙን “‘ሰው ማመን ቀብሮ ነው’ አለች…” በሚለው ኢትዮጵያዊ አባባል ማደንደን፤ ካልሆነም በአብዱ ኪያር አንደኛውና በተለይ ባቀነቀነው “ማንን ልውደድ / ማንን ልመን” ዜማ ማቅጠን ይቻላል) የራሳችን የሆነው፣ ዘመን ተሻግሮ እዚህ የደረሰውና ገና ወደፊትም ብዙ ዘመናትን እየተሻገረ የሚዘልቀው ቃል-ግጥም፤ እኛን፣ እራሳችንን፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሲሆን፤ ለዚህ ማሳያው ደግሞ ሰሞኑን የኢትዮጵያ የሰላም እና እርቅ ኮሚሽን ወደ ጦርነት ለገቡት ወገኖች ያስተላለፈውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ የመጣውና በከፍተኛ ደረጃ እያነጋገረ ያለው “ያለመተማመን ጥያቄና የመተማመኛ ፍለጋ” ጉዳይ ነው። ዝርዝሩን በሌላ ጽሑፍ የምንመለስበት ይሁንና ለዛሬ በሚከተለው ሃሳብ እናብቃ።
መተማመን ስትራተጂካሊ ማሰብን ይጠይቃል፤ ተስፋ መሰነቅን፣ የወደፊቱን ዓለም ከወዲሁ ብሩክ አድርጎ ማየትን፣ የተሻለ ነገን መጠበቅን፣ ሰብዓዊ ርህራሄን፣ ባለራእይ መሆንን፣ ከተሳሳተና ጠቅላይ ከሆነ (ለምሳሌ በዚህ ምድር ላይ የሚታመን ሰው የለም (ባለሙያዎች ለችግሩ ማሳያ “No one can be trusted”, “The world is a dangerous place” የሚሉ ምሳሌዎችን እንደሚያቀርቡት) ከሚል) ድምዳሜ መራቅን፤ ለራስ ቀና አመለካከት መኖርን፣ የሞላውን ማጉደልን ሳይሆን የጎደለውን መሙላትን፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው… አለመሆንን… ሁሉ የሚጠይቅ ታላቅ ሰብዓዊ ተግባር ሲሆን፤ ሰዎች፣ ቡድኖች፣ ማህበረሰቦች፣ እንደ አጠቃላይም ሕዝቦች ወደ መተማመን በመምጣት ሕይወትን ጣፋጭ፣ ኑሮን ሰላማዊ ያደርጉ፤ ተያይዘው ከመስጠም ተያይዘው መንሳፈፍ ላይ ያተኩሩ ዘንድ ይመከራሉ።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2015