ዓለም ከሚታመስበት ግን ደግሞ መፍትሔ ከጠፋላቸው ችግሮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተላቸው ተፈጥሯዊ ክስተቶች ሲፈተኑ ይስተዋላል፡፡ የምድራችን ሙቀት መጠን ከቀን ቀን በመጨመሩ የተነሳ በየቦታው ድርቅ እየታየ ነው፤ በርካታ ነፍሳት ከምድር ላይ እየጠፉም ይገኛሉ። በውቅያኖሶች መጠንም የሚስተዋለው አሉታዊ ለውጥ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ በአሁን ወቅትም ብዙዎችን መቆሚያ መቀመጫ እያሳጣቸው ነው፡፡
እንደ አፍሪካ ያሉ አህጉራት ዘመኑን የሚመጥን የአየር ንብረቱን ሊጠብቁ የሚችሉ ፋብሪካዎችን እና መሳሪያዎችን ባለመጠቀማቸው ሳቢያ በካርቦን ልቀት በሚፈጠሩ ችግሮች በእጅጉ ይፈተናሉ፡፡ ይሁን እንጂ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣው ችግር የአፍሪካ ብቻ ሆኖ አይቀርም፡፡ ላደጉት ሀገራት ጭምር ይተርፋል፡፡ ስለዚህ በጋራ በመሥራት ለችግሩ እልባት መስጠት ይገባል፡፡ ለዚህም ነው በርካታ ሀገራት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2050 የካርበን ልቀት መጠኑን ዜሮ እናደርጋለን በማለት እየተጉ የሚገኙት፡፡
የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችንም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የአየር ንብረትን በመጠበቅ ዓለማችን ከደረሰችበት ዘመናዊ አሰራር ጋር እንዴት አጣጥሞ መሄድ እንደሚገባ እናስቃኛችኋለን፡፡ ለዚህም ሊቲየም የተባለው ማዕድን ለአየር ንብረት ጥበቃ ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ዘመኑን የመጠነ ግብዓት መጠቀምና የአየር ንብረትን መጠበቅ ካስፈለገ አንዱ መሳሪያችን ይህ ማዕድን ነው፡፡ በርካታ ሀገራትም ይህንን ተገንዝበው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ልትሰራበት እንደሆነ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ባለው መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡
የተለያዩ የከበሩ ማዕድናትን መላው ዓለም ይፈልጋቸው እንጂ ሀብትነታቸው በጥቂት አካባቢዎች ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ በርካታ ማዕድናት ከሚገኘባቸው ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ ነች። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ያሏትን ሀብቶች ብቻዋን ለማውጣትና ጥቅም ላይ ለማዋል በእጅጉ ትፈተናለች። ከሌሎች ካደጉ ሀገራት እውቀት፤ መሳሪያና ገንዘብን የምትሻውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
እነኚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ አማራጯ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ጠንካራና አንቱታን ካተረፉ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና መሥራት ነው። ለዚህም የተለያዩ ተግባራትን ተከናውነዋል፡፡ አንዱ ለኩባንያዎች ፈቃድ ሰጥቶ ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ፈቃዱን ያገኙ ኩባንያዎች ብዙ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አንዱ ነው፡፡ ስለ ኩባንያው ምንነትና ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ? ወደሚለው ጉዳያችን ከመግባታችን በፊት ማዕድናቱ ምን ምን ጥቅም አላቸው? የሚለውን ጥቂት እናንሳ፡፡
ከሰሞኑ ቀንጢቻ ማይኒግ ኩባንያ ያለበትን ደረጃና የቀጣይ እቅዱን ለጋዜጠኞችና ለሼር ባለቤቶች ባስተዋወቀበት ወቅት የኩባንያው ጂኦሎጂስት ሚስተር ቻርልስ ቪዚያን ሊቲየም ስለተሰኘው ማዕድን ጥቅምና ተቋሙ ይዞት ስለመጣው ሀሳብ በስፋት አብራርተዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፤ ሊቲየም የተሰኘው ማዕድን ለዘመናዊ አውቶሞቢሎችና አውሮፕላኖች ባትሪ መሥሪያ የሚያገለግል ዋነኛ ግብዓት ነው፡፡ ከሞባይል ስልኮች እስከ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ድረስ በተለያዩ መተግበሪያዎች ውስጥ በማስገባት የሚያገለግሉ ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከማቻ መሳሪያዎች ናቸው። በከፍተኛ የኃይል እፍጋታቸው ምክንያት በጣም ተወዳጅ ሲሆኑ፤ ይህም ማለት ከክብደታቸው ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል ማከማቸት ይችላሉ፡፡ በሊቲየም የሚሰሩ ባትሪዎች የአየር ንብረትን ከመጠበቅ አኳያ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውም ናቸው፡፡
አሁን ላይ የሊቲየም ማዕድናት ከካርቦን ልቀት ቅነሳ ጋር በተያያዘ በጣም ተወዳጅና የሚመረጡ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪኖች በብዛት እየተመረቱ ለገበያ የመቅረባቸው ምስጢርም ይሄው ነው፡፡ ምክንያቱም የሊቲየም ብረት ፎስፌት ባትሪዎች ከከባድ ብረቶች እና ብርቅዬ ብረቶች ነፃ ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
የሊቲየም ባትሪዎች መርዛማ ያልሆኑ፣ የማይበክሉ ፍጹም አረንጓዴ የሚባሉ ሲሆኑ፤ በኢንዱስትሪው ዓለም የሚወደዱ ናቸው፡፡ እናም በዚህ የተነሳ እነዚህ ሁለት ማዕድናት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተፈላጊነታቸው በእጥፍ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዓለም ገበያ ላይ ዋጋቸውም በከፍተኛ መጠን ንሯል፡፡ ይህ ደግሞ ዓለም ሳይቀር ፊቱን ማዕድናቱ ያለበት ቦታ ላይ እንዲያዞር አስገድዶታል ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ይህ ሀብት ካለባቸው ሀገራት መካከል ተቀዳሚዋ መሆኗን ያነሱት ጂኦሎጂስቱ፤ ዓለም በእጅጉ ይፈልጋታል፡፡ አብሮ ለመሥራትም ይመኛታል፡፡ ቀንጢቻ ምንም እንኳን ዋና መሥሪያ ቤቱ አውስትራሊያ ቢሆንም አፍሪካ ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያን የመረጠው ለዚህ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ደግሞ እንደ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምዕራብ ጉጂ ዞን ሰባ ቦሩ ወረዳን ኩባንያው ማረፊያ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ቦታው በሊቲየምና በታንታለም ማዕድናት የበለጸገ ነው ሲሉ ቦታው ላይ ለምን ዓይናቸው እንዳረፈበት ይናገራሉ፡፡
ማዕድንን ለማልማት የውጭ ኩባንያዎች ዓይናቸውን በዚያ ስፍራ ላይ መጣላቸው ደግሞ ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ በመንግሥት በኩል ሲገለጽ ነበር። እንደ መንግሥትም ይህንን ፍላጎታቸውን ሊገፋው እንዳልወደደም በተደጋጋሚ አንስቷል። እሴት የሚጨምር ካለ በጋራ እሰራለሁ ሲልም በተለያየ አጋጣሚ ገልጸዋል፡፡ በዚህም ሀሳቡን የተጋሩት ብዙዎች ሆነዋል፡፡ ቀንጢቻ ማይኒንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ደግሞ ጥሪውን ተቀብሎ ከመጡት መካከል አንዱ ተደርጓል፡፡
የአፍሪካ የማዕድንና ኢነርጂ የኢትዮጵያ ተወካይ፤ የኩባንያው መስራች እና የኩባንያው ከፍተኛ ባለአክስዮን ሀጂ አሊ ሁሴን በበኩላቸው ስለጠቅላላ የኩባንያው እንቅስቃሴ አንስተዋል፡፡ እንዲህ በማለትም ነው ለታዳሚው ያስረዱት፡፡ ኩባንያው አራት ዓመታትን በሥራ ላይ አሳልፏል፡፡ የማዕድን ሥራ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ በመሆኑም ያንን ለማድረግ ቁርጠኛ ሆኖ ሥራው ላይ ደፋ ቀና ሲል ቆይቷል፡፡ ይህ ልፋቱ ደግሞ በቅርቡ የተሻለውን ለኢትዮጵያም ለኩባንያውም ያመጣል ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ሥራውን ሊያስጀምረው የሚችለውንና 150 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበትን ‹‹ፕሮሰሲንግ ፕላን›› የተባለውን ማሽን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ሁኔታዎችን አጠናቋል፡፡ እስከ መስከረም ድረስም ማሽኑ ገብቶ ሥራ ለመጀመር ታቅዷል፡፡
ማሽኑ በሰዓት 270 ቶን ሊቲየም የሚያመርት ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ምን ያህል ምርታማ ሊያደርገን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው፡፡ ለውጭ ገበያ ሊቲየምን እሴት ጨምሮ ከማቅረብ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦም አለው፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያን በሊቲየም ምርት ከታላላቆቹ ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል፤ ተወዳዳሪነቷንም ይጨምረዋል፡፡ በተለይ ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ከመፍታት አኳያ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ሳይታለም የተፈታ ነው ይላሉ፡፡
ኩባንያው ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት የበለጸገች መሆኗን የሚያሳይበት እንደሆነ የሚያነሱት ሀጂ አሊ፤ ኩባንያው በዋናነት ቀንጢቻን ሲመርጥ ሊቲየምንና ታንታለም በስፋት የሚገኝበት አካባቢ በመሆኗ በሁለቱ ማዕድናት ላይ ለመሥራት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሲከናወን ጥሬ እቃውን አውጥቶ ለመሸጥ ሳይሆን በሀገር ውስጥ አውጥቶ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ማቅረብን አላማ አድርጎ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ሥራውን የሚያከናውኑት ደግሞ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ማዕድን ሚኒስቴር ቢሮ ጋር በሽርክና እንደሆነ የገለጹት የኩባንያው መሥራች፤ ኩባንያው በሙሉ አቅሙ የሊቲየም ማዕድንን ማውጣት ሲጀምርና ለዓለም ገበያ ሲያቀርብ ኢትዮጵያ በዓመት አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ታገኛለች፡፡ በተጨማሪም ሀገሪቱ ከፍተኛ የታክስ ገቢ እንድታገኝ የሚያስችላት ይሆናል፡፡
የቀንጢቻ ማይኒንግ ድርጅት ተጠናቆ የሊቲየምና የታንታለም ማዕድናትን ለማምረት 80 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው የሚናገሩት መስራቹ፤ ለሥራው በዓለም ላይ አሉ የተባሉ ባለሙያዎችን ማሰማራቱንና ለቀጣይ ሥራውም እየተዘጋጀ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
ሀጂ አሊ፤ ሊቲየም ማዕድን በዋንኛነት ለመኪና፣ ለሞባይል እና ለላፕቶፕ ባትሪ መሥሪያነት የሚያገለግል ማዕድን ሲሆን፤ የቀንጢቻ ማይኒንግ ፒኤልሲ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የሊቲየም ማዕድን ማለትም የተፈጥሮ ነዳጅ ምትክ ማዕድን ለማውጣት ዝግጅቱን ጨርሶ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ ሥራ ያነሳሳቸው ደግሞ ዓለም የነዳጅ መኪና ትቶ ወደ ኤሌክትሪክ መኪና እየዞረ ባለበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ተፈጥሮ የቸረቻቸውን የማዕድን ሃብት በመጠቀም ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በማመን ነው ይላሉ፡፡
የሶላር ኢነርጂ እጅግ ተፈላጊ የኃይል ምንጭ እየሆነ መጥቷል። የኤሌክትሪክ መኪኖችም ሆኑ የሶላር ኃይል ቴክኖሎጂዎች ደግሞ ዋነኛ ግብዓታቸው ይህ የሊቲየም ማዕድን ነው የሚሉት ሀጂ አሊ፤ ሥራውን ሲያከናውኑ ማዕድኑን ወደ ውጭ እየላከ የበይ ተመልካች በማይሆንበት መልኩ ነው፡፡ ማለትም የሊቲየም ባትሪ ፋብሪካ በመክፈት እሴት ጨምሮ መሸጥ ዋነኛ ግባቸው እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
የሊቲየም ማዕድን ማውጣት ሥራ ብዙ ልፋትን ይፈልጋል፡፡ ለአብነት ወደታች እስከ አርባ ሺህ ሜትር መቆፈርን ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ኩባንያው ይህንን የማድረግ ሥራ አከናውኗል፡፡ ይህ ደግሞ የሊቲየም ማዕድኑ ከሀገራችን ከርሰ ምድር ወጥቶ ሌሎችን እንዲያረሰርስና ከዚያም ሀገሪቱ እንድትጠቀም የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ሀጂ አሊ፤ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ የገለጹት፤ ኩባንያው ማዕድኑን በጥናት በመለየት ናሙናውን ወደ ውጭ ሀገራት ልኮ የማረጋገጥ ሥራውን አጠናቋል፡፡ በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ ድርጅቱ የማምረት ሥራውንም ይጀምራል፤ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የሊቲየም ማዕድን አምራች ሀገር ያደርጋታል፡፡ ለዚህም የቀንጢቻ ማይኒንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሊቲየም ምርቶችን ለተለያዩ ሀገራት ኩባንያዎች ለማቅረብ ስምምነት እየተደረገ ይገኛል፡፡
የሊቲየም ምርትን በሀገር ውስጥ በተሻለ ጥራት በማምረት በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ እየተሰራ እንደሆነ ያነሱት ሀጂ አሊ፤ ማዕድኑን ለማምረት የሚያገለግል ፕሮሰሲንግ ፕላን ማሽንን አንድ ጊዜ ብቻ አስገብቶ አያቆምም፡፡ በቀጣይ ጊዜያትም የሚያስገባቸው ይኖራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ መልኩ ሀገሪቱን የሚጠቅም ነው፡፡ አንዱ ማዕድኑን በጥራት ለማምረት የሚያስችል ሲሆን፤ ሌላው የድርጅቱ እንቅስቃሴ በሀገር ውስጥ ለሚኖሩ ባለሀብቶች በተለያዩ የማዕድናት ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ መነሳሳትን ይፈጥራል ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ማዕድናቱን የማምረት ፕሮጀክት ለሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህም ኩባንያው ወደ ሥራ ሲገባ አንድ ሺህ የሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል፡፡ ሀገሪቱ በተለያዩ ማዕድናት የበለፀገች መሆኗን ከመገንዘብ በተጨማሪ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት አሟጥጦ መጠቀም እንዲቻልና የኢኮኖሚውን ዕድገት ከፍ ለማድረግም ሁነኛ መፍትሔ ይሰጣል ነው ያሉት፡፡
ኩባንያው ለሥራው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ መንግሥታዊ አካላትንና ግለሰቦችን የሸለመ ሲሆን፤ አንዱ ተሸላሚ ሥራውን እያከናወነ ያለበት ዞን ነው፡፡ ለሰባ ቦሩ ዞን የሁለት ሚለዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። በእርግጥ ኩባንያው ቀደም ብሎም ቢሆን ሥራውን ሲያከናውን ማኅበረሰቡን ሳይዘነጋ ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የአካባቢው ማኅበረሰብ በጣም የሚቸገርበትና በአንድ ጀሪካን እስከ 40 ብር እየከፈለ ውሃን እንዲያገኝ የሆነበት የውሃ ችግር ነው። ታዲያ ይህ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ በማድረግ በቀን 60 ሺህ ሊትር ውሃ የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያገኝበትን እድል ፈጥሯል፡፡ በተመሳሳይ ለጤና አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎችም በአካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ ችግር ነውና ይህንንም የማቅረብ ሥራ ሰርቷል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችንም አከናውኗል። ይሁን እንጂ ኩባንያው ይህ በቂ ነው ብሎ አያምንምና በቀጣይም ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ነሃሴ 19 / 2015