«አሸንዳ አሸንድዬ» የሰሜኑ ድምቀት

እየተገባደደ ባለው ወርሃ ነሐሴ ሁለት ተወዳጅ ባህላዊ በዓላት ተከብረዋል። እነዚህ ሃይማኖታዊና ትውፊታዊ ይዘት ያላቸው በዓላት የደብረ ታቦር “ቡሄ” እና “የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል” የሚል መጠሪያ ያላቸው የኢትዮጵያውያን ባህላዊ እሴቶች ናቸው። ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና የባህል መናገሻ ነች። ሕዝቦቿ በብዙ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ተከብበውና ተዋድደው የሚኖሩ የፍቅርና የመከባበር ተምሳሌቶች ናቸው። ሀገሪቱ የራሷ የዘመን መቁጠሪያና ፊደል ያላት፤ በሌላው ዓለማት በማይገኙና ተወዳጅ በሆኑ በዓላት፣ አልባሳትና የአመጋገብ ሥርዓት የምትታወቅም ነች። የቡሄና የልጃገረዶችና ወጣት ሴቶች ጨዋታ የሆነው አሸንዳና አሸንድዬም ከዚህ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው።

ኢትዮጵያ በዓለማችን ላይ ጥቂት ከሆኑና በርካታ ብሔሮችን አቅፈው ከያዙ ሀገራት ተርታ የምትመደብ ነች። ይህ ብቻ ሳይሆን ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ከመሆኗ አንፃር የዚያኑ ያህል እጅግ ብዙ እሴቶችና የጋራ ማንነቶችም የያዘች ነች። የቋንቋ፣ የአለባበስ፣ የሙዚቃና የልዩ ልዩ ባህላዊ ሥርዓቶች መገኛም ጭምር ነች። ከዓመቱ መጀመሪያ አንስቶ አዲስ ዘመን የዘመን መለወጫ እስኪበሰር ድረስ “ከመስከረም እስከ መስከረም” አያሌ ተወዳጅና በጉጉት የሚጠበቁ ክብረ በዓላት፤ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሥነ ሥርዓቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄዳሉ።

ዜጎች ከሃይማኖታቸው ከሚቀዳ የበዓል ሥርዓቶች የተገነባ ውብ ማንነት ከመላበሳቸውም ባሻገር፤ በመቻቻል ለዘመናት አብሮ በመኖር በዳበረው እሴት የተነሳ ሁሉም የሚጋራው ባህልና ኢትዮጵያዊ ቀለም እንዲሁ መገለጫው ነው። ዛሬ በ “ሀገረኛ” አምድ በልዩ ሁኔታ ዳሰሳ የምናደርግበት የ “አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል” የልጃገረዶች ጨዋታም ይህንኑ እውነት የሚያሳይ ነው። ለመሆኑ ይህ የልጃገረዶች በዓል መቼ፣ እንዴትና በማን ይከበራል? የሚከተለው ዳሰሳ መልስ ይሰጠናል።

ሻደይ-ሶለልና አሸንድዬ

በሻዳይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል የልጃገረዶች በዓል ታሪክ፣ አከባበሩና ክዋኔው ዙሪያ ጥናት ያደረጉት በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር መስፍን ታደሰ እንደሚናገሩት፤ በዓሉ ልጃገረዶች (ሴቶች) በነፃነት በአደባባይ ወጥተው የሚጫወቱበት ነው። ነሐሴ 16 ቀን ከሚከበረው የቅድስት ማርያም በዓል ጋር የተያያዘው ክብረ በዓል ከዋዜማው እስከ ማግስት ልጃገረዶች የአሸንዳ ቅጠልን አሸርጠው አደባባይ በመውጣትና በየቤቱ በመዞር እየጨፈሩና እያዜሙ የሚያከብሩት በዓል ነው። በተለይ በላስታ ላሊበላ በሚከበረው ሶለል በዓል ላይ ከ15 ዓመት በላይ የሆኑት ድኮት (የእጅ አምባር)፣ ሁለት አይነት መስቀል፣ በአንገታቸው ድሪ፣ የብር አልቦ እግራቸው ላይ ያጠልቃሉ፤ በጥልፍ ቀሚስ ተሽቆጥቁጠው ይሄዳሉ። ከ15 አመት በታች የሆኑት ከብር የተሰራ ድሪ፤ ትልልቅ ክብ ቀለበት ጆሮ ጌጥ፤ ከ10 ዓመት በታች የሆኑት ቁንጮና ጋሜ (መሀል ፀጉራቸው ተላጭቶ ዳርዳሩ ያደገ) የፀጉር ቁርጥ ይቆረጣሉ።

ጥናት አድራጊው የበዓል አከባበር ሥርዓቱንና ጭፈራውን አስመልክቶ እንደሚናገሩት ሴቶቹ ‹‹አስገባኝ በረኛ፣ አስገባኝ ከልካይ፤ እመቤቴን ላይ›› በማለት ማንጎራጎር ሲጀምሩ በሩ ይከፈትላቸዋል ‹‹ይሄ የማን አዳራሽ የጌታየ የድርብ ለባሽ፤ ይሄ የማን ደጅ የእመቤቴ የቀጭን ለባሽ›› በማለት እንደሚያዜሙ ነው። በእለቱ ከሚዘፈኑ ዘፈኖች መካከል በሰቆጣ ከተማ ታዋቂው ዘፈን ‹‹አሽከር አበባየ አሽከር ይሙት፣ ይሙት ይላሉ የኔታ አሽከር አይደለም ወይ የሚሆነው ጌታ›› እያሉ እንደሚያዜሙ ይገልፃሉ። በር ተከፍቶላቸው ከገቡ በኋላ የቤቱን ባለቤቶች ማወደስ ይጀምራሉ።

እንደ መምህሩ ገለፃ፤ ከውደሳዎቹም መካከል ‹‹ከፈረስ አፍንጫ ይወጣል ትንኝ፤ እሰይ የኔ ጌታ ጤና ይስጥልኝ፤ ምድር ጭሬ፣ ጭሬ አወጣሁ ማሰሮ እሰይ የኔ እመቤት ድልድል ወይዘሮ›› የሚለው ይገኝበታል። ይቀጥሉናም ‹‹ስለለየ፣ ስለለየ ….እሰይ የኔ እመቤት የፈተለችው ሸማኔ ታጥቶ ማርያም ሠራችው›› በማለት ያንጎራጉራሉ። ዘፍነው ሽልማት ካልተሰጣቸው ወይ ከዘገየ ‹‹አንቱን አይደለም የማወሳሳው፤ ቀና ብለው እዩኝ›› በማለት በነገር ሸንቆጥ ያደርጓቸዋል። በዚያን ቀን ያው ሽልማት መስጠት ግድ ነው፤ እሱን ተቀብለው ‹‹አበባየ ነሽ አበባየ ጉዳይ ሰመረች በአንች ላይ›› እያሉ ወደ ሌላ መንደር ይሄዳሉ።

ከላይ ለመመልከት እንደሞከርነው ይህ ክብረ በዓል ጨዋታ፣ ፍቅር፣ የአዲስ ዓመት መውጫ እንዲሁም ፍፁም ያልተበረዘ የዘመናት ባህልን የሚያመለክት ይዘት ያለው ነው። በዋነኝነት ግን ሴቶች ያለምንም ተፅዕኖ እና ያለማንም ከልካይነት የሚጫወቱበት፤ እናቶች ደግሞ ባህላዊ አልባሳት እና ጌጣጌጦችን በመግዛት ልጆቻቸውን በደስታ በዓሉን እንዲያሳልፉ የሚረዱበት ልዩ ሥነ ሥርዓት ነው።

አሸንዳ (በትግራይ)

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል የሚያስተምሩት አቶ መብራህቶም ገብረማርያም በትግራይ ልጃገረዶች የሚከበረውን የአሸንዳ በዓል አስመልክቶ ያደረጉት ጥናት እንደሚጠቁመው ወጣት ልጃገረዶች በየዓመቱ አሸንዳን በጉጉት ይጠባበቃሉ። አሸንዳ ከነሐሴ 16 ጀምሮ እንደየአካባቢው ከአንድ ሳምንት እስከ አንድ ወር ድረስ በውብ ሴቶች ጭፈራ ደምቆ የሚከበር እና በማኅበረሰቡ ትልቅ ተቀባይነት ያለው በዓል ነው።

የአሸንዳ በዓል ታዳጊ ሴቶች፣ ወጣት ልጃገረዶች እንዲሁም እናቶች በመሰባሰብ በቡድን በቡድን በመሆን “አሸንዳ” እያሉ በየሰፈሩ በመዟዟር ሲጫወቱ የሚቆዩበት ጊዜ ነው። ሴቶች ከጓደኞቻቸውና ከእኩዮቻቸው ጋር በመሆን ማራኪ የሆኑ አልባሳትንና ጌጣጌጦችን በመልበስ፣ የበዓሉ ዋና መገለጫ የሆነውን የአሸንዳ ቅጠል በወገባቸው ዙሪያ በማድረግ፣ ወደ አደባባይ በመውጣት በየሰፈሩ በየቤቱ በመሄድ የሚጨፍሩበት ወቅት ነው።

እንደ መምህሩ ዳሰሳዊ ጥናት የአሸንዳ በዓል በመላው የትግራይ አካባቢ በድምቀት የሚከበር ሲሆን የትግራይ ክልል መዲና በሆነችው በመቀሌ ከተማ በፌስቲቫል ደረጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በተገኙበት ለሶስት ተከታታይ ቀናት ይከበራል። የአሸንዳ በዓል በአብዛኛው የትግራይ አካባቢዎች “አሸንዳ” በሚል ይታወቃል በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ ስያሜ ያለው ሲሆን በአክሱም “ዓይኒ ዋሪ” ይባላል።

ቆልዓ ኣሸንዳ (የአሸንዳ ልጃገረድ)

እንደ ጥናት አድራጊው ገለፃ፤ የአሸንዳ ሳምንታት ልጃገረዶቹ ”ቆልዓ ኣሸንዳ” ወይም የአሸንዳ ልጃገረድ በመባል ይጠራሉ። የአሸንዳ ልጃገረድ በዚህ በጣም ተቀባይነት ባለውና በጉጉት በሚጠበቀው የአሸንዳ በዓል የተለመደ ልብስ ሳይሆን ለየት ያለና በተለያዩ ጌጣጌጦች የደመቀ ባህላዊ ልብስ ይለብሳሉ።

ሶለል (ላስታ ላሊበላ)

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው በበዓሉ ወቅት በሰሜን ወሎ ላስታ ላሊበላ እና በዙሪያው ያሉ ሴቶች ፀጉራቸውን ጋሜ፣ ቁንጮ፣ ሳዱላና በቀጫጭኑ ሹሩባ ይሰራሉ። አልባሶ፣ ጋሜ እና ድርብ ደግሞ ወደ ትግራይ ለዕለቱ የሚመረጡ የፀጉር አሰራር አይነቶች ናቸው። በበዓሉ ላይ የሚለብሷቸው አልባሳት እንደ አካባቢው ቢለያይም በአብዛኛው ሴቶች የሀበሻ ቀሚስ፣ የሻማ ጨርቅ ወይም ሽፎን የሚባለውን ሽንሽን ቀሚስ ለብሰው ይታያሉ።

መረጃው እንደሚጠቁመው በበዓሉ ዋዜማና እለት ለመድመቂያነት በጆሯቸው ላይ ጉትቻ፣ ለእጃቸወ አንባር፣ እግራቸው ላይ አልቦ፣ በአንገታቸው ላይ መስቀል፣ አሽንክታብ፣ ድሪ እና ሌሎች ጌጣጌጦችን ይጠቀማሉ። በዋዜማው ነሐሴ 15 ልጃገረዶች በቅቤና በኩል መዋብ ይጀምራሉ። የክረምቱ ዝናብ ያለመለመውን የአሸንዳ ተክል ቆርጦ ለወገብ እንዲመች ተደርጎ በማዘጋጀት እንደ አንቀልባ በወገባቸው ዙሪያ ያደርጉታል። ነሐሴ 16 ልጃገረዶች ተሰባስበው በጠዋት ወንዝ ወርደው እጅና እግራቸውን ይታጠባሉ። ይህም በአካል እና በመንፈስ ጽዱ እንደሚያደርጋቸው በማህበረሰቡ ይታመናል። ከዛም ቤተክርስቲያን በመሄድ ደጀ ሰላሙን ተሳልመው ለአምላካቸው ምስጋና በማቅረብ በዓሉን ማክበር ይጀምራሉ።

በአንድ ቡድን ውስጥ ከ5 እስከ 30 የሚደርሱ ሴቶች ተሰብስበው ከመካከላቸው መልካም ባህሪ ያላቸውን መርጠው ለቡድኑ መሪነት፣ ከበሮ መችና ገንዘብ ሰብሳቢነት በመሰየም ስለ አለባበስ፣ አጊያጊያጥ እና ከማን ቤት እንደሚጀምሩ በመነጋገር የዕለቱን ውሎ ይጀምራሉ። በአሸንዳ፣ በሻደይ፣ በአሸንድዬ፣ በሶለል በዓል ሴቶች ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ያለ ቤተሰብ ተፅዕኖ እየተጫወቱ የሚውሉበት፤ ከቤት ሥራ ነፃ የሚሆኑበት፣ እንደውም ቤተሰብ አልባሳትና ጌጣጌጦችን በመግዛት ልጆቹን አስውቦ ወደ በዓሉ የሚልክበት ሳምንት በመሆኑ “የሴቶች የነፃነት ጊዜ” ሊባል ይችላል።

ሃይማኖታዊ ይዘት

የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይና ሶለል በሰሜኑ ክፍል የሚከበር ልዩ የልጃገረዶች በዓል ቢሆንም ሃይማኖታዊ ይዘት እንዳለውም ይነገራል። በኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የበዓሉ መከበር ምክንያት እና አመጣጥ በመዛግብት ላይ ተቀምጦ ይገኛል።

የቤተክርስቲያን ታሪክ በኢትዮጵያ በሚል በተፃፈ መጽሐፍ ውስጥ እንደተመለከተው በዓሉ ኦርቶዶክሳዊ ይዘት ያለው ሲሆን ከነሐሴ 16 (የፆመ ፍልሰታ ፍቺ) እስከ ነሐሴ 21 ድረስ የሚከበር ነው። በተለይ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የደናግላን መመኪያ ተደርጋ የምትቆጠረውና የእየሱስ ክርስቶስ እናት የሆነችው “ቅድስት ድንግል ማሪያም” ትንሳኤና እርገት ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ይሄው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ሥርዓት ክብረ የበዓሉ ቅድመ ዝግጅቱ የሚጀመረውም የፍልሰታ ጾም ሲገባ አንስቶ ነው፡፡ በእምነቱ ሥርዓት ነጫጭ ልብሱን ለብሶ ከማስቀደሱና ከመቁረቡ በተጨማሪ በዚሁ ሰሞን ለአሸንድዬ በዓል አከባበር የሚሆኑ ባህላዊ አልባሳት ማለትም “ትፍትፍና ጥልፍ ቀሚስ፣ መቀነት፣ ልዩ ልዩ ጌጣጌጥ” ለምሳሌ ያንገት “መስቀል፣ የጆሮ ጉትቻ፣ የእጅ ድኮት፣ የእግር አልቦ፣ ድሪ ካሎስ (ማተብ) አምባር፣ ጉርሽጥ (እንሶስላ) ማሰባሰብና ማዘጋጀት፣ ልብስ ማጠብ፣ ፀጉር መሰራት ነው። በዚህ አግባብ በሃይማኖቱ ተከታዮች (ሴቶችና ሴት ልጃገረዶች) በዓሉ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በድምቀት ይከበራል።

እንደ መውጫ

ሀገራችን ኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት የሀገረ መንግስት ታሪክ፣ ውብ ባህልና ማንነት ያላቸው ብሔረሰቦች በጋራ ተዋደውና በአንድነት ተጋምደው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑት ማስረጃዎች መካከል ዛሬ በስፋት የተመለከትነው “የሴቶችና የሴት ልጃገረዶች” በዓል ነው። ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ እንደ “አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል” ዓይነት ለጆሮ ማራኪ፣ ዓይን ገብና ተወዳጅ የሆኑ እሴቶች ባለቤት ናቸው። ባህልና ወጋችን ለባዳው የሚያስቀና ለወዳጅ ሃሴትን የሚፈጥር ጭምር መሆኑን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። ኢትዮጵያውያን ጠላትን በአንድነት መክተው ድባቅ የሚመቱ ለሉዓላዊነታቸው መከበር በጋራ ዘብ የሚቆሙ ብቻ ሳይሆኑ በደስታቸውም ጊዜ አብረው የሚበሉ፣ የሚረዳዱና የሚከባበሩም ናቸው። ይህንን እውነት ደግሞ ከመስከረም እስከ መስከረም በሚከበሩ ውብ ባህላዊ ሀብቶችና እሴቶች ውስጥ ማግኘት እንችላለን። ሰላም!

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ነሃሴ 19 / 2015

Recommended For You