የባለፀጋው ክልል ተስፋ ሰጪ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ

ከዚህ ቀደም በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር የነበሩትን የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የከፋ፣ የዳውሮና የሸካ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳን (ልዩ ወረዳው አሁን በዞን ደረጃ ተደራጅቷል) በአንድነት በመያዝ በኅዳር ወር 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ 11ኛው ክልላዊ መንግሥት ሆኖ የተዋቀረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፤ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ ነው።

ክልሉ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቀጣና ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎችም የሚበቃ የተትረፈረፈ ሀብት አለው።ዓመታዊ ሰብል፣ ቡናና ቅመማ ቅመም፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች (Export Items)፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፎች በክልሉ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያስችሉ የምጣኔ ሀብት መስኮች ናቸው።በተለይም ክልሉ ያለው የቡና፣ የሻይ ቅጠል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የማዕድናት ሀብትና ለም መሬት ባለሀብቶችን በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያነሳሳ እና የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መልካም አጋጣሚና ፀጋ ነው።

ክልሉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚን በብርቱ የሚደግፉ ምርቶች መገኛ ነው።ከፍተኛ የቡናና የማዕድን ሀብቶችን የያዘው ይህ ክልል፤ ሀብቱ ከክልሉ አልፎ ለሀገርም የሚተርፍ ትልቅ ፀጋ ነው።ክልሉ አስደናቂ የሆነ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ልምላሜና የተፈጥሮ ሀብት ያለው በመሆኑ የባለሀብቶችን ትኩረት የሚስብ መሆኑ አያጠያይቅም።

የክልሉን ሀብቶች ለመለየት የሚደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ክልሉ ለዓመታዊ ሰብሎች፣ ለቡናና ቅመማ ቅመም እና ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የሚውል ሰፊና ምቹ መሬት አለው።በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎችም የኢንቨስትመንት መዳረሻና አማራጭ መሆን የሚችል ነው።

የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ክልሉ ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት ባለፀጋ ነው።ከወርቅ ማዕድን በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል የድንጋይ ከሰል በዳውሮ እና በኮንታ አካባቢዎች በስፋት ይገኛል። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን የብረትና የድንጋይ ከሰል ማዕድናትም ሌላው በክልሉ የሚገኙ ሀብቶች ናቸው።በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ማዕድን ለማዕከላዊ ገበያ ከሚያቀርቡ የሀገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሆኗል።በክልሉ ገና በጥናት ያልተለዩ ብዙ ሀብቶች አሉ።ኦፓልና ሌሎች ማዕድናትም በክልሉ ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል።

በርካታ ባለሀብቶች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል።ክልሉ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተሰሩት የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ሥራዎች የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር አስተዋፅኦ አበርክተዋል።በክልሉ በአጠቃላይ በተለያየ የሥራ ደረጃ ላይ የሚገኙና ለ112 ሺ 983 ዜጎች የሥራ እድል (7983 ቋሚ እና 105ሺ ጊዜያዊ) የፈጠሩ 380 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አሉ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ2015 የበጀት ዓመት አበረታች የኢንቨስትመንት አፈፃፀም ማስመዝገቡን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ መረጃዎች ያሳያል።የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ተስፋዬ በ2015 የበጀት ዓመት በክልሉ ስለነበረው የኢንቨስትመንት ሥራ እና ስለቀጣይ የዘርፉ ትኩረት መስኮች፣ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኢንቨስትመንት ዘርፍ አፈጻጸም

በ2015 የበጀት ዓመት በክልሉ ለ141 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል።ፈቃድ የወሰዱት ባለሀብቶች በግብርና (67)፣ በማምረቻ (21)፣ በአገልግሎት (53)፣ ዘርፎች የሚሰማሩ ሲሆን፤ ያስመዘገቡት የካፒታል መጠንም ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ነው።ለሦስቱም ዘርፎች 26ሺ ሄክታር መሬት ተላልፏል።የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ፕሮጀክቶች መካከል በግብርና 48፣ በማምረቻ 50 እና በአገልግሎት ዘርፍ ደግሞ ስድስቱ ወደ ሥራ ገብተዋል።

በበጀት ዓመቱ ለ2892 ዜጎች ቋሚ እና ለ79ሺ335 ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል።ጊዜያዊ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች ሥራ መልመድ በመቻላቸው ከመንግሥት ብድር አግኝተው በቋሚነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

ክልሉ ለግብርና ሥራዎች 30 ሺ 500 ሄክታር መሬት ለመለየት አቅዶ፣ 32 ሺ 170 ሄክታር መሬት መለየት ችሏል።ክልሉ ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚሆን የአቅም ልየታ ሥራ ሲያከናውን የግብርና ሚኒስቴርም ድጋፍ አድርጓል።ሦስት ሺ 600 አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ ሆነዋል።

ለ648 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ክትትል ተደርጓል።የአፈጻጸም ጉድለት ካሳዩ 36 ፕሮጀክቶች መካከል ለ18ቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፤ ዘጠኝ ፕሮጀክቶች ከተሰጣቸው መሬት የተወሰነው እንዲቀነስ ሲደረግ፣ ዘጠኝ ፕሮጀክቶች ደግሞ የወሰዱትን መሬት እንዲመልሱ ተደርጓል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በክልልነት ከተዋቀረ አጭር እድሜ ቢኖረውም ኢንቨስትመንቱ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ ሰፊ ጥናትና ውይይት ተደርጎበታል።ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ለማበረታታት የክልሉን ርዕሰ መስተዳድርና የካቢኔ አባላትን ጭምር ያሳተፈ የንቅናቄና የፕሮሞሽን ሥራ በስፋት ተሰርቷል፡፡

የባለሀብቱ ጥያቄዎች

በክልሉ በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሀብቶች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ በኢንቨስትመንት ሕግጋት ላይ ከተጠቀሱት ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ናቸው።በግብርና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚኒባስ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው በኢንቨስትመንት ማበረታቻ ደንብ (517/2014) ላይ ተመልክቷል።ክልሉ ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት ያለበት አካባቢ በመሆኑ ይህ ዓይነቱ የመኪና ድጋፍ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።ስለሆነም ባለሀብቶቹ ይህ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።በአንዳንድ አካባቢዎች ለግብርና ሥራዎች የሚያስፈልግ የሰው ኃይል እጥረት ይስተዋላል።ይህን ችግር ለማቃለልም ከሌሎች አካባቢዎች ሠራተኞችን በመውሰድ ለማሰራት ጥረት እየተደረገ ነው።

ክልሉ የባለሀብቶችን ፍሰት ለመጨመር የሚያደርጋቸው ማበረታቻዎች በአዋጅና በመመሪያ በተደነገጉ ማበረታቻዎች (Incentives) አሰጣጥ መሰረት የሚፈፀሙ ይሆናል።ባለሀብቶችን በቁጥርም ሆነ በጥራት ለማብዛት የቢሮክራሲ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ችግሮችን ከመፍታት በተጨማሪ፤ በሕግ ማዕቀፍ የተቀመጡ የማበረታቻ ስልቶችን መሰረት በማድረግ ትልቅ አቅም ያላቸውና በቁጥር የበዙ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ላይ እንዲሰማሩ ጥረት ያደርጋል።ቦታዎችን አዘጋጅቶ ለባለሀብቶች ማቅረብን ጨምሮ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ተግባራትን ያከናውናል።ባለሀብቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።

የመሰረተ ልማት አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ

ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ ያሉ የአስተዳደር እርከኖች ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።ባለሃብቶች ፈቃድ ለማግኘት በሚመጡበት ጊዜ ያለምንም ውጣ ውረድ፣ በፍጥነት እንዲስተናገዱ እየተደረገ ነው።ቀደም ሲል የክልሉ ዞኖች በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መዋቅር ውስጥ በነበሩበት ጊዜ ወደ ዞኖቹ የሚመጡትና የሚስተናገዱት ፕሮጀክቶች ከ20 አይበልጡም ነበር።አሁን ግን በዓመት ከ150 በላይ ፕሮጀክቶች እየመጡ ነው፤ በፍጥነት ውሳኔ አግኝተውና ፈቃድ ተሰጥቷቸው ሥራ እንዲጀምሩም እየተደረገ ነው።ይህን ማሳካት የተቻለው የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱ በመሻሻሉ ነው።

በእርግጥ ክልሉ በርካታ የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት አለበት።ችግሩን በማቃለል ኢንቨስትመነንት ፍሰቱን ለመጨመር የተጀመሩ ብዙ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች አሉ።በ‹‹ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት መርሀ ግብር›› (Universal Rural Road Access Program – URRAP) በኩል የሚከናወኑ የገጠር መንገድ ግንባታዎች የዚህ ጥረት አካል ናቸው።‹‹የጠጠር መንገድ መሆኑ እንጂ ክልሉ በመንገድ ረገድ ብዙ ችግር የለበትም›› የሚሉት አቶ ከበደ፣ የተጀመሩ የመንገድ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነም ያስረዳሉ።

የማኅበረሰብ ተጠቃሚነት

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ካሏቸው ፋይዳዎች መካከል አንዱ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጋቸው ነው።የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ባለሀብቶችን ወደ ክልሉ ሲያስገባ ባለሀብቶች በተለያዩ መንገዶች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በማሰብ ነው።ማኅበረሰቡ ከኢንቨስትመንት ስራዎች በሥራ እድል ፈጠራ፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በገበያ እድል ተጠቃሚ እንዲሆን ይጠበቃል።በዚህ ረገድ በክልሉ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለክልሉ ህብረተሰብ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንዳሏቸው አቶ ከበደ ይገልፃሉ።

‹‹ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ያላደረገ ሀብት፣ ሀብት ተብሎ ሊጠቀስ አይችልም።በክልሉ የሚገኙ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸውን ሲያከናውኑ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችንም እየሰሩ ይገኛሉ።ከእነዚህ ሥራዎች መካከል አንዱ የመንገዶች ግንባታ ነው።በበጀት ዓመቱ በባለሀብቱና በኅብረተሰቡ የጋራ ተሳትፎና ትብብር 52 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመስራት ታቅዶ፣ 88 ኪሎ ሜትር መንገድ ተሰርቷል።ባለሀብቶች ለትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም ለማኅበራዊ ጉዳዮች (ደጋፊ ለሌላቸው ህፃናትና አረጋውያን) በርካታ ድጋፎችን አድርገዋል።ከዚህ በተጨማሪም ባለሀብቶች ለአርሶ አደሮች ስልጠና በመስጠትና ምርጥ ዘር በማቅረብ ትልቅ ድጋፍ አድርገዋል።ኅብረተሰቡም ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ጥበቃና እንክብካቤ ያደርጋል።ይሁን እንጂ ድጋፉና ተሳትፎው በቂ ባለመሆኑ ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።ክልሉ ካለው አቅም አንፃር ከዚህ የበለጠ ስራ ስለሚጠበቅ በቀጣይ ይህን አሰራር በተደራጀ መልኩ መምራት ያስፈልጋል›› ይላሉ።

ቀጣይ የትኩረት መስኮች

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማበረታታት የሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ ነው።ክልሉ በርካታ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ፍላጎት አለው።ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ2016 በጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ፣ በርካታ ባለሀብቶች በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፎች እንዲሰማሩ ማድረግ ነው።ክልሉ ከግብርናው ዘርፍ ባሻገር ባለሀብቶች በማምረቻና በአገልግሎት ዘርፎች በስፋት እንዲሰማሩ የሚያስችል የመሬት ዝግጅት ተግባር አከናውኗል።

አብዛኞቹ ባለሃብቶች በምርቶች ላይ እሴት (Value) ጨምሮ ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ፣ በቀጥታ በግብርና ላይ መሰማራትን ይመርጣሉ።ይህ አሰራር የዘርፉንም ሆነ የአካባቢውን እድገት ይጎዳል፤ ምክንያቱም እሴት የተጨመረበት ምርት የተሻለ ዋጋ ያወጣል፤ የምርቱን ተፈላጊነትም ይጨምራል።ለምሳሌ በክልሉ ከፋ ዞን የሚመረተው ‹‹ውሽውሽ›› የሚባለው የሻይ ቅጠል እሴት ተጨምሮበት ለገበያ ባይቀርብ ኖሮ፣ ታዋቂና ተፈላጊ አይሆንም ነበር።ስለሆነም እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ተግባር በቀጣይ ትኩረት ይደረግበታል።ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ቢመጡ በስድስቱም ዞኖች ውስጥ የሚገኙ የከተማ አስተዳደሮች መሬት ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ከበደ ገልጸዋል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 18/2015

Recommended For You