ወይዘሮ መሰረት ካሳዪ በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የሱሉልታ ከተማ ጅዳ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ከዓመታት በፊት ነበር የምግብ ፍላጎታቸው ቀንሶ በተደጋጋሚ አክታ ያለው ሳል ሲያስቸግራቸው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ያቀኑት። በወቅቱ በተደረገላቸው ምርምራ የቲቢ ህመምተኛ መሆናቸው ስለታወቀ ለሁለት ዓመት የስድስት የስድስት ወር መድሀኒት እየተሰጣቸው መርፌም እየተወጉ ህክምናቸውን ሲከታተሉ ይቆያሉ፤ይሁንና ጤናቸው ወደ ነበረበት ሊመለስ አልቻለም።
ባደረጉት የህክምና ክትትል ለውጥ ያላገኙት ወይዘሮ መሰረት ህመሙ እየጠናባቸው ሲመጣና እቤት ውስጥም ለመንቀሳቀስ አቅም ሲያንሳቸው የተፃፈላቸውን ሪፈር ይዘው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ያቀናሉ።በሆስፒታሉ በተደረገላቸው ምርመራም ህመማቸው መድሀኒቱን የተላመደ ቲቢ የሚባለው አይነት እንደሆነ ይነገራቸዋል። ያ ወቅትም ለተላመደ ቲቢ የተሻለ ወጤታማ መድሀኒት አገልግሎት መስጠት የተጀመረበት በመሆኑ ከህክምና ባለሙያዎቹ ጋር ተነጋግረው ይህንኑ አዲስ ህክምና መከታተል ይጀምራሉ ።
ወይዘሮ መሰረት በወቅቱ በከፍተኛ ህመም ሲሰቃዩ ስለነበርና ከፍተኛ የክብደት መቀነስ ስለገጠማቸው ለሁለት ወር በሆስፒታሉ አልጋ ይዘው ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ይደረጋል። የሆስፒታል ቆይታቸውን አጠናቀው ከወጡም በኋላ በታዘዙት መሰረት ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በአሁኑ ወቅት በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ።
ወይዘሮ መሰረት ታመው ያሳለፏቸውን ሦስት ዓመታት ‹‹ረጅም ጊዜ መድሀኒት መውሰድ አስቸጋሪ ነው፤ ይርሳል፤ በዛ ላይ አንዳንድ ሰሞን ሙሉ ጤንነት ስለሚሰማ ለምን እንወስዳለን በሚል እንዘናጋለን።›› ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡
እሳቸው ሁለቱንም አይነት የቲቢ መድሀኒቶች ተጠቅመዋል፡፡የዳኑት አዲሱን ሲወስዱ ነው፡ ፡አዲሱ ሲወሰድ የመክበድ ስሜት እንዳለውና መዳህኒቱ ግን ፍቱን መሆኑን ጠቅሰው፣ረጅም ጊዜ አለመወሰዱም ሳይሰለችና ሳይቋረጥ ለመጨረስ ይረዳል ሲሉ ይናገራሉ።
የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል መድሀኒቱን የተላመደ ቲቢ (MDR) ህክምና ክፍል አስተባባሪና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ከዶክተር ዳንኤል መረሳ መድሀኒቱን በተላመደ ቲቪ በሽታ የሚሰጠው ህክምና የጎንዮሽ ጉዳት እንደነበሩት ይጠቅሳሉ፡፡ በተደረጉ ምርምሮች አሁን እየተሞከረ ያለው አዲስ መድሀኒት ግን ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት ይላሉ፡፡
በአዲስ መልክ ስለቀረበውና በሙከራ ላይ ስላለው የተላመደ ቲቢ ህክምና ምንነት ከዶክተር ዳንኤል መረሳ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ቲቢ በሽታ ምንድነው ?
ቲበር ክሎስስ (ቲቢ) ማይክሮ ባክቴሪያ ቲበር ክሎስስ በሚባል ባክቴሪያ የሚመጣና በትንፋሽ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው ፡፡በሽታው በአብዛኛው እስከ 80 በመቶ የሚያጠቃው ሳንባን ሲሆን፣ የተቀረው ደግሞ ከሳንባ ውጪ ያለውን ማንኛውንም የሰውነት ክፍል ሊያጠቃ ይችላል። በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1990 ጀምሮ የዚህ በሽታ ህክምና በሁሉም ጤና ጣቢያዎች በበቂ ሁኔታ ሲሰጥ የቆየ በመሆኑ የረጅም ጊዜ ልምድ ስላለ ህክምናው ውጤታማ ነው።
መድሀኒቱን የተላመደ ቲቢ
የሚባለውስ ምንድነው ?
መዳሀኒቱን ላልተላመደ ቲቢ ህመምተኞች ከሚሰጡት አራት አይነት መድሀኒቶች ውስጥ በጣም ጠንካራ ለሚባሉት ለሁለቱ በሽታው የማይበገር ሲሆንና እነዚያን መድሀኒቶች ህመምተኞች ቢወስዱም ውጤት ማምጣት/መዳን ሳይችሉ ሲቀሩ በሽታው መድሀኒቱን የተላመደ ቲቢ በሽታ ይባላል። በመሆኑም ታካሚዎች የተላመደ ቲቢ ካላቸው ለመጀመሪያው ቲቢ የሚሰጧቸውን መድሀኒቶች ቢወስዷቸውም ላያድኗቸው ወይንም በሽታው ሊጠፋላቸው አይችልም ማለት ነው።
መድሀኒቱን የተላመደ ቲቢ
ህክምና በኢትዮጵያ
ከዚህ በፊት መዳሀኒቱን የተላመደ ቲቢ ህመምተኛ ሲኖር የሚሰጠው ህክምና የዓለም ጤና ድርጅት በ2011 እንዲሰጥ ያቀረበውና ለሀያ ወራት የሚወስደው ረዥሙ ህክምና ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥም ስድስት አይነት መድሀኒቶችን በሽተኛው መውሰድ የሚጠበቅበት ሲሆን፣ በአማካይ ከአስር እስከ እስራ አምስት ኪኒኖችን በቀን መዋጥና ስምንት ወር የሚደርስ መርፌ መውሰድንም ይጠይቃል።
በሂደት በተደረጉ ምርምሮች በባንግላዲሽ መዳሀኒቱን ለተላመደ ቲቢ የሚሆን የዘጠኝ ወር ህክምና ተሞክሮ ጥሩ ውጤት አስገኘ። ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረው የሀያ ወር ህክምና የተሳካ ውጤት ያስገኝ የነበረው ከታማሚዎቹ 55 በመቶ ለሚደርሱት ብቻ ነበር። አዲሱ ግኝት ግን ይሄንን የውጤታማነት ደረጃ ወደ 89 በመቶ ማሳደግ ችሏል። ይህንንም መሰረት በማድረግ የመድሀኒቱ ውጤታማነት በሌሎች ሀገራትም ጥሩ ውጤት ማስገኘት አለማስገኘቱ በተለያዩ ሁኔታዎች መፈተሽ ይኖርበታል። እንዲሁም የ20 ወሩን ከዘጠኝ ወሩ አዲሱ ህክምና ጋር የሚያወዳድር ‹‹ስትሪም›› የሚባል ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት ሀገራት እ.አ.አ ከ2012 ጀምሮ እንዲሞከር ተደርጓል። ጥናቱ ከፍተኛ የባለሙያ የቅርብ ክትትል የሚያስፈልገው በመሆኑም በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው በአዲስ አበባ በሚገኙት የቅዱስ ጴጥሮስና አለርት ሆስፒታሎች ነው።
ጥናት እንደመሆኑ ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊው ፈቃድ ከብሄራዊ የጤና ስነ ምግባር ኮሚቴ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የመድሀኒትና የምግብ ቁጥጥርና አስተዳደር ባለስልጣን እንዲሁም በየሆስፒታሎቹ ከሚገኙ የጤና ስነ ምግባርና ገምጋሚ ኮሚቴዎች ፈቃድ ተወስዷል።
በዚህ ጥናት የሚሳተፍ ማንኛውም ታካሚ በጥናቱ ከመሳተፉ በፊት ስላሉት የህክምና አማራጮች ስለ ጥናቱ ምንነት በጣም ዝርዝር መረጃ እንዲሰጠው ይደረጋል። ይሄ ሲሆንም እንደ አስፈላጊነቱ ከቤተሰብ ከወዳጅ ጋር እንዲወያይም ይደረጋል። ይሄ ከተደረገና ህመምተኛው መስማማቱን በፊርማው ሲያረጋግጥ በጥናቱ እንዲካተት ይደረጋል። ይህም ሆኖ በጥናቱ መሳተፉ የተለየ ጉዳት እንዳያደርስበት የሚደረጉ ምርመራዎች አሉ። በምርመራውም ውጤት መሰረት ምንም ለጉዳት የሚያጋልጡት ነገሮች እንደማይኖሩ ሲረጋገጥ በጥናቱ እንዲሳተፍ ይደረጋል፡፡ በዘህም መሰረት በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል 71 ታካሚዎች ህክምናውን ወስደዋል።
ያለም ጤና ድርጅትም (ከስትሪም) የአጭር ጊዜ ህክምና ተግባራዊ ካደረጉ ሀገራት የተገኙትን ውጤቶች መሰረት በማድረግ ህክምናው መድሀኒቱን ለተላመደው ቲቢ መሰጠት ይችላል የሚል መመሪያ እ.እ.አ 2016 ጀምሮ አዘጋጅቶ አሰራጭቷል፡፡ በ2018 በድጋሚ ህክምናው ውጤታማ መሆኑን በማሳወቅ መሰጠት እንደሚቻል አመልክቷል።
ጥናቱ እ.አ.አ በመጋቢት በ2019 ሲጠናቀቅ ይፋ በተደረገው ውጤት መሰረት እንደ አጠቃለይ በሁሉም ሀገራት ህክምናው ከተሞከረባቸው 424 ታካሚዎች ላይ በተደረገው ግምገማ የዘጠኝ ወር ህክምናው ከሀያ ወር ህክምናው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ተቀባይነት ያለው ውጤት ማምጣት የሚችል ህክምና እንደሆነ ተረጋግጧል።
በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያም የጥናቱን ውጤት በመቀበል ህክምናው በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ህክምናውን መስጠት የተጀመረ ሲሆን፣ ቀጥሎም በአዲስ አበባ አለርት ሆስፒታልና በጎንደር ሲሰጥ ቆይቷል፡፡በአሁኑ ወቅትም እንደ ሀገር 55 በሚደርሱ የህክምና ማእከላት ህክምናው እየተሰጠ ነው።
ህክምናው ከተጀመረ አንድ ዓመት ቢጠጋም፣ህክምናው ዘጠኝ ወር ስለሚፈጅ ያስገኘው ውጤት ምን ይመስላል የሚለው ጥናት የሚሰራበት ወቅት አሁን በመሆኑ ውጤቱ የሚታየው ከወራት በኋላ ይሆናል። እስካሁን ባለው ሂደት ግን ጥሩ ውጤት እየታየ ነው።
የጎንዮሽ ጉዳትንም በተመለከተ የተደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው ሁለቱም ተቀራራቢ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በመሆኑም የዘጠኝ ወር ህክምናውን ለሀያ ወሩ ህክምና በመተካት ተመሳሳይ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ተረጋግጧል። ረዥሙ ህክምና መርፌው ለስምንት ወር ሲሰጥ የዘጠኝ ወር ህክምናው ለአራት ወር ነው የሚሰጠው፡፡ ይህም መርፌን ተከትሎ የሚከሰተውን የመስማት ችግር የዘጠኝ ወሩ የሚቀንስ ይሆናል። ይሄ ማለት በመርፌ የሚሰጠው ህክምና እስካለ ድረስ በመስማት አቅም ላይ የሚፈጠረው ችግር ቢቀንስም እንደማይጠፋ ነው። በመሆኑም ይህንንም ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ውጤቶችን ለማግኘት ሁለተኛው ክፍል ‹‹ስትሪም›› የሚባለው ጥናት እየተካሄደ ይገኛል። በዚህ ጥናት የሚከናወነውም መርፌ የሌለውን ህክምና መርፌ ካለው ህክምና ጋር ተነፃጽሮ ተመጣጣኝ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ወይ የሚለው ይሆናል።
ለዚህም አዲስ ‹‹ቤዳኩሊን›› የሚባል መድሀኒቱን ለተላመደ ቲቢ ህክምና የሚውል መድሀኒትን ጨምሮ መርፌ ሳይኖር የዘጠኝ ወር ህክምና ተወስዶ በመርፌ ከሚሰጠው ጋር ተመሳሳይ ውጤት ለማግኘት እየተደረገ ያለ ጥናት እንዳለም ዶክተር ዳንኤል ይጠቁማሉ ። ይሄ ጥናት ተጠናቆ ውጤታማ መሆኑ ሲረጋጋጥና ለህሙማኑ መሰጠት ሲጀምር መድሀኒቱን ያልተላመደ ቲቢን ከመርፌ ውጪ ማከም የሚቻልበት ሁኔታም እንደሚፈጠር አመልክተዋል፡፡ ህክምና በዚህም በተጓዳኝ ይከሰቱ የነበሩ የጎንዮሽ ጉዳቶችንም ያስቀራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ህክምናውን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚቆጣጠረውና የሚመራው በጤና ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የቲቢ መከላከልና ህክምና ክፍል እንደሆነና፤ መድሀኒቶቹም በጤና ሚኒስቴር በኩል እየቀረቡ አብራርተው፤በመድሀኒት አቅርቦትም ተደራሽነትም በኩል የገጠመ ችግር እንደሌለ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያና የቲቢ በሽታ
የዓለም ጤና ድርጅት በ2018 ባወጣው ሪፖርት መሰረት ኢትዮጵያ የቲቢ፤ መድሀኒቱን የተላመደ ቲቢና ኤች አይ ቪ ህመምተኞች ካሉባቸው ቀዳሚ 30 ሀገራት መካከል እንደምትመደብ ያሳያል። ሪፖርቱ በሀገሪቱ 172 ሺ የሚደርሱ የቲቢ ታማሚዎች በ2017 እንደ ነበሩ እንደሚገመት የጠቆመ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 5 ሺ 500 የሚደርሱት የተላመደ ቲቢ የነበረባቸው ናቸው። ይህም ከአዲስ ቲቢ ታካሚዎች መካከል ሁለት ነጥብ ሰባት በመቶ እንዲሁም ከዚህ ቀደም የቲቢ ህመምተኛ ከነበሩት ደግሞ እስከ 14 በመቶ ይደርሳል። ጥናቱ በተካሄደበት እአአ በ2017 በኢትዮጵያ 29 ሺ የሚደርሱ ታካሚዎች በቲቢ በሽታ እንደሞቱ ይገመታል።
በራስወርቅ ሙሉጌታ