ደግነት ምግባሩ ኮሜዲ ሥራው የሆነው- አለባቸው ተካ

ብዙዎች በሙሉ ስሙ አይጠሩትም። አንዳንዶች ደግሞ ከቅጽል ስሙ ውጪ አያውቁትም ‹‹አለቤ›› ሲባል ካልሰሙ በስተቀር። ለዚህ ግን ምክንያት አላቸው። ለሰዎች ያለው ፍቅርና በጎነት ውስጣቸው ገብቶ የስሙን ትርጓሜ በራሳቸው ተንትነው ለሁሉ ሰው ደራሽነቱ ‹‹አለ በቤቴ›› ሲሉ ይጠሩታል። ምክንያቱም እርሱ ሰዎች ቤት የሚደርሰው በገንዘብ ብቻ አይደለም። አይዟችሁ ማለት ብቻ አይበቃውም። በተቻለው መጠን በፈገግታ ውስጣቸውን እንዲያረሰርሱና ደስታ በቤታቸው እንዲሞላ አንድ ቦታ ቆሞ ብዙ ቦታዎች ላይ መድረስ የሚችል ባለተስጥኦ ነው። እንዴት ካላችሁ እርሱ ቀልድ አዋቂ ነውና በቴሌቪዥን መስኮት ራሱ በፈጠረው ቶክ ሾው ለብዙዎች አለኝታ መሆን ችሏል።

አለቤ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ሲል የማይስቅ፤ የማይደሰት አለ ለማለት ያስቸግራል። ምክንያቱም እርሱ የባለብዙ ተሰጥኦ ባለቤት ነውና። ክራርና ማሲንቆ፤ ጊታርና ኦርጋን በመጫወት ሳይቀር ሰዎችን ማዝናናት ይችልበታል። ከፍ ሲልም በድምጹ ያንጎራጉራል። ግጥም በመደርደርም ማንም አያክለውም። የእርሱ ተፈጥሮ ሁለት መገለጫዎች አሉት። አንዱ ለሰዎች በችግራቸው ጊዜ መድረስ ሲሆን፤ ሌላኛው በሥራው ሰዎችን ማስደሰት ነው። አለቤ ሌላም የተለየ ነገር አለው። ይህንን የደስተኝነት ምንጩን የሚያስተጋባውና የሚያጋራው ለሀገሩ ልጆች ብቻ አይደለም። ባህር ማዶ ጭምር ዘልቆ ተወዳጅነትን አትርፏል።

ባህር ማዶ መሻገሩ ሰዎችን ደስተኛ ለማድረግ ብቻ አልነበረም። በስራው ኢትዮጵያ ማን ናት፤ ዓለም ደሃ እያለ የሚጠራት ወይስ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ልጆች መፈጠሪያ ምድር የሚለውን ጠንቅቆ ለዓለሙ ሀገራት ለማስረዳት ሞክሯል። በዚህ ደግሞ በተለያየ ጊዜ ልዩ ልዩ ሽልማቶች ተበርክተውለታል። ሀገራችንን በበጎ ገጽታ ለዓለም ስለአስተዋወቀልን እናመሰግናለንም ተብሏል።

ለመሆኑ ይህ ባለታሪክ ሰው የት ተወለደ፤ አስተዳደጉ ምን ይመስላል ከተባለ ጥቂት እናንሳ። ሙሉ ስሙ አለባቸው ተካ ይባላል። በ1953 ዓ.ም በሰሜን ወሎ ውርጌሳ በምትባል ትንሽ ከተማ ነው የተወለደው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለውም በዚሁ በትውልድ ቀየው ውርጌሳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተከታትሏል።

ልጅነቱ በነጻነት የታጀበ በመሆኑ ልጆ ችሎታውን ወይም ተሰጦውን የተረዳው ገና ልጅ ሳለ ነው። በአካባቢው ውስጥ ቀልድ አዋቂነቱን የሚያጎሉ በርካታ ነገሮችን ይከውናል። የእድሜ ጓደኞቹ፤ የአካባቢ ሰዎች እንዲሁም ቤተሰቦቹ በዚህ ተግባሩ በጣሙን ይወዱታል። ደስተኛ መሆንን ሲሹም ፈጥነው የሚጠሩት እርሱን ነው። አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለም ቢሆን በትምህርት ቤቱ ተወዳጅ ኮሜዲ ነበር። ይሁን እንጂ ኮሜዲ የሚለውን ሙያ አያውቀውም። ሥራ እንደሚሆንም አያስብም። ምክንያቱም ወቅቱ ይህንን ለማወቅ እድል የሚሰጥ አልነበረም።

በወቅቱ መቀለድ ለአንዳንዶች ተሰጥኦ ሳይሆን ማፌዝ (መተረብ) ተደርጎ ነው የሚወሰደው። ስለዚህም ሙያ እንደሚሆን ታውቆ ሳይሆን እንዲሁ ጊዜን በደስታ ማሳለፊያ ተብሎ ይወሰዳል። እርሱም የሚያስበው ይህንኑ ነው። በራሱ ላይ ደስታ ፈጥሮ ሌሎችን ዘና ማድረግ መልካም ነው ብሎ ያምናል። ይህንን በማድረግም ዓመታትን አሳልፏል።

አለቤ ከደረጄ ኃይሌ ጋር በነበረው ቆይታ እንዲህ ብሎ ነበር። ሦስት ነገሮችን መሆን በልጅነቱ ያልማል። አንደኛው የፊልም አክተር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ኳስ ተጨዋች ነው። ሦስተኛው የሀገር አቋራጭ አውቶቢስ ሹፌር መሆን ነው። በዚህም በልጅነቱ ደብተሩን መሪ እያደረገ ጭምር ይለማመድ ነበር። እንዳሰበውም ገና ወጣት ሳለ የመንጃ ፈቃድ ካርዱን ያዘ። ነገር ግን ሞቱ በሚወደውና በሚፈልገው ሥራ አማካኝነት በመኪና አደጋ ሆነ።

አለባቸው ቀናት ወራትን፤ ወራት ተደምረው ዓመታትን ካስቆጠሩ በኋላ ሥራው ምን ላይ እንደሚያርፍ ተረዳ። ልምዱን ወደ ተግባር ቀይሮ በዘመናዊ መልኩ አሳድጎት ኮሜዲነትን ሙያው አደረገ። በዚህም አዲስ ነገር በራሱ ፈጠረ። ማለትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውንና በየሳምንቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ‹‹አለቤ ሾው›› የተባለውን የቴሌቪዥን ቶክ ሾው (TV Talk Show) አዘጋጀና አቀረበ።

ይህ የቴሌቪዥን ዝግጅት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት (ተወዳጅነት) የነበረው ነው። በብዙዎች ልብ ውስጥ ያለና ብዙዎችን ያነጸ ነው። በርካቶችም እሁድ ጠዋትን ጠብቀው የሚከታተሉት ነው። የሀገር መሪ ሳይቀር ምስክርነት የሰጠለት ነው። እንዴት ተረጋገጠ፤ አብነታችሁ ማነው ከተባለ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹ኮሜዲያን አለባቸው ተካን እጅጉን እወደዋለሁ፤ በጣምም አደንቀዋለሁ›› ብለውለታል።

አለቤ ‹‹የድሆች አባት›› እያሉ የሚጠሩትም በርካቶች ናቸው። ምክንያቱም እርሱ ከራሱ ይልቅ ሌሎችን ያስበልጣል። በሰዎች መደሰት የሚደሰት ነው። አሁንም ከዚሁ ከቴሌቪዥን ቶክ ሾው ሳንወጣ ማሳያ እናንሳ። አለቤ በዝግጅቱ ላይ የሚቀርቡ እንግዶችም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን የተረሱ ቀደምት የጥበብ ሰዎችን እንዲያስታውሱ ያደርጋል። የሚታገዙበትን ሁኔታም ይፈጥራል። በዚህ ደግሞ ብዙዎች ቀና ብለው እንዲሄዱና ከችግራቸው እንዲያገግሙ ሆነዋል። ይህና መሰል ድርጊቱ ደግሞ በኢትዮጵያ ከታወቁት፣ ከማይረሱት፣ የዘመኑ እና ታዋቂ ኮሜዲያኖች መካከል አንዱ እንዲሆን አድርጎታል።

አለባቸው ተካ በኢትዮጵያ የኮሜዲነት ታሪክ ውስጥ ታላቁን አሻራ ካኖሩት መካከል አንዱ ነው። እርሱ የኮሜዲነት ሥራ እንዲዘምንና እንዲተዋወቅ ካደረጉ ፈር ቀዳጆች ተርታ የሚሰለፍ ነው። እንደውም የመጀመሪያ የሚባል ስም የተሰጣቸው ከባልደረባው ልመንህ ታደሰ ጋር በመሆን ‹‹ስታንዳፕ ኮሜዲ (Standup Comedy)›› እንዲጀመር ምክንያት በመሆናቸው ነው። ይህ ተግባራቸው በዓለም አደባባይ ብቅ እንዲልም ከአስቻሉት ውስጥ አንዱ ነው። በኮሜዲ በኩል ሥራን በዓለም ጭምር መሸጥ እንደሚቻል ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ወደ ሌሎች አገራት በመሄድ አሳይቷል።

አለባቸው ኮሜዲ ብቻ አይደለም። ተዋናይና የመድረክ መሪም ጭምር እንጂ። እርሱ የያዘው መድረክ በሳቅ እንጂ በሀዘን አይዘጋም። ሁሉም የደስታ ስሜቱን ይዞ ወደቤቱ እንዲገባ የሚያደርግ ነው። የአለባቸው የደግነት ጥግ ሰርጉን ሳይቀር በድሆች ያሸበረቀ ነው። በእርግጥ በጊዜው ካለው ታዋቂነት አንጻር የሚያጅበው በርካታ ሰው አያጣም። አንቱታን ያተረፉ በርካታ ጓደኞችና ባለሀብቶችም መጥተው ያደምቁለታል። ሆኖም የእርሱና የባለቤቱ ምርጫ ግን ድሆች አድማቂዎቻቸው እንዲሆኑ ነው። ድሆች የገነት መግቢያ ቁልፍ መሆናቸውን ያውቃሉና እነርሱን እንግዶቻቸው አድርገዋል። በተለይም ወላጆቻቸውን በኤችአይቪ ኤድስ ያጡና ወላጅ አልባ የሆኑ ሕፃናት የእነርሱ የክብር እንግዳና የሰርጋቸው ውበት እንዲሆኑ ጋብዘዋቸዋል።

ስለ አለባቸው ብዙ ሰው ቢጠየቅ ከኮሜዲነቱ በላይ አንድ ነገር ላይ ያርፋል። በጎነቱ ላይ። እናም ይህንን ያየውና በትራፊክ አደጋው ጊዜ አብሮ የነበረው እርሱ ግን ከሞት የተረፈው ኤፍሬም ደስታ በጎነቱን የገለጸበትን አንድ ነገር እናንሳ። ‹‹የደግነት ትርጉሙን የማውቀው በአለቤ ነው፤ የሰው ችግር ያመዋል፤ ‹የለኝም› ማለት አይችልም፤ ለራሱ ከመኖር ይልቅ ለሌሎች መኖርን ይመርጥ ነበር›› ሲል በእንባ ጭምር ስለእርሱ ተናግሮለታል።

አለባቸው ለሀገር ያለውን አበርክቶ በአንድ ነገር ብቻ ገድቦ ማስቀመጥ አይፈልግም። ወጥቶ መቅረቱን ባያውቀውም ነገ እንደሚሞት ይረዳልና አሻራውን በማይረሳ መልኩ አኑሮ ማለፍን ይፈልጋል። በዚህም በየአቅጣጫው ስሙን ለመትከል ይተጋል። ማሳያው ደግሞ በስሙ ያቋቋመው የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን ነው።

አለባቸው ታሪክ ተካይነቱ ከሞተም በኋላ ቢሆን አልቆመም። ምክንያቱም ከዚህ ዓለም በሞት በተለየ 10ኛ ዓመቱ ላይ ሙት ዓመቱን ምክንያት በማድረግ በመጋቢት 2007 ዓ.ም በተዘጋጀው መድረክ ላይ ድንቅ ነገር እንዲከሰት ሆኗል። የአለባቸው የመድረክ አልባሳትና የግል ቁሳቁሶች (ፎቶግራፎች፣ ዋንጫዎች፣ መፅሔቶችና ሕይወቱን የሚዳስስ ዘጋቢ ፊልም…) ተማሪዎች እንዲያውቁት፤ እንዲመራመሩበትና ለትውልድ እንዲያሻግሩት በሚል ለጥናትና ምርምር ተግባራት ግብዓት እንዲሆኑ በማሰብ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም ተሰጥቷል። በእለቱ የተለያዩ ሰዎች ምስክርነታቸውን ሲሰጡም ነበር። ለቤተሰቡና ለኪነጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም ሀሳቡን አቅርበው ሥራውን አቀናጅተው ለአስረከቡ አካላትም ምስጋና ችረዋል።

አለባቸው ከቤቱ ሲወጣ እንደሚመለስ አምኖና ተስፋ አድርጎ ነበር። ሆኖም ጥር 7 ቀን 1997 ዓ.ም ግን ለእርሱ ተስፋውን የሚሞላበት አልሆነለትም። የካሜራና ኤዲቲንግ ባለሙያው ይልማ ቀለመወርቅንና ሌሎች የሥራ ባልደረቦቹን ይዞ ለሥራ ነበር በጠዋት ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ ጉዞውን ያደረገው። የቀን ጎዶሎ ሆነበትና ድንገት በተፈጠረ የመኪና አደጋ በ44 ዓመቱ ሕይወቱን አጣ።

አለባቸው የሦስት ልጆች አባት ሲሆን፤ ልጆቹንና ባለቤቱን ሳይሰናበት ነው በወጣበት የቀረው። የቀብር ስርዓቱ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ-ክርስቲያን በተፈፀመበት ዕለትም እድሜን እንደጅረት ያድርግልህ የሚባለውን ደግ ሰው በማጣቱ እንባውን ያላፈሰሰ የለም። በርካቶችም ለወራት ልክ እንደቤተሰብ ስለሚቆጥሩት ጥቁር ለብሰው አዝነውለት እንደነበር ይታወሳል። ከዚያም ባሻገር የአለባቸው መሞት ሀገርን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ጭምር ያነቃነቀ እንደነበር በዘገባዎች ማረጋገጥ ይቻላል። ምክንያቱም በቀብር ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና ወዳጆቹ ብቻ ሳይሆኑ ታላላቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም ናቸው። እንደ ቢቢሲ፤ አሶሺየትድ ፕሬስ የመሳሰሉት ለአለባቸው ሞት የዜና ሽፋን ሰጥተው ነበር።

ጀግኖቻችንን እየቀበርን ዝም የምንል ከሆነና ካላስታወስናቸው ታሪክ ሰሪና ጀግኖችን ዳግመኛ ለማግኘትና ለመፍጠር በእጅጉ እንቸገራለን። ምክንያቱም እነርሱ ሲያልፉ ሥራቸውም አብሮ ይቀበራል። የሚታወሱ ከሆነ ግን የሚማርባቸው፤ አዳዲስ ነገር የሚፈጥሩ ወጣቶች ብቅ እንዲሉ ይሆናሉ። በዚህም ይመስላል በተደጋጋሚ እንደ እነ ኮሜዲያን አለባቸው ተካን የሚዘክሩ የተለያዩ መድረኮች ብቅ የሚሉት። በዚያ ቦታ ላይም ስለ ዋሉት ውለታና ስለ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቻችው የሚነገረው። በእነዚህ መድረኮች ላይ ደግሞ ከሕጻናት እስከ አዛውንት ድረስ ስለሚገኝ መማማሪያ መድረክነቱ ወሰን አይኖረውም። አዛውንቱ ያለውን ይሰጣል ተተኪው ደግሞ ይቀበላል።

የአለቤም ስራዎች ዘመን ተሻጋሪዎች ናቸው። በተለይም እነዚሁ ስራዎቹ ከመዝናኛነት ባሻገር የበጎ ስራዎችም የሚከወኑባቸው ስለነበሩ የበጎ ፈቃድ ስራ በተነሳ ጊዜ ሁሉ አለቤ አብሮ ይነሳል የሀገር ባለውለታነቱም ስርክ አዲስ ሆኖ ይዘከራል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ነሃሴ 17/2015

Recommended For You