«እኛን ለውጭ ጠላት አሳልፎ ሊሰጠን የሚችለው የእርስ በእርስ አለመስማማታችን ነው»ዶክተር ደሳለኝ አምባው የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

ቅምቅም ኢየሱስ በሚል በቀድሞ መጠሪያ የምትታወቀው ቦታ የትውልድ ቀበሌያቸው ናት። ወረዳው መቄት፣ ዞኑ ደግሞ ሰሜን ወሎ ነው። የአስኳላውን ደጅ ከመርገጣቸው በፊት በአካባቢያቸው የቄስ ትምህርትን ልቅም አድርገው ተምረዋል። ወቅቱ ደርሶ የመጀመሪያ ደረጃ ወደሆነው ድርቀሰፋይት ትምህርት ቤት ሲያቀኑ ግን ከአንደኛ ክፍል መጀመርን ‹‹አሻፈረኝ›› አሉ። ‹‹ምን ሲደረግ ነው ገና ሀ..ሁ ካልቆጠሩ ተማሪዎች ጋር አንደኛ ክፍል የምገባው ሲሉም እምቢኝ›› በማለት አስቸገሩ። ለእምቢተኝነታቸው ምክንያቱ ማንበቡንም ሆነ መጻፉን አሳምረው ማወቃቸው ነው።

በመሆኑም የመደመርና የመቀነሱን ስሌት ለአንድ ሳምንት ያህሉ አጥንተው በቀጥታ ወደፈለጉት 2ኛ ክፍል ገቡ። በጥሩ ውጤት ወደ ሶስተኛ ክፍል ገብተው ብዙም ሳይቆዩ ታህሳስ አካባቢ ወደ 4ኛ ክፍል ተዛወሩ። በተመሳሳይ ሁኔታ 5ኛ ክፍልን ዘልለው 6ኛ ክፍል ገቡ። እርሳቸው ከስድስተኛ ክፍል በታች ያሉትን ጎዶሎ ቁጥር ክፍሎች ውስጥ ገብተው አልተማሩም ማለት ይቀላል።

6ኛ እና 7ኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተከታተሉት በፍላቂት አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመማር ከሰሜን ወሎ ወደ ደቡብ ጎንደር ሻገር ብላ በምትገኘው በንፋስ መውጫ ከተማ በሚገኘው ንፋስ መውጫ ትምህርት ቤት አቀኑ። 12ኛን ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ቢሆንም በሁሉም የትምህርት አይነት ጎበዝ የሆኑትን ያህል በሒሳብ ትምህርት ግን ደከም በማለታቸው እንደሌሎቹ የትምህርት አይነቶች ‹‹ኤ›› በማምጣት ውጤታማ መሆን አልቻሉም። በመሆኑም ሐዋሳ እርሻ ኮሌጅ ገብተው በዲፕሎማ ተመረቁ።

በዲፕሎማው ለአራት ዓመት ያህል ካገለገሉ በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የእንግሊዝ አገሩ ኦፕን ዩኒቨርስቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ማዕከል በመማር ተመረቁ። በተመሳሳይ በተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ካገለገሉ በኋላ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፌዴራሊዝምና የመንግሥት ጥናት (ፌዴራሊዝም ኤንድ ገቨርናል ስተዲስ) ተምረው መመረቅ ችለዋል። በዚህ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ስምንት ያህል አርቲክሎችንም ለማሳተም በቅተዋል።

የዛሬው የዘመን እንግዳችን የሆኑት ዶክተር ደሳለኝ አምባው ከ30 ዓመት በላይ የሥራ ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ በዲፕሎማቸው ለአራት ዓመት ያህል በጎጃም ሁለት እጁነሴ ወረዳ ውስጥ በምትገኝ አንዲት ቀበሌ ውስጥ በግብርና ሁለገብ ባለሙያነት አገልግለዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ ደግሞ ከቀበሌ ወደ ወረዳ በመውጣት በደብረማርቆስ ከተማ ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል። ከፍ ሲልም ወደ ክልል ወጥተው በባህር ዳር ከተማ የማኔጅመንት ኢንስቲትዩትን በዋና ዳይሬክተርነት፤ ቀጥሎም እዚያው ክልል ላይ የአቅም ግንባታ እና ሲቪል ሰርቪስ ቢሮን በኃላፊነት መርተዋል።

የካበተ ልምድ ባለቤት የሆኑት የዛሬ እንግዳችን የሶስተኛ ዲግሪያቸውን መመረቂያ ጽሑፍ የሰሩት በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት ፍትሃዊነት ላይ ሲሆን፣ ያሳተሟቸውም አርቲክሎች በዚህ ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው። እንግዳችን ዶክተር ደሳለኝ ከክልል ወደ ፌዴራል በመምጣት በከተማ ልማት ሚኒስቴር፤ በኋላም በትራንስፖርት ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታነት አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ይገኛሉ። አዲስ ዘመንም የዛሬ እንግዳው አድርጎ ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርጓል። መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ መልክ ሥራዎችን እየተገበረ እንደሚገኝ ይነገራል፤ በዋነኝነት እያከናወነ ያለው ምንድን ነው?

ዶክተር ደሳለኝ፡- ኢንስቲትዩቱ በዋናነት ያለው ተልዕኮ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት መስኮች ላይ እውቀት ተኮር የሆኑ እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ ጥናትና ምርምሮችን ማድረግ ነው። የምክክር መድረኮችንም ማዘጋጀትና ለፖሊሲ አውጭዎች ምክረ ሃሳቦችን ማቅረብም ተጠቃሽ ሥራው ነው። እንዲሁም የጥናትና የምርምር ሥራዎችን ማሳተምና ማሰራጨትም በተልዕኮው ውስጥ የሚካተት ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ያለው ሌላኛው ተልዕኮ ማማከርና ለውጭ ጉዳይ አገልግሎት ዲፕሎማቶችን፣ ባለሙያዎችን እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሥልጠና ያዘጋጃል። በጥቅሉ ሥራው ምርምርና ሥልጠና መስጠት ነው ሊባል ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ በምርምር ላይ ውይይትና ምክክሮችን ያካሂዳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፖሊሲ ገለጻና የቢሆን ትንተናዎችም ጎን ለጎን የሚካሄዱ ናቸው። ለምሳሌ አንዱ ትንተና የሰራንበትን ርዕሰ ጉዳይ ለመጥቀስ ያህል በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተደረገው ጦርነትን የተመለከተ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ያለው አንድምታ ምንድን ነው? በሚለው ላይ ያጠነጠነ ነው። በተመሳሳይ በጎረቤት አገሮች የተካሄዱ ምርጫዎችንም በዚሁ አግባብ ትንተና ያካሄድንበት ጉዳይ መሆኑን ለመጥቀስ እወዳለሁ።

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት የተቋቋመው በአዲስ አደረጃጀትና ሁለንተናዊ የለውጥ ጎዳና በመያዝ ነው። በዚሁ መሠረት በውጭ ግንኙነት ረገድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ሊመጡባት የሚችሉትን እና ያሉባትን ሀገራዊ ስጋቶች፣ ያሏትን መልካም አጋጣሚዎች እንዲሁም እድሎችን መለየት ነው። በተለይም በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት ለማካሄድ የተቋቋመ ተቋም ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የኢንስቲትዩቱ አደረጃጀት እንዴት ይገለጻል?

ዶክተር ደሳለኝ፡- የውጭ ጉዳይ አደረጃጀት መልክዓምድራዊ ነው። ከውጭ ጉዳይ ጋር በትይዩ እና በሚናበብ መልኩ ለመሥራት በምርምር ዘርፍ አምስት አደረጃጀቶች አሉን፤ እነዚህም የአፍሪካ ጉዳዮች፣ የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች፣ የኤዥያ፣ ፓሲፊክና ኦሽኒያ ጉዳዮች፣ የአሜሪካና አውሮፓ ጉዳዮች እንዲሁም የባለ ብዙ ወገን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ጉዳዮች ናቸው።

የአፍሪካ ጉዳዮች አደረጃጀት ስለ አፍሪካ የሚያጠና ሲሆን፣ ዋና ሥራው በምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ነው። በተለይም ከሰላምና ደህንነት ጋር እንዲሁም ከጸረ ሽብርተኝነትና ቀጣናዊ ትስስር እና ውሕደት ጋር የተያያዘ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ነው። እንደሚታወቀው መካከለኛው ምስራቅ ተለዋዋጭ የሆነ የፖለቲካ ትኩሳት የሚስተዋልበት ነው። እንዲያም ሆኖ መካከለኛው ምስራቅ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ እስራኤል ስትሆን The Abraham Accords Declaration ‹‹የአብርሃም ስምምነት›› በሚል በሚታወቀው መርህ ተፈራርመናል። ይህ የስምምነት ፊርማ አድጎ የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ደረጃ የደረሰ ነው።

ሶስተኛው የኤዥያ፣ ፓሲፊክና ኦሽኒያ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው። በዚህም በተለይ የቻይና ቲንክ ታንክ ወይም አሰላሳይ ኮር ቲም ጋር ተፈራርመናል። ይህ የሚያጠነጥነው ኢትዮጵያ ከቻይና እና ሕንድ ጋር ያላትን ግንኙነት እንዴት የበለጠ ማሻሻል ይቻላል በሚለው ላይ ነው። በእርግጥ ከቻይና ጋር ያለን ግንኙነት ጥሩ የሚባል ሲሆን፣ ከሕንድ ጋር ግን ገና በሚባል ደረጃ ላይ ያለ ነው። ከደቡብ ኮርያና ከአውስትራሊያ ጋርም እንዲሁ ለማጠናከር የሚሰራበት አደረጃጀት ነው። በጥቅሉ ኢትዮጵያ ከኢዥያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንዴት አጠናክራ መሄድ ትችላለች በሚለው ላይ ያተኮረ ነው።

አራተኛው የአሜሪካና አውሮፓ ጉዳዮች ሲሆን፣ ይህም በተለይ ከምዕራባውያኑ ጋር ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚገባው ግንኙነት ምንድን የሚለውን የሚመለከት ነው። የመጨረሻውና አምስተኛው አደረጃጀት የባለ ብዙ ወገን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅት ጉዳዮች ነው። ይህ እንደ አውሮፓ ሕብረት፣ አፍሪካ ሕብረት ብሎም ኢጋድና መሰል ሕብረቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት የሚለውን የሚያጠና ነው። በዚህ ዙሪያ ከምናደርገው ጥናት አንዱ በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ መቀመጫ እንዲኖራት ምን ብናደርግ የተሻለ ነው የሚል እና ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር እንድትሆን መደረግ ያለበት ምንድን ነው የሚለውን የሚመለከት ነው። እነዚህ አደረጃጀቶች ሁሉ የምርምር ዘርፉ የሚሰራቸው ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ከሌሎች ሀገሮች የወሰደው ልምድ ይኖር ይሆን?

ዶክተር ደሳለኝ፡- ከሌሎች ሀገሮች ጋር አጋርነት ፍለጋ እና በአውታረ መረብ ሥራ እንሰራለን። ለምሳሌ በቻይና እንደ እኛ አይነት ተቋም አለ፤ ይህ የእነርሱ ተቋም እኤአ በ1949 የተቋቋመ ነው። ተቋሙ በውጭ ጉዳይ ዙሪያ የቻይናን መንግሥት የሚያማክር ነው። እኛም የምንፈልገው ልክ እንደ ቻይናው አይነት ተቋም መሆን ነው። ከዚህ ተቋም ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል። የሰሯቸውን የምርምር ሥራዎች እንዲሁም የታተሙትንም ይልኩልናል። በተመሳሳይ በኔርዘላንድስ ከሚገኘው ተቋም ጋርም እንዲሁ ተፈራርመናል። ተቋማቱ ሥልጠናም ሰጥተውናል። ከእስራኤል ጋርም እንዲሁ አድርገናል። ከተለያዩ ሀገራት ተቋማት ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ስንፈራረም በውጭ ጉዳይ ይሁንታ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በሀገር ውስጥና በጎረቤት ሀገሮች የምትሰሩት ሥራ ትኩረቱ ምን ላይ ነው?

ዶክተር ደሳለኝ፡- ትልቁ ሥራችን ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር ነው። እንደሚታወቀው የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ችግር ያለበት ነው። ከዚህ የተነሳ እኛ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት እንዴት አድርገን እናጠናክር በሚለው ዙሪያ እንቅስቃሴ ጀምረናል። እንቅስቃሴያችን ደግሞ ጎረቤት አገሮችን በሚያዋስኑ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ያነጣጠረ ነው። በዚህም መሠረት ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር በመሥራት ለውጥ ለማስመዝገብ መንቀሳቀስ ጀመርን። ለምሳሌ በሱማሌ ክልል ካለው የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር አብረን መሥራት የሚያስችለንን ስምምነት ተፈራርመናል። ይህን ያደረግነው በዓላማ ነበርና የሱማሌን ክልል የሚያዋስኑ የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጎረቤቶቻችን ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመን አብረን መሥራት ጀመርን።

ጅግጅጋ ላይ በትኩረት የምንሰራው በሽብርተኝነት ዙሪያ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ እንዴት አድርገን መፍትሔ ማምጣት እንችላለን በሚል የምርምር ውይይትም ኮንፈረንስም የምናደርግ ይሆናል። በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የሱማሊኛን ቋንቋ የሚችሉ መምህራን ስላሉ በጋራ በመሆን በጸረ ሽብርተኝነት ላይ አብረን መሥራት ጀምረናል። ሥራችንም ከሱማሊያና ከሱማሌ ላንድ ጋር ያለንን ግኑኙነት ከማጠናከር ጋር የተያያዘም ነው።

በተመሳሳይ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆንም ከሱዳን ጋር ባለን የድንበር ውዝግብ ጋር ተያይዞ በጋራ ለመሥራት በሚያስችል ሁኔታ ተፈራርመናልም፤ ውይይትም አካሂደናል። ውይይታችንም ከድንበሩ ጋር በተያያዘ የመፍትሔ አካል መሆን የሚችል ጭምር ነው። ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዲሁ የተፈራረምን ሲሆን፣ በተለይ አተኩረን በቱሪዝም ዲፕሎማሲ ላይ እንሰራለን።

 በሌላ በኩል ገና አላጠናከርነውም እንጂ ከአሶሳ እና ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ጋርም በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ዙርያ ለመሥራት ዕቅድ አለን።

ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋርም በተለይ ኢትዮጵያ ፓን አፍሪካኒዝምን ጨምሮ በአፍሪካ ላይ ልተከተለው የሚገባ አሰራርን በተመለከተ ውይይት አካሂደናል። ገና ያልተፈራርመናቸው ሚዛን ቴፒና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎችም አሉ። በቀጣይ ከእነርሱም ጋር የምንፈራረም ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በተቋሙ የሚሰጡት ሥልጠናዎች በአብዛኛው ትኩረታቸው ምን ላይ ነው?

ዶክተር ደሳለኝ፡- በተቋሙ የሚሰጡት ሥልጠናዎች ሁለት አይነት ናቸው። ሥልጠናዎቹ በራሳቸው ደረጃ ያላቸው ሲሆኑ፣ ይኸውም ከጀማሪ እስከ ሚኒስትር የሚሰጡ ናቸው። ሠልጣኞች አንደኛውን ደረጃ በብቃት ካልሠለጠኑ ወደ ሁለተኛው ደረጃ መሸጋገር አይችሉም። ሥልጠናው እንደየአስፈላጊነቱ በውጭ አገር ሆነውም በኦንላይን የሚሰጣቸው ነው። ይሁንና ለጊዜው ሥልጠናው የተቋረጠ ሲሆን፣ ይኸውም የነበረውን ክፍተት ገምግመን የምንቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በአንዳንድ አምባሳደሮች ዘንድ በሀገራቸው እየተካሄደ ስላለ እንቅስቃሴም ሆነ ስለሌሎች ጉዳዮች ተወክለው ለሄዱበት ሀገር በመግለጽ ደረጃ ክፍተት እንዳለባቸው ይነገራል፤ በዚህ ዙሪያ በተለይ የተለያዩ የቋንቋ ክህሎት እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያ ኢንስቲትዩቱ ምን እየሠራ ነው?

ዶክተር ደሳለኝ፡- ያልሽው ጉዳይ አግባብነት ያለው ነው፤ በቅርቡ የዲፕሎማቶችና ድጋፍ ሰጪዎች ስምሪት ይደረጋል። ዲፕሎማቶች ከመሰማራታቸው በፊት በተቋማችንም ሥልጠና በመስጠት ላይ ነው። የቋንቋም ችግር በተለይ እንግሊዝኛም ሆነ ፈረንሳይኛ፣ ስፓኒሽ፣ አረብኛ እንዲሁም ቻይንኛን የመሳሰሉ ቋንቋዎችን ከመናገር አኳያ ችግር እንዳለ ተስተውሏል።

በእርግጥ ሁላችንም ዘንድ በተለያዩ ቋንቋዎች የመግባባት ችግር አለብን። ይህን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ይቻለን ዘንድ ማሠልጠን ጀምረናል። ለምሳሌ የፈረንሳይ ኤምባሲ ለፈረንሳይኛ ቋንቋ ለሥልጠናው የሚሆን ወጪ ስለሸፈነልን ለወጣቶቹ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎችን ጨምሮ በፍቃደኛነት ፈረንሳይኛ ሥልጠና በመጠት ላይ ነው።

በአዲሱ ዓመት ደግሞ የስፓኒሽ ቋንቋን የማሠልጠን ተግባር ይጀመራል። ልክ እንደ ፈረንሳይ ኤምባሲ ሁሉ የስፔን ኤምባሲም የሥልጠና ወጪያችንን የሚሸፍኑልን ይሆናል። ፖላንድም በተመሳሳይ ወጪውን በመሸፈን የሚያስጀምሩልን ይሆናሉ።

የቋንቋዎቹ በተገቢው መንገድ መናገር መቻል በተባበሩት መንግሥታት ላይም የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ስለሚያስችል ፋይዳው ላቅ ያለ ነው። በተለይ ለዲፕሎማሲያችን መጎልበት የአረብኛ ቋንቋን ማወቅ አስፈላጊ ነው። ስለሆነም ወጪውን የሚሸፍን አፈላልገን አረብኛውንም ቻይንኛውንም ለማስጀመር ፍላጎቱ አለን።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ለመሆን ጥያቄ ማቅረቧ ይታወቃል፤ ይህ ጥያቄዋ በቅርቡ ተቀባይነት ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል?

ዶክተር ደሳለኝ፡- በዚህ ጉዳይ ጥናት አጥንተን የቢሆን ትንተና ሰርተናል። ይህም የቢሆን ትንተናችን የሚያሳየው የማይሳካላት መሆኑን ነው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ጥረት ባለመደረጉ ነው። ይሁንና በአሁኑ ጥያቄያችን እድሉን ባናገኝ እንኳ በቀጣይ ሊሳካልን እንደሚችል ተስፋ አለን።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን እንዳለባት ብዙዎች ይስማሙበታል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ ?

ዶክተር ደሳለኝ፡– በነገራችን ላይ ከዚህ ካነሳሽው ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያይዞ አንድ ጥናት ተሠርቷል። የተሠራው ጥናት ለፖሊሲ ገለጻም ተዘጋጅቷል። ነገር ግን ምንም ይሁን ምን የቀይ ባህር ግብጽ አባይ ላይ ተጽዕኖ ከምታደርገው በላይ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖራት መከላከል ላይ ትተጋለች። በተለይ ደግሞ በታሪኳ ሁሉ ኢትዮጵያን ከሚጠቅም ነገር ሁሉ ለማስወጣት ትታትራለች።

ለምሳሌ ግብጽን ጨምሮ የተለያዩ የአረብ አገራትን ያካተተ አንድ የቀይ ባህርን የሚመለከት ማኅበር አለ። በዚህ ማኅበር ውስጥ በስትራቴጂካዊ መንገድ ታስቦበት ኢትዮጵያ ወደማኅበሩ ድርስ እንዳትል ተደርጋለች። ይህም ማለት በተቀመጠው ደንብ ላይ ያካተተችው ነጥብ ቢኖር ማኅበሩ የባህር ዳርቻ የሌላቸውን ሀገራት አያካትትም የሚል ነው። የዚህ ማኅበር አባል ሀገራት ከሆኑት ውስጥ ጂቡቲም ሱማሊያም ተጠቃሽ ናቸው።

ኢትዮጵያ የመከልከሏ ምስጢር የባህር ዳርቻ የላትም በሚል ቢሆንም ማኅበሩ ኢትዮጵያን ብቻ አለማካተቱ ሳይሆን እስራኤልንም የማይጨምር ነው። እስራኤል ያለመካተቷ ምክንያቱ ደግሞ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አረብ ያልሆኑ አይገቡበትም በሚል ውሳኔ ነው። ስለዚህ እስራኤል አረብ አይደለችምና ምንም እንኳ መልካምድራዊ አቀማመጧ መካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ቢያካትታትም በዚህ አመክንዮ እንዳትገባ ተደርጓል። በተመሳሳይ ምክንያት ኢራንም እንዳትገባበት ተደርጓል።

ሆኖም እኛ በቀይ ባህር ላይ ቦታ እንዳይኖረን የተሴርብንን ሴራ ተረድተን ከሠራን በቀላሉ ውጤት ማምጣት እንችላለን። ለምሳሌ ከእኛ ጋር የተሻለ ግንኙነት ያላቸው የአረብ አገራት ጋር ያለንን ግንኙነት የበለጠ ማሻሻል ያስፈልገናል። ለአብነት ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያለን ግንኙነት በጣም ሲሻሻል ግብጽ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ያስችለናል።

ነገር ግን ይህ የሚሆነው ሰላማዊ በሆነና በመግባባት መንፈስ ነው እንጂ በጉልበት የሚደረግ ነገር አለመኖሩ ልብ ሊባል ይገባል ባይ ነኝ። በምናደርጋቸው እያዳንዱ እንቅስቃያችን ምንም እንኳ ብሔራዊ ጥቅም የምናስከበር ቢሆንም ከሌሎቹ ጋርም የሚኖረን ግንኙነት መልካማ በሆነ ዲፕሎማሲ ላይ የተመሠረተ ነው።

ኢትዮጵያ የትኛውንም መብቷን ስትጠይቅ በጉልበት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያምነው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ የባህር በር ይኖራት ዘንድ መሻቷ ሲሆን፣ ይህንንም የማግኘት አማራጭን ለመጠቀም ትፈልጋለች። ያንን የምታደርገው ግን ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ እንደሆነ መዘንጋት የለበትም።

የባህር በር ለማግኘት የሚጠቅመንን አማራጭ ሁሉ መጠቀምም አንዱ ስልት ነው። ለምሳሌ በሰጥቶ መቀበል መርህ ልናስኬደው እንችላለን። እንዲህም ሲባል ለምሳሌ በረጅም ጊዜ ውል በመፈራረም የሚፈለገውን ወደብ ለማግኘት መስማማት አንዱ ስልት ሊሆን ይችላል። ከዚህ አኳያ የባህር በር ማግኘት የምንችላቸው አካባቢዎች የሚታወቁ ናቸውና አማራጮችን ሁሉ ለመጠቀም እንሻለን። የባህር በር እንዲኖረን የምናደርገው ጥረት በተሳቀቀ መንገድ ሳይሆን ሰጥቶ በመቀበል መርህ ነው።

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት፤ የታላቅ ሕዝብም ባለቤት ናት፤ የሕዝብ ቁጥሯ በራሱ ትልቅ ገበያ ነው። ይህ ትልቅ ገበያ ከውጭው ሀገር ጋር በአግባቡ የምንገበያይበትን መስመር መላ ማለትን የሚጠይቅ ነው። ስለሆነም ጥያቄያችንም በዲፕሎማሲያዊ መንገድና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ይሆናል ተብሎ የሚታመን ነው። ደግሞም በጉዳዩ ላይ በትኩረት የሚሠራ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- በኢንስቲትዩቱ በኩል በቀይ ባህር ዙሪያ ጥናት መጀመሩን ጠቅሰዋል፤ ምን ላይ የሚያተኩር ነው?

ዶክተር ደሳለኝ፡– አዎ! ጥናት ጀምረናል። ርዕሰ ጉዳይ ተነስቶ በጉዳዩ ላይ ደግሞ ስምምነት ላይ ተደርሶ ጥናት ማጥናት ተጀምሯል። እኛ በጉዳዩ ዙሪያ አጥንተን አማራጭ የሆኑ ሃሳቦችን ለመንግሥት ማቅረብ ነው። በቀይ ባህር ዙሪያ ጥናት ማጥናት ማለት ሁሉንም አማራጮች በዛ ውስጥ ተካተቱ ማለት ነው።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ፍላጎቷን ገና ባልገለጸችበት ሁኔታ ጉልበት ልትጠቀም ነው በሚል ከጎረቤቶቻችንም ጋር ለማነካካት በብዙ የሚጥሩ እንደነበሩ ማስተዋል ችለናል። ይህን አይነት ወሬ የሚያስወሩ አካላት ደግሞ ኢትዮጵያ የያዘችው ርዕይ እንዳይሳካላት የሚፈልጉ እንደሆነ እሙን ነውና ፍላጎታቸውን አንስተውም።

እኛ አማራጭ ነው ብለን የምንለው ከቀይ ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ ያለውን ነው። አንድ ቦታ ላይ ብቻ ሆነን ቁንጽል የሆኑ ጥናት አናጠናም። ጉዳዩ በዚህ አግባብ የተጀመረ ሲሆን፣ ወደፊትም ስኬታማ እስክንሆን ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡- ሥራችሁን የምታከናውኑበት ስትራቴጂ እንደምን ይገለጻል?

ዶክተር ደሳለኝ፡– እኛ የምንሠራው ረቂቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን መሠረት አድርገን ነው። እሱ ደግሞ በቅርቡ ይጸድቃል ብለን እየጠበቅን ነው። ማንኛውንም የውጭ ግንኙነት ሥራችንን ስንሰራ ረቂቅ ፖሊሲውን መሠረት አድርገን ነው። በእስካሁኑም ሒደት ያጋጠመን ችግር የለም። ምክንያቱም የውጭ ግንኙነታችንን፣ ሰላምና ደህንነታችንንም ሆነ ሌላ ጉዳያችንን ረቂቁን ፖለሲ ተንተርሰን እየሠራን ነው።

ለምሳሌ እኤአ ከ2020 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓለም መንግሥታት አዳዲስ ስትራቴጂዎች መውጣት የጀመሩበት ጊዜ ነው። ለማሳያ ያህል የአሜሪካ የውጭ ደሕንነት ስትራቴጂ ወጥቷል፤ እንዲሁም አሜሪካ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጋር የምትሰራበት ስትራቴጂ አውጣታለች። ጃፓንም የራሷን የደሕንነት ስትራቴጂ አውጥታለች። በተመሳሳይ ጀርመንም እንግሊዝም የራሷን ሰነድ አውጥተዋል። ከዚህ ውስጥ አንዳንዱ በተለይ ከሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በኋላ የወጣ ነው። ይህ ሰነዳቸው ግልጽ የሆነው ነው። ድብቁ ሰነድ ደግሞ አለ።

ቻይና ደግሞ የውጭ ግንኙነት ሕግ በሚል አውጥታለች። በተለይ ግሎባል ዴቨሎፕመንት ኢኒሼቲቭ፣ ግሎባል ሴኩሪቲ ኢኒሼቲቭ፣ ግሎባል ሲቪላይዜሽን ኢኒሼቲቭ በሚልም ሶስት ኢኒሼቲቮችን አውጥታለች።

አዲስ ዘመን፡- ዲፕሎማቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ምን ምን ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ይላሉ?

ዶክተር ደሳለኝ፡– እያንዳንዱ ሀገር የየራሱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ነው የሚሠራው። ዲፕሎማቶቻችን በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም ሆነ በማህበራዊው ጉዳዩ ላይ የሚሰሩት የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የእያንዳንዱን ሀገር ስትራቴጂ ማወቅ ግድ የሚል ነው። ያም በመሆኑ በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች የተለያዩ ሀገራት ስትራቴጂ ተነቦ ለስራችን በግብዓትነት እንድንጠቀመው ሆኗል። በግልጽ የወጣውን ስትራቴጂ ቀርቶ ድብቁን ፍላጎታቸውንም ማወቅ በተሻለ ለመንቀሳቀስ የሚያግዝ ነው። ሁሉም የሚሠራው ከዚህ አቅጣጫ አንጻር ነው።

በነገራችን ላይ የተረዳነው ነገር ቢኖር ሁሉም አፍሪካ ላይ ለመረባረብ ያሰፈሰፈ ብቻ ነው። ምክንያቱም አፍሪካ ጥሬ ሀብት ያላት ከመሆኗ በተጨማሪ የሕዝብ ቁጥሯም ለገበያም ሆነ ለሥራ ምቹ ነውና ከሱ መጠቀም አለብን የሚል አተያይ አላቸው። ይህንን ድብቅ ፍላጎታቸውንም ጠንቅቆ በማወቅ ነው የኢትዮጵያን ጥቅም ማስጠበቅ የምንችለው። የኢንስቲትዩቱ የሥራ መዳረሻው ለመንግሥት አማራጭ የፖሊሲ ሃሳብ ግብዓት የሚሆን ነገር ማቅረብ ነው። እየሠራን የምንገኘውም በዚህ መንገድ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከውጭ የሚቃጣባት ድብቅ ሴራ አሊያም ተጋላጭነቷ እንዴት ይገለጻል?

ዶክተር ደሳለኝ፡– ኃያላን መንግሥታት ማለትም እርስ በእርስ በተለያዩ ጥቅሞች ላይ የሚሻኮቱ ሀገራት የሚስማሙት ጉዳይ ቢኖር በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ብቻ ነው። እንደሚታወቀው ምዕራባውያኑ ቻይናን ካልያዝን ባይ ናቸው። እርስ በእርስ የሚተያዩት የባላንጣነት ያህል ነው። እንዲያም ሆኖ ሁሉም የየራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

እኛ ኃያላኑ እርስ በእርስ በሚያደርጉት ሽኩቻ በሚፈጠር ጥቅም ነው ጥቅማችንን እያስጠበቅን ያለነው። ለምሳሌ ሁሌ አርብ አርብ በተቋማችን ውይይት አለ፤ ይኸውም አገራት ምን ሲሆኑ ነው ጥቅምና ጉዳታችንን የምንረዳው የሚለው ጉዳይ በስፋት ይቅርባል። በተለይ አንዱ ከአንዱ ጋር ሲስማም ይሁን ሲጣላ የኢትዮጵያ ጥቅምና ጉዳት ምንድን ነው የሚለውን ለይተን እናየዋለን። ለሚመለከተውም እናቀርባለን።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ስጋቴ ነው ብላ የምትጠቅሰው ችግር ምንድን ነው?

ዶክተር ደሳለኝ፡- ስጋት የሚሆነው ከውጭው ይልቅ የውስጥ ተገላጭነቱ ነው። ከዚህ ውጭ ለሌላ ሀገር ኢትዮጵያ ተጋላጭ የሚያደርጋት ሁኔታ የለም። እኛን ለውጭ ጠላትም አሳልፎ ሊሰጠን የሚችለው የእርስ በእርስ አለመስማማታችን ነው። ይህ አለመስማማት የሚኖር ከሆነ ግን የውስጥ አለመስማማታችንን ተጠቅሞ የውጭ ጠላት በቀላሉ ሊያገኘን ይችላል።

ለምሳሌ በግብጽ በኩል የሚመጣን ተጽዕኖ የአደባባይ ምስጢር ነው። ምናልባትም እርሷን ደግፈው የሚንቀሳቀሱ ሀገራት እንዲሁም በተዘዋዋሪ መንገድ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ። እሱ ግን የሚያይለው የእኛ እርስ በእርስ አለመስማማት ሲጎለብት ነው። ምንም እንኳ ከአባይ ግድብ ጋር ተያይዞ የግብጽም ሆነ የምዕራባውያኑ ሴራ ቢኖርብንም እኛ ትልቅ ሕዝብ ያለን ታላቅ አገር እንደመሆናችን የውስጥ ተጋላጭነታችን ቢስተካከል የዚያን ያህል የሚያሰጋን ነገር አይኖርም።

አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ተቋሙ በዋናነት ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለሚመለከተው አካል ለፖሊሲ አውጪዎች የሚሆን ምክረ ሃሳብ ማቅረብ ነው፤ ከዚህ አኳያ ምን ተጨባጭ ሥራ አከናወናችሁ?

ዶክተር ደሳለኝ፡- በጥናትና ምርምር የደረስንበትን ምክረ ሃሳብ ለውጭ ጉዳይ እናቀርባለን፣ ኮንፈረንስና ሲሚናር ደግሞ እናካሂዳለን። እነዚህ ሁሉ ግብዓት እየሆኑ ናቸው ብለን እናምናለን። ከዚህ የተነሳ ሌሎች ተጨማሪ የቤት ሥራዎች እየተሰጡን ነው። ጠንካራ የምርምር ቡድንም እየተፈጠረ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

ዶክተር ደሳለኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 13/2015

Recommended For You