የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያ ፋይዳ እና ስጋት

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ነሐሴ 01 ቀን 2015 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የዋጋ ንረትን በከፍተኛ ደረጃና በቀጣይነት ሊቀንሱ የሚችሉ የተለያዩ የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን አድርጓል።

የዋጋ ንረቱን ለማርገብ ቦርዱ ያሳለፋቸውን የገንዘብ ፖሊሲ ማሻሻያዎች አስመልክቶ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ለመንግሥት የሚሰጠው የቀጥታ ብድር ባለፈው ዓመት ከተሰጠው ከ1/3ኛ እንዳይበልጥ በሌላ አነጋገር በ25 በመቶ እንዲገደብ፤ በ2016 በጀት ዓመት ሰኔ መጨረሻ የሀገር ውስጥ ብድር ዕድገት በ14 በመቶ ጣሪያ እንደሚገደብ፤ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ከብሔራዊ ባንክ ከሚወስዱት የብድር ፋሲሊቲ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበረው የውጭ ምንዛሬ የማስተላለፍ ግዴታ ከ70/30 ወደ 50/50 እንዲሻሻል ተወስኗል። በዚህም በመመሪያው መሰረት ላኪዎቹ ካፈሩት የውጭ ምንዛሪ 50 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ፣ 10 በመቶውን አብረው ለሚሠሩት ባንክ እንዲሰጡ እና 40 በመቶውን ለራሳቸው እንዲጠቀሙ መወሰኑንም ገዡ ጠቁመዋል።

ይህ ውሳኔ የዋጋ ንረትን በማርገብ ረገድ ምን ያህል ሚና ይጫወታል? እርምጃው በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? የዋጋ ንረትን በወሳኝና ተከታታይ በሆነ መንገድ መቀነስ ካልተቻለ እንደ ሀገር ምን ቀውስ ያስከትላል? በሚል አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጉዳዩ ዙሪያ የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግሯል።

በኢፌዴሪ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የባንክና ፋይናንስ ፖሊሲ ጥናት ክፍል አስተባባሪ እና በሙያቸው ደግሞ ፋይናንሻል ኢኮኖሚስት የሆኑት ተወልደ ግርማ (ዶክተር) እንደሚሉት፤ በእርሳቸው እምነት ለሀገሪቱ የዋጋ ንረት ሦስት ዋና ዋና አንኳር መንስኤዎች አሉ። አንደኛው በመንግሥት በጀትና ወጪ መካከል ያለ አለመጣጣም ነው። ሁለተኛው ሀገሪቷ ወደ ውጭ ከምትልከውና ከውጭ በምታስገባው እቃዎች እንዲሁም አገልግሎቶች መካከል መሀል ያለው ልዩነት ነው። ሶስተኛው የተቋማት ሕግን የማስፈጸም አቅም ውስንነት ነው።

ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ የወሰዳቸው እርምጃዎች ምን ያህል ለውጥ ያመጣል የሚለውን ከነዚህ ሦስት የዋጋ ንረት መንስኤዎች ጋር አዛምዶ ማየት እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ጠቅሰው፤ ውሳኔውን ከመንግሥት ገቢና ወጪ አለመጣጣም አኳያ ሲታይ፣ ለአብነት ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ጦርነት ብቻ ቢያንስ ወደ 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን የኢትዮጵያ ብር ሀገሪቷ እንዳወጣች ይታመናል። የሀገሪቷን የሁለት ዓመት በጀት ሊስተካከል ጥቂት የቀረው ገንዘብ ነው። ይህም የመንግሥት በጀትና ወጪ ይበልጥ ልዩነቱ እንዲሰፋ አድርጎታል።

በዚህም በተለይ ከደርግ ውድቀት ማግስት መንግሥት የቀጥታ ብድርን አቁሞ የመንግሥትን የግምጃ ቤት ሰነድ በመሸጥና በመለወጥ ላይ የተመሰረተ ብድር ነበር የሚያካሂደው። ነገር ግን ከጦርነቱ ማግስት መንግሥት ተመልሶ ወደ ቀጥታ ብድር ገብቷል። ይህም የሀገሪቱን የዋጋ ንረት በእጅጉ እንደሚጨም ረው ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል ሀገሪቱ መሰብሰብ ያለባትን ግብር በሚፈለገው ደረጃ እየሰበሰበች እንዳልሆነ ገልጸው፤ እየተገባደደ ባለው በጀት ዓመት መንግሥት ከግብር ወደ 560 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል። ነገር ግን የ2016 ዓ.ም በጀት የተያዘው ከ800 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። ይህ ማለት መንግሥት ወደ 240 ቢሊዮን ብር ገደማ በብድር ወይ ከሌላ ዓለም በእርዳታ ለማግኘት አቅዶ ነው በጀት ዓመቱን የጀመረው። ይህ የሚያሳየው በበጀትና ወጪ መካካል አለመጣጣም መኖሩን ነው።

በበጀትና ወጪ አለመጣጣም ምክንያት የሚመጣውን የዋጋ ንረት ለማስቀረት ባንኩ የመንግሥትን ቀጥታ ብድር በ25 በመቶ እና የሀገር ውስጥ ብድርን ደግሞ በ14 በመቶ እንዲገደብ አድርጓል። ይህም ወደ ኢኮኖሚው የሚረጨውን ገንዘብ ለመቀነስ ታስቦ የተወሰደ እርምጃ ነው። የዋጋ ንረቱን የሚያረጋጋ በጣም ትልቅና ቆራጥ ውሳኔ ነው።

ሆኖም መንግሥት ከጦርነት አዙሪት የማይወጣ ከሆነ፤ የግብር አሰባሰብ ሂደቱን ፍትሀዊ አድርጎ ማስቀጠል ካልቻለ … ወዘተ መንግሥት ቀጥታ ብድር ማቆም የሚችልበት ዕድሉ እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል። ስለዚህ የባንኩ ውሳኔ ተግባራዊ ይደረጋል ወይ የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

ሌላው ባለፈው ዓመት የባንኮች አማካኝ የብድር ዕድገት 30 በመቶ እንደነበር አውስተው፤ የሀገር ውስጥ ብድር ዕድገትን በ14 በመቶ መገደቡ ትልቅ ውሳኔ ነው። ሆኖም ውሳኔው ተጓዳኝ ችግሮችን ይዞ ሊመጣ ይችላል። ምክንያቱም የሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግር የዋጋ ንረት ችግር ብቻ አይደለም። ሥራ አጥነትም አንዱ ችግር ነው። ሥራ አጥነት ከሚቀረፍባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ለግል ባለሀብቱ የሚሰጥ ብድር ነው። የሀገር ውስጥ ብድር ወደ 14 በመቶ ወረደ ማለት የግል ባለሀብቱ ሊያገኝ የሚችለውን የብድር ዕድል ያጠበዋል ማለት ነው። ውሳኔው የዋጋ ንረቱን በማስተካከል ረገድ ትልቅ ተጽኖ ቢኖረውም በአገሪቱ ካለው ሥራ አጥ ቁጥር አንጻር ውሳኔው በተመሳሳይ ተግባራዊነቱ ላይ ጥርጣሬ የሚያስነሳ ነው።

ብሔራዊ ባንክ ወደ ኢኮኖሚው ብዙ ገንዘብ መርጨት ሲፈልግ የሚያበድርበትን ወለድ ይቀንሰዋል። በተቃራኒው ወደ ኢኮኖሚው የሚረጨውን ገንዘብ መቀነስ ሲፈልግ ደግሞ የሚያበድርበትን ወለድ ከፍ ያደርገዋል። ስለዚህ ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ከሚወስዱት የብድር ፋሲሊቲ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል የተደረገው ወደ ኢኮኖሚው የሚረጨውን ገንዘብ ለመቀነስ ታስቦ ነው። ይህ ውሳኔ ወደ ኢኮኖሚው የሚረጨውን ገንዘብ በመቀነስ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት አንዱ ሳይንሳዊ ዘዴ ነው። ነገር ግን አሁን ባለው የሀገሪቱ ሁኔታ የዋጋ ንረቱ 29 በመቶ ገደማ ነው። ወለዱ ከሀገሪቱ የዋጋ ንረት አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ ባንኮች ከቸገራቸው ከብሔራዊ ባንክ ተበድረው 18 በመቶ ወለድ ቢከፍሉ ትርፋማ ይሆናሉ። ወለዱ ከመበደር አያግዳቸውም። ለመበደር ወደ ኋላ አይሉም። በመሆኑም የዋጋ ንረቱን ከማረጋጋት አኳያ የሚጠበቀውን ያህል ለውጥ ላያመጣ ይችላል።

የሀገሪቱን ኤክስፖርት እየጎዱ ካሉ ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ የውጭ ምንዛሪ የማስተላለፍ ግዴታ (forex surrender requirement) እንደሆነ ተወልደ (ዶ/ር) ገልጸው፤ ላኪዎች ካገኙት የውጭ ምንዛሪ ውስጥ 20 በመቶ ሲወስዱ የነበረውን ወደ 40 በመቶ ማሳደጉ በጣም ጥሩ እርምጃ ነው። ነገር ግን ውሳኔው ሰዎችን በእጅጉ አበረታቶ ኤክስፖርት እንዲያደርጉ የሚያደርግ አይደለም። የሀገሪቱን ኤክስፖርት ለማሳደግ ከዚህ በላይ ማበረታቻ ማድረግ ያስፈልጋል።

ምክንያቱም አንድ ሰው እቃ ሽጦ መቶ ዶላር ቢያመጣ በወቅታዊ ሕጋዊው የምንዛሪ ዋጋ ብሔራዊ ባንክ በ55 ብር አባዝቶ ይሰጣል። ነገር ግን ይህ ሰው ያገኘውን ምንዛሪ በጥቁር ገበያው መንዝሮ ቢሸጥ 100 በመቶ ልዩነት አለው። ይህ ማለት አንድ ሰው እቃ ሽጦ ምንዛሪ ሲያመጣ 100 በመቶ ታክስ ይደረጋል ማለት ነው። ላኪዎችን በጣም የሚያከስር ነው። ስለዚህ መንግሥት ለሚፈልገው ሴክተር በተለይ ለላኪዎች ልዩነቱን በመደጎም በጥቁር ገበያው ተቀራራቢ ዋጋ መንዝሮ ቢሰጥ፤ አንድ ዶላሩን ወደ ሕገወጥ አያሸሹም፤ ሁለት የኤክስፖርት ዘርፉን ይበልጥ ማበረታታት ወይም ማሳደግ እንደሚችል ይናገራሉ።

እንደ ምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርሄ (ዶክተር) ትንታኔ ደግሞ፤ በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የገንዘብ ፍሰት በሚኖርበት ጊዜ በአቅርቦትና በፍላጎት መሃል ያለውን አለመመጣጠን ያባብሰዋል። ምክንያቱም ብዙ ገንዘብ ሰዎች እጅ ላይ ሲኖር፤ አንድን እቃ ተወዳድረው በምንም ዋጋ ለመግዛት ቁርጠኛ ይሆናሉ። ስለዚህ በኢኮኖሚው ውስጥ የገንዘብ ፍሰቱ መብዛት ለዋጋ ግሽበት አንዱ መንስኤ ነው።

ስለዚህ “ሰዎች እጅ በርከት ያለ ገንዘብ ስላለ የዋጋ ግሽበት ይኖራል” በሚል እሳቤ ብሔራዊ ባንክ የሀገር ውስጥ ብድርን 14 በመቶ ገድቧል። ስለዚህ ባንኮች የሚሰጡት ብድር እየቀነሰ ሲሄድ ሰዎች እጅ ያለ ገንዘብ እየቀነሰ ይሄዳል። ባንኩ የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት የወሰደው እርምጃ ትክክለኛ ነው።

ምክንያቱም ባንኮች የሚሰጡት ብድር ሲታቀብ፤ ህብረተሰቡ እጅ የሚገባ ገንዘብ እየቀነሰ ይሄዳል። ይህም ከባንክም ተበድረው ይሁን በሌላ መንገድ ያገኙ ጥቂት ባለገንዘቦች ዋጋውን እያናሩ የሚሄዱትን እድል ይገታዋል። አንድን እቃ ወይም አገልግሎት ለማግኘት የሚስተዋለውን ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ ውድድር ያስቀረዋል። ይህ ውሳኔ በእርግጥ በተወሰነ መንገድ ልማትን ሊጎዳ ወይም ሊያስተጓጉል ይችላል። ነገር ግን የዋጋ ግሽበቱ አብዛኛውን ህብረተሰብ ክፍል ስለሚጎዳ በልማቱ መጎዳት ይሻላል በሚል የህብረተሰቡን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት የተወሰነ ውሳኔ እንደሆነ ይናገራሉ።

እንዲሁም ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ ከሚወስዱት የብድር ፋሲሊቲ ላይ የሚከፍሉት ወለድ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉ በተመሳሳይ ወደ ሰዎች እጅ የሚገባውን ገንዘብ በመቀነስ የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ባለሙያው ገልጸው፤ ዓለም ላይ ያሉ መሰል ብሔራዊ ባንኮች የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት የሚወስዱት እርምጃ አንዱ የወለድ መጠን ከፍ ማድረግ ወይም ዝቅ ማድረግ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የገንዘብ ፍሰቱን መቀነስ ነው።

ለአብነት ልክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደምንለው የአሜሪካ ፌዴራል ሪዘርብ የተሰኘው ተቋም የወለድ መጠኑን ከ1 ነጥብ 25 ወደ አምስት በመቶ አሳድጎት ነበር። በዚህም የሀገሪቱን የዋጋ ግሽበት አሁን ላይ ከዘጠኝ በመቶ በታች አውርዶታል። ስለዚህ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበቱን ለማረገጋት የወለድ መጠኑን ወደ 18 በመቶ ከፍ ማድረጉ ትክክል ነው። የወለድ መጠኑ ዝቅተኛ በመሆኑ ባንኮችን ከመበደር እንደማያግዳቸው የተወልደን (ዶ/ር) ሀሳብ ይጋራሉ።

ነገር ግን ዓለም ላይ ያሉ ብሔራዊ ባንኮች የዋጋ ንረትን ለማርገብ ማድረግ የሚችሉት የገንዘብ ፍሰት መቀነስና ወለድ መጨመር ነው። ወለድ ሲጨምሩ ብድር እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ በተዘዋዋሪ የሰው እጅ ያለው ገንዘብ እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው። ከዚህ አኳያ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው እርምጃ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት አንድ መንገድ ብቻ ነው። ባንኩም ከዚህ ውጭ ምንም ሊያደርግ አይችልም።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁን ላይ ኮቪድ ባስከተለው ጠባሳ፣ በራሺያና ዩክሬን ጦርነት ቀውስ ምክንያት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ዓለም ውስጥ አለ። በዚህም የአቅርቦት ሰንሰለቱ ተናግቷል። በጦርነት መሀል ያሉት ሀገሮች 30 በመቶ የሚሆነውን የዓለምን የምግብ ፍጆታ የሚያቀርቡ ናቸው። ሀገራቱ ጦርነት ላይ በመሆናቸው በተለይ ስንዴና የምግብ ዘይት ዋጋው እየናረ ሄዷል።

ከዚህ አንጻር ብሔራዊ ባንክ የወሰደው የገንዘብ ማሻሻያ ፖሊሲ ምንም አይፈይድም። ባንኩ የወሰደው እርምጃ የሚጠቅመው በሀገር ውስጥ ከልክ በላይ የተረጨው ገንዘብ ሲሰበሰብ፤ በሰዎች እጅ ላይ ያለ ገንዘብ እያነሰ ይሄዳል። ይህንን ተከትሎ የዋጋ ግሽበቱ በሂደት ይቀንሳል የሚል እምነት በመኖሩ ነው።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዋግ ግሽበት ዋና መንስኤው ከውጭ በሚገቡ እቃዎች ነው። ለአብነት የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር የትራንስፖርት ዋጋ ይጨምራል። የትራንስፖርት ዋጋ ሲጨምር የምግብ ፍጆታ እቃዎች ዋጋ ይጨምራል። አስመጪዎች በውድ እቃ ሲያስገቡ በዚያው ልክ ዋጋ ይጨምራሉ። ይህ ለዋጋ ንረቱ ትልቅ እንድምታ አለው። ስለዚህ የብር ምንዛሪ ዋጋ እያሽቆለቆለ የሚሄድ ከሆነ የዋጋ ግሽበቱ እየቀጠለ ይሄዳል። ስለዚህ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ሌሎች የመፍትሄ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የውጭ ምንዛሪ ከማስተላለፍ ግዴታ አኳያ የሀገሪቱ ኤክስፖርት እየቀነሰ መሄዱን ባለሙያው ገልጸው፤ ለአብነት አንድ ኪሎ ቡና አምርቶ ለኤክስፖርት አዘጋጅቶ ለመላክ 700 ብር ይፈጃል። የዓለም ገበያ ላይ አራት ዶላር ነው ዋጋው። አራት ዶላር አሁን ባለው የምንዛሪ ዋጋ 220 ብር ነው። ስለዚህ አንድ ቡና የሚልክ ሰው 500 ብር እየከሰረ ኤክስፖርት የሚያደርግበት ምክንያት የለም። ይህ ማለት ኤክስፖርቱ እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው።

አሁን ላይ 50 በመቶ ለብሔራዊ ባንክ፣ 10 በመቶ አብረው ለሚሰሩት ባንክ እና 40 በመቶ ዶላሩን ደግሞ ነጋዴው እንዲጠቀም ተደርጓል። አንድ ነጋዴ ከ20 በመቶ በእጥፍ ወደ 40 በመቶ የውጭ ምንዛሪ ሲያገኝ ባገኘው ምንዛሪ ከውጭ እቃ አምጥቶ (መድሃኒት፣ ወዘተ) በፈለገው ዋጋ ሽጦ ይጠቀማል። ይህ ማለት ቡና ወይም ሌላ እቃ ልኮ የደረሰበትን ኪሳራ ሌላ እቃ አምጥቶ ሽጦ በሚያገኘው ትርፍ ያካክሳል ማለት ነው። ይህም ላኪዎችን ያበረታታል። በተዘዋዋሪ ደግሞ ሀገሪቱ ኤክስፖርት እንዲጨምር ያደርጋል።

ሆኖም ይበልጥ የሀገሪቱን ኤክስፖርት ለማሳደግ የተለየ አይነት የምንዛሪ አሠራር መዘርጋትና ብሩ እንዲንሳፈፍ ወይም ዶላር በገበያ ዋጋ እንዲመነዘር ማድረግ ይገባል። በገበያ ዋጋ ቢንሳፈፍ ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶች የራሳቸውን ስለሚያገኙ ኪሳራ አይኖረውም።

በ2016 የዋጋ ግሽበቱን ከ20 በመቶ ለማውረድ እንዲሁም በ2017 ደግሞ 10 በመቶ በታች ለማድረስ ታቅዷል። አይደለም 20 በመቶ 10 በመቶ በጣም ብዙ ነው። የአንድ አገር ኢኮኖሚ ጤናማ የሚባለው የዋጋ ግሽበቱ ሁለት በመቶ ሲሆን ነው። ስለዚህ በዋጋ ግሽበቱ ቋሚ ገቢ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞችና ጡረተኞች በእጅጉ እየተጎዱ ነው። በዚህም ይህ የማህበረሰብ ክፍል በመንግሥት ሥርዓት ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል። የልማት ዕድገት ሊቋረጥ ይችላል። ተባብሶም በዋጋ ንረት ሳቢያ በሱዳን እንደተቀሰቀሰው የማያበራ ግጭትና ጦርነት ሊፈጥር ይችላል ብለዋል።

በጥቅሉ እንደባለሙያዎቹ እምነት ሀገሪቱ ከገባችበት የጦርነት አዙሪት ተላቃ በግብርና የተጀመረውን ምርትና ምርታማነት ይበልጥ በማሳደግ፤ የእቃዎች ዝውውርን የሚያውኩ ችግሮችን በመቅረፍ፤ በለውጡ እየታየ ያለውን የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ ገደብ የማጠናቀቅ ቁርጠኝነትን አጠናክሮ በማስቀጠል፤ ዜጎች በቀላሉ ሥራ መፍጠር የሚችሉበትን አገልግሎትና ምርት በማቅረብ ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ የዋጋ ንረቱን በወሳኝነትና ተከታታይ መንገድ መቀነስ ካልተቻለ የዋጋ ንረት በሌሎች ሀገሮች እንዳስከተለው አይነት ህዝባዊ ነውጥ እንደሚያስከትል ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን   ነሐሴ 16/2015

Recommended For You