እየተዝናኑ መማር

 የሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች የሚመሩትን ፕሮግራም ‹‹እየተዝናናችሁ የምትማሩበት›› ሲሉ እንሰማለን። እንደዚህ ብለው ግን የሚነግሩን ስለአንዲት የውጭ አገር ዝነኛ አርቲስት የእርግዝና ድግስ (ቤቢ ሻወር) ሊሆን ይችላል፡፡ በበኩሌ አያዝናናኝም፤ አያስተምረኝምም።

እየተዝናኑ መማር ያልኩት ለተማሪዎች ነው። ሰሞኑን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈትነው ውጤት እየተጠባበቁ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ እረፍት ላይ ነው፡፡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም እረፍት ላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ተማሪዎች የቀጣዩን ዓመት ትምህርት ያጠናሉ፡፡ በሬዲዮና ቴሌቪዢን የሚሰጡ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን ይከታተላሉ፡፡ በዛሬው የትዝብት ዓምዳችን እንዲህ አይነት ትምህርት የሚሰጡ መገናኛ ብዙኃንን እናመሰግናቸዋለን፡፡

በነገራችን ላይ ‹‹ትዝብት›› ሲባል ብዙዎቻችን ትዝ የሚለን ወቀሳ ብቻ ነው፡፡ አድናቆትም ትዝብት ነው፡፡ ። ለምሳሌ፤ እንደ ምርጫ ባሉ ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ታዛቢ ተብለው የሚቀመጡ አሉ፡፡ ስህተትን ብቻ ለመታዘብ ሳይሆን ያስተዋሉትን ጥሩ ነገርም ለመመስከር ነው፡፡

በትዝብት ስም ከሚጻፉ ጽሑፎች (የእኛን ጨምሮ) የምናነበው መስተካከል አለባቸው የምንላቸውን ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነው፤ ወቀሳዎች ይበዛሉ፡፡ ትክክል ነው። መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዲስተካከሉ መታዘብና መውቀስ ያስፈልጋል፡፡ በዚያው ልክ ግን ጥሩ የሆኑ ነገሮችንም ማድነቅ ሌሎች ጥሩዎችን መፍጠር ነው፡፡

ወቅቱ የክረምት ወቅት ነው፡፡ ለተማሪዎች የእረፍት ወቅት ስለሆነ በየቤታቸው ናቸው፡፡ የእረፍት ወቅት ነው ማለት ግን ከትምህርት ይርቃሉ ማለት አይደለም፡፡ መስከረም ላይ ወደሚቀጥለው ክፍል ስለሚገቡ የሚቀጥለውን ክፍል የትምህርት አይነቶች ከወዲሁ ይጀምሯቸዋል፡፡ ያለፉትን ክፍልም ለሚቀጥለው ስለሚያግዝ ይከልሱታል፡፡

ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ደግሞ (ሰሞኑን የተፈተኑት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች) ስለ ዩኒቨርሲቲ ሕይወት ማወቅ ይፈልጋሉ፤ ከዩኒቨርሲቲ ለእረፍት የተመለሱ ተማሪዎችንም ይጠይቃሉ፡፡ መገናኛ ብዙኃን ይከታተላሉ፡፡ ስለዚህ መገናኛ ብዙኃን ለተማሪዎች በሚሆን መንገድ ማቅረብ አለባቸው፡፡ ከምንም በላይ ግን ዋናው ነገር ከ12ኛ ክፍል በታች ያሉት ተማሪዎች ጉዳይ ነው፡፡ ለእነዚህ ተማሪዎች ትምህርት መሰጠት አለበት፡፡ ለምሳሌ በኢቴቪ መዝናኛና የልጆች ቻናል ላይ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችና ጥያቄና መልስ አለ፡፡

ጥያቄዎቹ እንደሌሎቹ ጥያቄና መልስ ውድድሮች የጠቅላላ ዕውቀት ሳይሆኑ መደበኛ የትምህርት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት እንዳየሁት፤ ጥያቄ ይጠየቃል፤ ተማሪዎች በስልክ ይመልሳሉ፤ ከመለሱ በኋላ ስቱዲዮ ያለው መምህር ያብራራል፡፡ ልክ መማሪያ ክፍል ውስጥ የሚጠየቁት አይነት ማለት ነው፡፡

የቴሌቪዥኑ ስክሪን ላይ “Which one of the Following ….?” የሚለውን ሳይ ወደ ልጅነቴ ነው የተመለስኩት፡፡ መጀመሪያ እንዳየሁት፤ እንዴት ይሄን ትምህርት መዝናኛ ቻናል ላይ ያደርጉታል ብዬ ነበር። እያደር ሳስበው ግን ተማሪዎች የእረፍት ጊዜ ላይ ስለሆኑ እየተዝናኑ የሚማሩት ነው፡፡ በዚያ ላይ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሚተነተኑበት የዜና ቻናል ቢሆን ልጆች አያዩትም፡፡ እየተዝናኑ መማር ማለት ይህ ነው፡፡

መምህራን አንዳንድ ጊዜ ‹‹እየተጨናነቃችሁ አታጥኑ›› ይላሉ፡፡ አሁን ወቅቱ ክረምት ነው፤ ተማሪዎች በፈተና የሚጨናነቁበት አይደለም፡፡ እስከ አሁን የተማሯቸውንና በሚቀጥለው ክፍል የሚማሯቸውን በዚህ ሁኔታ ማጥናታቸው ወደ ውስጣቸው እንዲሰርፅ ያደርጋል። በዚያ ላይ ደግሞ ጥያቄ ለመለሱ ተማሪዎች የመጽሐፍ ስጦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም ሌሎች ተማሪዎች እንዲነቃቁና እንዲከታተሉ ያደርጋል፡፡ እያዝናኑ ማስተማር እንዲህ ነው! በዚሁ እግረ መንገድ በሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም አይቼ ካመሰገንኳቸው ልጠቃቅስ፡፡ ይሄም እያዝናና የሚያስተምር ሆኖ ያገኘሁት ነው፡፡

በአንድ የቴሌቪዥን ቻናል ላይ አንድ የመዝናኛ ፕሮግራም አየሁ፡፡ ተወዳዳሪዎቹ የሚጠየቁት በክረምት ወቅት አርሶ አደሩ የሚያንጎራጉራቸውን ቃል ግጥሞች ነው፡፡ ለከተሜ ነዋሪ ከባድ ይመስላል፡፡ ባለማወቃቸውም ስንኙን ራሳቸው በሚፈልጉት መንገድ (ቤት እንዲመታ ብቻ) ጨረሱት፤ ይሄ ያሳዝናል። የአርሶ አደሩን ጥበብና ቅኔ ማስታወሱ ደግሞ ትምህርት ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ጋዜጠኛዋ ጥያቄዎቹን በሚገባ ታብራራቸዋለች፡፡

በቴሌቪዥን የመዝናኛ ፕሮግራሞች ብዙም አስተውየው የማላውቀውን ከዚሁ ቴሌቪዥን አርሶ አደሩ ለሚያመርታቸው የቅመማቅመምና እህል አይነቶች ትኩረት መስጠቱ ነው፡፡ ተወዳዳሪዎቹ የእነዚያን የቅመማቅመም አይነቶች እንዲናገሩ መደረጉም ሌላው የተወዳደሩበት ጉዳይ ነበር፡፡ ቀላል ይመስለን ይሆናል፤ ዳሩ ግን ልብ ያልተባለና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ የሀገር ምርት ነው፡፡

እየተዝናኑ መማርም ሆነ ማስተማር ሲባል የግድ ለተማሪዎች ብቻ አይደለም፡፡ ተፈጥሮንም ሆነ ማኅበራዊ ሕይወትን በማወቅ ሁላችንም ተማሪዎች ነን፡፡ ስለዚህ ለአዋቂዎችም ቢሆን እያዝናና የሚያስተምር ነገር ጥሩ ነው፡፡ በብዙ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ የሚነሳው ቅሬታ የውጭ መገናኛ ብዙኃን አሠራሮችን መኮረጅ ነው፡፡ ከራስ ፈጠራ ይልቅ የውጭ ሀገራትን አይቶ ለማስመሰል መሞከር ነው፡፡ የራሳችን የሆነ ነገር የሚያዝናና አይመስለንም፡፡ ግን ደግሞ ለባሕላችን ትኩረት አልሰጠንም እያልን እንታዘባለን፤ እንወቅሳለን፡፡

ከላይ የጠቃቀስኳቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ያስተዋልኳቸው ነገሮች ግን እያዝናኑ ያስተማሩኝ ናቸው። ምንም እንኳን የተማሪዎች ጥያቄ ትኩረት የሚያደርገው ተማሪዎች ላይ ቢሆንም፤ ልጆችን በዚህ መንገድ መቅረጽ የእኛ የአዋቂዎች ድርሻ ነው፡፡ ልናበረታታቸው የሚገባን እኛ ነን፡፡ ለተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ለመምህራንም የሚሆን ነው፤ በየዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎችም የሚሆን ነው፡፡

የኬሚስትሪ ወይም ፊዚክስ ጥያቄ ሲጠየቅ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠራ ሰው ይማርበታል፤ ጂኦግራፊም ወይም ሌላ የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ሲጠየቅም እንደዚሁ በየዘርፉ ያለ ሰው እየተዝናና ይማርበታል፡፡ የአርሶ አደሩን የስነቃል ጥበብ ውጤቶች ማስታወስ ለከተሜው እንደ አዲስ ያዝናናዋል፤ ለሚያውቀውም ያስታውሰዋል፤ ታሪክና ባሕሉም እንዲሰነድ ያደርጋል፡፡

በማኅበራዊ ገጾች (ዩትዩብ) ‹‹ሰርፕራይዝ፣ ፕራንክ…›› እና በመሳሰሉት የሚያዝናኑ ነገሮችን እናያለን፡፡ በዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን ደግሞ አንዳንድ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚያስተምርና የበጎ አድራጎት ሥራ የሚሠራ ፕሮግራም ሊመሰገን ይገባል፡፡ ለምሳሌ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ ‹‹ተከፍሏል›› የሚባለው ፕሮግራም እያዝናና የሚያስተምር ነው፡፡

ያ ዕድል ያጋጠማቸው ሰዎች ቀኑን ሙሉ ጉሊት ቢውሉ ምናልባትም ምንም ሳይሸጡ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ቴሌቪዥን ጣቢያው ግን በዕለቱ ሊያገኙ የሚችሉትን ይከፍላቸዋል፤ በድርጊቱም ዘና ብለው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡ በአርዓያነቱ ደግሞ ሌሎችን ያበረታታል ማለት ነው፡፡

በመጨረሻም፣ በእንደዚህ አይነት ወቅት ከምንም በላይ ለተማሪዎች የበለጠ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባበት ጊዜ ነው። ክረምት ነውና መደበኛ ትምህርት ባይማሩም ቀለል ባለ መንገድ ትምህርታቸውን እንዳይረሱት ማድረግ ያስፈልጋል። እያዝናናችሁ የምታስተምሩ መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች ምሥጋና ይገባችኋል። ተማሪዎችም

እየተዝናናችሁም ቢሆን ከትምህርት አትራቁ።

መልካም የእረፍት ጊዜ!!!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *