የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ኮከብ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ምርጫ ያካሄዳል፡፡ ማህበሩ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመትም ኮከብ ተጫዋችና ኮከብ ወጣት ተጫዋችን መርጧል፡ ፡ የተካሄደው የኮከቦች ምርጫ ዓለም አቀፍ አሰራርን የተከተለ ትክክለኛ አካሄድ መሆኑንም ማህበሩ አስታውቋል፡፡
ማህበሩ ከተቋቋመ አራት ዓመታትን ያስቆጠር ሲሆን የእግር ኳስ ተጫዋቾችን መብትና ጥቅምን ለማስከበር የተቋቋመ ነው፡፡ ማህበሩ የ2015 ዓ.ም የዓመቱ ምርጥ ተጫዋቾች ምርጫን በዚህ ሳምንት ይፋ ሲያደርግ በአዋቂ እግር ኳስ ተጫዋቾች የቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ የክንፍ ተጫዋች ቢኒያም በላይ የተመረጠ ሲሆን፣ በተስፈኛ ወጣት ተጫዋች ዘርፍ የአዳማ ከተማው ዮሴፍ ታረቀኝ ተመርጧል፡፡
ምርጫው በውድድር ዓመቱ በክለቦቻቸው ጥሩ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾች በእጩነት ቀርበው ከተወዳደሩ በኋላ የሚካሄድ ሲሆን፣ የ16ቱ የሊጉ ክለቦች በአምበሎቻቸው አማካኝነት ማህበሩ ባስቀመጠው በይነ መረብ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡ ይህንንም ድምጽ በመደመር ማህበሩ የዓመቱን ኮከብ ተጫዋች እና ወጣት ኮከብ ተጫዋችን እንደሚመርጥ የማህበሩ ጸሐፊ ኢንስትራክተር ዮሐንስ ሳህሌ ተናግረዋል።
በአዋቂዎች ዘርፍ የዘንድሮ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አለልኝ አዘነ ከባህር ዳር ከተማ፣ ቢኒያም በላይና ሌሎች በሊጉ ጥሩ የውድድር ዓመትን ማሳለፍ የቻሉ ተጫዋቾች ተካተዋል። በወጣቶች ደግሞ የአዳማ ከተማው ተጫዋች ዮሴፍ ታረቀኝና አማኑኤል በዕጩ ተፎካካሪነት የተካተቱ ናቸው። በኮከብነት የተመረጠው ቢንያም በላይ በውድድር ዓመቱ ባሳየው ብቃት ክለቡን ለሊጉ አሸናፊነት ማብቃት ችሏል። የ25 ዓመቱ የክንፍ ተጫዋች 30 ጨዋታዎች ላይ ለክለቡ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን 2458 ደቂቃዎችን በሜዳ ላይ ቆይቷል። በቆየባቸው ደቂቃዎች 1 ጎል እና 5 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበልም ችሏል። የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው ሌላኛው ተፎካካሪ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በ30 የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች 2595 ደቂቃዎችን በሜዳ ላይ መቆየት የቻለ ሲሆን 23 ጎሎችን አስቆጥሮ 3 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል በውድድር ዓመቱ ድንቅ ጊዜ አሳልፏል። ሽልማቱን ለመቀዳጀት በፍክክር ውስጥ ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል በወልቂጤ ከተማ ድንቅ የውድድር ዓመትን ያሳለፈው ጌታነህ ከበደ፣ የድሬዳዋ ከተማው ቢኒያም ጌታቸው እና የባህር ዳር ከተማው አለልኝ አዘነ ዋነኞቹ ነበሩ። የወጣቶቹን ዘርፍ ያሸነፈው የ18 ዓመቱ የአዳማ ከተማ ተጫዋች ዮሴፍ ታረቀኝ ከሁለተኛው ቡድን አድጎ በውድድር ዓመቱ አስደናቂ ብቃት በማሳየት የዓመቱ ኮከብ ወጣት ተጫዋች ለመባል በቅቷል። ተስፈኛው ተጫዋች ለክለቡ በ18 ጨዋታዎች ተሰልፎ 8 ጎሎችን አስቆጥሯል። ዘንድሮ ካገኘው የመጫወት ዕድል አኳያ ጥሩ የሚባል ብቃትን በማሳየቱም በቀጣይ ዓመታት ተስፋ ከተጣለባቸው ኮከቦች አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሌላው ዓለም እንደሚደረገው በሊጉ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ምርጫውን ማካሄ ዳቸው ሙያውን የጠበቀና ዓለማቀፋዊ አሰራርን የተከተለ እንደሚያደርገው ኢንስትራክተር ዮሐንስ አስረድተዋል።
ተጫዋቾች የማህበሩ አባል በመሆናቸውና መመሪያና ደንቡን በማወቃቸው በምርጫው ሂደት የገጠመ ችግር አለመኖሩን የጠቀሱት ኢንስትራክተር ዮሐንስ፣ ማህበሩ በኮከብነት ለሚመርጣቸው ተጫዋች ከምስክር ወረቀት በተጨማሪ የማህበሩ ቦርድ በሚያሳልፈው ውሳኔ መሠረት ሌሎች ሽልማቶችን እንደ ሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡
የኮከቦቹ ምርጫ የእግር ኳስ ቤተሰቡ ትክክለኛውን አመራርጥ እንዲረዳ ከማድረጉም በተጨማሪ ተጫዋቾች አብረው ከሚጫወቱት ከኔ የተሻለ ነው ብለው መምረጣቸው ትልቅ ኩራትና ክብረ መሆኑንም አክለዋል። ይህም ዓለም አቀፍ አሰራር በመሆኑ ለስፖርቱ ክብርና ለተጫዋቾች መነሳሳትን እንደሚፈጥረም ኢንስትራክተር ዮሐንስ አስረድተዋል። ‹‹ሙያ በሙያተኛ ሲሰራና ድጋፍ ሲያገኝ ለሙያውም ትልቅ ክብር ነው›› በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2015