ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ ነው

 አዲስ አበባ፡- ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። በበጋ መስኖ ስንዴና በጥምር ግብርና በርካታ አርሶ አደሮች እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጿል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ካህሊ ጀምበሬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ እየሰራ ነው። በ2015 በጀት አመት ኮሌጁ ካከናወናቸው የመማር ማስተማርና የምርምር ስራዎች በተጓዳኝ አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴ በመተግበር ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል።

እንደ ዶክተር ካህሊ ገለጻ፤ ለአርሶ አደሮች ምርጥ ዘርና መሰል የግብርና ግብዓት አቅርቦት ድጋፍ በማድረግ አርሶ አደሩ ስንዴን በመስኖ በመዝራት ምርት ማግኘት ይቻላል። ይህንንም ዩኒቨርሲቲው ባለው የግብርና ምርምር ጣቢያዎች ሰርቶ በማሳየት ተነሳሽነት እንዲኖራቸው ተደርጓል።

የማዳበሪያና የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ አርሶ አደሩ በመስኖ እንዲጠቀም እያደረገ ነው ያሉት ዶክተር ካህሊ፤ በማዕከላዊ ጎንደርና በምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ወረዳዎችና በጎንደር ከተማ አስተዳደር ለተመረጡ አርሶ አደሮች 545 ሄክታር መሬት በኮሌጁ ድጋፍ የበጋ መስኖ ስንዴ አልምተዋል ብለዋል።

546 ኩንታል ዘርና 546 ኩንታል ዩሪያና ዳፕ የአፈር ማዳበሪያ በዩኒቨርሲቲው በጀት ለአርሶ አደሮች መቅረቡን የገለጹት የኮሌጁ ዲን፤ አንድ ሺ 723 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል። በዚህም ከ14 ሺ 870 በላይ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰዋል። ከሚቀጥለው በጀት አመት ጀምሮ በሁሉም የጎንደር ዞኖች አርሶ አደሮች በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ለማስቻል ከግንዛቤ ፈጠራ እስከ ሙያዊ ድጋፍ የደረሰ ሥራ እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።

ኮሌጁ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን “ናቡ” የሚባል ፕሮጀክት በምስራቅ ደምቢያ ወረዳ ጥቁር አዝሙድን ወደ ዘይት የሚቀይር ፋብሪካ ሥራ መጀመሩን የገለጹት ዶክተር ካህሊ፤ ይህም በቅመማቅመም የታወቀውን የደንቢያ አካባቢ እሴት በመጨመር የአምራቹን አርሶ አደር ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ለበርካታ አመታት ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴ የሚከተል በመሆኑ ኮሌጁ ባካሄደው ጥናት የግብርና ሜካናይዜሽን የመጠቀም ፍላጎት መኖሩን በተሰራ ጥናት ትራክተርን በተመጣጣኝ ዋጋ አግኝተው የእርሻ ስራቸውን እንዲያከናውኑ በጎንደር አካባቢ ለተመረጡ 30 ገበሬዎች ማቅረብ መቻሉን ዶክተር ካህሊ ገልጸዋል።

የኮሌጁ ዲን፤ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ገንዳ ውሃ ላይ አንድ ችግኝ ጣቢያ በማቋቋም ቆላማ አካባቢ ያሉ ዛፎችን ዝርያቸው እንዳይጠፋ የመንከባከብና የመጠበቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በወገራ ወረዳ ሞዴል የሚሆን ተፋሰስ ተመርጦ አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተሰርቷል ሲሉም ገልጸዋል።

በዚህም ጥምር ግብርናን የመተግበር ሥራ መሰራቱንና ወገራ ወረዳ በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ አካባቢ በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ ከአዊ ዞን “አኬሻ ዲከረንስ” የሚባል ዛፍ በመውሰድና በመትከል በሦስት አመት ውስጥ የአፈሩ ለምነት እንዲመለስ የሚያደርግ ሥራ መሰራቱን ዶክተር ካህሊ ገልጸዋል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 27/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *