ለመስክ ሥራ ከአዲስ አበባ ውጭ ቆይቼ ስመለስ የሚያጋጠመኝ ችግር ነው። የመስክ ጉዞ ጣጣ ስለሚበዛበት አዲስ አበባ ስንገባ ይመሻል። የአዲስ አበባ መንገድ ደግሞ የተዘጋጋ ስለሆነ ቤት ለመድረስ የበለጠ ይመሻል። ከቤቴ አካባቢ ስደርስ ሱቅ የሚባል ነገር፣ ምግብ ቤት የሚባል ነገር አይኖርም። አብዛኞቹ ይዘጋሉ። መድኃኒት ቤቶች ሳይቀር በጊዜ ይዘጋሉ። ይሄ ነገር በተለይም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ልማድ ሆኖ ቀረ።
ገና ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እንኳን ሳይሆን አገልግሎት ሰጪ ቤቶች ሁሉ ተዘግተው ሳይ፤ እንዴት አንዲት ዓለም አቀፍ ከተማ በፈለጉ ሰዓት የፈለጉት ነገር የማይገኝባት ትሆናለች? እያልኩ አስባለሁ። በሌሊት ሊሰሩ የሚችሉት ጭፈራ ቤቶች ብቻ ናቸው። ከዚያ አለፍ ሲል ደግሞ ግሮሰሪዎች ናቸው። ለሁሉም ሰው አገልግሎት የሚሰጡት ግን ዝግ ናቸው።
እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያስታወሰኝ ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች ሥራ በፈረቃ ሊሆን ነው የሚሉ ዜናዎች እዚህም እዚያም መዘዋወራቸው ነው። ከሳምንታት በፊት ደግሞ በሠራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ውስጥ አንድ የክፍለ ከተማ ሠራተኛ ስለሁኔታው እያጫወተኝ ነበር። ለጊዜው ጉዳዩ ያለቀለት ባይሆንም ሀሳቡ እና ጅማሮው አለ።
ለፈረቃ ሥራው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም አንደኛው ግን ‹‹አዲስ አበባ ተኝታለች›› ከሚል የመጣ ነው። አዲስ አበባን ያህል ትልቅ ዓለም አቀፍ ከተማ ተኝታለች፤ ከሚሰራበት ሰዓት ይልቅ የማይሰራበት ሰዓት እየበለጠ ነው። ውድ የሆነው ጊዜ እና የሰው ኃይል እየባከነ ነው። የመውጫና መግቢያ ሰዓት አንድ ዓይነት በመሆኑ መንገዶችም እየተጨናነቁ ነው።
ወደ መግቢያዬ ልመለስና፤ ታዲያ የመንግሥት ሠራተኞች ሥራ በፈረቃ መሆን የግል ንግድ ቤቶች ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? ያሰኝ ይሆናል። እርግጥ ነው የግል ንግድ ቤቶች በፈረቃ እንዲሰሩ በመንግሥት አይገደዱም፤ ዳሩ ግን ቢዝነስ ያስገድዳቸዋል። ለምሳሌ፤ የሥራ ፈረቃው እስከ ምሽት አራት ወይም አምስት ሰዓት ይቆያል እንበል። በዚያን ሰዓት መደበኛ እንቅስቃሴ አለ ማለት የግል ንግድ ቤቶች ተጨማሪ ሠራተኛ ቀጥረውም ቢሆን በፈረቃ ይሰራሉ ማለት ነው። መንግሥት አስገድዷቸው ሳይሆን ለቢዝነስ ሲሉ፤ ምክንያቱም በዚያን ሰዓት የሚንቀሳቀሰው ሕዝብ አገልግሎት ይፈልጋል። ማታ በጊዜ የሚዘጉት ተገልጋይ ስለሌለ ነው። አብዛኛው ሰው ከምሽት 2፡00 በፊት ተጠቃሎ ስለሚገባ ነው። ከዚያ በኋላ የሚያመሸው ደግሞ መጠጥ እንጂ ሌሎች ነገሮች ላይ እምብዛም ስለሆነ ነው። መደበኛ እንቅስቃሴ ካለ ግን መደበኛ አገልግሎቶች ይኖራሉ ማለት ነው።
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም፣ የግል ንግድ ቤቶችም ክፍት ሆኑ ማለት፤ አዲስ አበባ እውነተኛ ዓለም አቀፍ ከተማ ሆነች ማለት ነው። የከተማ ደንቡ እንደዚያ ነው፤ በከተማ ቀኑ እና ሌሊቱ እምብዛም ልዩነት የለውም፤ ሁሌም እንቅስቃሴ ነው። ስለዚህ የሥራ ፈረቃው ለሠራተኞች ጥቅም ብቻ ሳይሆን ከተማዊ ገጽታንም ያሳምራል ማለት ነው።
በፈረቃ ሥራው ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ይሰጣሉ። በዚሁ ሰሞን በሠራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ውስጥ እና በማህበራዊ ገጾች ሲወሩ ከሰማኋቸው ስጋቶች አንዱ የደህንነት ሥጋት ነው። በተለይም በምሽት ሰዓት ዝርፊያ የተለመደ ሆኗል፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለሕይወት አስጊ የመሆን ደረጃ ላይ የደረሱ እገታዎችና ድብደባዎች እያጋጣሙ ነው። 10 ሺህ ብር ለማያወጣ ስልክ ብለው የሰው አካል የሚያበላሹ ወንበዴዎች መኖራቸው ግልጽ ነው።
ዳሩ ግን እነዚህ ወንጀሎች በምሽት የበዙበት ምክንያት ጨለማ ስለሆነ ብቻ አይደለም፤ በምሽት እንቅስቃሴዎች የተገደቡ ስለሆነ ነው። እንቅስቃሴዎች የተገደቡ ናቸው ማለት አንድ ግለሰብ ብቻውን ቢንቀሳቀስ አስፈሪ ነው ማለት ነው። በዚያን ሰዓት የእንቅስቃሴ ነፃነት ያላቸው ሌቦች ናቸው። እንቅስቃሴው መደበኛ ቢሆን ግን ልክ እንደ ቀኑ ይሆናል ማለት ነው። መንገዱ ሁሉ ሰው ከሆነ ያን ያህል አይደፋፈሩም። ምሽቱን የሚፈልጉት ለጨለማው ብቻ ሳይሆን ለፀጥታው ጭምር ነው።
ይህ ማለት ግን ጨለማው አያግዛቸውም ማለት አይደለም። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህን ነገር ሲያስብ መሠረተ ልማቶችንም አብሮ ማሰብ አለበት። በተለይ በቂ አምፖል የሌለባቸው መታጠፊና የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ስጋት ናቸው። የተቆፋፈሩ መንገዶች መስተካከል አለባቸው። የፀጥታ አካላት በበቂ ሁኔታ ሊመደቡ ይገባል። ምክንያቱም ምንም ቢሆን የሰው ቁጥር እንደ ቀኑ አይበዛም፤ ምሽት ሲሆን መቀነሱ የግድ ነውና ዘራፊ መብዛቱ አይቀርም።
የፀጥታ ኃይል ተጠናክሮ፣ የጨለማ ቦታዎች ሁሉ መብራት ከኖራቸውና መደበኛ እንቅስቃሴዎች ከተለመዱ ዝርፊያ እየቀነሰ ይሄዳል ማለት ነው። ምንም እንኳን ዘራፊ በቀንም የሚያጋጥም ቢሆንም የምሽት ሲሆን ግን የተባባሰ ነው። ስርቆትን ሥራዬ ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት ተስፋ ሲቆርጡ ሌላ አማራጭ ይፈልጋሉ። ስለዚህ የፈረቃ ሥራ መጀመሩ በተገቢው መንገድ ከተሰራበት የሌባ ቁጥርን ይቀንሳል እንጂ አይጨምርም።
እኛ ኢትዮጵያውያን ጊዜ እንደምናባክን ዓለም አውቆብናል። ቢያንስ ግን የሀገሪቱ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ እንኳን ጊዜ ዋጋ ይኑረው። በአዲስ አበባ ተጀምሮ ውጤቱ ሲታይ ሌሎች ከተሞችም ይሰሩበታል ማለት ነው። ያኔ በመንግሥት አቅጣጫ ሳይሆን ራሱ ልማድ ይሆናል፤ ንግድ ቤቶች ምናልባትም 24 ሰዓት የሚሰሩ ይሆናሉ። እኛ ኢትዮጵያውያን ከምሽት በኋላ ምንም ነገር የሚሰራ አይመስለንም፤ አሁን የታሰበው የፈረቃ ሥራ ይህን የገነገነ ልማድ መለወጥ ያስችላል።
ለጊዜው ይፋ ባይሆንም የፈረቃ ሥራው ሌላኛው ጠቀሜታው ሠራተኞች የራሳቸውን ሥራ እንዲሰሩ ነው ተብሏል። የጠዋት ተረኛ የሆነ ከሰዓት የራሱን ሥራ ይሰራል፤ የከሰዓት የሚሆነውም እስከሚገባ ድረስ የራሱን ሥራ ይሰራል። ይህ ደግሞ ፈጠራንና ትጋትን ያለማምዳል ማለት ነው። እዚህ ግባ ለማይባል ሥራ ከጠዋት እስከ ማታ የቢሮ ወንበር ላይ መዋል ብክነት ነው። ያ ሰው የግል ሥራውን ቢሰራ ለግሉ ብቻ ሳይሆን ለሀገሩም ይጠቅማል። ዜጎች በኢኮኖሚ ራሳቸውን ሲችሉ ነው አንዲት ሀገር ተጠቀመች የሚባለው። ብዙ ሠራተኛ ከጠዋት እስከ ማታ ቢሮ ውስጥ አጉሮ ማዋል እንዲያውም የሀገርና የመንግሥት ሸክም እንዲሆኑ ማድረግ ነው።
በርግጥ ነው ፈረቃ ተደረገ ማለት ሁሉም ሰዎች ሥራ ፈጥረው ይሰራሉ ማለት አይደለም፤ የግማሽ ቀን የቅጥር ሥራ ያገኛሉ ማለትም አይደለም፤ እሱ እንደ ግለሰቦች ጥረት ይወሰናል። ዳሩ ግን ዕድሉን መፍጠርና አሰራሩን ማለማመድ ጥሩ ጅማሮ ነውና ይበል ያሰኛል። ዕድሉ የተፈጠረላቸው ሠራተኞችም የተሰጣቸውን ግማሽ ቀን ለመቀመጥና ለመተኛት ሳይሆን ለሥራ ይጠቀሙት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2015