በርካታ ዓመታትን ወደ ኋላ መለስ ብለን በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ኩነቶች እንደነበሩ የምናስታውስበት አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን ለዛሬ በርከት ያሉ ጉዳዮችን ያስቃኘናል፡፡ ለዚህም በተለይም በ1950ዎቹና 70ዎቹ የነበሩ ዘገባዎችን መርጠናል፡፡ ከመራረጥናቸው ዘገባዎች መካከል የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ 67ኛ ዓመት የልደት በዓል አከባበር፣ የሶቪየት ሕብረት ሕፃናት ስጦታ፣ 28 ሠራተኞች ሳንሠራ ደሞዝ ይከፈለናል ስለማለታቸው፣ 22 ጠንቋዮች እራሳቸውን ስለማጋለጣቸው፣ የ40 ዓመት ሴትም በአንድ ጊዜ 3 ልጆችን መገላገላቸው የሚያስታውሱን ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በመጨረሻም «አብረን እንሳቅ አብረን እንኑር» እያልን፤ ከሚለው ገጽ ላይ ሁለቱን በመምረጥ አሰናድተን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የተወዳጁን ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የስድሳ ሰባተኛውን ዓመት የልደት በዓል እጅግ ከፍ ባለ ደስታ ያከብራል
ይህ ዘመን የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት አርቆ አስተዋይነት በአሜሪካና በኤውሮፓ፣ በእሲያ፣ በአፍሪካ ክፍለ ዓለማት ከሚገኙት የወዳጅ አገሮች ጋር የኢትዮጵያን ሕዝብ በፍቅርና በወዳጅነት ያስተሳሰሩበት አዲሱ ሰለሞን የተባለው የግርማዊነታቸው ሰውነት በመላው ዓለም ውስጥ ዓለምን ያስደነቁበት ጊዜ ነው።
ከዚህም በቀር ደግሞ ይህ የዛሬውን የልደት በዓል ብዙ ዘመን ሙሉ በአስደናቂ ሥራ ሲጌጥ ለቆየው ለግርማዊነታቸው ዘመነ መንግሥት ወደ 68 ዓመት መተላለፊያ በር ስለሆነ ከፍ ባለ ሁኔታ እናከብረዋለን።
ሐምሌ 16 ቀን 1954 ዓ.ም የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘ ኢትዮጵያ የስድሳ ሰባተኛው የልደት በዓል አከባበር ፕሮግራም
1ኛ. ሐምሌ 16 ቀን 1954ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት 21 መድፍ ይተኮሳል፤
2ኛ. ግርማዊት እቴግ መነን በታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ በኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ፀሎት ያደርሳሉ፤
3ኛ. ግርማዊት እቴጌ መነን ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል መሳፍንት፣ መኳንንቶች፣ ወይዛዝሮችና የመንግሥት ሠራተኞች፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሆኑት ነጋዴዎችና ታላላቅ ሰዎች በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ይቀበላሉ፤
4ኛ. በአራት ሰዓት ተኩል ግርማዊት እቴጌ መነን በቤተ መንግሥት ሠገነት ወጥተው ለተሰበሰበው ሕዝብ ይታያሉ። በዚህ ጊዜ በከተማው በአዲስ አበባ ሕዝብና በራሳቸው ስም ንግግር ያደርጋሉ።
5ኛ. በስድስት ሰዓት የውጭ አገር መንግሥታት እንደራሴዎች በቤተ መንግሥቱ የክብር መዝገብ ላይ ስማቸውን ይፈርማሉ።
ልብስ ሚሊቴር ወይም ገበርዲን
ሲቢል ሞርኒንግ ኮት
ወይዛዝርት የከተማ ልብስ
6ኛ. ግርማዊት እቴጌ መነን በስድስት ሰዓት ስለ በዓሉ ክብር መንግሥት ለኢትዮጵያ መሳፍንት ሚኒስትሮች፣ መኳንንቶችና ለመንግሥት ሠራተኞችና ለካህናቶች፣ በከተማው ነዋሪ ለሆኑት ታላላቅ ግብዣ ያደርጋሉ።
7ኛ. በዚሁ ቀን ከምሽቱ በ2 ሰዓት ስለ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በዓል ክብር የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ቤት የራት ግብዣ ያደርጋሉ።
ልብስ ነጭ ክራባት
ከዚህ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል።
(አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 1954 ዓ.ም)
……..
የሶቪየት ኅብረት ሕፃናት ለኛ ሕፃናት
ስጦታ ላኩ
በሶቪየት ሕብረት በኪርጌዚያ ሪፐብሊክ የተለያዩ መንደሮች የሚኖሩ ሕፃናት በትርፍ ጊዜያቸው በእርሻ ቦታዎች በመሠማራት እየሠሩ ባጠራቀሙት ገንዘብ የገዟቸውን አሻንጉሊቶችና ልዩ ልዩ መጫዎቻዎች ለኢትዮጵያ ሕፃናት እንዲውል በርዳታ ልከዋል።
ስጦታውን የላኩት የሶቪየት ኅብረት ሕፃናት የኢትዮጵያ ሕፃናት የደስታ ኑሮ እንዲኖሩ እንደሚታገሉ ከስጦታው ጋር በላኩት ደብዳቤ ማረጋገጣቸውን ጓድ አምባሳደር ኪርናሶቪ ስኪይ ገልጠዋል።
(አዲስ ዘመን የካቲት 24 ቀን 1971ዓ.ም)
……..
28 የገጠር ፕሬዤዎች ሠራተኞች ሳንሠራ ደሞዝ ይከፈለናል ይላሉ
በገጠር ፕሬዤዎች ድርጅት በአዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት 28 አናጢዎችና ግንበኞች ለአራት ወራት ሥራ በማስፈታት 14ሺህ 892 ብር ደመወዝ በነፃ የከፈላቸው መሆኑንና በመሥሪያ ቤቱ ውስጥም ከፍተኛ የሥራ መዝረክረክ መኖሩን ከገጠር ፕሬዤዎች ድርጅት አጠቃላይ የሠራተኞች ማህበር ጽሕፈት ቤት ሁኔታውን እንዲያጣራ የተላከው ቡድን አጋለጠ።
(አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 ቀን 1971ዓ.ም)
……..
የ40 ዓመት ሴት በአንድ ጊዜ ሦስት
ልጆች ወለዱ
ሐረር (ኢ.ዜ.አ) ወይዘሮ ፋጡማ ኢብሮ የተባሉት የ40 ዓመት ሴት ሐረር ከተማ በሚገኘው በምሥራቅ አርበኞች ሆስፒታል ውስጥ ባለፈው ዓርብ 3 ሕፃናትን በአንድ ጊዜ መገላገላቸውን አቶ ሽፈራው አቢቢ የሆስፒታሉ አስተዳደር አስታወቁ።
ከሕፃናቱም መካከል መጀመሪያ የተወለደው ወንድ 4 ኪሎ ከሃያ አምስት ግራም ክብደት ሲኖረው ተከትለው የተወለዱት ሌሎች አንድ ወንድና ሴት ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ኪሎ ከ20 ግራም ክብደት እንዳላቸው ተገልጧል።
(አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 1971ዓ.ም)
……..
22 ጠንቋዮች ራሳቸውን አጋለጡ
ደሴ,(ኢ.ዜ.አ) ወሎ ውስጥ በደላንታ ወረዳ የኢላና ትምህርት ቤት መምህራን ከጣርዳት፣ ከደሀናንና ከዝባን የገበሬ ማኅበራት ጋር በመተባበር በመካከላቸው የተሰገሰጉትን 22 አባይ ጠንቋዮች ራሳቸውን አጋልጠው ክቡር ወደሆነው የሥራ መስክ እንዲሰማሩ አደረጉ።
እነዚሁ 22 አባይ ጠንቋዮች በተሰጣቸው ትምህርት አምነው ድቤዎችን (ከበሮዎችን)፣ እንዲሁም በእጃቸው ይገኙ የነበሩትን ልዩ ልዩ የጥንቆላ ዕቃዎችንና መጽሐፍት ለገበሬ ማኅበራቱ በራሳቸው ፈቃድ አስረክበዋል። አባይ ጠንቋዮቹ ካስረከቧቸው ዕቃዎች ውስጥ በተለይ ከበሮዎቹ በአካባቢው ለሚቋቋመው የኪነት ቡድን መገልገያ እንዲሆን መሰጠቱ ተገልጧል።
(አዲስ ዘመን መጋቢት 23 1971 ዓ.ም)
……..
አብሮ መሣቅ
አብሮ መኖር
ከቤቱ ሠርግ አለው
ስትተኛ ሙቃ
ስትኖር ተሳስቃ
ስትሄድ ገንዘብ ንቃ።
ሸጋ መልከ መልካም ድቡልቃ ሚስት ያለው ከሰው ሠርግ አይሄድም ከቤቱ ሠርግ አለው።
ስትኖር ተነዛንዛ
ስትተኛ ቀዝቅዛ
ስትሄድ ገንዘብ ይዛ።
ነዝናዛ የሆነች ፈዛዛ ሚስት ያለው ከሰው ለቅሶ አይሄድም ከቤቱ ለቅሶ ነው።
………
ቃጫ ፋብሪካ
ሸበቶ:- የኔ ወንድም ይህ አስፋልት ወዴት ይወስዳል?
መላጣ:- ቃጫ ፋብሪካ ያደርስሃል
(አዲስ ዘመን መስከረም 20 ቀን 1958ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2015