ከአስከፊው ስደት በኋላ ተመላሽ ሴቶችን ለማቋቋም ምን ተሰራ ?

ፋጡማ መሐመድ ተወልዳ ያደገችው በሰሜን ሸዋ ዞን ፋልማ ገጠር መንደር ውስጥ ነው። የፋልማ መንደር ለፋጡማ ሁሉም ነገርዋ ናት። አፈር ፈጭታ፤ ውሃ ተራጭታ፤ ከእኩዮችዋ ጋር ቦርቃ ያደገችባት እና እትብቷ የተቀበረበት ነው።

ሆኖም ከድሃ ቤተሰብ የተወለደችው ፋጡማ ፋልማን ብትወዳትም እዛው ኑሮ ቀልሳ፤ አግብታ፤ ወልዳና ከብዳ ለመኖር አልታደለችም። በየቀኑ እንደምርጊት እየከበደ የሄደው የኑሮ ውድነት የነፋጡማን ቤተሰብ በእጅጉ ፈተነው። ያለ እናት ፋጡማንና አራት ታናናሽዋን በእርሻ ሥራ የሚያስተዳድሩት አባቷ ከእለት ወደ እለት የኑሮ በትሩን ያሳረፍባቸው ይዟል።

ይህንን የተመለከተችው ፋጡማ አንድ ነገር ለማድረግ ወሰነች። ወደ አረብ ሀገር ሄዳ አባቷን ማሳረፍና ከተጫነባቸውን የኑሮ ቀንበር ለማቃለል ተመኘች። የቀን ከሌሊት ሃሳቧም አረብ ሀገር ሆነ። ትምህርቷን እርግፍ አድርጋ በመተው አረብ ሀገር የምትሄድበትን መንገድ ብቻ ማሰላሰል ያዘች።

አረብ ሀገር የሚልኩ ደላሎችም ሸዋ ሮቢት ከተማ እንደሚገኙ ስለሰማችም ወደዛው አቀናች። ሴቶችን ወደ አረብ ሀገር በሕገወጥ መንገድ በመላክ ታዋቂ ከሆነው ደረጄ ከተባለው ደላላ ጋር ሰዎች አገናኟት። ደላላው ደረጄም ለጉዞው 30ሺ ብር እንደሚያስፈልጋት ነግሯት በአጭሩ አሰናበታት። ፋጡማ ግን እንኳን 30ሺ ብር አንድ ሺ ብርም በእጇ አልነበረም። ያላት ብቸኛ አማራጭ አባቷ የሚያርሱባቸውን ሁለት በሬዎች መሸጥ ብቻ ነበር።

ሆኖም በሬዎቹ ሲሸጡ ቤተሰቡ ጦሙን ማደሩ አይቀርምና ሁኔታው አሳሰባት። ነገር ግን ቶሎ ወደ አረብ ሀገር ሄዳ በምታገኘው ገንዘብ ሌሎች ተጨማሪ በሬዎችን መግዛት እንደምትችል ስታስብ ወዲያው ተጽናናች። አባቷንም አሳምና በሬዎቹ ተሸጡ። የተባለውን ብርም ለደላላው ደረጄ ካስረከበች በኋላ የፋጡማ ሕገወጥ ስደት ተጀመረ።

ሸዋሮቢትን መነሻ ያደረገው ጉዞ የመጀመሪያው መዳረሻ አዲስ አበባ ነበር። በስም እንጂ በግብር የማታውቃትን አዲስ አበባን ስትረግጥ ነገሮች ተደበላለቁባት። በአንድ በኩል የሕንጻዎች ብዛትና ሰማይ ጠቀስነት አስደመማት በሌላ በኩል የሕዝቡ ብዛትና ግርግር አስጨነቃት። ሆኖም አዲስ አበባን በቅጡ ሳታቃት እሷና መሰሎቿ በአንዲት ጠባብ ክፍል ለሶስት ቀናት ታሽገው ተቀመጡ።

በአራተኛው ቀን ምሽት በአንድ ደላላ አማካኝነት እየተነዱ በአንድ የጭነት መኪና ላይ ከተጫነ ኮንቴነር ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ። ወደ ማያውቁት ቦታም ጉዞ ተጀመረ።

መኪናው ጨለማውን እየሰነጠቀ ያለ ማቋረጥ ይጓዛል። ሆኖም ፋጡማም ሆኑ ሌሎች ስደተኞች የልባቸው መዳረሻ አረብ ሀገር ነውና ጉዞውን በተስፋ ከመመልከት ውጭ የተሰማቸው ስጋት አልነበረም። ሆኖም ጉዞው አስጨናቂ ነበር። በጠባቡ ኮንቴነር ውስጥ ሴቶች በመጠቅጠቃቸው እንደልብ አየር ማግኘት አስጨናቂ ነበር። በዚህ ላይ ሙቀቱ አስጨንቋቸው ወደ ላይ ወደ ላይ ሽቅብ የሚገፋቸው በርካቶች ነበሩ። ይህን መቋቋም ለፋጡማ ከባድ ነበር። ሆኖም አረብ ሀገር ለመድረስ ትንሹ መስፈርት መሆኑ የገባት ቆይቶ ነበር።

በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ እያለች በውድቅት ሌሊት ከመኪና እንዲወርዱ ታዘዙ። አንድ ሽርጥ ያደረገ ሰው ከኮንቴነር ውስጥ አንድ በአንድ እየተንጠባጠቡ የወጡትን ሴቶች እያዋከበ ይወስዳቸው ጀመር። በዛ ውድቅት ሌሊት እንደ እንፋሎት የሚፋጀው በርሃ እግርን ይለበልባል፤ ሰውነትን በላብ ያጠምቃል፤ አየር እንደልብ መሳብም አስቸጋሪ ነው።

ጉዞው ቀጥሏል። የአሸዋው ግለትና የአካባቢው ሙቀት በቀላ የሚገፋ አልነበረም። ሙቀቱን መቋቋም ያቃታቸው አንድ በአንድ መንጠባጠብ ጀመሩ። እነሱን ለማንሳት የሚሞክሩ በደላላው ስድብና ዱላ ስለደረሰባቸው ሁሉም በልቡ እያዘነ ጉዞውን ከመቀጠል ውጭ አማራጭ አልነበረውም። በየበረሃው የቀረው ቀርቶ ፋጡማን ጨምሮ የተቀሩት ሴቶች ከብዙ ድካም በኋላ ከአንድ የባህር ጠረፍ ደረሱ። ቆማ ስትጠብቃቸው ከነበረች አንዲት ትንሽ ጀልባ ላይ እንዲሳፈሩም ታዘዙ። ትንሿ ጀልባም በሕገ ወጥ ስደተኞች ተሞላች። ይህም አልበቃ ብሎ የጀልባዋ ሾፌር በአንዱ ስደተኛ ላይ ሌላውን እየጠቀጠቀ ጀልባዋ ከአፍ እስከገደፉ ጢም አለች።

ፋጡማ እየሆነ ባለው ነገር ተገረመች። ሆኖም የነገውን ተስፋ በማለም ስቃይዋን ዋጥ አድርጋ በተጨናነቀችው ጀልባ ላይ ተሳፍራ ጉዟን ቀጠለች። በየመሃሉ ጉዞው የከበዳቸውና ሕመም የጸናባቸው ተጓዦች እየተመነጠሩ ወደ ውሃ ሲወረወሩ ተመለከተች። ፋጡማ ባየችው ጭካኔ ሰው መሆኗ አስጠላት። ‹‹እንዴት ሰው በሰው ላይ ይሄን ያህል ይጨክናል›› ስትል ለራሷ አወራች።

እንባዋም በሁለት ጉንጮቿ ላይ ሲወርድ አልታወቃትም ነበር። ከቤቷ የተነሳችበትን ቀን ረገመች። ያለ እናት ያሳደጓት አባቷና ታናናሽ እህቶቿና ወንድሞቿ ትዝ አሏት፤ ሆዷ ባባ።

ሆዷ ተረብሾ ሽቅብ ሊላት ቢሞክርም በጨካኙ የጀልባዋ ሾፌር ወደ ውሃ ላለመወርወር ጤነኛ መስላ ለመታየት ሞከረች። ብርታቱን እንዲሰጣትም ወደ ፈጣሪዋ ጸለየች።

በኃይለኛ ንፋስና ወጀብ ስትንገላታ የቆየችው ጀልባ ከጠረፍ ደረሰች። ጀልባዋ ላይ የተሳፈሩት በሙሉ እንዲወርዱ ታዘዙ። ከጥቂት እግር ጉዞ በኋላም ሳኡዲ አረቢያ እንደሚገቡና ደላሎችም ወስደው ከሰው ቤት እንደሚያስቀጥራቸው ይዟቸው የመጣው የጀልባ ሾፌር አበሰራቸው። ከጥቂት ደቂቃ በኋላም በአንድ ደላላ እየተመሩ መጓዝ ጀመሩ። ከሰዓታት ጉዞ በኋላ ሳኡዲ መግባታቸው ተነገራቸው።

ሲጠብቃቸው የነበረው ደላላም እነፋጡማን አንድ በአንድ እየወሰደ ሲጠባበቁ ለነበሩ የቤት ሠራተኛ ፈላጊዎች አስረከቧቸው። ፋጡማም ከአንዲት በእድሜ ከገፋች አረብ እጅ ወደቀች። በማታውቀው የአረብኛ ቋንቋም እያወከበች ወሰደቻት።

ፋጡማ ከአሰሪዋ ዘንድ ከደረሰች ጀምሮ ያለመታከት የእለት ሥራዋን ትሰራ ጀመር። ከጠዋት ጀምራ አራት ወለል ፎቅ የሆነውን ቤት ስታጸዳ ትውላለች። ያንን እንደጨረሰች ልብስና የቤት ዕቃ የማጠብ ግዴታ አለባት። ለቤተሰቡም ምግብ የማብሰሉም ኃላፊነት የተተው ለፋጡማ ነው። በዚህ አይነት መልኩ ከጠዋቱ 11 ሰዓት የተጀመረው ሥራ እስከ ሌሊቱ 8 ሰዓት ይቀጥላል።

በዚህ ላይ የአሰሪዋ ጸባይ ከባድ ነበር። በውሃ ቀጠን መጨቃጨቅ ይቀናታል። እያንዳንዱን ዕቃ እየፈተሸች በአግባቡ አልተጸዳም፤ ልብሱ በአግባቡ አልታጠበም፤ ምግቡ አይጣፍጥም በሚሉ ምክንያቶች ፋጡማን ትነተርካታለች። አልፎ ተርፎም ጸጉሯን ጨምድዳ ትደበድባታለች።

ፋጡማ ይህንን መቋቋም አቃታት። እራሷን ለማጥፋትም ታስባለች። ሆኖም አባቷ እሷን አምነው የሸጧቸው በሬዎች ትዝ ይሏታል። ቤተሰቡ በእሷ ምክንያት ሲራብና ለልመና ሲወጣ ይታሰባታል። እህት ወንድሞቿ ሲረግሟት በዓይነ ህሊናዋ ይመጣባታል። ሀገር መንደሩ ቤተሰቦቿን የገደለች ጨካኝ ሲላት ይታወሳታል።

ስለዚህም የሆነው ቢሆን ቻል ማድረግ እንዳለባት ይሰማታል። ለአባቷ እና ለእህት ወንድሞቿ ስትል የመጣውን ለመቻል ወስናለች። ሆኖም የአሰሪዋ ንትርክና ጭቅጭቅ አልፎ ተርፎም ዱላን መቋቋም ከምትችለው በላይ ሆነባት። ከዚህም ብሶ ብርጭቆ ሰብረሻል፤ በአግባቡ ምግብ ማበሰል አትችይም፤ ለጤና ሕክምና ያወጣሁት ወጪ አለ፤ የደላላ ከፍያለሁ በሚሉ ምክንያቶች የሁለት ወር ደመወዟን አልከፈለቻትም። በሶስተኛው ወርም እነዚሁ ምክንያቶች ተደግመው ደመወዟን ልታገኝ አልቻለችም።

ስለዚህም ያላት አማራጭ ከአሰሪዋ ቤት አምልጦ መጥፋትና ሌላ አማራጭ መፈለግ ነው። አሰሪዋ መተኛቷን ከአረጋገጠች በኋላ በለበሰችው ልብስ ብቻ ከቤት ወጥታ ጠፋች። እግሯ ወደ አመራትም ኮበለለች። የተወሰነ ከተጓዘች በኋላ ግን ፖሊሶች አስቆሟት። መኖሪያ ፈቃድ እንደሌላት ሲረዱም በመኪና ወሰደው እስር ቤት ከተቷት።

ፋጡማ የገባችበት ቦታ እስር ቤት መሆኑን ያወቀችው በርካታ ኢትዮጵያውያንን ካገኘች በኋላ ነው። በርካቶቹ እንደርሷ በአሰሪዎቿ በደል ደርሶባቸው አምልጠው ሲጠፉ የተያዙ፤ አንዳንዶቹም በሀገሪቱ የተከለከሉ መጠጦችን ሲሸጡ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው ለእስር የተዳረጉ መሆናቸውን ተረዳች።

አንዳንዶቹ ከ20 ዓመታት በላይ በሳኡዲ አረቢያ የኖሩ፤ ትዳር የመሰረቱና ልጆችን ያፈሩ ናቸው። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን በቂ ጥሪት ያልቋጠሩና በሳኡዲ አረቢያ መንግሥት ትዕዛዝ ታፍሰው ከሀገር እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው ናቸው። ቀሪዎቹ ከወራት እስከ አመታት የቀን ሥራ ሲሰሩ የቆዩ፤ በማዳም ቤቶች ተቀጥረው በቤት ሠራተኝነት ሲያገለግሉ የኖሩ ናቸው።

ሁሉንም ግን የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ። ወራትም ሆነ አመታት የሰሩት አንዲትም ጥሪት አላፈሩም። ወደ ሀገራቸው ለመግባት ፍላጎት ቢኖራቸውም ብዙዎቹ እጃቸው ላይ ምንም ነገር ስለሌለ ምን ይዤ ልመለስ በሚል ፍራቻ እስር ቤት መቆየቱን ይመርጡታል።

ሆኖም እስር ቤቱ በየጊዜው እየመጣ በሚታጎረው ስደተኛ ተጨናንቋል። የእስረኞች አያያዝም ሰብዓዊነት የጎደለውና አዋራጅም ነው። ሕጻናት ልጆች ይዘው የገቡ ሰደተኞችና እርጉዝ ሴቶችም ሳይቀሩ ምቾት በጎደለው አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ውለው ለማደር ተገደዋል። ሆኖም በዚህ መሃል አንድ ጥሩ ዜና ተሰማ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሳኡዲ ሀገር የሚገኙ ዜጎቹን እንደሚመለስና ለዚህም በእስር ቤት ጭምር የሚገኙ ስደተኞች እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ መልዕክት ተነገራቸው። ፋጡማን ጨምሮ ብዙዎቹ በመንታ ሃሳብ ተጠመዱ። በአንድ በኩል በባዶ እጃቸው ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ‹‹አንድ ነገር ይዘው ይመጣሉ፤ ያሳልፉልና›› ብለው የሚጠብቋቸውን ቤተሰቦቻቸውን አንገት ሲያስደፉ ይታያቸዋል። በሌላ በኩል ከእስር ቤት ስቃይና መከራ መገላገላቸው እፎይታ ይሰጣቸዋል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ የኢትዮጵያ መንግሥት መጓጓዣ አውሮፕላን መድቦ በርካቶችን ወደ ሀገር ቤት ማስገባት ጀመረ። የፋጡማ ተራ ደረሰና እሷም የኢትዮጵያን ሰንደቅ ተሸክሞ በሚጓዘውና ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካ ኩራት በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍራ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ደረሰች።

እንደደረሰችም ብዙዎች እንደሚደርጉት ተደፍታ የኢትዮጵያን መሬት ሳመች። አየሯን ማገች። ለሀገሯ ምድር ያበቃትንም አምላክ አመሰገነች።

ፋጡማ ወደ ቀዬዋ ከተመለሰች በኋላ በመንግሥት ድጋፍ ተደርጎላት አነስተኛ የሸቀጥ ሱቅ ከፍታ በመሥራት ላይ ትገኛለች። በመንግሥት ከተደረገላት የ18ሺ 200 ብር ድጋፍ በተጨማሪ ከብድር ተቋማት ተጨማሪ በመውሰድ ሱቋን በማደራጀት ላይ ትገኛለች። ሆኖም ፋጡማ እንደምትለው ድጋፉ ጥሩ ቢሆንም አሁን ካለው የኑሮ ውድነትና የሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ የሚሰጠው ድጋፍ በቂ አይደለም።

በርካቶችም ገንዘቡን ከወሰዱ በኋላ ለግል ፍላጎታቸው ስለሚያውሉት በመንግሥት የታሰበው የሥራ ፈጠራ ዕቅድ የታለመለትን ግብ ላይመታ ይችላል። ስለሆነም የሚደረገው ድጋፍ ሊጨምርና ክትትልና ድጋፉም በዛው መጠን ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ትገልጻለች። ባንኮችን ጨምሮ ሌሎች የብድር ተቋማት ከስደት ተመላሾች ብድር የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ ሊፈጥሩ እንደሚገባም ትናገራለች።

ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያረጋግጠውም እስከ 2015 በጀት አመት መጨረሻ ድረስ 114ሺ152 ዜጎች ከሳኡዲ አረቢያ የተመለሱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 33ሺ 642 ተመላሾች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ከስደት ተመላሾችን ለማቋቋም ከኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ባሻገር ሥነልቦና ስልጠናም እየተሰጠ መሆኑን ተገልጿል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *