ቤተመጻሕፍትና የተማሪዎች የእረፍት ጊዜ

ተማሪና ትምህርት እንደማይነጣጠሉ ሁሉ፤ ተማሪና እረፍትም የሚለያዩ አይደሉም። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ “ተፈጥሯዊ” ሲሆን፣ ሰርቶ ማረፍ እንዳለ ሁሉ አርፎ መሥራትም ያለ በመሆኑ ነው።

አሁን ያለንበት ወቅት ክረምት ሲሆን ወሩም ሐምሌ ነው። የሚቀጥለው ደግሞ ነሐሴ። ያ ማለት፣ ተማሪዎች መስከረም (አዲስ አመት) መጥቶ፣ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ወደ ትምህርት ገበታቸው እስኪመለሱ ድረስ እረፍት ናቸው ማለት ይሆናል። ይህ ደግሞ በየአመቱ የሚቀጥል፤ ያለ፣ የነበረና የሚኖር ነው።

አሁን ጉዳያችን፣ “ይህ የእረፍት ጊዜ በተማሪዎች ዘንድ እንዴት ይታያል?” ከሚለው በተጨማሪ፣ ይህ ከሌሎቹ እረፍቶች አኳያ ረዘም ያለ እረፍት “እንዴት እየታለፈ ነው፤ ተማሪዎችስ ጥቅም ላይ እያዋሉት ነው፣ ወይስ አይደለም?” የሚሉትን በማንሳት እየሆነ ያለውን፤ እንዲሁም፣ መሆን ያለበትን በተመለከተ ሀሳብ መለዋወጥ ነው።

“እረፍት” እንዴት ማ(ሳ)ለፍ ያለበት መሆኑን በተመለከተ “ይሄ ነው” የሚል ቁርጥ ያለ መልስ የለም፤ አይኖርምም። ምክንያቱም እረፍትን የማሳለፍ ጉዳይ ከብዙ ጉዳዮች ጋር ስለሚገናኝ ነው። ከኢኮኖሚ አቅም አኳያ፣ ከፍላጎትና ዝንባሌ አኳያ፣ እድሜና ጤና፣ እምነት… ጋር ሁሉ ቀጥተኛ የሆነ ትስስር ወይም ግንኙነት ስላለው ነው።

ይሁን እንጂ፣ እረፍትን በተመለከተ እንደ አጠቃላይ በማየት አንዳንድ ሀሳቦችን መሰንዘር ይቻላል። ለምሳሌ፣ ተማሪዎች፣ ፖሊሶች፣ የሀገር መሪዎች፣ የብሔራዊ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ….. የእረፍት ጊዜያቸውን በምን በምን አይነት ተግባርና እንቅስቃሴ እንደሚያሳልፉ በማጥናት አንዳች ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻላል። ለጊዜው ከወቅቱ አኳያ ጉዳያችን ተማሪዎች ናቸውና እረፍትን ከእነሱ ጋር አያይዘን አንዳንድ ጉዳዮችን እናንሳ።

ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ እያሉ በአብዛኛው እሚመሩት በራሳቸው የግል እቅድ ሳይሆን በሚማሩበት ትምህርት ቤት እቅድ ነው። በመሆኑም፣ በተመደበላቸው ክፍለ ጊዜ የተመደበላቸውን የትምህርት አይነት ይከታተላሉ። የእረፍት ጊዜያቸውም ያ የትምህርት ቤቱ እቅድ አካል ነውና ለእረፍት መውጣት ባለባቸው ጊዜ ይወጣሉ። መግባት ባለባቸው ጊዜ ደግሞ ይገባሉ። ይህ የአሁኑ፣ የክረምቱ እረፍት ግን ከዚህ የተለየ ነው።

ይህ የክረምት እረፍት ሙሉ በሙሉ በራሱ(ሷ)፣ በግለሰቡ(ቧ) ተማሪ መዳፍ ውስጥ ነው። ሌላ የሚያገባው አካል አለ ከተባለም ቤተሰብ ነው።

ይህ የእረፍት ጊዜ ተማሪው ካነበበበት የንባብ ጊዜ ይሆናል። ተማሪው አልባሌ ቦታ የሚውልበት ከሆነ የባከነ ጊዜ ይሆናል። የባከነ ብቻም ሳይሆን ያባከነም ሆኖ ያልፋል። ተማሪ(ዎች)ው በግልም ሆነ በቡድን ሽር ሽር (ጉዞ) ከሄዱበት እረፍቱ ወይ የሀገርህን እወቅ፤ አለበለዚያም የመዝናኛ እረፍት ጊዜ ሆኖ ያልፋል። ስፖርት ማዘውተሪያን ከጎበኙበትም እንደዛው ነው። በመሆኑም የተማሪዎች የእረፍት ጊዜ የተማሪዎቹን ብልሀት የተሞላበት የጊዜ አመራርና አጠቃቀም ይፈልጋል ማለት ነው።

በሌላው ዓለም፣ በተለይም ባደጉት ሀገራት የተማሪዎችን የእረፍት ጊዜ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚሰሩ ሰፋፊ ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ ያህልም በሽርሽር የሚኬድባቸው ቦታዎች ይዘጋጃሉ፤ ምርጥ ምርጥ ሲኒማዎች ለእይታ ይቀርባሉ፤ ትያትር ቤቶች በብዛት ክፍት ይሆናሉ፤ ጂሞች (በነፃም፣ በክፍያም) ተዘጋጅተውና በራቸውን ከፍተው ሰልጣኝ ልጆችን ይጥብቃሉ። በመሆኑም ልጆች የመረጡት ጋር በመሄድ የእረፍት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። ቤት ውስጥም ከሆነ ምርጥ ምርጥ የልጆች ፕሮግራሞች ስለሚኖሩ ልጆች እየተዝናኑ፣ በእግረ መንገዳቸውም እውቀት እየቀሰሙ የእረፍት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። በዚህ በኩል የወላጆች ሚና ቀላል አይሆንም እና ኃላፊነታቸው ከባድ ይሆናል። በንባብ ቤቶችም እንደዛው።

ከሁሉም በላይ፣ ምናልባትም ወሳኝ በሆነ መልኩ ለተማሪዎች የእረፍት ማሳለፊያ እንደ ንባብ ቤት የሚመረጥ የለም። ተማሪዎች እንደየእድሜያቸው፣ ፍላጎታቸው፣ ዝንባሌና ችሎታቸው መጻሕፍትን የሚያገኙበትና የሚያነቡበት ስፍራ እጅጉን ያስፈልጋቸዋል።

እንደሚታወቀው፣ ቤተመጻሕፍት የተመረጡ፣ ለዚሁ ጉዳይ ተብለው ታስቦባቸው የተገነቡ የማንበቢያ ስፍራዎች ናቸው። በመሆኑም ለማንበብም ሆነ መጻፍ፣ በተለይ በአሁኑ ዘመን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም ከላይብራሪዎች የተሻለ ስፍራ የለም። በመሆኑም፣ በተለያዩ አካባቢዎች፣ በተለይም በከተሞች እነዚህን የመሳሰሉ ቤተመጻሕፍት ይኖሩ ዘንድ ይጠበቃል። ምክንያቱም እንደ እነዚህ አይነት ቤተ መጻሕፍቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተማሪዎች ሌሎች ስፍራዎች ካሉ ተማሪዎች በተሻለ ደረጃ የእረፍት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ ማለት ነው።

ወደ ቤተመጻሕፍት ሄዶ የእረፍት ጊዜን ማሳለፍ ከማንበብ ባለፈ ጥቅሙ ብዙ ሲሆን፣ አንዱም አዳዲስ ጓደኛ ማፍሪያም መሆኑ ነው። ሌላው ደግሞ፣ በጋዜጦችና መጽሄቶች …… አማካኝነት ትኩስና አዳዲስ ሀገርና ዓለም አቀፍ መረጃዎች የሚገኙ መሆኑ ነው። አዎ፣ በተለይ በደንብ በተደራጀ ቤተመጻሕፍት ውስጥ እነዚህንና ሌሎችንም ማግኘት ይቻላልና ተማሪዎች ወደ እነዚህ ቤተመጻሕፍት ቤት ሄደው የእረፍት ጊዜያቸውን ቢያሳልፉ ከሚጠብቁት በላይ ያተርፋሉ። ጊዜያቸውንም ተደስተው ያሳልፋሉ። ስለዚህ፣ የልጆች ምርጫም ሆነ የቤተሰብ ግፊት በአካባቢ ወዳሉ ቤተመጻሕፍት ይሆን ዘንድ ነው ባለሙያዎች የሚመክሩት።

በተለይ በአሁኑ ጊዜ፣ ምንም እንኳን በቂ ናቸው ማለት ባይሆንም፣ በየክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች (ለምሳሌ አዲስ አበባ) ቤተመጻሕፍት እንዳሉ በአመት በአመት ከሚቀርቡ የንባብ ማጠናከሪያ ኤግዚቢሽኖች መረዳት ይቻላል። በተለይ አንዳንዶቹ በሚገባ የተደራጁና ጥሩ የሚባል የመጻሕፍት ክምችት ያላቸው ናቸው። ይህ የሚናገረው ነገር ቢኖር በየአካባቢው ያሉ ተማሪዎች ወደ እነዚህ ቤተመጻሕፍት በመሄድ የእረፍት ጊዜያቸውን ትርጉም ባለውና በሚያስተምር፣ በሚያዝናና (ንባብ አንዱ ጥቅሙ ማዝናናቱ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ እርስ በእርስ በሚያስተዋውቅና ጥሩ ጓደኛ(ኞች)ን መመስረት በሚያስችል ሁኔታ ማሳለፍ የሚችሉ መሆኑን ነውና ተማሪዎች እድሉን ይጠቀሙበታል ተብሎ ይታሰባል።

እዚህ፣ የአዲስ አበባውን አነሳን እንጂ በሌሎች ከተሞችም (ደረጃቸው ቢለያይም) ቤተመጻሕፍት እንደሚኖሩ ይታወቃል። ያ ማለት ግን ሁሉም አላቸው ማለት ስላልሆነ በርካታ ቤተመጻሕፍትን የመገንባት የቤት ሥራዎች የሚጠብቋቸው ከተሞች (አካባቢዎች) አሉ።

ቤተመጻሕፍት እራሳቸውን የቻሉ ዓለማት ናቸው ማለት፣ ዓለም ቤተመጻሕፍት ውስጥ አለች እያልን ነው። በመሆኑም፣ አንድ ሰው ቤተመጻሕፍት ገባ ማለት ዓለምን ያለ ምንም ወጪና ድካም በእጁ አደረገ ማለት ይሆናልና ወደ ቤተመጻሕፍት ጎራ ከማለት አኳያ ማንም ሰው ሊሸወድ አይገባውም ማለት ነው።

ስለ ተማሪዎች የእረፍት ጊዜና እንዴት ማሳለፍ እንደሚገባቸው ከነፋይዳው እዚህ ድረስ ካወራን፣ አሁን ደግሞ እዚህ መሀል አራት ኪሎ ወደሚገኘው ዘመናዊው ቤተመጻሕፍት እንምጣና ያለውን ሁኔታ ባጭሩ እንመልከት።

ይህ ዘመናዊ ቤተመጻሕፍት ባለፈው አመት (ታኅሣሥ ወር) የተመረቀ ግዙፍ ተቋም ነው። በመሆኑም ልክ በዘመናዊነቱና ግዝፈቱ ልክ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች እየገቡና እየተጠቀሙ ይገኛሉ። በበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች እየተዘወተረ፤ በተለይም በተማሪዎች በኩል ቀዳሚ ተመራጭ መሆን የቻለ ቤተመጻሕፍት ነው።

አብርኆት ቤተመጻሕፍት እንደ ስሙ፤ የትምህርተ አብርሆት አባት “Papa Enlightenment Subject” መሆኑ የሚነገርለት እና ስመ ጥሩው ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንት ፍቺውን “እራሳችንን ከገባንበት ድቀት እና ባዶነት ነጻ የምናወጣበት” በማለት እንዳስቀመጠው፤ (በተለይ በአግባቡ እየተደራጀ ሲሄድ) የእውቀት ምንጭ፣ የለውጥ መነሻ፣ ብርሃን ፈንጣቂ – – – ተቋም እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው። በመሆኑም፣ በዚህ ተቋም (በተለይም በእረፍት ላይ የሆናችሁ ተማሪዎች) ጊዜን ማሳለፍ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ሲሆን፣ ከሚገኘው እውቀት ባሻገር የአካባቢው ውበትና የአየሩ ነፋሻነት በራሳቸው የሚሰጡት እርካታ አለና የዛ ሁሉ ጥቅም ተካፋይ መሆንን ያስገኛል።

ስለዚህ፣ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ስለተገነባውና በአፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ አስር ቤተመጻሕፍት አንዱ ስለሆነው አብርኆት ቤተመጻሕፍት ትንሽ ማለት ያስፈልጋልና አንዳንድ መረጃዎችን እናስቀምጥ። (ለተጨማሪ፣ የቤተመጻሕፍቱን ፌስቡክ ገፅ (Abrhot Li­brary ግሩፕ)ን መቀላቀል ወይም መጎብኘት ይቻላል።)

አብርኆት ቤተመጻሕፍት በአራት ወለሎች ተከፍሎ በውስጡ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን መጽሐፍት የሚይዝ መደርደሪያ የተገጠመለት ሲሆን፤ ከ120 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ መመገቢያ ካፌ፣ ስምንት የመጻሕፍትና ተጓዳኝ አገልግሎት መስጫ ሱቆች አሉት።

ይህ ዘመናዊ ቤተመጻሕፍት በውስጡ (ከ120,000 በላይ የሆኑትን ዓለም አቀፍ ኅትመቶችን ሳይጨምር) 400,000 መጻሕፍትን፤ ከ240,000 በላይ በስስ ቅጂ የተዘጋጁ እና 300,000 የሚጠጉ ጥናታዊ ጽሑፎችን … የያዘ ሲሆን… ለዓይነ ስውራን አንባቢያንም ምቹ ሆኖ የተሰራና የብሬል መጻሕፍት ክምችትንም የያዘ ነው:: እንዲሁም፣ ለሕፃናት፣ ለሚያጠቡ እናቶች፣ ለጥናትና ምርምር ሰዎች…ሁሉ ምቹና የተለየ የማንበቢያ ስፍራዎችንም የያዘ ነው።

በአንድ ጊዜ 2ሺህ 500 አንባቢያንን ማስተናገድ በሚችለው በዚህ ግዙፍ ላይብራሪ ዙሪያና ውስጥ አምፊ ትያትር እና መጫዎቻ ስፍራዎች መኖራቸው በራሱ በአይነቱ ልዩ የሚያደርገው ይሆናል።

ከላይ በጠቀስነው የተቋሙ ደጋፊዎች ድረገፅ ላይ ሰፍሮ እንደተመለከትነውና እንደሚታወቀውም፣ አብርሆት (Enlightenment) እውነትንና ዕውቀትን መሠረት በማድረግ ከድንቁርና ቀንበር ነጻ የመውጣት ሂደት ነው። እውነትን በአመክንዮ፣ በክርክር፣ በማስረጃ፣ በምርምር፣ የመፈለግ መንገድ ነው። ዕውቀት ወደ እውነት ለመድረስ ሁነኛው ጎዳና ነው ተብሎ ይታሰባል (ነውም)። በአመክንዮ የሚመሠረት የሰው ልጆች ማኅበራዊ ኑሮ በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ፣ መቻቻል ያለበት፣ ነጻነትን የሚያጎላና ለለውጥ ልብን ክፍት ያደረገ እንደሆነ ከላይ የጠቀስነው ፈላስፋ ያምናል። ስለዚህ የሰው ልጅ ስለራሱ፣ ስለዓለምና ስለሌላውም ሁሉ የተሻለ ዕውቀት እንዲኖረው እና ማኅበራዊ ሕይወቱን በአምክንዮ እንዲመራ ያስፈልጋል። ለዚህም መጻሕፍት፣ ፀሐፊያን እና ንባብ ያስፈልጋሉ። ይህ እውነት ከሆነ፣ የአብርኆት ቤተመጻሕፍት እውን መሆን ትክክለኛ ምርጫ ነው ማለት ነውና በእረፍት ጊዜ ብቻ ሳይሆን፤ ሁሌም፣ መቼም … ከአብርኆት መጥፋት አይገባም ማለት ይሆናልና እሰየው ነው።

ይህንን ካልንና ርዕሰ ጉዳያችን የእረፍት ጊዜን በንባብ ማሳለፍን የሚመለከት ከሆነ፣ በአሁኑ ሰዓት በዚህ ምቹና ምሉእ በኩለሄ በሆነ ቤተመጻሕፍት “እነ ማን ምን እያደረጉ ነው?” የሚለውን እንመልከት።

ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ሲባል በቤተመጻሕፍቱ ተገኝተን መረጃዎችን ለማጠናቀር ባደረግነው ጥረት በአሁኑ ሰዓት፣ በተለይም የተማሪዎችን እረፍት መሆን ተከትሎና የማትሪክ ፈተና ዝግጅትን ተንተርሶ ቤተመጻሕፍቱ እጅግ ተጨናንቆ፣ ወንበር አጥተው ቁጭ ብለው የሚያነቡትን ሳይጨምር፣ አንባቢያን ቦታ የለም ተብለው እስኪመለሱ ድረስ ነው ተቋሙ ሲያስተናግድ የነበረው።

“በቁጥር መግለፅ ይቻላል ወይ?” የሚለውንም አንስተን ለመወያየት የሞከርን ሲሆን፣ “አዎ” ከሚለው በመቀጠል፣ በቀን 10ሺህ አንባቢያንን፣ የምርምር ሰዎችንና ሌሎችንም ሲያስተናግድ እንደነበር ለማወቅ ችለናል። ትንሹ የአንባቢ ቁጥር ይታወቅ እንደሆነም ጠይቀን፣ በቀን ትንሹ የአንባቢ ቁጥር 6‚000 እንደሆነም የተነገረን ሲሆን፤ በአጭሩ፣ አብርኆት ቤተመጻሕፍት በቀን ከ6ሺህ እስከ 10ሺህ ተስተናጋጆችን የሚያስተናግድ መሆኑ ላይ ግንዛቤ ሊያዝ እንደሚገባ ተግባብተን ተለያይተናል።

በቦታው ተገኝተን ካነጋገርናቸው የቤተመጻሕፍቱ ተጠቃሚ ተማሪዎች ያገኘነው መልስም የእረፍት ጊዜያቸውን በአግባቡ፣ ዘና ብለው እያጣጣሙት እንደሆነና ለዚህም (በተለይም የተለያዩ መጻሕፍትን፣ ጋዜጦችን … ለማንበብ) አብርኆት ቤተመጻሕፍት በከፍተኛ ደረጃ እንደጠቀማቸው፤ ከጓደኞቻቸውም ጋር ለመገናኘት ምቹ እንደሆነላቸው የሚያረጋግጥ ምላሽ ነበርና ሁሉም ይህንኑ አይነት የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ዘዴን ተግባራዊ ቢያደርግ የሚለው መልእክታችን ይሆናል።

ይህ ከላይ የጠቀስነው፣ የአንዱና ታላቁ ቤተመጻሕፍትን የተመለከተ ብቻ ሲሆን፣ በየአካባቢው፣ በየተቋማቱ … ያሉ ቤተመጻሕፍትም ቁጥሩ ይለያይ እንጂ የየራሳቸው አንባቢዎች ኖሯቸው ሲያስተናግዱ መሰንበታቸውንና እያስተናገዱም እንደሚገኙ ይገመታል።

ባጠቃላይ፣ የእረፍት ጊዜ ማለት ከነበረው መደበኛ ተግባር ውጭ ሆነውና ዘና ብለው ሌሎች ተግባራትን የሚያከናውኑበት ማለት እንጂ ጭራሽ ከዓለም ውጭ የሚሆኑበትና አእምሮን ምንም በማያነቃቃ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የሚያሳልፉት ማለት አይደለም። በመሆኑም፣ ከላይ ደግመን ደጋግመን እንዳልነው፣ ባለሙያዎችም አስረግጠው እንደሚመክሩት የእረፍት ጊዜን ንባብን እና በመሳሰሉት ተግባራት ማሳለፍ ይገባል እንላለን።

መልካም የእረፍት ጊዜ ለተማሪዎቻችን!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 24/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *