ሀዲስ ዓለማየሁ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብርን እኔ ጻፍኩት፤ ወጋየሁ ንጋቱ ነፍስ ዘራበት›› እንዳሉት ነው።ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ለሀገራቸው ክብር ተሰዉ፤ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ሕያው እንዲሆኑ አደረጋቸው።‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት›› የተሰኘው የጸጋዬ ገብረመድኅን ግጥም አቡነ ጴጥሮስ በዛሬ ወጣቶች ዘንድ እንዲታተም አደረገ።ግጥሙ እንዲህ የሚሉ ስንኞች ነበሩት።
አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣ በፋሽስታዊ ነቀርሳ፣
ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ፡፡
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣ እንደኮረብታ ተጭኗት፣
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቁል
ጠምዝዟት፣
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት፣
ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት፡፡
እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን፣
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝ እመብርሃን፣
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣ እንዳልዘነጋት
ኢትዮጵያን …
ከ87 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ለፋሽስት ጣሊያን ወራሪ አልገዛም ብለው ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ለሀገራቸው ክብር ተሰውተዋል። የሰማዕቱ የሀገር ክብር ስሜት እነሆ ዛሬ ድረስ ለብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች ማስተማሪያ እና ምሳሌ ነው።እኛም በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን እኝህን ሰማዕት የሃይማኖት አባትና አርበኛ እናስታውሳለን።
አቡነ ጴጥሮስ የሃይማኖት አባት ብቻ አልነበሩም፤ የነፃነት ታጋይና ሰማዕት ሆነዋል። ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት ለሃይማኖታቸውና ለአገራቸው ነፃነትና ሉዓላዊነት ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ክብር መገለጫ ናቸው።
አቡነ ጴጥሮስ የተወለዱት በ1875 ዓ.ም ነው። የልጃቸውን የእውቀት ጮራ ለማየት ጉጉት ያደረባቸው ወላጆቻቸው፣ የልጃቸው ዕድሜ ገና ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ለጋ አዕምሯቸውን በእውቀት ያንፁላቸው ዘንድ ባህታዊ ተድላ ለሚባሉ መምህር በአደራ ሰጧቸው። እርሳቸውም በዚያው ገዳም በጥንታዊው የቤተ ክርስቲያኗ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በሚያስደንቅ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቀቁ። ከዚያም የቅኔ ትምህርታቸውን ለማበልፀግ ወደ ጎጃም በመሄድ በዋሸራ የቅኔ ትምህርት ቤት ተማሩ።
በውስጣቸው የሰነቁት የመማር ፍላጎት ኃይልና ብርታት ሆኗቸው፣ እንደቅኔው ሁሉ የዜማውንም ትምህርት በሚገባ ለመማር ከቅኔው አውድማ ጎጃም ወደዜማው ምድር ጎንደር ተሻገሩ። በዚያም የዜማን ትምህርት ተከታትለው ጨረሱ። ገና በልጅነታቸው ከደብረ ሊባኖስ ወደ ጎጃም፤ ከጎጃም ወደ ጎንደር የወሰዳቸው የትምህርት መንገድ ወሎ አደረሳቸው።ቦሩ ሜዳ ከተባለው ስፍራ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጽሐፍት ትርጓሜ ትምህርቶችን ማለትም መጽሐፈ ብሉያትን፣ ሀዲሳትን፣ ሊቃውንትንና መነኮሳትን በብቃት አስኬዱ።
በ1900 ዓ.ም ልክ እንደርሳቸው ሁሉ እውቀትንና ጥበብን ፍለጋ የገቡትን ደቀ መዛሙርት ለማስተማር ወሎ ውስጥ አማራ ሳይንት በተባለው ቦታ ወደሚገኘው ምስካበ ቅዱሳን ገዳም በመሄድ ወንበር ዘረጉ። በዚያም ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔንና መጽሐፍትን አስተማሩ። ከዚያም በኋላ ወደ ደብረሊባኖስ በመሄድ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈፀሙ።
በ1910 ዓ.ም ወላይታ ለሚገኘው ደብረ መንክራት ምሑር ኢየሱስ ገዳም በመምህርነት ተሾሙ። በዚያም ለስድስት ዓመታት ያህል ካገለገሉ በኋላ በ1916 ዓ.ም ወደ ዝዋይ ተሻግረው የመምህርነት ተግባራቸውን ለሦስት ዓመታት ያህል አከናውነዋል።በ1919 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርጎ የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንስሐ አባት ሆኑ፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች እንድትመራ ከግብፅ እስክንድርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ስምምነት ላይ ሲደረስ በትምህርታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች ተመርጠው ነበር።አቡነ ጴጥሮስ ከነዚህ አባቶች አንዱ ለመሆን በቁ።በ1921 ዓ.ም ከግብፅ እስክንድርያ መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መዓረገ ጵጵስና ተቀብለው ‹‹አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምስራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሰሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ›› ተብለው በመንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የታሪካቸው ደማቅ አሻራ የሚጻፍበት ክስተት የተፈጠረው።አቡነ ጴጥሮስ በመንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ከተሾሙ ከሰባት ዓመታት በኋላ፣ በ1928 ዓ.ም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች።አቡነ ጴጥሮስም ወራሪው የኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ ሲመለከቱ ልባቸው በከፍተኛ የኃዘን ጦር ተወጋ።
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን የአቡነ ጴጥሮስ ትካዜና
ፀሎት በምናባዊ ሕሊናው በግጥም እንዲህ ብሏል።
አዬ! ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ፣ እንዲህ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም የላት…
አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መከራ ለኃዘንና ለቁጭት ዳርጓቸው ይህንን ግፍ አይተው ማለፍ አልፈለጉም፤ ይልቁንም ከአርበኞች ጋር በመሰለፍ አርበኞችን ያበረታቱና ይደግፉ ጀመር።
ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል የሚፈፅመውን ገደብ የለሽ ግፍ ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ለማሳወቅ ባሕር አቋርጠው ከሄዱ በኋላ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ኃይላቸውን አሰባስበው በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ሠራዊት ለመውጋት በወሰኑበት ወቅት አቡኑ የአርበኞቹን ኅብረት ለመባረክና ሞራላቸውን ለማጠንከር ወደ አዲስ አበባ ሄደው ነበር።
በወቅቱ በነበረው የመረጃ እጥረትና የቅንጅት ጉድለት ምክንያት የታሰበው ጥቃት ባይሳካም ‹‹የመጣሁበትን ሳልፈፅም ወደኋላ አልመለስም፤ ብችል በአዲስ አበባም ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት ሕዝቡን በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርገዋለሁ፤ ካልሆነም እዚሁ እሞታለሁ›› በማለት ሕዝቡ ለፋሺስት እንዳይገዛና አስተዳደሩንም እንዳይቀበል ያስተምሩ ጀመር።
ዳሩ ግን ጠላት በመላ ከተማው ያሰማራቸው በርካታ ባንዳዎች አወኳቸው። በዚህም ምክንያት ጳጳሱ እንዳሰቡት ሊንቀሳቀሱ ባለመቻላቸው በወቅቱ የኢጣሊያ እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ኃይሉ እጃቸውን ሰጡ። ራስ ኃይሉም ለፋሺስቱ አስተዳደር የበላይ ለነበረው ለሮዶልፎ ግራዚያኒ አሳልፈው ሰጧቸውና የፋሺስት ጦር ቤተ መንግሥት ውስጥ አስገብቶ አሰራቸው።
ከዚያም ጳጳሱ የኢጣሊያን ገናናነት አምነው እንዲሁም የንጉሥ ኢማኑኤልንና የቤኒቶ ሙሶሎኒን ገዢነት ተቀብለው በሃይማኖታዊ ተልዕኳቸው እንዲሰብኩ ተጠየቁ። ጥቂት ኢትዮጵያውን ሀገራቸውን ከድተው በአድርባይነትና በጥቅም ለግፈኛው ጠላት ድጋፍ እንደሰጡ ሁሉ ጳጳሱም ጣሊያኖች የነገሯቸውን ተግባራዊ ቢያደርጉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪነትንና ለስብከት ማስፋፊያ የሚሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና የተንጣለለ መኖሪያ እንደሚሰጣቸው የሚያረጋግጥ መደለያ ተንቆረቆረላቸው። ለጥቅም ያደሩ የእምነት አባቶችም ኢጣሊያውያን የሰጧቸውን እድል እንዲጠቀሙ ጳጳሱን ይማፀኑ ጀመር።
አቡኑም ‹‹ለመሆኑ የኢጣሊያንን ገናናነት እንዳምን፣ የኢማኑኤልንና የሙሶሎኒን ገዢነት እንድቀበል ነው የፈለጋችሁት?›› ብለው መስቀላቸውን ጠበቅ ላላ እያደረጉ ጠየቁ። ‹‹በትክክል!›› አሉ ጣሊያኖች። ‹‹ማመን ብቻ በቂ ነው፤ ከዚያ ሥልጣኑ፣ ገንዘ…›› አላስጨረሷቸውም።
ይህን ጊዜ ጳጳሱ ገሰጿቸው። ‹‹በቃችሁ! በቃችሁ! ይህቺ ክብሯን የደፈራችኋት ሀገር ለመሆኑ ‹መኳንንት ከግብፅ ይወጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች› የተባለላት ቅድስት አገር መሆኗን ታውቃላችሁ? ይህቺ የቆማችሁባት ምድር ለእብሪተኞች ረመጥ፣ እንደ እሳት የምታቃጥል መሆኗን ብታውቁ ኖሮ ምን ያህል ጥርሳችሁ በኃዘን እየተፋጨ በተንገጫገጨ ነበር።ግን ግብዝ ሆናችኋል፤ በኃይላችሁ ተማምናችኋል።እኔ የምፈራው የሰው ሰይፍ አይደለም።የእናንተ እብሪት፣ የእናንተ ጉልበት ትንሽ ጉም ነው፤ ነፋስ የሚበትነው።እና የፋሺስት ኢጣሊያን የበላይነት ከምቀበል ሞቴን እመርጣለሁ።ወደ እግዚአብሔር እጆቿን የዘረጋችውን ቅድስት አገሬን እብሪተኛ ሲደቀድቃት እንዲኖር አልፈቅድም፤ እምነቴም በፍፁም አይፈቅድልኝም!›› አሉ ጳጳሱ አምርረው። ቀጥለውም ‹‹የኢጣሊያን ገዢነት የተቀበላችሁ ሁሉ አወግዛችኋለሁ! የኢጣሊያን ገዢነት ከተቀበለ እንኳን ሰው ምድሯ የተረገመች ትሁን!›› አሉ ጣታቸውን ወደላይ ቀስረው ሰማይ ሰማይ እየተመለከቱ።
እንዲፈፅሙ የተጠየቁትን ፍርጥም ብለው ‹‹እምቢ!›› ያሉት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ።ለፍርድም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ነበሩ።አቡነ ጴጥሮስ የቀረበባቸው ወንጀል ‹‹ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራሳቸውም አምጸዋል፤ ሌሎችም እንዲያምጹ አድርገዋል›› የሚል ነበር፡፡
ፋሺስቱ ዳኛም ‹‹ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ባለስሥልጣኖች እንዲሁም ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣሊያን መንግሥት ገዢነት አምነው ‹አሜን› ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?›› ሲል ጠየቃቸው። አቡነ ጴጥሮስም እንዲህ ብለው መልስ ሰጡ። ‹‹አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፤ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ … እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ ተከታዮቼን ግን አትንኩ! …›› አሉ። ዳኞቹም ጳጳሱ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ፈረዱ።
ከፍርዱ በኋላም ተመልሰው ወደእስር ቤት ተወሰዱና ተዘጋባቸው። ሌሊትም ዶፍ ዝናብ ሲዘንብ፣ ጎርፉ ሲጋልብና ነጎድጓዱ ብልጭ ድርግም ሲል በግፍ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው አቡነ ጴጥሮስ ‹‹ሰዓሊለነ ቅድስት ኢትዮጵያን ጠብቂያት እመብርሃን … ሕዝበ ኢትዮጵያን ጠብቅ …›› እያሉ ፀሎታቸውን ያደርሳሉ።
ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሰዓት ጥሩምባ ተነፍቶ ሕዝቡ ግድያው ከሚፈፀምበት ቦታ አራዳ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በታች ከአትክልት ተራ ፊት ካለው ቦታ ላይ ተሰበሰበ። አቡነ ጴጥሮስ በፋሺስት ወታደሮች ታጅበው መጡ። ሞት አይፈሬው የነፃነት አርበኛም ‹‹ዓይንዎን በጥቁር ጨርቅ እንዲሸፈኑ ይፈልጋሉ?›› ተብለው ተጠየቁ። ‹‹እናንተ እንደፈለጋችሁ አድርጉት፤ እንደ እኔ ምርጫ ግን የወራሪን፣ የእብሪተኛን ሞት ፊት ለፊት ገጥሜ ድል አድርጌ መሞት ስለምፈልግ ባትሸፍኑኝ ደስ ይለኛል፤ ሞቴ አያሳፍረኝም። የምሞተው ለሀገርና ለትልቅ ሕዝብ ነው›› በማለት የዓይናቸውን መሸፈን ተከላከሉ።
ጳጳሱም ፊታቸውን ወደ ምዕራብ እንዳዞሩ ስምንት ወታደሮች የመሣሪያቸውን አፈ ሙዝ አነጣጠሩባቸው። ሕዝቡና ሰማዩ እኩል አጉረመረሙ። ኮማንደሩ ‹‹ተኩስ›› የሚል ትዕዛዝ የሚሰጥ የግፍ ቃታዎች ተሳቡ። ‹‹ሥልጡን ነን፤ ሰብዓውያን ነን›› የሚሉት ነጮች አረመኔያዊ ድርጊት ፈፀሙ። አቡነ ጴጥሮስ በስምንት ጥይቶች ተደበደቡ፤ ከአንገታቸው በታች ሰውነታቸው ቢበሳሳም ነፍሳቸው አልወጣችም ነበር። ኮማንደሩ ሽጉጡን ከክሳዱ በመምዘዝ በሦስት ጥይቶች ጭንቅላቸውን ሲመታቸው ሕይወታቸው አለፈች። በሚወዱት የኢትዮጵያ አፈር ላይ ወደቁ። የኢትዮጵያ መወረር የእሳት አሎሎ ሆኖ ሲቃጠል የነበረው አንጀታቸው ተሰብስቦ ተኛ፡፡
አቡነ ጴጥሮስ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ክብርና ነፃነት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ።ያን ዕለት ኢትዮጵያ እጆቿን ዘርግታ ጮኸች። የአዲስ አበባ ሰማይ በግፍ ደመና ተዋጠ። እንቅልፍ ከነዋሪዎቿ ርቃ ወደ ምድረ በዳ ተሰደደች፤ ኡኡታ ከጋራ ጋራ አስተጋባ። ሞታቸውን በዓይኑ ያየው ሰው ሁሉ ወሬውን ሰምቶ ከሚከተለው እየቀደመ መንገድ አሳብሮ የአርበኞችን ፈለግ ተከትሎ ወጣ።መርዶው መርዶ ሆኖ አርበኞችን እንዲያኮሰምን ሳይሆን ቁጭት ለኳሽ ሆኖ በዱር ተናኘ፡፡
‹‹ኮርየር ደላሴራ (Corriere Della Sera) የተባለው ጋዜጣ ወኪል የነበረው ኢጣሊያዊ ጋዜጠኛ ቺሮ ፖጃሌ አቡነ ጴጥሮስ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሂደት ባሰፈረው ጽሑፍ ካካተተው ሀሳብ ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
‹‹ … ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም፣ ፊታቸው ዘለግ ያለ፣ መልካቸው ጠየም ያለ አዋቂነታቸውና ትህትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር። በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ … እኝህ ጳጳስ ሐቀኛ ነበሩ። ነገር ግን ለኢጣሊያ ለጋስዮን ታዝዞ የመጣው አስተርጓሚ ዳኞች የሚሉትን ብቻ ከማስተርጎም በቀር ጳጳሱ የሚናገሩትን ሐቀኛ ንግግር አላስተረጎመም። እኔ እንኳን የሰማሁት በአዲስ አበባ ለሠላሳ ዓመታት የኖረው የእቴጌ ሆቴል ኃላፊ የነበረው የግሪክ ዜጋ ማንድራኮስ አጠገቤ ተቀምጦ ስለነበር የተናገሩትን ሁሉ ስለገለጠልኝ ነው። እኔ እንደሰማሁት ፍርዱን ለመስማት በብዛት የተሰበሰቡት ጣሊያኖችና ታዝዞ የወጣው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሐቀኛ የሆነውን ንግግራቸውን ቢሰሙ ኖሮ ልባቸው ይነካ ነበር …››
በተጨማሪም ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ «አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ?» ሲል ሙሴ ፓይላክን ጠይቋቸው እርሳቸውም የሚከተለውን ተናግረዋል። «አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለውም የያዙትን መስቀል አማትበው ሕዝቡን ባረኩ። የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ከተቱት። ወዲያው ወታደሮች በእሩምታ ተኩሰው ገደሏቸው። ይህ እንደሆነ አስገዳዩ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ …››
አቡነ ጴጥሮስ በፅናትና በጀግንነታቸው ዓይኖቻቸውን በጠላቶቻቸው ዓይን ላይ ተክለው የአረመኔዎችን ሕሊና በረጋግደው እውነቱን እንዲያይ አደረጉት። የነፃነት መቅረዙ ላይ ራሳቸውን ሻማ አድርገው መቅረዙን ለኮሱት። እርሳቸው ግን በእውነት አደባባይ ላይ በተከሉት ሐውልት ለዘላለም በፅናት ቆሙ። የእርሳቸው መስዋዕትነት የኢትዮጵያውያን ጀግኖችን እልህ አፋፍሞ እንደቋያ እሳት ይበልጥ እያንቀለቀለ በየቦታው እንዲስፋፋ አደረገው።የኢጣሊያውንን ጭካኔ ያዩት የኢትዮጵያ ጀግኖች ውርደትንና ስቃይን ከእንግዲህ አናይም ብለው ‹‹ኧረ ጥራኝ ጫካው›› በማለት ቤታቸውን እየዘጉ፣ ቀያቸውን እየለቀቁ ‹‹ዱር ቤቴ …. መደፈር ሕመሜ ….. ነፃነት ገዳሜ›› አሉ። በፅኑ ትግላቸውም ፋሺስትን አንበርክከው የኢትዮጵያን ነፃነት አስመለሱ። ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስም እነሆ የአገር ፍቅር ማሳያ ሆነው በታሪክ ይታወሳሉ።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም