አዲስ ዘመን ድሮ

አዲስ ዘመን የታሪክ መነፅር ነው፣ ቀደም ባሉት ዘመናት ምን ተብሎ ነበር..፣ ምንስ ተከስቶ ነበር ብለን ካሰብን አዲስ ዘመንን መለስ ብለን መቃኘት ብቻ መልስ ይሰጠናል። ሳምንታዊው የአዲስ ዘመን ድሮ አምድም በየዘመኑ የተፈጠሩ አበይት ክስተቶችን ያስታውሰናል። ለዛሬም እንደተለመደው ዓመታትን ወደ ኋላ ተጉዘን በየዘመኑ በጋዜጣው የሰፈሩ ዘገባዎችን ለመመልከት የተለያዩ ጉዳዮችን መርጠናል። ባለፈው እሁድ የተከበረውን የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ 131ኛ ዓመት የልደት በዓልን አስመልክቶ የኢትዮጵያን የነጻነት በዓል ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ ሀገራት ለንጉስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተላኩ ደብዳቤዎች እናስታውሳለን። በተጨማሪም ማሪያም የሱፍ ጀማል በኢትዮጵያ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ማስገንባት መጀመሯን፣ የመሬት ከበርቴው ታድኖ መገደሉን፣ የኢትዮጵያ ጋዜጦች በካናዳ፣ የቄራዎች ማኅበር ማሳሰቢያ መስጠቱን እንዲሁም ሰው ምን አለ..ከሚለው የጋዜጣው ቀደምት ገጽ ላይ ያገኘነውን ሃሳብ በማካተት አቅርበናል።

የመልካም ምኞት ቴሌግራሞች

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ

የኢትዮጵያን የነጻነት በዓል ምክንያት በማድረግ ለግርማዊነትዎ መልካም ፀጋ፣ ወዳጅ ለሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብልጽግና እንዲደርሰው ያለኝን የደስታ ምኞት እገልጻለሁ።

ሻርል ደጎል

የፈረንሳይ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት

ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት

የኢጣሊያ ሕዝብና እኔ እራሴ የኢትዮጵያን ሕዝብ የነጻነት በዓል ምክንያት በማድረግ ለግርማዊነትዎ ፀጋ ፣ ወዳጅ ለሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልማት ይደርሰው ዘንድ ያለኝን ምኞት እንደገና እገልጻለሁ።

ጂኦቫኒ ግሮንኪ

የኢጣሊያ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት

(አዲስ ዘመን 1958 ዓ.ም)

ማሪያም የሱፍ ጀማል ባለ 4 ኮከብ ሆቴል ማስገንባት ጀመረች

አዲስ አበባ:- በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነችው አትሌት ማሪያም የሱፍ ጀማል በአዲስ አበባ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ማስገንባት ጀመረች።

በአሁኑ ጊዜ በባህሬን ለ 1ሺህ 500 ሜትር የምትወዳደረው የ2007 የዓለም ኮከብ እጩ አትሌት የነበረችው ማሪያም የሱፍ ጀማል ባለፈው ሰኞ ከማድሪድ ወደ ፍራንክፈርት በመጓዝ ላይ እያለች ለጋዜጣው ሪፖርተር አውሮፕላን ላይ በሰጠችው መግለጫ እንደገለጸችው፤ሆቴሉን የመገንባት እንቅስቃሴ ባለፈው ታኅሳስ ተጀምራል። የግንባታ ስራውም በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል።

(አዲስ ዘመን ህዳር 12 ቀን 2000 ዓ.ም)

የኢትዮጵያ ጋዜጦች በካናዳ

በየእለቱና በየሳምንቱ እየታተሙ የሚወጡት ጋዜጦች ማለትም አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድና የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ሞንትሪያል ወዳለው ( At water) አት ዋትር ወደሚባለው የሕዝብ መጽሐፍት ቤት ደርሰው መነበብ ከጀመሩ ሶስተኛ ወራቸውን ይዘዋል።

………..

ጋዜጦቹን ተረክቦ በማስተናገድ ላይ ያለው መጽሐፍት ቤት ጋዜጦቹን በቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ችግር እንደገጠማቸው ገልጸው፤ ጊዜ ካለንና የሚቻል ከሆነ እያንዳንዱ ጋዜጣ ታትሞ የወጣበትን ቀንና ወር እንድንጽፍበትና እንድንተባበራቸው በመጠየቅ ላይ ስለሆኑ በተለይ በአማርኛ እየታተሙ የሚወጡት ጋዜጦች የታተሙበት እለት በአውሮፓውያን ቀን አቆጣጠር ከኛው የቀን አቆጣጠር ጎን ታትሞ ቢወጣ ችግሩን ሊያቃልል ይችላል።

(አዲስ ዘመን መስከረም 19 ቀን 85 ዓ.ም)

የመሬት ከበርቴ የነበረው ከተሸሸገበት ታድኖ ተገደለ

የገጠርና የከተማ የመሬት ከበርቴ የነበረው ዳተኛ ኮሎኔል ታደሰ ተሰማ ከመኖሪያ ቤቱ ሸሽቶ ከተደበቀበት ሥፍራ በጸጥታ አስከባሪዎች ክትትል ከትናንት በስቲያ ዕለት መገደሉን አንድ የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ትናንት አስታወቀ። ሌተናል ኮሎኔል ታደሰ ቀደም ሲል ፀረ አብዮት ሴራ ሲፈጽም ስለተደረሰበት በጂማ ከተማ ከሚያካሂደው ከፍተኛ የከብትና የዶሮ እርባታ እንዲሁም ከወተት ውጤት ንግዱ በርግጎ ከአምስት ግብረ አበሮቹ ጋር ወደ ወጨጫ ማርያም አካባቢ ሸሽቶ በውንብድና ተግባር ተሠማርቶ ነበር።

የጸጥታ አስከባሪዎች ወደዚሁ አካባቢ ተልከው በተከፈተው ተኩስ ሁለት የወንበዴው ግብረ አበሮች ሲገደሉ ከጸጥታ አስከባሪዎች ሁለት ሞተዋል።

ከዚያም ሌተናል ኮሎኑል ታደሰ ተሰማ አምልጦ አዲስ አበባ መምጣቱ ስለተረጋገጠ ጸጥታ አስከባሪዎች ባደረጉት ጥብቅ ክትትል ከተሸሸገበት ሥፍራ ደርሰው እጁን እንዲሰጥ በማድረግ ታድኖ ተገደለ።

(አዲስ ዘመን ጥር 4 ቀን 1967 ዓ.ም)

ከኢትዮጵያ ቄራዎች ማኅበር የተሰጠ ማሳሰቢያ

ዘወትር ጤነኛ ለመሆን በኢትዮጵያ ቄራዎች ድርጅት ተገቢ ምርመራ ተደርጎለት የሚታረደውን ሥጋ ተመገቡ። የሥጋ ከብቶች የሳንባ ነቀርሳና ጠንቀኛ ሕመሞች ይገኝባቸዋል።

በተጨማሪም እባብ የነደፈውና የታመመ ውሻ የነደፈው ከብት ስለሚያጋጥም አንትራክስ የተባለው ጊዜ የማይሰጥ በሽታ ያስከትላል። ስለዚህ ሥጋ በምትገዙበት ጊዜ ጤንነቱ ሳይመረመር የታረደ ከብት ምግብነቱ ለጤንነት እጅግ አስጊ ነው።

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 24 1958ዓ.ም)

ሰው ምን አለ?

የቴሌቪዥን ጣቢያ የጊዜ መሻሻል ቢያደርግ ምናለበት። በአሁኑ የሥራ ጊዜ በሚባልበት ጊዜ በጊዜ ተኝቶ በማለዳ መነሳት ስለሚያስፈልግ ፕሮግራሙን በሁለት ሰዓት ከመጀመር ይልቅ ከሁለት ሰዓት በፊት የሚቀርቡትን ፕሮግራሞች ከሁለት ሰዓት በፊት ጀምሮ ዜናውን እንደተለመደው በሁለት ሰዓት ቢያነቡ በጊዜ ለመተኛትም ሆነ በጊዜ ለመንቃት ያመቸን ነበር።

ዘኪ አብዱላሂ

ምንም እንኩአን ጥቁር ቢሆኑ በመላው ዓለም የተደነቁ ናቸው። አድካሚነታቸው ለተሸካሚዎች እንጂ ለመላው ሰብዓዊ ፍጡር ድሎትን ይሰጣሉ። ምንድናቸው;

—ከሰል—

ማስታወቂያ

ዘመናዊና ልዩ የሆነው ሸሚዝ ራይል ብሩክ ብቻ ነው። ራይል ብሩክ ሸሚዝ ንጽሕናንና የጊዜ ቁጠባን ለሚወዱ ሁሉ ተስማሚ ነው። መተኮስ የማያስፈልገውና ኮሌታው የማይጨማደድ ሲሆን፣ በእኩል ሰዓት ውስጥ ታጥቦ የሚደርቅ ነው።

(አዲስ ዘመን መጋቢት 10 ቀን 1958ዓ.ም)

የወይዛዝርት ገጽ

አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

ለወይዛዝርት ገጽ አዘጋጅ

አዲስ አበባ ከእጮኛዬ ጋር ቀለበት ለመመላለስ ተስማምተናል፤ ነገሩ በጠብ ሳይሆን ዘመዳሞች ሆነን በመገኘታችን ነው። ስለእዚህ ቀለበት የሚመለሰው በሕዝብ ፊት ነው ወይስ እኔና እሱ ብቻ በግል ነው የምናደርገው;

በጥር ወር ጋብቻ የሚበዛበት ምክንያት ምንድነው; በሃይማኖት በኩል የታዘዘ ነገር አለ;

-የለም ፆሙ ሳይገባ ለመሻማት ነው።

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 18 ቀን 1958ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *