ልጆች እንዴት ናችሁ፤ እረፍት እንዴት ይዟችኋል? መቼም አሪፍ ነው እንደምትሉኝ አልጠራጠርም። ምክንያቱም እናንተ ጎበዞች በመሆናችሁ ለእናንተ ጠቃሚ በሆኑ ሥራዎች ላይ ተሰማርታችሁ ጊዜያችሁን በአግባቡ ትጠቀማላችሁ። ይህንን ማድረጋችሁ ደግሞ በተለያየ ስጦታ ባለቤት እንድትሆኑ ያደርጋችኋል። ለአብነት ልዩ ተሰጥኦዋችሁን አውቃችሁ በዚያ ዘርፍ የበለጠ እንድትሰሩ እድሉን ታመቻቹበታላችሁ። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ልጅ ደግሞ የዛሬ እንግዳች ታዳጊ ጆናህ ላሰን ነው።
ጆናህ በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስም ከፍ ያደረገ ልጅ ነው።የ15 ዓመት ልጅ ቢሆንም ስለኢትዮጵያ አርቆ የሚያስብና የኢትዮጵያ ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት አማራጭ እንዲያገኙ መደላደልን የሚፈጥር ነው። ለአብነትም በትውልድ አካባቢው ላይ የተለያዩ ተግባራትን ከውኗል።አንዱ ትምህርት ቤቶችን ለማሻሻል፣ ልጆችን ለማስተማር የሚያግዙ ነገሮችን ያደረገው ነው።ለምሳሌ፡ – ከቤተሰቦቹ ጋር ሆኖ ያሰራው ቤተመፃህፍትና የሳይንስ ቤተ ሙከራ በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
ልጆች ጆናህ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር በትውልድ አካባቢው የሚኖሩ ሕጻናት በዘላቂነት እንዲታገዙም ያደርጋል። በዚህ ደግሞ በርከት ያሉ ተማሪዎች ተስፋ አግኝተዋል።
ጆናህ እኤአ በ2008 ነው በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል የተወለደው። እናቱ እርሱን ለማሳደግ የሚያስችል አቅም የላትም። ስለዚህም ሰዎች እንዲያገኙት በማሰብ በኮባ ቅጠል ጠቅልላ እስኪወስዱት ድረስ እየተከታተለችው መንገድ ዳር አስቀመጠችው። የዚህን ጊዜ ብዙም ሳይቆይ ለቅሶውን የሰማች አንዲት ሴት አነሳችው። አሁን ጆናህ በሚያግዛቸው የሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ እንዲያድግ ሰጠችው። እርሱም ሕጻናት ማሳደጊያውን ቤቴ ብሎ መኖር ጀመረ። ሆኖም በሕጻናት ማሳደጊያው ውስጥ ብዙ አልቆየም። ምክንያቱም አሁን ቤተሰቡ የሆኑት ሰዎች ወደ አሜሪካ ወስደውታል።
ልጆች ጆናህ ወደ አሜሪካ ሲሄድም ተአምረኛ ልጅ ነበር።ምክንያቱም ቀኗ ለአሜሪካውያን የደስታና ለየት ተደርጋ የምትከበር ናት። ይህችም ቀን የአሜሪካኖች የነጻነት ቀን ነበረች። እናም ቤተሰቡ በዚያች ቀን ወደሀገራቸው ስላመጡት ደስተኛ ነበሩ።በእርግጥ ቤተሰቦቹ ልክ እንደወሰዱት ዝም ብለው ትምህርቱን እንዲከታተል አላደረጉትም። መጀመሪያ ያደረጉት ሙሉ ሕክምና እንዲያደርግ ነው። እናም በውጤቱም ደስተኛ አልሆኑም።ምክንያቱም ሀኪሙ ጆናህ የአዕምሮው እድገት አዝጋሚ ነው ብሏቸዋል።
የጆናህ ቤተሰቦች ልጃቸው በዚህ ደረጃ ላይ መሆኑ አሳስቧቸዋል።ምን ሊያደርጉለት እንደሚችሉም ግራ ተጋብተዋል።ይህንን እያሰላሰሉም ነው ለዓመታት ያሳደጉት። ሆኖም ጆናህ ግን የተለየ ልጅ ነበር የሆነው።እንደተባለውም ዘገምተኛ አይደለም።የፈጣን አዕምሮ ባለቤት እንጂ።በዚህም ቤተሰቡ እጅግ ተደሰተ፤ ጭንቀቱን አስወግዶም የሚያስፈልገውን መሙላት ጀመረ። እያደር ሲያድግም ለማመን የሚያቅት ልጅ ሆነ። ልዩ ተሰጥኦው እርሱን ብቻ ሳይሆን እነርሱንም አስተዋወቃቸው።
ጆናህ እጅግ ልዩ ተሰጥኦ ያለው ልጅ ነው።እንደእድሜ ጓደኞቹ ጊዜውን በጌምና ስልክ በመጎርጎር አያሳልፍም። ከዚያ ይልቅ እጆቹን የሚያሳርፋቸው በልዩ ተፈጥሮ በተካነበት የእጅ ጥበብ ላይ ነው። በጣም ታዋቂ የዳንቴል ውጤቶችን ይሰራል። መጥለፊያ ኪሮሽ ይዞም እጅግ የተዋጣላቸው የጥልፍ ሥራዎችን ያመርታል። እንደውም አንዴ ከያዘው በአርባ ደቂቃ ውስጥ አንድ የሹራብ ኮፍያ ሰርቶ ማጠናቀቅ ይችላል።
ልጆች ጆናህ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚሁ የሙያ ሥራው ተወዳድሮ አንደኛ የወጣ ልጅ ነው። ውድድሩ ደግሞ ከተራ ግለሰቦች ጋር ሳይሆን በሙያው ረጅም ዓመታትን ካሳለፉ ሰዎች ጋር ነበር። እናም በሚሰራቸው የሹራብ ስራዎች አሁን ላይ ዓለም ያውቀዋል። በኢንተርኔት አግራሞትን ፈጥሮ ተከታዮቹ ብዙ ናቸውም።እንደውም እኤአ ከ2019 ጀምሮ በአሜሪካን ሀገር ግርምት ፈጣሪ ከሆኑ ሰዎች መካከል ተቀምጧል። ‹‹ጆናህ የጥልፍ ጥበበኛው ክሮቼት ፕሮዲጊ›› የሚል የአድናቆት ስምም ተሰጥቶታል። በዚህ ደግሞ ትላልቅ የሚባሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቃለ መጠየቅ አድርገውለታል።ታላላቅ የሚባሉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አቅርበውት ተሞክሮውን አካፍሏል።
ጆናህ የልጅ አዋቂ፤ ለጋስና ክህሎትን ለሌሎች የሚያጋራ ሥራ ፈጣሪ ልጅ ነው።ምክንያቱም ከ10 ዓመታት በላይ በልብስና እደ ጥበብ ሥራ የሥራ ልምድ አለው።በዚህ ደግሞ በተለይም የሀገሩን ልጆች ከመደገፍ አኳያ የማያደርገው ነገር የለም።አንዱ ታዋቂነቱንና ልዩ ስጦታውን በዩቲዩብ ቻናሉ ላይ በመጠቀም ሀገሩን ያስተዋውቃል። ለሀገሩ ልጆች መደረግ ስላለበት ነገር መረጃ ይሰጣል። በተመሳሳይ ጎፈንድሚ በማሰባሰብ ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያደርጋል።
ልጆች ጆናህ ከዚህ በተጨማሪ የሚሰራቸው ሥራዎች አሉ። በሙያው ሌሎችን ሰዎች ማገዝና የሥራ እድል መፍጠር ነው። እንዴት ካላችሁ የእርሱን ሕይወት በማጋራትና ሥራውን እንዴት እንደለመደው በማስተማር ነው። ሙያውን ለምደው እንዲሰሩበት የመለማመጃ ጊዜን በዩቲውቭ ቻናሉ ከፍቶ ስልጠና ይሰጣል።ሌላው ጆናህን ለየት የሚያደርገው ነገር የራሱን የሕይወት ውጣውረድ በመጸሐፍ መልክ ጽፎ ለአንባቢያን ማድረሱ ነው። መጸሐፉን የጻፈው በ12 ዓመቱ ሲሆን፤ ሰዎች ከእርሱ ሕይወት ተምረው ችግሮቻቸውን እንዲፈቱበት የሚያስተምርበትም ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም