የ20ኛውን ክፍለ ዘመን ሙዚቃዎች ያጣጣመ ሰው አያሌውን አለማስታወስ አይችልም። ‘ጓል አስመራይ፣ ቻለው ሆዴ፣ ላንቺ ምን ሰርቼ፣ ማልቀስ ምን ጠቀመ፣ አደራ እየሩስ፣ ላሌ ጉማ፣ እናቴ ናፈቅሽኝ፣ እንደሄድኩ አልቀርም… ወዘተ’ በመሳሰሉ ሙዚቃዎቹ መድረክ ላይ ሆኖ ብዙዎችን በእንባ አራጭቷል። ስለ አያሌው መስፍን ስር መሰረቱን ለማወቅ ለሚፈልግ ሰው የማወቅ ጥሙን ለማርካት በቂ ባይሆንም በዛሬው የዝነኞች አምዳችን ከሕይወቱ ምንጭ እየቀዳን ለጠብታ ያህል ልናቀምው ወደድን።
የዜማና ግጥም ደራሲ፣ ድምጻዊ አያሌው መስፍን በ1942 ዓ.ም በወሎ ክፍለ ሀገር በየጁ አወራጃ ተወለደ:: አያሌው ተወልዶ በእጁ እየዳኸ በጉልበቱ ተንፏቆ በእግሩ ድክ ድክ ለማለት ሲውተረተር ደግፋ ያቆመችው ሙዚቃ ሳትሆን አትቀርም። አያሌው ስለ ሙዚቃ አይደለም ሙዚቃን ለማወቅ በማይቻልበት እድሜ ላይ ሆኖ ስለ ሙዚቃ ማሰላሰል ጀምሮ ነበር። ያቺ ከልቡ ላይ ገብታ የተቀጣጠለችው የሙዚቃ ፍም ገና በለጋ እድሜው የሙዚቃን ዳና ተከትሎ የእድሜ ዘመን የሙዚቃ ተጓዥ አደረገችው። እናም ጉዞው ተጀመረ።
ጥበብ ከድንጋይ ፍም ይበልጥ የጋለች ነች። የሙዚቃ ስበትም ከመሬት ስበት የላቀ ነው። ባህርና ውቅያኖስ በውስጣቸው ከሚሸከሙት በላይ የመሸከም ምትሃታዊ ኃይል አላት። በዚያች ትንሽዬ የአያሌው ልብ ውስጥ ያለች የሙዚቃ ጥበብ ስታናውዘው አንዴ ከዚህ አንዴ ከዚያ እንዳይቆም እንዳይቀመጥ ለጉድ ወዘወዘችው። ያውም ገና በልጅነት እድሜ። ወላጆቹ ደብተርና እስክሪፕቶ እየገዙ ወደ ትምህርት ቤት ቢሰዱትም ይቺ የሙዚቃ ፍቅር በየት በኩል የመማሪያ ወንበር ላይ ታስቀምጠውና ድንገት ከክፍል ውልፍት ብሎ ይወጣል። ‘እህሳ.. አሁንስ ምን ላድርግሽ ሙዚቃ?’ ሲል ይጠይቃታል። ና! ተከተለኝ ትለውና እጁን ይዛ አስከትላው እልም ትላለች። ከሚወዳት በላይ ሙዚቃም ሳትወደው አትቀርም። መዳረሻቸው ሁሌም አዝማሪዎች በመሰንቆ ከሚጫወቱበት ስፍራ ላይ ነው። ‘ተመልከት እንግዲህ’ ትለዋለች ሙዚቃ። ወይ ነዶ! ወይ ነዶ! ልቤ አለቀለሽ እንደ እሳት ነዶ! ማለት ይሄኔ ነው። የአያሌው ልብ እንደ ኤርታሌ ወላፈን መንተክተክ ይጀምራል። በውሃ የማይጠፋ እሳት፣ የሙዚቃ ፍቅር ይስበዋል። ይወስደዋል። እናም አያሌው ትምህርቱ ለሕይወቱ መሰረትና ወሳኝ መሆኑን ቢያውቅም ይህ ስበት ግን የማይቋቋመው ሆነ። ወደ ትምህርት ቤት ለማቅናት በጠዋቱ ደብተሩን ሸክፎ እየወጣ ሃሳቡ ከትምህርት ቤት መገኛው ግን የአዝማሪዎቹ ደጃፍ ሆነ። አያሌው የሙዚቃ ፍቅር አየለችበት።
1956 ዓ.ም አያሌው 14 ዓመቱ ነበር። መሸከም ከሚችለው አቅሙ በላይ ብዙ የሃሳብ ጓዞችን በአዕምሮው ተሸክሞ ማውጣትና ማውረድ የእለት ተእለት ግብሩ ሆኗል። ይበላል አይጠግብም፣ ይጠጣል አያረካውም፣ ይታቀፋል ምቾች አይሰማውም፤ ምክንያቱም የልቡ ማረፊያ የደስታው ምንጭ፣ ሙዚቃ ከምትባል ነገር ዘንድ ሃሳብና ምኞቱ ነሁልሎ ነበር። ከመናገር ይልቅ ማንጎራጎር ይቀናዋል። ልቡን የሰለበችውን መሰንቆ መሳይ ነገር እያበጀ ከዚያ የሚወጣውን ድምጸት ከራሱ ድምጽ ጋር እንደምንም እያዋሃደ ረሃቡን ለማስታገስ ይታገላል። 14 ዓመት ከሞላው በኋላ ግን የሁል ጊዜ የሃሳብ ሸክሙን ለማቅለል ወሰነ። ሁሌም ሙዚቃ እየመጣች በጆሮ ሹክ የምትለውን ሃሳብ ለመቀበልና የምትለውን ሁሉ ለማድረግ ቆረጠ። እንዲህም ሳይላት አልቀረም ‘በሃሳብሽ ተስማምቻለሁ እሺ አሁን ምን ላድርግ..’ ‘ና ዝም ብለህ ተከተለኝ’ አለችው። አያሌው መስፍን ከቤት ጠፍቶ ለቤተሰቦቹ አንዳችም ሳይል በ14 ዓመቱ ሙዚቃን እየተከተላት አዲስ አበባ ገባ።
አያሌው የአዲስ አበባን አፈር እረግጦ ውሃዋንም ጠጣ። ከሀገሩ እጁን ይዛ ያስወጣችው ሙዚቃ መቼም ከአዲስ አበባ ግርግር ጥላው የምታልፍ አልነበረችምና ወደ አንድ ግሩም መንገድ አመለከተችው። በወቅቱ የብሔራዊ ቲያትር ድምጻውያንን አወዳድሮ ለመቅጠር ማስታወቂያ አውጥቶ ነበር። እናም አያሌው ተመዝግቦ ወደ ፈተናው አዳራሽ ገባ። ከትንሹ አያሌው በስተጀርባ ቆማ በርታ የምትለው ሙዚቃ እራሷ ነበረችና ፈተናውን በአንደኝነት አጠናቀቀ። በስተመጨረሻ በአንደኝነት ማጠናቀቁን ሲሰማ ወሰን አልባ ደስታ ተሰማው። ውስጡም በብርሃን ተስፋ ተሞላ። ድንገት ግን ያቺ ብርሃን እንደ ንፋስ ላይ ሻማ መውለብለብ ጀመረች። እስከዛሬ ከሙዚቃ አስበልጦ ግድ ያልሰጣት አንዲት ሃሳብ የእድሉን እጣ ፈንታ ለመወሰን ከልቡ ላይ ትወራጭ ጀመር። አባቱ ትዝ አሉት። ‘አሁን አባቴ ድምጼን በራዲዮ ቢሰማው ምንድነው የምሆነው….ልጄ አዝማሪ ሆነ ሲል አፈላልጎ ነው የሚገድለኝ…’ በሚል ሃሳብ ውስጡ ተሸበረች። የአባቱ በቁጣ የነደዱ አይኖች ከፊቱ ቆሞ ሲገርፉት በአይነ ህሊናው ታየው። ለሳምንታት በውስጡ ስትዋዥቅ የነበረችው የሙዚቃ ብርሃን በሃሳብ አውሎንፋስ ድርግም ብላ ጠፋች። አያሌው የብሔራዊ ቲያትርንም ሆነ ሙዚቃ ለመተው ወሰነ። ፊቱን አዙሮ ወደ ኋላ ተመለሰ።
ከሶስት ዓመታት ቆይታ በኋላ በ1959 ዓ.ም በቀድሞው የክብር ዘበኛ ሠራዊት ውስጥ በወጣት ሻምበልነት ማዕረግ ተቀጠረ። በዚያም እስከ 1959 ዓ.ም ድረስ ቆየ። አያሌው ሙዚቃን ለመተው የወሰነ ቢሆንም አንድም ቀን ግን ስለሙዚቃ ሳያስብ ውሎ አድሮ አያውቅም ነበር። በስበት የተሞላችው የሙዚቃ ብርሃን ከውስጡ ጨርሶ አልጠፋችም ነበርና ከውስጡ ብልጭ እያለች ትጠፋለች። ትታ ላትተወው ትቶ ላይተዋት በአንድ መንገድ ላይ ነበሩ። አሁን ግን ምንም አይነት ምክንያቶች ላያስቆሙት ምሎና ተገዝቶ ተመልሶ ወደ ሙዚቃ መጣ። እሷም አላሳፈረችውም። ሌላ ጊዜ፣ ሌላ እድል ሰጠችው። በዚያው በ1959 ዓ.ም ከአንድ ባንድ ውስጥ ተቀጥሮ የመስራት ዳግም እድል አገኘ። አያሌው በባንዱ ስር ሆኖ ወደ ጅማ አቀና። ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ከጅማ ተመልሶ ወደ አዲስ አበባ ገባ። የአያሌውን ችሎታ ቀምሶ ላጣጣመው ሁሉ ጣፋጭ ነበርና በየትኛውም ስፍራ ተቀጥሮ ለመስራት አልተቸገረም። ከዚያ በኋላ ፈጣን ኦርኬስትራ በመባል በሚታወቀው በወይዘሮ አሰገደች አላምረው ቤት (ፓትሪስ ሉሙምባ የሚባል የማታ ክበብ ውስጥ) በሳምንት አምስት ብር እየተከፈለው ከሚወዳት ሙዚቃ ጋር ተዋዶና ተዋህዶ መኖር ጀመረ። በዚያው ዓመት ብቻ 16 የሚሆኑ ዘፈኖቹን አዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በራዲዮ አቀረበ:: የአያሌው ስም በመላ ሀገሪቱ እየናኘ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የዝናን ካባ ደረበ። በባንዱ ውስጥ ይከፈለው የነበረው የአምስት ብር ደመወዝም በአንድ ጊዜ ወደ 15 ብር ተመነደገ።
1962 ዓ.ም የኦርኬስትራን ባንድ ለቆ ቀደም ሲል ትቷት ወደ ሄደው ብሔራዊ ቲያትር ተመልሶ መጣ። ነገር ግን ብሔራዊ ቲያትር እጣ ክፍሉ አይደለችም መሰል አሁንም ለ3 ወራት ያህል ብቻ ነበር የቆየው። ከዚያ ወጥቶ ወደ ፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ክፍል በመግባት እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ሰራ። የአያሌው ሌላኛው የምኞት ሃሳብ የራሱን ባንድ ማቋቋም ነበር። እናም እየተዘዋወሩ በተለያዩ ባንዶች ውስጥ መስራቱን አቁሞ ‘ጥቁር አንበሳ’ የተሰኘውን ባንድ አቋቋመ። ባንዱ የተዋጣለት ነበር። በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 14ቱም ክፍለ ሃገራት ከባንዱ ጋር እየተዘዋወረ ስራዎቹን ለማቅረብ ቻለ።
ጊዜው ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ የሰማኒያኛውን የልደት በዓላቸውን የሚያከብሩበት እለት ነበር። በእለቱ የጥሪ ካርድ ደርሷቸው በመድረኩ ላይ ከነበሩ ሰዎች መሃከል የዚያን ጊዜ ወጣት አያሌው መስፍን አንደኛው ነበር:: የልደት በዓላቸውን ባከበሩበት እለትም በኪነ ጥበቡና በተለያዩ ዘርፎች ለሃገራቸው ባለውለታ የነበሩ ሰዎችን ሸልመው ነበር:: ከንጉሱ ፊት ቀርቦ እጅ በመንሳትም የወርቅ ሽልማት ወስዶአል:: በወቅቱ ይሰራ የነበረው በጦር ሰራዊት ባንድ ውስጥ ነበርና ከሽልማቱ በኋላ የበላይ ኃላፊው የነበረው ጀነራል እጁን ይዞ ወደ ንጉሱ በመሄድ ሽልማቱ ያንሰዋል ሲል ነገራቸው:: ከሌሎች በተለየም ለአያሌው በድጋሚ የወርቅ ሰዓት አበረከቱለት:: ይህ ሽልማት ለእርሳቸውና ለአያሌው የመጨረሻው ይመስላል። ከእጃቸው የመጨረሻዋን የሽልማት ጽዋ አንስቶ ሄደ።
እንደ ነበረ የሚቆይ ምንም ነገር የለም። ጊዜ በጊዜ፣ ዓመታት በዓመታት፣ መንግስትም በመንግስት ይሻራል። የንጉሱ ዘውዳዊ ሥርዓት ተደምስሶ የደርግ መንግስት መንበሩን ሲቆጣጠር ለአያሌው ጥሩ ጊዜ አልነበረም:: ቀደም ሲል በርካታ ችግሮች ያጋጠሙት ቢሆንም ይሄኛው ግን ዘሎ የማያልፈው ገደል ነበር:: እያመቻመቸ ከሚወደው ሙዚቃ ጋር የመስራት እድሎች ቢኖሩትም እርሱ ግን ብዙ ነገሮች አልዋጥልህ እያሉት ከነበረው ስርዓት ጋር አንገት ላንገት መተናነቅ የግድ ሆነበት:: ስርዓቱ እያመጣ ብዙ ነገሮችን ሲጥልበት እርሱ ግን ቀን እስኪያልፍ…በሚል ብሂል አንገቱን ደፍቶ ለመሸከም አልፈቀደምና እያሽቀነጠረ ይጥላቸዋል:: “እንደ ሰራሁት ስራ ቢሆን ኖሮማ በሰዓቱ የሞትን ጽዋ የምጎነጭ ነበርኩ” ይላል አያሌው ከአንድ ሚዲያ ላይ ቀርቦ ነገሮችን ሲያስታውስ:: በዚያን ወቅት እርሱም ከመስራት መንግስትም እርሱን ከመቅጣት ወደኋላ አይሉም ነበር። አያሌው የሰራቸው 12 ያህል ሙዚቃዎች ወደ ሕዝብ ጆሮ እንዳይገቡ ተደረገ። ኦርጂናል ስራዎቹም ከያሉበት እየተፈለጉ ይቃጠሉ ጀመር። ከ1971 ዓ.ም እስከ 1983 ዓ.ም የነበሩት ጊዜያት ለአያሌው በእጅጉ ፈተና ነበሩ። አያሌው በየትኛውም አይነት መድረክም ሆነ የሙዚቃ ስራ እንዳይሳተፍ ታገደ። ይህ ብቻም ሳይሆን ከሀገር እንዳይወጣም ጭምር ማዕቀብ ተጣለበት። በአንድ ወቅት ግን አንድ ሃሳብ ብልጭ አለለት። ለረዥም ጊዜ ካሰላሰለ በኋላም የግሉን ‘ኦፕሬሽን’ በድል ለመወጣት እቅድ ነድፎ ወደ ተግባር ገባ። የእርሱ ስራ የሆኑ 4 ሺህ የሙዚቃ ኮፒዎችን በራሱ ወጪ አዘጋጀ። እቅዱ እነዚህን ኮፒዎች ውስጥ ለውስጥ ለሕዝቡ በድብቅ አሰራጭቶ ከሀገር መኮብለል ነበር። ሁሉንም ነገር ጨርሶ ለማደል ሲል ግን ተያዘ። ጥቂት የማይባል ጊዜም በእስር ላይ ቆየ። ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ አያሌው ከሆዱ ስቦ የያዘውን አየር አውጥቶ ለመተንፈስ ቻለ። የኢህዴግ መንግስት በገባ ማግስትም ከደርግ መንግስት ሸሽጎ ያቆያቸውን ስራዎቹን በመያዝ እግሬ አውጪኝ ሲል ኮብልሎ ወደ አሜሪካን ሀገር ተሰደደ።
ኮብላዩ የሙዚቃ ሰው ኑሮውን በአሜሪካን በማድረግ ለረዥም ጊዜ በዝምታ አሳልፏል። ከብዙ ዝምታዎች በኋላ ግን እዚያው ባህር ማዶ እያለ በፈረንጆቹ 1998 ዓ.ም “ሀሳቤ” የተሰኘ የሙዚቃ ስራ ይዞ ወጣ:: የአያሌው ሙዚቃዎች በብዛት ፈንኪ ወይንም ኢትዮጵያዊ ወጉን ያለቀቀ የፖፕ ስልት በመሆኑ ከዚህ ስራ በኋላ የነጮቹንም ቀልብ ስቧል:: አንድ ነጭ የሙዚቃ ባለሙያም አያሌውን እያፈላለገ ካለበት ድረስ መጥቶ ከእርሱ ጋር ቆይታ አደረገ:: ከዚያ በኋላም በነጮች መድረክ ላይ ቆሞ በሚያስደምም ሁኔታ ‹ሃሳቤን› አቀነቀነ:: እውነቱን ለመናገር እንደ እድሜውና ለአስርት ዓመታት ከሙዚቃ ታግዶ እንደመቆየቱ የስራው ጣዕምም ሆነ የአቀራረብ ብቃቱ ያልተጠበቀ ነበር:: አያሌው ከመድረኩ ላይ ነግሶ በክብር ወረደ:: ረዘም ላሉ ዓመታት ከአሜሪካን ሰንብቶ ከጥቂት ዓመታት በፊትም የሀገሩን አፈር ለመርገጥ በቅቷል።
ኮብልሎ ያልቀረው የጥበብ ሰው ለ55 ዓመታት በሙዚቃ ፍቅር ኖህልሎ፣ ሙዚቃንም ብሎ ኖረ። ከውስጡ በሙዚቃ ከጎኑ ደግሞ በልጅ ልጆች እንደተከበበም አሁንም አለ።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16 ቀን 2015 ዓ.ም