ፒያሳ በድምፅ ማጉያ በታጀበ የህክምና እርዳታ ተማፅኖ፣‹‹የሙዚቀኛና ዘማሪ እገሌና እገሊት አዲስ ስራ ተለቀቀ›› በሚል ጆሮ የሚበጥስ ማስታወቂያ፣ በመንገድ ላይ ነጋዴዎች ‹‹የግዙን››ጥሪ ድምፅ ታውካለች፡፡ የሚያስተናንቅ የሃሳብ ልዩነት ከሌለን አንድ ጓደኛዬ ጋር አንድ ካፌ ተቀምጠናል፡፡ ቡናችንን እየጠጣን እንደወትሮው የሚያስማማንን እንጂ የሚያለያየንን ገሸሽ በማድረግ ሁለታችንም ያዘልነውን ወሬ እያወረድን ነው።
ከፊት ለፊታቸው ሁለት ወንዶች እና አንድ ሴት ተቀምጠዋል፡፡ ሁሉም ተንቀሳቃሽ ስልካቸው መስኮት ላይ አፍጥጠዋል፡፡ የመፅሃፉ ርእስ እና መቼ እንዳነበብኩት ትዝ ባይለኝም እንደህ አይነት የወጣት ስብስብን የተመለከተ አንድ ፀሃፊ፣ head down generation ሲል እንደገለጻቸው አስታውሳለሁ፡፡
‹‹head down generation›› አንድ ላይ ቢሆኑም የተለያዩ የእርስ በእርስ መስተጋብር ከመፍጠር የተቆጠቡና አካባቢያቸው ያለውንና ከመቃኘት ይልቅ ሙሉ ትኩረታቸውን ስልካቸው ላይ ያደረጉ፣ People will look more at their phone then at their surroundings የሚገልፅ ነው፡፡፡
የዚህ ትውልድ መገለጫ ከሆኑት ሶስቱ ወጣቶች አንደኛው እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም እንዲሰሙለት የፈለገውን ቪድዮ ድምጹን ከፍ አድርጎ ያደምጣል፡፡ ያስደምጣል፡፡ በስልኩ ውስጥ በአፋዊ ጩኸትና በቃላት ድሪቶ የሚጫወት ሰው ድምፅ ይሠማል፡፡ መልከ መልካማ እንስት እየሰማችው ባለችው መደነቃ በገፅታዋ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ ድንገት ‹‹ጋዜጠኛ ማለት እንዲህ ነው›› ስትል ገጽታዋን በአንደበታ ገለፀች፡፡ አጠር ብሎ ወፈር የሚለው ወጣት ‹‹አስገባላቸው› ሲል ድምፅ አወጣ፡፡ አድናቆት ይሆን አስተያየት መለየት አልቻልኩም፡፡
የሰማሁት ትእይንት ድንገት ስሜቴን ሲቀይረው ታወቀኝ፡፡ ዝም ያልኩ ይምሰል እንጂ ከራሴ ጋር ተቋስያለሁ፡፡ ምንም ያልመሰለኝ ለመምሰል ብታገልም ውስጤ ግን ተረብሿል:: ችላ ያልኩት እንኳን ብመስልም በሁለመናዬ ንዴት መሰራጨቱ ይታወቀኛል።
እየቆየ ገፅታዬ ላይ የንዴት ስሜት ያስተዋለው ወዳጄ ታዲያ ‹‹ምነው ድንገት…››ሲል ትዝብቱን በጥያቄ መልክ አቀረበልኝ። ውሀ ቀጠነ በሚል ሰበብ አሊያም ፀጉር እየሰነጠቁ፣ ቪዲዮ እየቆራረጡ፣ ቃላቶች እየሰነጠቁ ማዘጋጀት በርካቶች ከመቀመጫው እያስነሳ፣ እያስቀመጠ በስሜት እያስጋለበ ሲያስጨፍር መመልከት ከማሳዘን አልፎ እያበሳጨኝ መሆኑን አወጋሁት፡፡ የግለሰቦች ድግስ አሊያም ምርቃት እንዲሁም አኗኗር የሚዘግበው ሁሉ ‹‹ጋዜጠኛ›› የሚል ካባ እየለበሰና በበርካቶች ዘንድም ጋዜጠኛው ጋዜጠኛዋ በሚል ማእረግ እያስጠራ መቀጠሉ እያንገበገበኝ መሆኑን አጫወትኩት፡፡
ነገሩን እየሳቀ ዘና፣ ቀለል አድርጎ የሚያልፈው መስሎኝ ነበር። ይሁን እንጂ ተሳስቻለሁ። ትዝብቱ የእኔ ብቻ አይደለም፡፡ የእርሱም ጨምር ነው፡፡ ብስጭታቸውን መደበቅ ከማይችሉት ጓደኛቼ ግንባር ቀደሙ ነውና ጊዜ ሳያጠፋ ‹‹ጋዜጠኛ›› ተብዬዎቹ በርትተው እየቀለዱበት መሆኑን አወጋኝ፡፡
በተለይ በተለይ ከትንሽ እስከ ትልቅ አርቲስቶች አንድ ቴሌቪዥን አሊያም ሬድዮ ጣቢያ ላይ እንግዳ እያቀረቡ ከመጠሪያ ስማቸው በፊት አርቲስትና ጋዜጠኛ የሚል ማእረግ እያስጨመሩ መሆኑ ከግርምት ባለፈ ለትዝብት የሚዳርግ መሆኑን አብራራልኝ፡፡
እኔ የምለው ቆይ ጋዜጠኛ ማነው? ለእኔ ጋዜጠኝነት ጠያቂነት ነው፡፡ መላሽነት ነው፡፡ መርማሪነት ነው፡፡ ምክንያታዊነት ነው፡፡ ጥልቁን አዋቂነት ነው፡፡ ረቂቁን ተረጂነት ነው፡፡ እውነትን ፈላጊነት ነው፡፡ ወሳኝ ጥያቄ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ከባድ መልሱንም መፈለግ ጭምር ነው፡፡ ጋዜጠኝነት እውቀት ነው፡፡ ሚዛናዊነት ነው፡፡ አርቆ አሳቢነት ነው፡፡ ሃላፊነት መሸከም ነው፡፡ ተሰጥኦና እና ፍላጎት ነው፡፡ አሰላሳይና ትሁት መሆን ጭምር ነው፡፡
ጋዜጠኛ ሰፊውን ዓለም በጭላንጭል እይታ የሚመለከት አይደለም፡፡ ጋዜጠኛ ቀላሉን የሚመርጥ አይደለም፡፡ ጋዜጠኝነትም በተንኮል ያልታጠፈ፣ በምቀኝነት ያልተቆለመመ፣ በራስወዳድነት ያልተንጋደደ ተግባርና ምግባር ይጠይቃል፡፡ መማር እና እውቀትን መጨበጥ የግድ ይላል፡፡
ከዚህ በተቃርኖ አሁን አሁን በዩቲዩቡ መናገር የህልውናቸው ምስክር ወይም ማረጋገጫ አድርገው የሚወስዱና ካልተናገሩ የሌሉ የሚመስላቸው በርካታ ጋዜጠኞች ተፈልፍለዋል፡፡ መሰል ‹‹ጋዜጠኞች›› ‹‹እንዴት እንዲህ ይሆናል ሲሉ?›› እንዴት እንዲህ አይሆንም ለሚለው መልስ ቦታ የላቸውም፡፡ ሃሳብ፣ ተግባርን ህልማቸው ቡድናዊ፣ በደንብ ሲጠና ደግሞ ግላዊ ነው።
በአሠራሩም አንዱ ጋዜጠኛ ከሰለጠነበት ውጭ በማያውቀውና በማይረዳው መስክ፣ በሌላው የሥራ ዘርፍ ውስጥ ገብቶ አይዘባርቅም፤ አይፈተፍትም። ሙያው የራሱ የሆነ መስፈርትና መመዘኛዎች፣ ስነምግባርና ተአማኒነት (ethics and Integrity) አለው። ሜዳውም ከአንዱ ጠርዝ ወደሌላው ጠርዝ ተስፈንጥሮ ያሻን የሚዘላብድበት አይደለም።
ይሑንና በኢትዮጵያ ትላንት ስለ ምግብ ዝግጅት ፈትፍተው ሲተነትኑ የተመለከትንና ያደምጥናቸው ዛሬ በሚያስደንቅ ፍጥነት ማልያ ለውጠው ስለ ፖለቲካ ሲደሰኩሩ መታዘባችን ደግሞ የሙያው ክብር ጥልቅ ገደል ውስጥ እየገባ ስለመምጣቱ በቂ ምስክርነትን የሚሠጥ ነው።፡
አንድ መታወቅ ያለበት ሃቅ ቢኖር ታዋቂ ሁሉ አዋቂ አይደለም፡፡ እድል ገጥሞት አሊያም ነዋይ ስላለው ብቻ አንድ ስቱዲዮ ውስጥ የባጥ የቆጡና ማውራት፣ መዝለፍ እንዲሁም የሶሻል ሚዲያዎች እንግዳ ጋብዞ በዩቲዩብ መድረክ ሲሳደብ ዝም ብሎ አንገት እየነቀነቁ ማዳመጥ ጋዜጠኝነት አይደለም፡፡ ጋዜጠኛም አያስብልም፡፡
ለመሰል ‹‹ጋዜጠኞች›› መበራከት ምክንያቱ ብዙ ነው፡፡ ዋናው ግን /ሚዲያ ሊትሬሲ/ ወይንም የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መሠረታዊ እውቀታቸው ዝቅ ያለ፣ ስለተመለከቱትም ሆነ ስላደመጡት እንዲሁም ስላነበቡት ምንነቱን በቅጡ የማይረዱ፣ ብቻ በሩቁና በጭፍን የሚደመድሙ የመበራከት ውጤት ነው፡፡
እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ አይመዝኑም። አይመረምሩም፡፡ ፈትነው አያጣሩም፡፡ በትንሹ ተረድተው በትልቁ የሚፈርዱ ናቸው፡፡ ቀድሞ ባወቁት ወይም በተነገራቸው ልክ ለመደምደም የሚቸኩሉ፣ የተመለከቱትና ያደመጡትን ሁሉ የመጨረሻ ልክ አድርገው የሚቀበሉ ናቸው፡፡
ይሕ ሲባል ግን በእውቀቱ፣ በተግባሩም በምግባሩም አንቱ የተባሉ ድንቅ ሙያተኞችና ምስጉንና ጉምቱ አድማጭ ተመልካቾች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ይሕ እሳቤም ግዙፍ አላዋቂነት ነው፡፡ ይሑንና ከዚህ የተቃርኖ የሚሰለፉና ‹‹ጋዜጠኛ›› የሚል ማእረግ ለራሳቸው የሠጡ ግለሰቦች የኢትዮጵያ አሁናዊ አደጋ ስለ መሆናቸው እምነቴ የፀና ነው፡፡ ሁሉም እየተነሳ ‹‹ጋዜጠኛ›› የሚል ካባ የሚደርብ ከሆነ ከሁሉ በላይ ስለ ሚዲያ በቂ ግንዛቤ በሌለባት አገር መጪውን አሳሳቢ ያደርገዋል። በዚህ ከቀጠለም ሙያው ወደ ስርአተ ቀብሩ መጋዙ አይቀሬ ነው፡፡
በእርግጥ ችግሩ በፈጣን የችግር አፈታት ዘዴ«Quick fix» ሊፈታ እንደማይችል ይገባኛል። ይሁንና መፍትሄ የሌለው አንድም ችግር እንደሌለም ከሚያምኑት ወገን ነኝ። እናም አካሄዳችንና የምንሄድበት መንገድ፣ ሳንደርስም መድረሻችንን ያመላክታልና ቆም ብለን ብንናስብ መልካም ነው፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም