አላዋቂነት ጨካኝ ያደርጋል!

ከአንድ ወር በፊት አካባቢ ይመስለኛል። ላምበረት መናኸሪያ አካባቢ ቆሜ የሰርቪስ ትራንስፖርት እየጠበቅኩ ነው። ከአውቶቡስ መጠበቂያ ማረፊያው ላይ ቢጫ ፌስታል የያዙ አንድ ሦስት ሴቶች ተቀምጠዋል። ከኋላዬ አንድ በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው መጣ። ደላላ መሆኑ ነው። አንደኛዋ ልክ ስታየው ፌስታሏን አንጠልጥላ ቶሎ ወደ አጠገቡ ሄደች።

በግልምጫና በቁጣ ‹‹የታለ ተያዥሽ?›› አላት። እሷም በፍርሐት እና በመለማመጥ ገና ‹‹ማግኘቴን ስላላወቅኩ ነው፤ ቤቱን ልወቀውና….›› እያለች ስትለማመጥ አሁንም በቁጣ አቋረጣትና አምቧረቀባት። የቤት ሰራተኝነት ሥራ ፈልጋ መሰለኝ።

እንዲህ እየገላመጣት ሌላኛው ጓደኛው መጣና ‹‹ምን እያለች ነው? አለው። ‹‹ተዋት ባክህ!….›› እያለ አሁንም ያመናጭቃታል። ልጅቷ በጣም ጨንቋታል። ሁለቱ ሴቶች ግን ቁጭ ብለዋል። ምናልባት እኔ ከመድረሴ በፊት ከዚችኛዋ ጋር ተነጋግረው መሰለኝ። እንደዚሁ እያመናጨቃት ትቷት ሄደ።

ሰው የቱንስ ያህል መሃይም ቢሆን እንዴት ይሄ ይጠፋዋል? ሥራውን እና የምትሰራበትን ቤት ሳታገኝና ሳታውቀው እንዴት ተያዥ ይዛ ትዞራለች? ተያዥ የሚሆን ሰው መቼም ቢያንስ ሥራ ያለው ሰው ነው። በሥራ ቀን እንዴት እሷን ተከትሎ ይዞራል? ሰውየው እኮ ሰው እንጂ ዕቃ አይደለም! ተያዥ የሚያስፈልገው ሥራው ከተገኘ በኋላ አይደለም ወይ?

ቤቱን ልወቀውና እያለችው ነው እየገላመጠ ትቷት ሄደው። መጀመሪያውኑስ ከሌለው ‹‹የለኝም!›› ቢላት ምን ነበር? ጤነኛ ሆኖ ቆሞ የሚሄድ ሰው እንዴት ይሄ ይጠፋዋል?

በዚህ እየተገረምኩ ሳለ ባለፈው አርብ ደግሞ ከዚህ የባሰ የሚያስገርም ነገር አጋጠመኝ። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሰራተኞች መዝናኛ ክበብ ውስጥ ነው። ከመግቢያው ጥግ ላይ ተቀምጫለሁ። አንድ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ዬ አንዲት ፌስታል ያንጠለጠለች ልጅ ይዞ መጣ። በሩ አካባቢ ያለው የካፌው ጫፍ ላይ ሲደርስ በቁጣ ቃላት ‹‹ሂጂ ግቢና እዚያ ቁጭ በይ!›› አላት። ልጁ ወይም የቅርብ ቤተሰቡ ልትሆን ትችላለች በሚል ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም።

እሱ በቁጣ ‹‹ሂጂ ቁጭ በይ!›› ሲላት እሷ ደግሞ ግራ ገብቷት ቆማለች። እንደምንም እየተቆጣና እየገፋፋ አስገብቶ አስቀመጣት። ከዚያ መለስ ብሎ በሩ አካባቢ ሲደርስ እየሳቀና በከፍተኛ ምፀት ‹‹ደስ ያለሽን እዘዢ፣ እኔ እከፍላለሁ!›› አላት። እሷ መልስ አትሰጠውም። ልክ ያልሆነ ነገር እንዳለ ተጠራጠርኩ።

ልጅቷን እንዲህ ብሎ ሲወጣ አንደኛው የካፌው አስተናጋጅ አየውና ሰላም ተባባሉ። ይተዋወቃሉ ማለት ነው። የዚያው አካባቢ ሰው ቢሆን ነው ብዬ አሁንም ብዙ ትኩረት ሳልሰጠው ተውኩት።

ከሰዓታት ቆይታ በኋላ ከአንድ ባልደረባዬ ጋር ሻይ ልንጠጣ ድጋሚ ስንሄድ ያቺ ልጅ እዚያው ቦታ ላይ አለች። ለባልደረባዬ አስተውየው የነበረውን ነገር ነገርኩት። ወዲያውኑ ጥሏት የሄደውን ሰውዬ ሰላም ሲለው የነበረውን አስተናጋጅ ጠራሁት። ልጅቷ ምን ሆና ነው? ብዬ ስጠይቀው ሙሉ ዝርዝሩን ነገረኝ።

ሰውየው ደላላ ነበር። ልጅቷን ሥራ አገኝልሻለሁ፤ የተረጋገጠ ነው አለኝ ብሎ ብር ተቀብሏታል። ብሩን ተቀብሎ ‹‹እዚህ ጠብቂኝ አሁኑ መጣሁ›› ብሏት ነው የሄደው። ስልኩንም ስትደውል አጥፍቶታል። ልጅቷ ያላትን ብር ሁሉ ለእሱ ሰጥታ ባዶዋን ናት። ይህን ሁሉ ለአስተናጋጁ የነገረችው በኋላ ነው። ይህን ያደረጋት ሰውዬ ግን ከእሷ የተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ ነው ያለው። ምን ያህል መሃይምና ጨካኝ ቢሆን ይሆን?

በእንዲህ አይነት ደላሎች ላይ በተደጋጋሚ የቅሬታ ዘገባዎች ሲሰሩ ይታያል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሰራው ዘገባ ነበር። ሪፖርተሩ ሥራ ፈላጊ መስሎ ነው ለአገናኝ ኤጄንሲዎች የደወለላቸው። ምን ያህል ራሳቸውን በድብቅና በጥንቃቄ እንደሚያንቀሳቅሱ ያስታውቅ ነበር። አድራሻቸውን በትክክልና በግልጽ አይናገሩም። እነዚህ ኤጄንሲዎችና ደላሎች አያስቀጥሩም፤ ሥራቸው ማጭበርበር ነው። ከሥራ ፈላጊዎች ገንዘብ የሚቀበሉት ከመቀጠራቸው በፊት ነው፤ ምክንያቱም እንደማይቀጠሩ ያውቁታል።

ማጭበርበር ያለ ነው እንበል፤ ቢያንስ ግን በዚህ ልክ እንዴት ህሊና ይፈቅዳል? ምንም እንኳን የስርቆትና የማጭበርበር ትንሽ ባይኖረውም ቢያንስ ግን የሚበላው ካጣ ሰው ላይ እንዴት ይዘረፋል? መንግሥት እንዲህ አይነት አጭበርባሪዎችን ሥራዬ ብሎ በመከታተል መቀጣጫ ሊያደርግ ይገባል!

ከድህነት በላይ ችግራችን አለመሰልጠን ነው። በእርግጥ የድህነታችንም ምክንያቱ አለመሰልጠን ነው። ሲባል እንደምንሰማው በበለፀጉት ሀገራት አስተናጋጅ የሌለበት ካፌና የገበያ ቦታ ሁሉ አለ። ማንም ደንበኛ የተጠቀመበትን አስቀምጦ ይሄዳል። ይህን ነገር አንዳንድ ሰዎች ‹‹እነርሱ ሁሉ ነገር የተሟላላቸው ስለሆኑ ነው›› ይሉ ይሆናል። የተሟላላቸው ግን ከቁስ ይልቅ አዕምሯቸው ነው። የሰለጠኑት ሀገራት ውስጥ የመጨረሻ ድሃ የሚባለው ራሱ ሳይከፍል ሊሄድ አይችልም።

ንፅፅሩን በራሳችን ሀገር ሁኔታዎች ማየት እንችላለን። የጽዳት ሥራ የሚሰሩ ሰዎች በሺዎች የሚቆጠር የታሰረ ብር አግኝተው አስረከቡ ሲባል በዜናዎች በተደጋጋሚ ሰምተናል። የእነዚህ ሰዎች ኑሮ ከአገናኝ ኤጄንሲዎች በታች እንደሚሆን ይገመታል። ዳሩ ግን እምነት አላቸው፤ ህሊና አላቸው። በተዘረፈ ገንዘብ የሚበላ ነገር አይጣፍጣቸውም። ያንን ገንዘብ ቢወስዱት ምን ያህል እንደሚጠቅማቸው ያውቃሉ።

ህሊና ሲጠፋ ግን ይሉኝታ ቢስና ሀፍረተ ቢስ ያደርጋል፤ ነውረኛ ያደርጋል። ለዚህም ነው በተለያዩ ወንጀሎች እየተያዙ የሚታሰሩት። ህሊናቸው ብቻ ሳይሆን አካላቸውም እስረኛ ሆኖ ይኖራሉ።

የድለላ ሥራ አስፈላጊ በመሆኑ አምናለሁ። ሥራ ፈላጊዎችም ሆኑ ዕቃና ቤት ገዥዎች የሚፈልጉት ነገር የት እንዳለ አያውቁም። ደላላ ያንን በማቀላጠፍ ሥራ ያቀላል። ውጣ ውረድን ይቀንሳል። ይህ ዘመናዊነት ነው። ዳሩ ግን ማጭበርበርና ዘረፋ ሲሆን ኋላቀርነት ነው።

በጎ ሰው ለመሆን ምንም አይነት ወጪ አይጠይቅም። የተቸገረን ሰው ለመርዳት የገንዘብ አቅም ያስፈልግ ይሆናል። ቢያንስ ግን የተቸገረን ሰው አለማጭበርበር በራሱ ደግሞ በጎነት ነው። የማይሆን ነገር አድርጉ ማለት አረመኔነት ነው።

እስኪ ያ ደላላ ያቺን ልጅ ሥራውን ሳታገኝና የምትቀጠርበትን ቤት ሳታውቀው ተያዡን የት ብላ ነበር የምታመጠው? ከዚህ ሁሉ ሥራ የለም፤ አላገኘሁም ቢላት ምን ችግር አለው?

የሰዎች ግላዊ ባህሪ አንድ አይነት ይሁን ማለት አይቻልም። ባህሪያችን እንደየመልካችን ይለያያል። ዳሩ ግን ሌሎችን የሚረብሽ ነገር፣ ሌሎችን ጉዳት ላይ የሚጥል ነገር ማድረግ ደግሞ በህሊና ብቻ ሳይሆን በህግም ወንጀል ነው። መሰልጠን እኩል ባያደርገን እንኳን ህግ እኩል ያደርገናል። የሰው ልጅ ሥልጣኔ ደግሞ ለህግና መርህ ተገዢ መሆን ነው።

ስለዚህ ለህግም ለህሊናችንም ተገዢ እንሁን!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 12/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *