የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ፣ ለአሽከርካሪም ሆነ ለእግረኛ እምብዛም ምቹ አይደለችም። የአሽከርካሪም ሆነ የእግረኛ መንገድ በብዛትም በጥራትም የሌላት ከመሆኑ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት በየተሽከርካሪ መንገዱ እየተፈጠረ ያለው መጨናነቅ ምጥ እንደያዛት ሴት እያስጨነቃት ይገኛል።
ይህን ችግር ለመሸሽ የከተማዋ ነዋሪዎች በተሽከርካሪ ከመጓዝ ይልቅ በእግር መሄድ ምርጫቸው ቢያደርጉም ለዛ የሚሆን ምቹ ሁኔታ የለም። በእግር መጓዝ ተገቢና የሚደገፍ ቢሆንም ለእግረኛ ምቹ መንገድ ካለመኖሩ በተጨማሪ፤ ከሥራ ወጥቶ ከአንዱ የከተማዋ ጫፍ እስከሌላኛው የከተማ ጫፍ በእግር መጓዝ የሚታሰብ አይደለም።
ምንም እንኳ የመንገድ መጨናነቅ ችግር ከተሽከርካሪ ቁጥር መጨመር ጋር የተገናኘ ቢሆንም፤ በዋናነት የሚጠቀሰው የተሽከርካሪ ቁጥር ብዛት ሳይሆን በቂ የመንገድ ግንባታ አለመኖር እንደመነሻ ምክንያት እየተጠቀሰ ነው። ይህ የሚባለው ጎረቤት ሀገር በሆነችው በኬንያ ዋና ከተማ በናይሮቢ ያለው የመኪና ቁጥር በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ካለው የመኪና ቁጥር እና ከሌሎችም ከተሞች ጋር በማነፃፀር ነው።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ የተለያዩ የመንገድ ግንባታዎች በዕቅድ ተዘጋጅተው ግንባታቸውን ለማከናወን ጥረት ተደርጓል። ይሁንና በዲዛይን ክለሳ፣ በወሰን ማስከበር ችግር፣ በፋይናንስ እጥረት እና በሌሎችም የተለያዩ ምክንያቶች በተያዘላቸው ጊዜ የሚጠናቀቁበት ሁኔታ እጅግ አናሳ ነው። ነገር ግን ዘግይተውም ቢሆን የሚጠናቀቁበት ሁኔታ ስለመኖሩ አይካድም። በተቃራኒው አንዳንድ መንገዶች ደግሞ በዕቅድ ውስጥ ስለመካተታቸው፣ ዲዛይናቸው ስለማለቁ እና በጀትም የተያዘላቸው መሆኑ ይገለጻል፤ ይሁንና ግንባታቸው መጠናቀቁ ቀርቶ መጀመራቸውም ህልም እንደሆነ ዘመናት ያልፋሉ።
እነዚህ የታቀዱ መንገዶች ወደ ግንባታ የተገባባቸው አለመሆኑ ደግሞ የከተማዋን የመንገድ ችግር የበለጠ ጎልቶ እንዲታይ ምክንያት ይሆናሉ። ታስበው እና ታቅደው ዘመናትን በማስቆጠር ወደ ግንባታ ካልተገባባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንደኛው ከአዲሱ ገበያ የሚነሳው የቀለበት መንገድ ነው። ይህ የቀለበት መንገድ ከአዲሱ ገበያ በመጀመር በቀጨኔ አልፎ፤ በሽሮ ሜዳ አድርጎ፤ በፈረንሳይ ሌጋሴዮን እና በቤላ አቆራርጦ መገናኛ ተርሚናል ካለው የቀለበት መንገድ መነሻ ጋር የሚገጥም ነው። ይህ መንገድ ስለመኖሩ መነገር ከጀመረ ሁለት አስርት ዓመታት ቢቆጠሩም አሁንም የጅማሮ ምልክት እየታየበት አይደለም።
አጠቃላይ የከተማዋ የቀለበት መንገድ በ1991 ዓ.ም. ተጀምሮ ከላይ የተጠቀሰው የተወሰነው ቀርቶ በከፊል ተጠናቅቆ ክፍት ቢሆንም፤ በተቃራኒው ከፊሉ መንገድ ግን ግንባታው ባለመጠናቀቁ የታሰበውን ውጤት ሙሉ ለሙሉ ማምጣት አልተቻለም። የእዚህ የመንገድ ግንባታ ጉዳይ ሲነሳ፤ የአዲስ አበባን መንገዶች የትራፊክ መጨናነቅን ከማስተንፈስ በተጨማሪ ለሥራ ዕድል ፈጠራም የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ ብዙ ጥናት ማካሄድ ሳያስፈልግ የተወሰኑ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን በማገላበጥ ምላሽ ማግኘት ይቻላል።
የሥራ ዕድል መፍጠሩን በተመለከተ ለይደር እናቆየውና በዋናነት የቀለበት መንገድ ስለመቆሙ የቀረበ ቅሬታ ላይ እናተኩር። የውጭ ምንዛሪ ከብር ጋር የነበረው ልዩነት መስፋትና እጥረት፣ ባለፉት ዓመታት በነበሩ የግንባታ ግብዓቶች ላይ በታዩ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪዎች ሳቢያ እንዲሁም በከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ምክንያት ወይም በሌሎች የተለያዩ ሰበቦች ለምን የቀለበት መንገድ ግንባታ ቆመ? የሚል ቅሬታ ዝግጅት ክፍላችን ድረስ መጥቷል።
የቅሬታው ፍሬ ነገር
አቤቱታ አቅራቢው ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ያመጣቸው የአዲስ አበባ የቀለበት መንገድ ጉዳይ ነው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የወቅቱ የአዲስ አበባ ከንቲባ በአምባሳደር ኩማ ደመቅሳ ከዊንጌት አዲሱ ገበያ የተገነባው መንገድ በሚያዚያ 2004 ዓ.ም ተመርቋል። በመንገዱ ምረቃ ቀን ‹‹በዚሁ አይቆምም፤ መንገዱ ይቀጥላል፤›› በማለት ቃል ተገብቶም ነበር።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ለመንገዱ ግንባታ ‹አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ተመድቧል።› ተብሎም ነበር። እያንዳንዱ መንገዱ የሚነካው ይዞታ የሚፈርስ መሆኑን ለማመልከት በየአጥሩ የኤክስ ምልክት ተደርጓል። ግምት የሚሰጥ መሆኑ ተጠቅሶ፤ መለስ ፋውንዴሽን አካባቢ ምትክ ቦታ ይሰጣችኋል ተብለው ቦታውን በግላቸው ሔደው አይተዋል። ነገር ግን ቀን ቀንን እየተካ ወራት አልፈው ዓመታት ቢቆጠሩም የመንገዱ ጉዳይ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል።
አቤቱታ አቅራቢው ቤታቸው አዲሱ ገበያ ማርቆስ መጋዘን አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአዲሱ ገበያ ጀምሮ በስጋ ቤቶቹ መደዳ ወደ ቀጨኔ መንገዱ እስከ አሁን ባለመስፋቱ ብዙ አደጋ እየደረሰ ነው። ደጃፋቸው ላይ ያለው መንገድ ጠባብ መሆኑን ተከትሎ፤ ከአንድም ሁለት ጊዜ ግቢያቸው ውስጥ መንገድ የሳቱ ሁለት መኪናዎች ገብተው አደጋ ሳይደርስባቸው ተርፈዋል።
እንደ አቶ ተገኑ ገለፃ፤ ከጎናቸው ወንዝ በመኖሩ፤ በሽታ እና በብርድ እየተሰቃዩ ነው። ከአካባቢው መኖሪያቸውን ሽጠው መኼድ ቢፈልጉም፤ የተገባውን ቃል ተስፋ አድርገው እስካሁኑ ቆይተዋል። አሁንም ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ቅሬታ ለማቅረብ የተገኙት ጉዳዩን አጣርቶ በቀጣይ የሚሆነውን እንዲያሳውቃቸው በማሰብ ነው።
ይህንን ሲሉ በተለያዩ ጊዜያት በየመገናኛ ብዙኃኑ በተለይም በዚሁ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እና በሪፖርተር ጋዜጣ ታትመው የወጡ ዘገባዎችን በእማኝነት በመጥቀስ ነው፤ ቅሬታ አቅራቢው፣ ግንባታው በእርግጥም ታቅዶ እንደነበር እና አሁን እየተገነባ አለመሆኑን በማብራራት ምላሽ ይሰጠን ይላሉ።
አቤቱታ አቅራቢው፣ ‹‹የቀለበት መንገዱ የዘገየበት ምክንያት በትክክል ይገለፅልን። መሠራት የሚገባው ነገር ለምን አልተሠራም? ›› ሲሉ ከጠየቁ በኋላ፤ ከመንገዶች ባለስልጣን የሚሰጠው መልስ እንደበፊቱ ድፍንፍን ያለ እና ግልፅነት የጎደለው መሆን የለበትም ይላሉ። ጨምረውም የተመደበው አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የት ገባ? የሚለው ላይ ምላሽ መሰጠት አለበት ይላሉ።
በ2010 ዓ.ም ይገነባል ተብሎ የሚፈርሱ ቤቶች ተለይተው ካርታ እና ሌሎችም ማስረጃዎች ያላቸው ነዋሪዎች ለክፍለ ከተማው አቅርቡ ተብለው ቢያቀርቡም፤ የመንገዱ ጉዳይ ተመልሶ ተቋርጧል። ማስረጃቸውን ያቀረቡ ነዋሪዎችም ሳይነሱ፤ ወይም ተረጋግተው እንኖራለን ብለው የሚፈልጉትን ግንባታ ሳያከናውኑ ዓመታትን ለማስቆጠር ተገደዋል።
ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ ብዙነሽ ተገኑም፤ የአካባቢው መንገድ ጉዳይ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ሲነገርለት የቆየ ቢሆንም፤ እስከ አሁን የተከናወነ ግንባታ የለም። የዚህን ምክንያት በተጨባጭ የሚያውቁ አለመሆኑን አስረድተዋል፤ ነገር ግን ከፋይናንስ እጥረት ጋር የተያያዘ መሆኑን በስሚ ስሚ ማወቃቸውን ገልፀዋል።
ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት፤ በአሁን ወቅት ከአዲሱ ገበያ መቀጠል ያለበት የቀለበት መንገድ ግንባታ ተቋርጦ ቦታው ትላልቅ ተሽከርካሪዎች የሚውሉበት እንዲሁም ልጆች ኳስ የሚጫወቱበት ብቻ ሳይሆን አልባሌ ተግባራትም የሚፈፀምበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንንም የሚመለከተው አካል ሊያውቀው ይገባል ብለዋል። መንገዱ ቢቀጥል የከተማውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ችግር ያቃልላል የሚል እምነት እንዳላቸው እና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለመንገዱ ትኩረት እንዲሰጥ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
አቤቱታውን ተከትለን በተለያዩ ጊዜያት የአዲሱ ገበያ የቀለበት መንገድ ግንባታን በተመለከተ ለማጣራት ባደረግነው ሙከራ የተለያዩ ዘገባዎችን አግኝተናል። ከዚህም ውስጥ አንዱ ዘገባ እ.ኤ.አ. በየካቲት ወር 2014 በታተመው በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያገኘነው ሲሆን፣ በጋዜጣው ላይም የሰፈረው ለቀለበት መንገድ ግንባታ ባለይዞታዎች ንብረቶቻቸውን በሦስት ወራት እንዲያነሱ ትዕዛዝ መሰጠቱን በተመለከተ እና ግንባታው ሊካሔድ መሆኑ ነው። ይህ መረጃ ከአስር ዓመት በፊት የተዘገበ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ዝግጅት ክፍሉ ያጣራቸው በወቅቱ የተካሔዱ ዘገባዎች
‹በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ባለቤትነት እየተገነባ ለሚገኘው የቀለበት መንገድ ቀሪውን የመጨረሻ ምዕራፍ ግንባታ ለመጀመር፣ ከአዲሱ ገበያ እስከ መገናኛ ድረስ ለሚገኙ ነዋሪዎችና ድርጅቶች ንብረቶቻቸውን እንዲያነሱ የከተማው አስተዳደር ትዕዛዝ አስተላለፈ› የሚለው ዘገባ ተሠራጭቷል። መንገዱ ያልፍባቸዋል ተብሎ ከታቀዱ አካባቢዎች ውስጥ በከተማው ከፍተኛ የንግድ ሥራ የሚካሄድበት አንጋፋው የሽሮ ሜዳ የባህል ልብስ ማምረቻና መሸጫ የሆነው የገበያ ማዕከል አንዱ መሆኑ በዘገባው ተብራርቷል።
ከዊንጌት አዲሱ ገበያ ያለው የቀለበት መንገድ አዲሱ ገበያ አካባቢ
ነጋዴዎቹ፣ የአስተዳደሩ አካላት ንብረታቸውን በማንሳት እንዲተባበሩ ጥሪ ማድረጋቸውን እና በሽሮ ሜዳ የገበያ ማዕከል ውስጥ በንግድ ሥራ የተሰማሩ ነጋዴዎች ለሪፖርተር ሃሳባቸውን እንዳካፈሉ የተዘገበ ሲሆን፤ በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት የወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ወርቅነህ፣ አካባቢውን ማፅዳት የመንግሥት ሥራ በመሆኑ በተለይ የአስተዳደሩ የመሬት ጉዳይ ኃላፊን እንደሚመለከት፣ ነገር ግን የዲዛይንና የሰርቬይ ሥራው ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ሥራው በሦስት ወራት ውስጥ ይጀመራል የሚል እምነት እንደሌላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል ተብሎ በጋዜጣው ታትሟል።
የቀለበት መንገዱ ግንባታ በ1991 ዓ.ም. ተጀምሮ የተወሰነው ክፍል ቢጠናቀቅም፤ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው በ1995 ዓ.ም. እንደነበር ተጠቅሷል። ነገር ግን በ1995 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የተነገረለት ይህ መንገድ ከታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ በአሥር ዓመታት የዘገየ መሆኑን እና ለዚህም የመንገድ መዘግየት የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ሲጠቅስ እንደነበረ መዘገቡ ይታወሳል ተብሏል።
ከወሰን ማስከበር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች፣ የውሃ፣ የቴሌና የኤሌክትሪክ ኃይል መስመሮችና የበጀት አለመሟላት የመሳሰሉት ምክንያቶች ለግንባታው መዘግየት አስተዋጽኦ እንደነበራቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ የመጨረሻ ምዕራፍ ከአዲሱ ገበያ በመጀመር በቀጨኔ፣ በሽሮ ሜዳ፣ በፈረንሳይ ሌጋሴዮን ፣ በቤላ አድርጐ መገናኛ ተርሚናል ካለው የቀለበት መንገድ መነሻ ጋር የሚገጥም መሆኑ ተዘግቧል።
የቀለበት መንገዱን በተቋራጭነት ግንባታውን እያከናወነ የነበረው የቻይናው ሲ.አር.ቢ.ሲ ኩባንያ መሆኑ እና በወቅቱ ለግንባታው የተበጀተው ወደ 780 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ነበር። ነገር ግን ግንባታው ለረጅም ዓመታት ከመጓተቱ ጋር ተያይዞ የግንባታ መሣሪያዎችና የግብዓት ዋጋ፣ የባለሙያ ክፍያና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎች በመጨመራቸው፣ አጠቃላይ በጀቱ ወደ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንዳሻቀበ ተጠቁሟል ተብሎም ነበር።
ከከተማው የቀለበት መንገድ ውስጥ 37 ኪሎ ሜትር ተጠናቅቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑ፤ በጊዜው ባስቆጠራቸው አሥራ አራት ዓመታት ውስጥ 37 ኪሎ ሜትሩን የቀለበት መንገድ ገንብቶ ለመጨረስ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የወጣ፣ ቀሪውንና የመጨረሻውን ምዕራፍ ለማጠናቀቅ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መመደቡ ታውቋል።
በሌላ በኩል በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም በተመሳሳይ መልኩ መንገዱን የተመለከተ ዘገባ ለንባብ በቅቷል። ‹የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር ፈቺ ማን ነው?› በሚል ጠያቂ ርዕስ በተፃፈው አጀንዳ በተመሳሳይ መልኩ የቀለበት መንገዱ ስለመቆሙ፤ ነገር ግን ግንባታው ቢቀጥል የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር በዋናነት የመንገድ መጨናነቅን ሊቀንስ እንደሚችል ተብራርቷል።
ሌሎችም የተለያዩ ከአዲስ አበባ የቀለበት መንገድ ጋር የተያያዙ ዘገባዎች የተላለፉ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ ያሰበውን ሥራ ዳር ለማድረስ ግን እንቅፋት እየሆኑ ናቸው የሚላቸው የመንገዶች ወሰን ማስከበር፣ የግንባታ ቁሶች መጥፋትና በማያቋርጥ ሁኔታ የተከሰተው የዋጋ ንረት፣ እንደችግር ተቀምጧል።
አቤቱታ አቅራቢው እነዚህን እና ሌሎችም ዘገባዎችን መነሻ በማድረግ የቀለበት መንገዱን የመጨረሻውን ምዕራፍ ለማጠናቀቅ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መመደቡ ተገልጿል። ይህ ገንዘብ የት ገባ? የሚለውን እና ሌሎችም ተያያዥ ጥያቄዎችን በቀጥታ ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ጠይቁልን ሲሉ በቃል እና በፅሁፍ አቤቱታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን አቅርበዋል።
የቀረበውን አቤቱታ መሠረት በማድረግ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምላሽ ይስጠን ስንል ለባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ለአቶ እያሱ ጥያቄዎቹን ይዘን ቀርበናል።
የቀለበት መንገድ ግንባታ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደው መቼ ነበር? እስከ አሁን ግንባታው ያልተጀመረው ለምንድን ነው? የተያዘው በጀት የት ደረሰ? ከአዲሱ ገበያ መገናኛ የሚደርሰው የቀለበት መንገድ ግንባታው የሚጀምረው መቼ ነው? ተነሺዎች ተነግሯቸው ምትክ ቦታ ከተዘጋጀ በኋላ ለምን አልተሰጣቸውም? የሚሉ እና የተያያዙ ጥያቄዎችን ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አቅርበን ምላሻቸውን ሰጥተውናል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ምላሽ
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን በሰጡን ምላሽ እንዳስረዱት፤ በእርግጥ በአዲስ አበባ የውስጠኛው የቀለበት መንገድ ተብሎ የሚጠራው የመንገድ ክፍል መገንባት ከጀመረ እጅግ በጣም ረዘም ያለ ጊዜ ምናልባትም ሁለት አስርት ዓመታትን አስቆጥሯል። እስከ አሁን ድረስ ወደ 37 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገዱ ክፍል በሶስት ምዕራፍ የተገነባ ሲሆን፣ የቀለበት መንገዱ መጠሪያው እንደሚያመለክተው ክብ ቅርፅ እንዲኖረው ተደርጎ በከተማዋ ያለውን መንገድ በኔትወርክ ማገናኘት ነው። ከዚህ አንፃር እስካሁን ባለው ሂደት 37 ኪሎ ሜትር የሚሆነው መንገድ ተገንብቷል።
አሁን ላይ እንደቀለበት መንገድ መገናኘት ያለበት ከፅዮን ሆቴል አካባቢ ካለው የቀለበት መዳረሻ መንገድ ተነስቶ እስከ የመገናኛው ዳያስፖራ መንገድ ድረስ ያለውን ክልል ያካትታል ተብሎ ታስቦ ነበር። ነገር ግን የቀረው የመንገድ ክፍል አጠቃላይ የቦታ አቀማመጥ ሲታይ ተራራማ በመሆኑ እና ከዛም በተጨማሪ በርካታ ትላልቅ ድልድዮችን እና መሻገሪያዎችን የሚጠይቅ በመሆኑ ከዛ አንፃር ከፍተኛ ወጪን እንደሚጠይቅ ለማወቅ መቻሉን ይናገራሉ። በዚህ ምክንያት መከናወን አልቻለም ይላሉ።
ከላይ የተጠቀሰው አንዱ ምክንያት መሆኑን በመጠቆም፤ ሌላኛው በየጊዜው የከተማዋ ማስተር ፕላን ከተማዋ በደረሰችበት ዕድገት ልክ ክለሳ የሚደረግ መሆኑን አስታውሰዋል። በመሆኑም ክለሳው ፀድቆ ተግባራዊ ተደርጓል። በአሁን ወቅት አስረኛው ማስተር ፕላን ፀድቆ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንና ከዚህ አንፃር መንገዱ በመጋጠሙ አጠቃላይ የከተማዋ የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ ምን የተሻለ ነገር ይፈጥራል? ምን ጉድለቶች ይኖሩበታል? የሚሉት ነገሮች ተካተው ጥናት እየተካሔደ መሆኑንም አመልክተዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኢያሱ እንደተናገሩት፤ የመንገድ ግንባታ የሚከናወነው በቅደም ተከተል ነው። ከፍተኛ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ባለባቸው ቦታዎች ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶ አዳዲስ የመንገድ ግንባታ ወይም የነባር መንገዶች ማሻሻያ ይከናወናል። ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ ዋናው የትኩረት አቅጣጫ ቀድመው የተጀመሩትን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት ነው።
በዋናነት ግን አሁን አቤቱታ በቀረበበት መስመር ከሁለት ሺ በላይ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች መነሳት ያለባቸው ሲሆን፣. ይህም ከፍተኛ ካሳ የሚጠይቅ ነው። በተጨማሪ ትልልቅ ድልድዮች እና ቀደም ብለው የተዘረጉ መሠረተ ልማቶች በመኖራቸው ወጪው ከፍተኛ ነው። ስለዚህ አንደኛው ትልቁ ነገር ግንባታውን ለማከናወን ወደ ፊት ከፍተኛ ገንዘብ ማፈላለግን መጠየቁ ነው ብለዋል።
መንገዱ ከፍተኛ የበጀት አቅምን ከመጠየቅ ባሻገር አሁን ላይ የኮንስትራክሽን ዋጋ እየጨመረ መምጣቱ እና ከማስተር ፕላኑ አንፃር ቀደም ሲል የነበሩ ነገሮች እየተከለሱ ናቸው፤ በመሆኑም ከትራፊክ ፍሰቱ አንፃር ያሉ ሁኔታዎችም ታሳቢ እየተደረጉ ቀጥለው ጊዜው ሲደርስ ይህ መንገድም ይገነባል ብለዋል። ሁሉም ቦታ ላይ የመንገድ ግንባታው ያስፈልጋል። ነገር ግን የትኞቹ ቦታዎች ላይ ቅድሚያ መሰጠት አለበት የሚለውን ማየት ደግሞ የግድ መሆኑን አስረድተዋል።
በወቅቱ ከተላለፈው ዘገባ እና አቤቱታ አቅራቢው ያነሱት ቅሬታ ላይ በመመስረት በጊዜው ተመድቦ የነበረው በጀት የት ደረሰ? እንዲያውም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተበጅቶ እንደነበር መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በወቅቱ ከነበረው በጀት አመዳደብ አንፃር ይህን ያህል በጀት ተመድቦ ነበር የሚለውን ማጣራት ያስፈልጋል ብለዋል። አሁን ይህን ያህል በጀት ተመድቧል ለማለት እንደሚያዳግታቸው አመላክተዋል።
በዋናነት ግን መያዝ ያለበት መንገድ የሚገነባው የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ቀልጣፋ ለማድረግ መሆኑን በመጠቆም፤ አሁን የተጀመሩትን ለማጠናቀቅ ቅድሚያ እንደሚሰጥ እና ወደፊት ግን ገንዘቡ በተገኘ ጊዜ ሥራ ላይ ባለው በማስተር ፕላኑ መሠረት ቀሪው የመንገድ ግንባታ የሚከናወን ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። ይህንንም ጊዜው ሲደርስ ይፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ግንባታውን ለማከናወን ምን ያህል ሰው ከቦታው ላይ ይነሳል? የሚለው ጥናት ሊደረግ የሚችል መሆኑን አስታውሰው፤ ወደ ማስነሳት የሚደረሰው በባለስልጣኑ ፕሮጀክቱ ተዘጋጅቶ እና በፕላን ኮሚሽን ፀድቆ ወደ ትግበራ ሊገባ ሲል መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም ለክፍለ ከተማዎች የመሬት ልማት ማኔጅመንት መረጃው ተልኮ ግምቱ ተሰልቶ ሲቀርብ ግምቱ ተሰጥቷቸው ይነሳሉ። ከዚህ ውጪ ምናልባት የሃሳቡ አቅራቢ በሃሳብ ደረጃ ምን ያህል ተነሺዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ጥናት ሲካሄድ ከነበረው መረጃ ተነስተው ጉዳዩን አንስተዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በተረፈ በጀት ተይዞ ግንባታ ባይከናወንም ወደ ሌላ የማዘዋወር ሁኔታ መኖሩ በየትኛውም ተቋም የተለመደ አሰራር መሆኑን በማስታወስ፤ ቅድሚያ ማግኘት ሲኖርበት እና ገንዘቡ እንደተገኘ በፕላን ኮሚሽን በማፀደቅ ግንባታው እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2015