«ራዕያችን ከሲዳማ አልፈን ኢትዮጵያን ማበልጸግ ነው» አቶ ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

የሀገሪቱ 10ኛ ክልል ሆኖ ከሶስት ዓመት በፊት ራሱን በራሱ ማስተዳደር የጀመረው የሲዳማ ክልል የሶስተኛ ዓመት የክልል ምስረታ ቀንን ከሰሞኑን በደማቅ ሥነ ሥርዓት በሃዋሳ ከተማ አክብሯል፡፡ ይህ ክልል በሶስት ዓመት ጉዞው ሕዝቡ የታገለለት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ከማሳካት አኳያ ምን ሰራ፤ በቀጣይስ ምን ታቅዷል የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎችን በመያዝ አዲስ ዘመን የሁልጊዜ ተባባሪው ከሆኑት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከአቶ ደስታ ሌዳሞ ጋር ቃለ ምልልስ አካሒዶ ተከታዩን አጠናቅሯል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- ሲዳማ ክልል ከሆነ ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል፤ በእነዚህ ዓመታት የተገኙት ትሩፋቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ደስታ፡– መልካም ነው፤ አስቀድሜ ግን መላው የክልላችን ነዋሪዎችን እንኳን ለሶስተኛው ዓመት የክልል ምስረታ ጊዜ አደራሳችሁ ልላቸው እወዳለሁ፡፡ ሲዳማ ክልል ከሆነ ሶስት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ስኬትም ድክመትም መኖሩን እውን ነው፡፡ ሕዝቡ ክልል ለመሆን ሲታገል የቆየው ሁለት መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን በማንገብ ነው፡፡ አንደኛው ፖለቲካዊ የሆነና የመታወቅ ፍላጎት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ኢኮኖሚያዊ መሻሻሎችን በመሻት ነው፡፡

ለምሳሌ ፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸውን ጉዳዮች ያነሳን እንደሆነ በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ ሲዳማ በከፍተኛ ደረጃ የታወቀባቸው ወቅት ነው፡፡ በተለያዩ አውዶች ተሳትፎውም ሆነ አስተዋጽኦው ያደገበት፣ ስሙ በተደጋጋሚ የተጠራበት ነው፡፡ በሶስቱ ዓመታት በክልሉም ሆነ በተለያዩ ሀገራዊ መድረኮች ራሱን ያየበትም ጊዜ ነው፡፡ በተለይም የሲዳማ ባህሉ፣ ማንነቱና እሴቱ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ድረስ የታወቀበትም ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ይህ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ሲዳማ ከደቡብ ክልል ጋር ስለነበር ሀገራዊ በሆኑ መድረኮች ላይ ራሱን ሆኖ ሳይሆን የሚንቀሳቀሰው በደቡብ ክልል ውስጥ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ ጎልቶ መውጣት አልሆነለትም ነበር፡፡ አሁን ግን ሲዳማ ፖለቲካዊ ጥያቄው በምልዑነት በመመለሱ ደስተኛ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ በክልሉ ውስጥ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡

ሁለተኛው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሲሆን፣ በተለይ ጎልተው ከመጡ የሕዝብ ጥያቄዎች መካከል የመጀመሪያው የመንገድ ይሰራልን ጥያቄ ሲሆን፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ድግሞ በሁለተኛ ደረጃ የተነሳ ጥያቄ ነው፡፡ ከእነዚህ ሁለቱ በተጨማሪ የመብራት፣ የጤና ተቋማት ማጠናከር ላይና የውስጥ ግብዓት ይሟላልኝ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ይገንቡልን የሚለው ተከታትለው ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በከተማ አካባቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በተለይ ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች በተከታታይ ያነሳ ነበር።

ሆኖም ሁሉንም ጥያቄዎች በአንድ ጀምበር መመለስ ስለማይቻል ቅድሚያ እንዲመለሱለት በሚፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ በማተኮር ባለፉት ሶስት ዓመታት ስንሰራ ቆይተናል፡፡ በተለይ የመጀመሪያው ጥያቄ መንገድ በመሆኑ ሽፋኑን ለማሳደግ በየአቅጣጫው ክረምት ከበጋ የሚያስገቡ መንገዶች በመሠራታቸው በአሁኑ ወቅት በሁሉም አቅጣጫ ከቀበሌ ቀበሌ የሚያገናኝ መንገድ ተከፍቷል፡፡ ከዚህም የተነሳ የመንገድ ሽፋኑ በአጠቃላይ 85 በመቶ መድረስ ችሏል፡፡ ከአንድ ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ሕዝቡ ወደዋና መንገድ መውጣት ችሏል፡፡

ሁለተኛው ጥያቄ የንጹህ መጠጥ ውሃ በመሆኑ ያገኘነው በጀት በጣም ውስን ቢሆንም፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃን በተመለከተ እንዲሁ ሕዝቡን ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ሥንሰራ ቆይተናል፡፡ በዚህም በ2013 ዓ.ም ክልል ሆነን ስንመሰረት የመጠጥ ውሃ አማካይ የሲዳማ ሽፋን 38 በመቶ ያህል ብቻ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ የውሃ ተቋማትን ገንብተን ለአገልግሎት በማብቃታችን ሽፋኑ 55 በመቶ ማደግ ችሏል፡፡ በእርግጠኝነት ደግሞ ከውሃ ጋር ተያይዞ የያዝናቸው ፕሮጀክቶች ካለቁልን በ2016 በጀት ዓመት ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው ሽፋን ብንቀድም እንጂ የሚያንስ አይሆንም፡፡

ከጤናም ሆነ ከትምህርት ጋር በተያያዘ በትኩረት የሠራን ሲሆን፣ ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ሳምንት ውስጥ ካስመረቅናቸው ተቋማት ውስጥ ስምንት የጤና ጣቢያዎች ይገኙበታል፡፡ በሶስት ዓመታት ውስጥ 13 ጤና ጣቢያዎችንና ሁለት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን ገንብተናል፡፡ ሌሎች ማሻሻያ የሚደረግባቸውና በግንባታ ላይ ያሉ ሆስፒታሎች ደግሞ አሉ፡፡ ግዙፍ የሆነ የላቦራቶሪ ተቋምም ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ የማሻሻያውንም ጨምሮ አዳዲስ በጤናው ዘርፍ ከ30 በላይ የሚሆነውን ለአገልግሎት አብቅተናል፡፡ ፡

ከግንባታው ጎን ጎን የመድኃኒት ጉዳይ በሕዝብ ዘንድ የሚቀርብ ጥያቄ በመሆኑ በሶስቱም ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ሰላሳ ሚሊዮን ብር እየመደብን መድኃኒት እየገዛን ተደራሽ እንዲሆን አድርገናል። በክልላችን በቅርቡ ተመርቀው ወደሥራ ከገቡ ጋር ተያይዞ ወደ 15 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችና አምስት ጀነራል ሆስፒታሎች ሲኖሩ፣ ሃዋሳ ሪፈራል የሚባል ደግሞ በፌዴራል መንግሥት የሚተዳደር አንድ ሆስፒታል አለ፡፡ በጠቅላላ በክልል 21 ሆስፒታሎች ይገኛሉ፡፡ ጤና ጣቢያዎችን ስንመለከት 135 ሲሆኑ፣ 13 ጤና ጣቢያዎች ደግሞ እየተገነቡ ይገኛል፡፡

በእስካሁኑ በሶስት ዓመት ውስጥ በ90 ሚሊዮን ብር መድኃኒት የገዛን በመሆናችን ይህንኑ ለተወሰኑ ዓመታት በማስኬድ የራሱ የሆነ ፈንድ እንዲኖረው ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡ በዚህም በክልላችን የመድኃኒት ፈንድ የሚተዳደርበትንም ማኑዋል አዘጋጅተን በክልሉ የጤና ቢሮ አማካኝነት መመሪያ በማውጣት ሥርዓት እያበጀንለት ነው፡፡

ከዚሁ ከጤናው ዘርፍ ሳንወጣ በክልሉ ቀደም ሲል የዲያሊስስ አገልግሎት የሚሰጠው የግል ተቋም በሃዋሳ ያለ ሲሆን፣ እሱም ዋጋው ከፍ ያለ ነው፤ ይህን አገልግሎት ለመስጠት ይርጋለም ሆስፒታል ላይ ከሚያግዙን አካላት ጋር በመጻጻፍ ሰባት ማሽን ከውጭ ማስገባት ችለናል፡፡ በቅርቡም ወደሥራ ለማስገባት በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- የጠቃቀሷቸው የልማት ሥራዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወኗቸው ናቸው፤ በቀጣይስ የክልሉን ብልጽግና ለማረጋገጥ ያስቀመጣችሁት አቅጣጫ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ደስታ፡- በእኛ ክልል ተነጋግረንበት ብልጽግና የሚለውን ራሱ በሁለት ከፍለነዋል፡፡ አንደኛውን የጋራ ብልጽግና ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የቤተሰብ ብልጽግና ብለን ወስደነዋል፡፡ ብልጽግናን ማረጋገጥ የወቅቱ ተልዕኮ ነው፡፡ ዘመኑ ኢትዮጵያ በብልጽግና የምትጓዝበት ነው። ራዕያችን የበለጸገን ማኅበረሰብ በመገንባት ኢትዮጵያን ማበልጸግ ነው፡፡ የበለጸገ ማኅበረሰብ ማለት ደግሞ ይህን ሊተረጉመው የሚችለው የሕዝቡ የተሻሻለ የአኗኗር ዘይቤ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የቤተሰብን ብልጽግና ማረጋገጥ የሚቻለው እንዴት ነው?

አቶ ደስታ፡- በቤተሰብ ብልጽግና ላይ በእያንዳንዱ ቤት መንግሥት ገንዘብ አይልክም፡፡ ብልጽግናውን ሊያረጋግጥ የሚችለው የዛ ቤተሰብ ጠንካራ ሥራ ነው፡፡ የጋራ ብልጽግና በመንግሥት መሪነት የሚረጋገጥ ሲሆን፣ የቤተሰብ ብልጽግና ደግሞ በራሱ በባለቤቱ ነው፤ ይህም የአኗኗር ዘይቤው የሚወሰነው በገቢው መጠን ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ክልል በቤተሰብ ስላለው የአኗኗር ሁኔታ ጥናት አካሄድን፤ የጥናቱ ዋናው መነሻ ደግሞ የመኖሪያውን ሁኔታ፣ የአመጋገቡና ጠቅላላ እንቅስቃሴውን ያጠናው ቡድን ይዞ የተመለሰው ግኝት እንዳሳየን ከሆነ ፈጥኖ ውጤታማ የሆነው የጋራ ብልጽግና ነው እንጂ የቤተሰብ ብልጽግና እንዳለሆነ አሳይቶናል፡፡ በዚህም በተፈለገው ልክ መፍጠን አለመቻሉን አስተዋልን፡፡

በዚህ መቆም አልፈለግንም፤ የቤተሰብ ብልጽግና ያልፈጠነበትን ሁኔታ ማጥናት ቀጠልን፡፡ በመሆኑም የተለያዩ አጥኚ ቡድኖችን መልሰን አሰማራን፡፡ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መረጃን መሠረት ያደረገ ትንታኔ ተጠንቶ መጣ።

በጥናቱም (የከተማ ነዋሪው በተለያየ የቢስነስ እንቅስቃሴ ላይ መሰማራቱ እንደተጠበቀ ሆኖ) የመጣው ግኝት የሚያመለክተው የሲዳማ ማኅብረሰብ 80 በመቶ ያህሉ ኑሮውን ያደረገው በገጠሩ ክፍል ነው፡፡ ይህ ማለት የኑሮ መሠረቱ መሬት ነው ማለት ነው፡፡ በመሬት ላይ ሊመረት የሚችለው ደግሞ የግብርና እና የእንስሳት ርባታ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ በወቅቱ የብልጽግና ዋና መሠረቱ ሆኖ የመጣው መሬት ነው፡፡

መሬት ካለ ደግሞ ምርትና ምርታማነት የሚመጣው እንዴት ነው የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በገጠር የሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል የመሬት ይዞታው ምን ያህል ነው የሚለው ተጠንቶ ነበርና በጥናቱ የተገኘው ግኝት ግን ያመላከተን መሬት አለው ተብሎ ከተገመተው ሕዝብ 27 በመቶው ዜሮ ነጥብ 25 ሔክታር መሬት ብቻ ነው ነው። ስለሆነም በዚህ መሬት ሰርቶ ብልጽግናን ያመጣል ማለት ዘበት ሆኖ አገኘነው፡፡

እኛ ደግሞ የአኗኗር ዘይቤው የተሻሻለ እንዲሆን ስንጠብቅ የነበረው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለውን ሕዝብ ነው፡፡ ስለሆነም ሌላ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ተረዳን፡፡ ቀሪው ሕዝብ ደግሞ ያለው የመሬት መጠን ዜሮ ነጥብ አምስት ሔክታር ወይም ግማሽ ሔክታር መሬት ያለው ሆኖ አገኘነው፡፡ ይህ ማለት 49 በመቶ የሚያክለው ሕዝብ ያለው የመሬት መጠን ግማሽ ሔክታርና ከዛ በታች የሆነ ነው፡፡ በዚህ አነስተኛ መሬት ላይ የቱንም ያህል ታታሪ ብንሆን ብልጽግና ይሉት ነገር የማይታሰብ መሆኑን ተረዳን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለዚህ ያስቀመጣችሁት ሌላ የብልጽግና አማራጭ ይኖር ይሆን?

አቶ ደስታ፡- አማራጩ ሰፊ መሬት የማይፈልግ በትንሽ መሬት ላይ ሊሠራ የሚችል የእንስሳት አማራጭ ሲሆን፣ ይህም የብልጽግና መሠረት ሆኖ አገኘነው፡፡ ይህ እኛ ያሰብነው አሠራር ወደ ሱማሌ፣ አፋርና ቦረና አካባቢ ላለ ሃሳቡን እምብዛም ላይረዳ ይችላል፡፡ ምክንያቱም እነሱ አካባቢ የበለጸገ ሰው ብለው የሚያስቡት በመቶ የሚቆጠሩ ከብቶች ያለውን ነው፡፡ የእኛ አካሔድ ደግሞ ዝርያው የተሻሻለ ቁጥሩ ደግሞ ያልበዛ ላሞችን ማርባት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ለምሳሌ በጥናት የደረስንበት ግኝት እንዳሳየን ከሆነ አንድ አርሶ አደር ሶስት ላሞችን ለማሰር የሚያስችለው ቦታ ዘጠኝ ካሬ ሜትር ብቻ ነው፡፡ ከአንዷ ላም በቀን በአማካይ 15 ሊትር ወተት ቢገኝ ከሶስቱ 45 ሊትር በትንሹ ማግኘት እንደሚቻልም ተረዳን፡፡ በዚህ አጋጣሚ በመስክ ሥራ ላይ እየተንቀሳቀስኩ ባለበት ጊዜ ከጎበኘኋቸው የርባታ ቦታዎች አንዱ በሆነው በይርጋለም ከተማ አንዲት ላም በቀን 34 ሊትር ወተት ከመስጠቷ የተነሳ ስሟ ‹ጎርፌ› ተብሎ እስከመጠራት መድረሱን ለመረዳት ችያለሁ። ከ22 እስከ 26 ሊትር ድረስ የሚሰጡ ላሞችም በርካታ ናቸው። እንደተናገርኩት በክልላችን ሰፋፊ እርሻ ባለመኖሩ እንደሌላው ክልል የትራክተር ብዛት አላስፈለገንም፤ የእኛ ኩታ ገጠማችን ቡና ነው፡፡ ስለዚህ እንስሳት የሲዳማ ክልል ብልጽግና ነው የማለታችን ምስጢር አንዱ ይህ ነው፡፡

በዚህ አይነት አሠራር የእንስሳት ዝርያ በዓመት እንደ ክልል 75 ሺ የሚሆኑ ጥጆችን እንዲወለዱ 100 ሺ ላሞችን በማዳቀሉ ረገድ አቅድ ይዘን ሶስት ዓመት ሰርተናል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዚህ መልኩ ሰርተን ከ 71 ሺ እስከ 76 ሺ ጥጆችን ማግኘት ችለናል፡፡ ይሁንና ምንም እንኳ እኛ የምንፈልገው ሴት ጥጆችን ቢሆንም ሲወለዱ የነበረው ሴቶችም ወንዶችም ነበሩ፡፡ በዚህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግን ሴት ጥጆችን ብቻ እንዲወለዱ የሚያደርገውን ቴክኖሎጂ ተከትለን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

ከዚህ የተነሳ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ ዝርያቸው የተሻሻሉ ላሞች በ2014 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ላይ 326 ሺ ደርሰዋል፡፡ ይህን በ2015 በጀት ዓመት መጨረሻ 390 ሺ ለማድረስ ተሠርቷል፡፡ አጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ወደ ሁለት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን የቀንድ ከብት በክልላችን ይገኛሉ። ይህ ግን ቁጥር ብቻ በመሆኑ የምንፈልገው ዝርያቸው የተሻሻለና ምርታማ የሆኑ ወደ አንድ ሚሊዮን ላሞች ዝቅ ማድረግ ነው። በዚህ መሠረት እየሰራን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ ‹‹የጥጆች ቀን›› በሚል በተመሳሳይ ወቅት የተወለዱ ጥጆች በሙሉ ሌላውን ለማነሳሳትና ለማበረታታት ለኢግዚቢሽን ይወጣሉ፡፡ ይህ ልምምዳችን ሶስት ዓመትን አስቆጥሯል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በስድስት ካሬ ሜትር ላይ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑ ዶሮዎችን ማርባት እንደሚቻል አጥንተን ወደሥራ ገባን፡፡ በተለይ የዶሮዎችን ዝርያ በትኩረት ሰራንበት፡፡ ዝርያቸው የተሻሻሉ ዶሮዎች በዓመት ውስጥ ለ 300 ቀናት እንቁላል መጣል የሚችሉ ናቸው፡፡ እንቁላል ለመስጠት መኖ የሚፈልግ በመሆኑ የ 300 ግማሹን በአማካይ ያዝን። ስለዚህ የቤተሰብ ብልጽግና እንዲመጣ የተለየና ሰፊ የሆነ መሬት ስለማይፈልግ የተለየ ዘዴ ይዘን መጣን፡፡ በ2015 በጀት ዓመትም የአመራረት ዘዴውን ቀይረን ተግባራዊ አድርገናል፡፡

ይህም የሌማት ትሩፋቱን ሥራ ነው፡፡ ከሌማት ትሩፋቱ ደግሞ የመጀመሪያ የሆነው ዝርያቸው የተሻሻሉ እንስሳትን እያንዳንዱ ቤተሰብ ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው የዶሮ ልማትን፣ ሶስተኛው ደግሞ የንብ ማነቡን ሥራ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ዓሳ ላይም ውስን ጀምሮችን ሠርተን አይተናል፤ ሴቶች ደግሞ የሐር ትልን እንዲሁ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ዶሮን በተመለከተ ባለፈው በ2013 እና 2014 በአንድ ዓመት ብቻ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶሮዎችን ለአርሶ አደሩ አድርሰናል፡፡ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ደግሞ የመሬት ጥበት ላላቸው አራት ሚሊዮን ዶሮ እናሰራጫለን በሚል አቅደን ባለንበት እንደ አገር በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ላይ የሌማት ትሩፋት የሚል ታወጀ፡፡ ይታወጅ እንጂ እኛ ከችግራችን ተነስተን ያመጣነው መፍትሔ በመሆኑ እንደክልላችን ከአራት ወር ቀደም ብለን አውጀን ሥራውን እየሠራን የነበርን ብንሆንም መንግሥት ካወጀ በኋላ ግን የገጠመን ነገር ቢኖር ምርጥ ዝርያ የሆነ ዶሮ ማግኘት አለመቻል ነው፡፡ ደብረ ዘይት ከሚገኘው ከኢትዮ ቺክን ጋር አስቀድመን ውል የገባን ቢሆንም፤ ከእወጃው በኋላ ሁሉም ክልል በሚያስብል መልኩ ውል በመግባቱ እጥረቱ አጋጠመን፡፡

ችግሩ ባስ በማለቱ ሲዳማ አንድ የዶሮ ልማት ኢንተርፕራይዝ ስላለው እና እኛም ጫጩት የሚፈልፍሉ ማሽኖች ስላሉን በራሳቸው ዶላር ከውጭ አገር እንቁላል ገዝተው የሚያመጡ ባለሀብቶች በማስፈልፈያ ማሽናችን ተጠቅመው መልሰው ለእኛው እንዲሸጡልን በማድረግ እኛ ደግሞ የአንድ ቀን ጫጩት ገዝተን የሥራ እድል ለፈጠርንላቸው ወጣቶች በማስተላለፍ እነርሱ ለ48 ቀን አሳድገዋቸው ቄብ ሲሆኑ ለአርሶ አደሮች ማድረስ ጀመርን። በዚህ አይነት አሠራር ታግዘን እናሳካለን ብለን በእቅድ የያዝነውን አራት ሚሊዮን ዶሮዎችን ማሳካት ችለናል። በዚህ አሠራራችን እንደፌዴራል በተገመገመው ግምገማ ስኬታማ የሆነው ክልላችን ነው። የሲዳማ የገቢ ምንጭ እንስሳት ናቸው በሚል እየመራን እንገኛለን፡፡ ከዚህ ተሞክሮ ተነስተን በ2016 በጀት ዓመት ስምንት ሚሊዮን ዶሮዎችን ለማሰራጨት አቅደናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ወደተሻሻሉ ላሞች ልመልስዎትና ከጥቂት ላሞች ምርታማነትን ለማግኘት የመኖ ጉዳይ የግድ እንደሚል ግልጽ ነው፤ በዚህ ረገድ ምን የታሰበ ነገር አለ?

አቶ ደስታ፡- በዚህ ረገድም አስበን እየሰራን ነው፤ እንቅስቃሴ የጀመርነውም ፓኬጁን አሟልተን ነው፡፡ የእንስሳቱን መኖ የማልማቱ ጉዳይ በራሱ በአንድ ዲፓርትመንት የሚመራ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ለእያንዳንዱ አርሶ አደር መኖ እንዴት እንደሚያዘጋጅ ሥልጠና ተሰጥቶታል፡፡ አርሶ አደሩ ደግሞ የገቢውን ጣዕም ማጣጣም ከጀመረ ሥራውን ቀን ብቻ ሳይሆን ማታም ጭምር ይሠራል፡፡

ከዚህ ሌላ በአካባቢያችንም ሆነ በሀገራችን ድርቅ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ስለመሆኑ አስተውለናል። በመሆኑም ዝግጅት ለማድረግ አልቦዘንም፡፡ እኛ ዘንድ በ2013ም በ2014ም ድርቅ አጋጥሞን ነበር፡፡ ይህ ድርቅ በርትቶ ከመጣ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ባለው በእንስሳትና በእርሻ ላይ ያለውን ሥራችንን እንዳያስተጓጉል በመስጋታችን የእንስሳት የመኖ ባንክ ጎን ለጎን ማቋቋም ስላለብን በአምስት ወረዳዎች ላይ መኖ የሚከማችባቸውን መጋዘኖች ሠራን፡፡

በበጋው የአካባቢ ጥበቃ የተፋሰስ ሥራ ስለምንሠራ የተጎዱ አካባቢዎችን ከእንስሳት ንኪኪ ነጻ እንዲሆኑ ባደረግን ጊዜ ሳር ስለበቀለ ወጣቶች ተደራጅተው እንዲጠብቁ አደረግን፡፡ በአንድ በኩል ለወጣቱ የሥራ እድል የፈጠርን ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሳር አጭደው እንዲሸጡ በማድረግ እኛው ራሳችን ገዥ ሆነን የመኖ ባንክ ለማከማቸት በቃን፡፡

እንደሚታወቀው ደግሞ ድርቅ በዚህ ዓመት በክልላችን የከፋ ጉዳት ባለማስከተሉ በየማከማቻ ባንኩ መኖ አለን። በቅርቡ በቦረና በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከብቶች የሚመገቡት ባለመኖሩ ከተከማቸው ላይ ድጋፍ በማድረግ የበኩላችንን ለመወጣት ችለናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ላሞች በክልሉ በስፋት ስለተሰራጩ ከፍተኛ የወተት ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃልና ይህንንስ በምን መልኩ ለማስተናገድ አሰባችሁ?

አቶ ደስታ፡- በክልላችን የወተት ተፋሰስ ብለን የለየንበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህንን በዩኒየን አደራጅተናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወተት የጎርፍ ያህል በሚያስብል ሁኔታ ወደ ገበያ መቅረብ ጀምሯል፡፡ ይህ በመሆኑ ወተትን እሴት ጨምሮ ሊያዘጋጅ የሚችል ይርጋለም ላይ አግሮፕሮሰሲንግ በሚል ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ተቋቁሟል፡፡ ፋብሪካው የወተት ምርትን በስፋት የሚቀበል ነው፡፡ ብዙ ቶን ወተት ተቀብሎ በተለያየ አይነት ምርት መቀየር የሚችል ነው። እነዚህ ምርቶች ደግሞ በሀገር ውስጥ ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆኑ ወደዓለም ገበያ በተለይም ወደ አረቡ ዓለም ገበያ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ የሚነጥፍ ገበያ የለም።

በመሆኑም የግብርና ሥራው እንደተጠበቀ ሆኖ በእንስሳቱና በዶሮው ላይ ለየት ያለ ሥራ በመሥራት የተሳካ የቤተሰብ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በመረባረብ ላይ ነን። ክልል ከሆንን በኋላ አሠራራችንን እያሻሻልንና የሕዝቡንም ተጠቃሚነት እያረጋገጥን እንገኛለን፡፡ ሕዝቡም ባየውና በመጣው ለውጥ በጣም ደስተኛ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሲዳማ በክልልነት ከተደራጀ ሶስት ዓመታትን አስቆጥሯል፤ የዞን አደረጃጀቱ ለምን ዘገየ? መጠሪያውንስ ስለምን በአቅጣጫ ማድረግ ተፈለገ?

አቶ ደስታ፡- ሶስት ዓመት የመቆየታችን ዋናው ምስጢር በጀት ለመቆጠብ በማሰባችን ነው፡፡ በዚህ በቁጠብነው ገንዘብ ደግሞ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ዞን ቀደም ብለን አደራጅተን ቢሆን ኖሮ ዞን በማደራጀታችን ብቻ ተጨማሪ ግማሽ ቢሊዮን ብር ይጠይቀን ነበር። በተወሰነ መልኩም ቢሆን የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በመሞከራችን ለጊዜው አቆይተን የነበረውን የዞን ማደራጀት ሥራችንን አጠናቀን ባለፉት ሳምንታት ውስጥ የዞን መዋቅሩን ይፋ አድርገናል፡፡ በእርግጥ ሃዋሳ ከተማ ከዚህ ቀደሞም ያው በዞን መዋቅር ውስጥ ያለ ነው፡፡

የተቀረውን ግን ከሕዝቡ ጋር ባደረግነው ውይይት የተነሳ ስምምነት ላይ በመድረሳችን አራት ዞኖችን የማዋቀር ሒደትን ተከትለናል፡፡ በእርግጥ ሰው ይጠብቅ የነበረው በየሰፈሩና በእያንዳንዱ ወረዳ ዞን መሆንን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያት ደግሞ ዞን ሲመጣ ቅጥር እንደሚኖር በመታሰቡም ጭምር በመሆኑ ፈጥኖ የሥራ እድል ለማግኘት ካለው ጉጉት የተነሳ ነው፡፡ ይሁንና እያንዳንዱን ወረዳ ዞን ማድረግ ዘላቂ ችግርን የሚፈታ አስተሳሰብ እንዳልሆነ ከሕዝቡ ጋር መክረናል። በእርግጥ ዞን ሲመጣ በሌላ በኩል ወጪንም አብሮ ይዞ ይመጣል። ይህ ደግሞ መሠረተ ልማቱ እንዳይሰራ የሚያደርግ ነው በሚለው ስምምነት ላይ በመደረሱ የዞን አደረጃጀቱ በሰላም ተጠናቋል።

የየዞኑ ስያሜ የሚያመላክተው አቅጣጫን ብቻ አይደለም። ሲዳማ የሚለውን ስያሜ በማካተት ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን፣ ደቡባዊ ሲዳማ ዞን፣ ምስራቃዊ ሲዳማ ዞንና ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን በሚል የተዋቀረ ነው፡፡ ሲዳማ አንድ ነው፡፡ የአንዱን ወረዳ ስም ለመውሰድ ቢሞከር የጎሳ ስም ያላቸው የወረዳ መጠሪያዎች ስላሉ ሌላ ችግር ይዞ እንዳይመጣ በመታሰቡ ነው። በአንድ ዞን ውስጥ ደግሞ የተለያዩ ወረዳዎች በመኖራቸው ሁሉንም ሊያስማማ ስለማይችል አንድ ሊያደርግ የሚችለውን ሲዳማ የሚለውን መጠሪያ አስገብተናል፡፡ በአንደኛው ጎሳ የዞኑን ስያሜ ቢሰጥ ለተሰጠው ኩራት ላልተሰጠው ደግሞ ሌላ ችግር እንዳይሆን ጭምር ነው፡፡

ሲዳማ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ክልል ለመሆን አንግቧቸው የተነሳው የክልል አጀንዳዎቹ በአግባቡ እየተመለሱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የክልሉ ሕዝብም የታገለልትን ዓላማ እያሳካ ነው፡፡ ከድህነት ለመውጣት ደግሞ በቅርብ ርቀት ላይ እንገኛለን፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃም ቢሆን ምሳሌ ወደመሆን እየተቃረብን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- እንስሳትና ዶሮ ላይ በመመሥረት ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ የሚጠብቅባቸው ግማሽና ከግማሽ ሔክታር መሬት በታች ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፤ የተቀሩትስ የኅብረተሰብ ክፍል ያለውን መሬት በምን አይነት አግባብ ነው የሚጠቀምበት?

አቶ ደስታ፡- በሲዳማ 50 በመቶ የሚሆነው ቆላማ አካባቢ ያለው ሕዝብ የሚመገበው በቆሎ ሲሆን፣ 50 በመቶ የሚሆነው በደጋማ አካባቢ የሚመገበው ደግሞ የእንሰት ምርትን ነው፡፡ በክልላች በእስካሁኑ ሒደት በመሠረታዊነት የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡት እነዚህ ሁለት ምርቶች ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑ በቆሎ ላይ በትኩረት መሥራት ይኖርብናል፡፡

እኛ በልግ አምራች በመሆናችን ከመጋቢት ጀምሮ በቆሎ ይመረታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለአርሶ አደሩ አቅርበናል፡፡ በዚህም ወደ 80 በመቶ የሚሆነውን የበቆሎ ማሳ በምርጥ ዘር እንዲሸፈን አድርገናል፡፡ ምንም እንኳ ማዳበሪያ እንደ ሀገር እጥረት ቢኖርም ከሞላ ጎደል ሥራውን ለመሥራት ሞክረናል፡፡ የቀረው የክረምት የግብርና ሥራ ከሐምሌ ጀምሮ የሚዘራ በመሆኑ የማሳ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ በተለይ ደጋማው አካባቢ ስንዴ፣ ገብስና ጥርጣሬ ይዘራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ካነጋገርኳቸው የክልሉ ነዋሪዎች እንደተረዳሁት እንደ ሀገር ያለው የሥራ አጥነት ችግር በሲዳማም በስፋት ይታያል፤ ይህን ችግር ከመፍታት አኳያ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ ደስታ፡- የሥራ አጥነቱ ችግር አለ፤ እኛ አካባቢ ደግሞ ችግሩ የሚሰፋው ሰው ሥራን የሚፈልገው በቅጥር መልክ በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ ሲዳማ ክልል ከሆነ መዋቅር ይሰፋል በሚል ሁሉም የሚፈልገው መቀጠርን ነው፡፡ ያንን ግን ማድረግ አልተቻለም፡፡ በዛ ላይ በክልሉ 96 ሺ የመንግሥት ሠራተኛ አለ፡፡ በመሆኑም የሚመጣው በጀት ሁሉ የሚውለው ለደመወዝ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ልማት ለመሥራት ይጎዳል፡፡ እንደ ክልላችን በሶስት ዓመት ውስጥ 13 ሺ ሠራተኛ ቀጥረናል፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ስድስት ሺው መምህራን ናቸው፡፡ ይህ በዚህ አይቆምም፤ ይቀጥላል። ይሁንና ለሁሉም የሥራ እድል መፍጠር አይቻልም፡፡ በምናወጣው ክፍት ቦታ ግን መወዳደር ይቻላል፡፡

መቀጠርን ማሰብ ብቻ ሳይሆን ገቢ የሚገኝበትንም የሥራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት መነሳሳት የግድ ይላል፡፡ በዘርፉ ግንዛቤ መስጠትና ቦታዎችን ማመቻቸት ከእኛ ይጠበቃልና ያንን እያደረግን ነው፡፡ እንዴት መሥራት እንደሚቻል በዘርፉ ዙሪያ የተሻለ መረጃ ይኖራቸዋል ያልናቸውን አነቃቂ አካላትን ጋብዘን የማነቃቃቱን ሥራ ስንሰራ ቆይተናል፡፡ በዚህም ለውጥ ማየት ችለናል፡፡ ምክንያቱም ‹‹ቅጠሩን›› ከሚል አስተሳሰብ ‹‹ሥራ ልፍጠርና አጋዙን›› ወደሚል አመለካከት መምጣት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ሥራ ላጡ ወጣቶች የሥራ አማራጮችን በማቅረብ ላይ እንገኛለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረገው የትምህርት ቤቶች አቅም ማሳደግ ንቅናቄ ላይ ክልሉ ሊያስኬደው ያሰበው በምን አገግባብ ነው?

አቶ ደስታ፡– የትምህርት ጥራትንም ሆነ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማደራጀቱን ተግባር ውጤታማ ለማድረግ ‹‹የትምህርት አብዮት በሲዳማ›› ብለን አውጀን መንቀሳቀስ ጀምረናል፡፡ በትምህርቱ ላይ አብዮት የከፈትንበት ምክንያት የትምህርት ስብራቱን ለመሙላት ነው፡፡ በዚህ ሒደት ያስተዋልነው የመምህራንን የአቅም ጉድለት ሲሆን፣ ይህም ክህሎትና የተነሳሽነት ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ያስተዋልነው የግብዓት ጉድለትን ነው፡፡ ሌላው ለየት ያለው ጉድለት ብለን ያልነው ተማሪዎች ወደ አንደኛ ክፍል ሲመጡ ቢያንስ ለማንበብ ብቁ ሆነው መሆን ነበረበት፡፡ ይህ ግን አልሆነም፡፡

ስለዚህ በ2014/15 በጀት ዓመት በተለይ በመምህራን ላይ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ሞክረናል፡፡ ወደ 324 ሚሊዮን ብር አውጥተን መጽሐፍትን አሳትመን ከሞላ ጎደል አቅርበናል። በዚህ አሠራራችን ከሌሎች ክልሎች መቅደም ችለናል። በአስር ሃይስኩሎች ላይ ተጨማሪ አስር አስር ብሎኮችን ሰርተን የመማሪያ ክፍል መጨናነቅ እንዳይኖር ሞክረናል፡፡ የቦታ ርቀት አለብኝ በሚል ማኅብረሰቡ ላነሳው ጥያቄ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሰርተን ሶስቱን አጠናቀናል፤ ሁለቱ ደግሞ በመጠናቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ህጻናት አንደኛ ክፍል ሲገቡ ፊደል ባለመለየታቸው ሲቸገሩ ነበርና በየቀበሌው አንዳንድ ቅድመ መደበኛ መማሪያ ትምህርት ቤት ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጎን የመገንባት እቅድ ያዝን፡፡ በክልላችን ያሉት ደግሞ 500 ቀበሌዎች ናቸው። በመጀመሪያ በመቶ ቀበሌዎች ላይ ለመገንባት አቅደን የተወሰኑ በመገንባታቸው በተጠናቀቀው ዓመት ለምረቃ የበቁ አሉ፡፡ ይህንንም ግንባታ የክልላችንም ባለሀብቶችንና የመንግሥት ሠራተኛውን አሳታፊ አድርገንበታል፡፡

በሌላም በኩል ባለሀብቶቹ ወደ 72 ትምህርት ቤት እንደሚገነቡ ቃል የገቡ ሲሆን፣ የመንግሥት ሠራተኛው ደግሞ የአንድ ወር ደመወዙን በመልቀቅ 145 ሚሊዮን ብር መያዝ ችለናል፡፡ በዚህ ደግሞ ወደ 20 ትምህርት ቤት መገንባት ይቻላል፡፡ አንዱ ትምህርት ቤት ብቻ የሚሰራው በሰባት ሚሊዮን ብር፡፡ በዚህ መሠረት 100 ትምህርት ቤት በ2016 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየሠራን ሲሆን፣ ያቀድነውም በየዓመቱ መቶ ትምህርት ቤቶችን ለመሥራት ነው፡፡ አስሩን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መርቀናል። እንደ ሀገር በተጀመረው ንቅናቄ ደግሞ በነባር ትምህርት ቤቶች ያልተሟላውን እንሰራለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ በክልሉ በምን አግባብ እየተካሄደ ነው?

አቶ ደስታ፡- ክብርት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በተገኙበት ሁለተኛው ዙር የአረንገጓዴ ዐሻራ ተጀምሮ ሥራዎች እየተቀላጠፉ ናቸው፡፡ በሁለተኛው ዙር እንተክላለን ብለን የያዝነው እቅድ 306 ሚሊዮን ችግኝ ሲሆን፣ ለምግብነት የሚውሉና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ይበዛሉ፡፡ በእስካሁኑ ሁለት ሶስተኛው ችግኝ ተተክሏል፡፡ በተለይ ሐምሌ አስር ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ ለመትከል የተዘጋጀን ሲሆን፣ ቀሪውን ደግሞ እስከ ሐምሌ 30 ድረስ ተክለን እናጠናቅቃለን።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ደስታ፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡

 አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *