ኮማንደር እንዳሻው ከአዳራሹ ሲወጣ ቀይዳማ ፊቱ ገርጥቶ ነበር፡፡ የቢሮውን በር ከፍቶ ከመግባቱ ስልኩ አንቃረረ፡፡ ከንዴቱም ከድካሙም ገና አላገገመም ነበር፡፡ ማረፍ ፈልጓል፣ መረጋጋትም..እና ደግሞ በጽሞና ማሰብ፡፡ ቢሮ ሲገባ ከራሱ ጋር ሊያወራ ፕሮግራም ይዞ ነበር፡፡ ወደጠረጴዛው ተራምዶ ስልኩን አነሳው፡፡ እጀታውን ወደጆሮው ከማስጠጋቱ አንድ ድምጽ ተቀበለው፡፡
‹ፌልሶር እባላለሁ፡፡ የአይሁድ አለቃ ነኝ፡፡ እየሱስን የሰቀልነው እኔና ጭፍሮቼ ነን፡፡ ዓለም በእኛ በኩል እንደምታልፍ ልነግርህ ነው የደወልኩት፡፡ ደግሞ ሩጫህን አቁም መቼም አትደርስብንም›፡፡ ከረጅም ሳቅ ጋር ስልኩ ተቋረጠ፡፡ ሲስቅ ከርፋፋ ነው፡፡ የምድራችን አስቀያሚው ሳቅ ከእሱ ጉሮሮ ውስጥ ስለመውጣቱ ተጠራጣሪ አይኖርም፡፡ ኮማንደር እንዳሻውም የታዘበው ይሄን ነበር፡፡ አጠገቡ ቢሆን ኖሮ ከሳቁ ባለፈ ወላቃ ጥርሱን ያስተውል ነበር፡፡
ኮማንደር እንዳሻው የስልኩን እጀታ ከጆሮ ግንዱ ላይ ሳያወርድ ለረጅም ጊዜ ቆየ፡፡ ይሄን ሰው ነው የሚፈልገው፡፡ በህይወቱ እጅግ የፈተነው አንድ ሰው እሱ ነው፡፡ አሁን በስልኩ ውስጥ ያወራው ሰው፡፡ አምስት ሰዓት አለፍ ባለ ማግስት እንዲህ እንደአሁኑ እየደወለ ‹ፌልሶር ነኝ..የአይሁድ አለቃ፣ መቼም አትደርስብኝም› ሲል ከአስቀያሚ ሳቁ ጋር አላግጦበት መልሱን እንኳን ሳይሰማ ይዘጋበታል፡፡ ላለፉት ስድስት ወራት በዚህ ሰው ውንብድና ጽሞና ውስጥ ወድቋል፡፡ በልዩ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ሊያውሉት ክትትል ቢያደርጉም እጃቸው ግን አልገባም፡፡ ማነው? አያውቀውም። በህይወቱ አንድ ምኞት ብቻ አለው ይሄን ወንጀለኛ ለፍርድ ማቅረብ። ሁለት የምርመራ አባላት ወደክፍሉ ሲገቡ ባሰሙት የኮቴ ድምጽ ከሃሳቡ ወጣ፡፡ ስልኩን ቦታው መልሶ እልህ በተሞላበት አይን እጅ ነሳቸው፡፡ አልቆየም ገና እግራቸው ወለሉን ከመርገጡ በዘወትር ጥያቄው ‹ምን አዲስ ነገር አለ? ሲል ተቀበላቸው፡፡
ምን ፈልጎ ምን እንዳጣ ያውቃሉ፡፡ በዚህ ሰዓት እንዲሆንለት ቢጠየቅ የሚመልሰው አንድ መልስ እንዳለው ይሄንንም ያውቃሉ፡፡ ወደቢሮው የገባን መርማሪ ፖሊስ እንዲህ ብሎ ነው የሚጠይቀው። በፌልሶር ጉዳይ እንዲህ ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ ግን አዲስ ነገር ነግረውት አያውቁም፡፡ ‹አዝናለው ኮማንደር! የአንዱ መርማሪ ድምጽ ተሰማ፡፡
ኮማንደር እንዳሻው ፊቱን አጨፍግጎ ወደ መርማሪው ቀና አለ፡፡ በልቡ መጥፎ ነገር እንዳይነግሩት የሚማጸን ይመስላል ግን አዝናው ተብሎ በተጀመረ ወሬ ጥሩ ነገር ሰምቶ አያውቅም፡፡
ሁለተኛው መርማሪ ቀጠለ ‹ሌላ ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ የአምስት ታዳጊ ህጻናት አስከሬን በተመሳሳይ ግድያ በተዘጋ ቤት ውስጥ ተገኝቷል፡፡ የሁሉም ታዳጊ አሟሟት እንደዚህ ቀደሙ ተመሳሳይ ነው፡፡
‹እንደዚህ ቀደሙ ማለት? ከኮማንደሩ አፍ ደካማ ድምጽ ወጣ።
‹አምስቱም ህጻናት ከአቅማቸው በላይ በሆነ መደፈር..› መርማሪው አልጨረሰውም.. ኮማንደሩም እንዲጨርስ አላስገደ ደውም፡፡ ዝም ተባባሉ፡፡ ዝምታ በዋጠው ክፍል ውስጥ የኮማደር እንዳሻው ጣቶች ጠረጴዛውን እየቆረቆሩ ስልት አልባ ድምጽ ያሰማሉ፡፡ በኮማንደር እንዳሻው ልብ ውስጥ እነዛ ጣቶች ጠረጴዛው ላይ ሲያርፉ የሚያወጡት ድምጽ ህይወታቸውን ላጡት ነፍሶች ምሾና ዋይታ ሌላም መልክ ነበራቸው፡፡
ዝም ሲል ያውቁታል፡፡ ሞት እንኳን በዝምታው የእሱን ያክል አስፈሪ እንዳልሆነ ያውቃሉ፡፡ ዝም ካለ ተቆጥቷል፣ አዝኗል ማለት ነው፡፡ እና ደግሞ መቼም ያልደረሱበት የኃይል ሞገድ፡፡ ከጽሞናው የሚነጥቀውን ሰው አይወድም፡፡ ተባብረው ዝም አሉት፡፡
እግሩን እየጎተተ ትቷቸው ወደውጪ ወጣ፡፡ ጸሀይ ያለወትሮዋ ገና በቀን በደመና ተውጣ ነበር፡፡ እንደእሱ ግራ የገባው ያኮረፈ ቀን ተቀበለው፡፡ ከፊት ለፊቱ አንድ ጸጉራም ሰው ይታየዋል፡፡ እንደደመናማው ቀን ደመና የመሰለ ሰው፡፡ ወደእሱ እየመጣ መሰለው፡፡ ፈገግ ያለም ይመስለዋል፡፡ በፈገግታው መሀል ጥርስ አልባ ድዱን ያስተዋለም ይመስለዋል፡፡ ተበሳጭቶ ስለነበር በአንዱም እርግጠኛ አልነበረም፡፡ አጠገቡ ደርሶ በትከሻው ገፍቶት ሲሄድ ተሳስቶ እንጂ ሆን ብሎ የገፋው አልመሰለውም ነበር፡፡
……….
ቤት ሲደርስ ልጁ ጸዐዳ ቡና አፍልታ ጠበቀችው፡፡ እንዲህ ደክሞት የሚበረታው በልጁ መኖር ነው፡፡ በልጁ መኖር ብዙ አለመኖሮችን ድል ነስቶ ያውቃል፡፡ እያያት በዝምታ ተለጎመ፡፡ ሳያያት ኖሮ አያውቅም፡፡ በሌለችበት ሁሉ ያያታል፡፡ በወንድነቱ ውስጥ የእሷ መኖር ከብዙ ዝቅታ ታድጎታል፡፡ ሰሞኑን ደስ ብሏታል። በእሷ ደስታ ውስጥ የእሱ ነፍስ ናት የምትስቀው፡፡
‹እንዴት ነው እጮኛሽ? እንደምትፈልጊው አይነት ሰው ሆኖ አገኘሽው? ጠየቃት ከብዙ ዝምታ በኋላ አይኖቹን ወደአይኖቿ ሰዶ፡፡
‹አዎ አባ..ሳይገባኝ ያገኘሁት ይመስለኛል፡፡ ሁሉ ነገሩ እንዳንተ ነው፡፡ እግዚአብሄር ለምን እንዲህ እንደወደደኝ አላውቅም፡፡ በአባትና በባል የታደለች የመጀመሪያዋ እድለኛ ሴት ነኝ፡፡
‹አንቺ ከዚህም በላይ ደስታ የሚገባሽ ሴት ነሽ፡፡ በአንቺ ደስታ የኔ ነፍስ እንደምትስቅ አትርሺ› አላት፡፡
‹አውቃለው አባ..የእኔ ደስታ የአንተ እንደሆነ፡፡ አስተዋውቃችኋለሁ እያልኩ አንተም እሱም አልመች አላችሁ፡፡
‹በሚመጣው ሰንበት ቤት ይዘሽው ትመጪና ታስተዋውቂኛለሽ›
‹እሺ አባ፡፡ አንተስ የያዝከው ኬዝ እንዴት ሆነልህ? እስካሁን ወንጀለኛው አልተያዘም?
በጥልቅ ከተነፈሰ በኋላ ‹አልተያዘም፡፡ ዛሬም የአምስት ህጻናትን አስከሬን በተዘጋ ቤት ውስጥ አግኝተናል፡፡ ሲል ወደዝምታው ተመለሰ፡፡
‹እንደበፊቱ ተደፍረው?
‹ጭንቅላቱን ከፍና ዝቅ በማድረግ ‹አዎ› አላት፡፡
አለቀሰች፡፡ አባቷ ስለዛ ወንጀለኛና ስለነዛ ንጹሀን ህጻናት ነግሯት ሳታለቅስ ቀርታ አታውቅም፡፡ በነገራት ቁጥር እንዳለቀሰች ነው፡፡ አሁንም አለቀሰች፡፡ ስታለቅስ አባብሏት አያውቅም፡፡ እስኪበቃት ይጠብቃል፡፡ ጥርሷን ነክሳ ‹ምን አይነት አረመኔ ነው..እስክትል ይጠብቃታል፡፡
……………….
‹ነገ ቅዳሜ አይደል ከአባቴ ጋር አስተዋውቅሀለው፡፡ ቤት ይዘሽው ነይ ብሎኛል›
‹የኔ ቆንጆ ነገ እኮ ሥራ አለኝ፡፡ በሚቀጥለው ቅዳሜ ቢሆን ምኞት ይሰጠኛል› ሲል ጉንጭዋን ነካ አደረገው፡፡ ይሄ ከእሷ ጋር የነበረው የመጨረሻ ትውስታ እንደሆነ ያውቀዋል፡፡ አባቷን ለመበቀል እንደቀረባት ያውቃል፡፡ አፍቅሯት በቀሉን ከመተው በፊት ያሰበውን ማድረግ አለበት፡፡ በዚህ ከቀጠለ ሞቷን ሽሮ ሚስቱ ነው የሚያደርጋት፡፡ ያን ከዛሬ አስራ አምስት አመት በፊት ወንጀል ሰርቶ ወህኒ ቤት እድሜ ልክ ያስፈረደበትን አባቷን የሚበቀለው በእሷ በኩል ነው፡፡ ከወህኒ ቤት አምልጦ ከወጣ በኋላ ብዙ ክትትል እየተደረገበት ነው፡፡ ራሱን ቀይሮ ባይንቀሳቀስ ኖሮ በዚህ ልክ ባልተራመደ ነበር፡፡ በእሷ በኩል አባቷን ከተበቀለ በኋላ ያኔ የሰው ነፍስ አጥፍቻለው ሲል እዛው አባቷ ቢሮ ወንጀለኛ ነኝ ሲል ይሄዳል።
በዝምታ ትከሻው ላይ ደገፍ አለች፡፡ ‹አባቴ በኔ ደስታ ገነት ውስጥ እየኖረ ነው፡፡ ነገ ወስጄህ ባስተዋውቅህ ደስ ይለኝ ነበር›።
‹የኔ ነፍስ አባትሽን ለመተዋወቅ ከኔ በላይ የቸኮለ የለም፡፡ ከነገ በኋላ ሁሉም ነገር አንቺ እንዳልሽው ይሆናል›› ሲል ትከሻው ላይ እንዳለች እጁን ልኮ ዳበሳት፡፡
‹እሺ እንዳልክ ይሁን›፡፡ አለችው፡፡
‹የኔ ቆንጆ..ሰኞ አራት ሰዓት ላይ መጀመሪያ የተቀጣጠርንበት ቤት በር ጋ እጠብቅሻለው፡፡
‹እዛ ምን አለ?..ቦታው እኮ ያስፈራል የኔ ውድ›
‹እኔ እያለሁ ዓለም ሊያስፈራሽ አይገባም፡፡ እኔ በአንቺ ዓለምን እንደደፈርኩ አንቺም በኔ ዓለምን መድፈር አለብሽ›
‹እሺ እንዳልክ ይሁን..እመጣለሁ፡፡
……….
ሰኞ አምስት ሰዓት ላይ..እንዲህ ሆነ..
መርማሪው ፖሊስ የኮማንደር እንዳሻውን ቢሮ ከፍቶ ሲገባ ባልተለመደ ባህሪ ነበር፡፡
‹ይቅርታ ኮማንደር..
‹በጠዋቱ ምን ልትነግረኝ ነው?
‹ዛሬ ጠዋት አንዲት ወጣት ሴት በተዘጋ ቤት ውስጥ ተገድላ ተገኝታለች፡፡ ፖሊስ ከስፍራው ደርሶ የፎቶ ማስረጃ እንዲይዝ ተጠይቋል፡፡
ኮማንደር እንዳሻው አንድ ነገር ብቻ ነበር ያደረገው..ጠረጴዛው ላይ ያስቀመጠውን መለዮውን አድርጎ ቢሮው የገባውን ፖሊስ አስከትሎ ወደተባለው ቦታ ሄዱ፡፡
በስፍራው ብዙ ሰዎች ተሰብስበው ተመለከቱ፡፡ የቤቱ በር ተሰብሮ ክፍሉ ውስጥ ሲገባ..ኮማንደር እንዳሻው መቼም እንዴትም ከማይሽረው ህመሙ ጋር ነበር የተገናኘው፡፡ አንድ ልጁ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድላ ርቃኗን ወለሉ ላይ ሲያየው ራሱን ለመሳት ጊዜ አልወሰደበትም ነበር፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ ኮማንደር እንዳሻው ቢሮ አንድ ሰው መጣ…‹ሩጫዬን ጨርሻለው፡፡ ስትፈልገኝ የነበርኩት ሰው እኔ ነኝ፡፡ በልጅህ ነፍስ ከሩጫዬ ቆሜያለው፡፡ አሁን እንደፈለክ ልታደርገኝ ትችላለህ።
አውቆታል..ፌልሶር ነው፡፡ ከአስራ አምስት አመት በፊት በከባድ ወንጀል ህግ ፊት አቁሞት እንደነበርና እድሜ ልክ እንደተፈረደበት ያውቃል፡፡ ከእስር ቤት አምልጦ ራሱን በመቀየር በህግ ሲፈለግ እንደነበርም ያውቃል፡፡ አጠገቤ ሽጉጥ አለ፡፡ ግን በሽጉጦ ቢገለው የልጁንና የነዛን ብዙ ህጻናት ነፍስ እንደማይታደገው ያውቃል፡፡ ዓለም ላይ ለዚህ ሰው የሚሆን ብዙ ሞት ፈለገ አላገኘም፡፡
እናም ዝም አለው…አጠገቡ የቆመውን ወንጀለኛ ትቶ ወደሥራው ተመለሰ፡፡ ሞት እረፍት ነው፡፡ ይሄን ሰው ገድዬ እንዲያርፍ ማድረግ የለብኝም፡፡ ዓለም በሥራው ታሰቃየው ሲል ተወው፡፡
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2015