ትውልድን ከአደንዛዥ እፅ ሱስ የመታደግ ትግል

በዓለም አቀፍ ደረጃ ማኅበራዊ ቀውስ እየፈጠሩ ካሉ ችግሮች መካከል አንዱ የአደንዛዥ እፅ ዝውውርና ሱስ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ሱስ አስያዥ ለሆኑ የተለያዩ ነገሮችና እፆች ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች በተለይም ታዳጊዎችና ወጣቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንና ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በተለያዩ ጊዜያት ይፋ የተደረጉ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡ በችግሩ ምክንያት የሚፈጠሩ ቀውሶች ቤተሰብን፣ ህብረተሰብንና ሀገርን ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ነው፡፡ ይህ አደገኛ ችግር ያሳሰባቸው በጎ አሳቢ ዜጎች፣ ችግሩ ከዚህ የበለጠ ቀውስ እንዳያስከትል በየጊዜው የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡

ዛሬ የአደንዛዥ እፅ ሱስ መስፋፋትን ለመግታት እየተጉ የሚገኙትን የ‹‹ላግዛት የበጎ አድራጎት ድርጅት›› መስራቾች በአካባቢያቸው ይመለከቱት የነበረው ነባራዊ ሁኔታ የችግሩን አሳሳቢነት ይበልጥ ጉልህ አድርጎ አሳያቸው፡፡ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች የአደንዛዥ እፅ ሱስ ተጠቂ ሆነው ሲመለከቱ እነዚህን ሰዎች በመርዳት ከገቡበት ችግር ውስጥ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ፅኑ እምነት አደረባቸው። ስለሆነም በችግሩ ምንጭ ላይ አተኩሮ የሚሰራና ታዳጊዎች የችግሩ ሰለባ ከመሆናቸው አስቀድሞ ተጋላጭ እንዳይሆኑ የቅድመ መከላከል ተግባር የሚያከናውን የበጎ አድራጎት ተቋም ማቋቋም እንዳለባቸው ወስነው በኅዳር ወር 2014 ዓ.ም ‹‹ላግዛት የበጎ አድራጎት ድርጅት›› የተባለ ምግባረ ሰናይ ተቋም መሰረቱ፡፡

ድርጅቱ አምስት የቦርድ አባላት አሉት፤ አባላቱ በሙሉ ሴቶች ናቸው፡፡ መስራቾቹ የፕሮጀክት ሃሳቡ እንዴት እንደሚተገበር የሥራ እቅዶችን (ፕሮፖዛል) አዘጋጅተው፣ ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ ከሚሰሩ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ችግሩን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ተነጋግረው እና የባለሙያዎች ምክርና ሃሳብ በበጎ አድራጎት ድርጅቱ የድርጊት መርሃ ግብር (Action Plan) ውስጥ እንዲካተት አድርገው እውን ያደረጉት ምግባረ ሰናይ ተቋም ከአደንዛዥ እፅ ሱስ የነፃ ትውልድ የመፍጠር ራዕይን አንግቦ ሥራውን ጀመረ፡፡

ወይዘሪት ጽዮን ዓለማየሁ የ‹‹ላግዛት›› የበጎ አድራጎት ድርጅት መስራችና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናት፡፡ ድርጅቱ ‹‹ላግዛት›› ተብሎ የመሰየሙ ምክንያት ምን እንደሆነ ስታስረዳ ‹‹ላግዛት የሚለው ቃል የሴት ፆታን የሚያመለክት ነው፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ የችግሮች ሰለባዎች የሚሆኑት ሴቶች ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ በብዙ ችግሮች የምትፈተነውን ሴቷን እንርዳት፣ እናግዛት የሚለውን ሃሳብ ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ታዳጊዎችን በመልካም ሥነ-ምግባር በማነፅ መልካም ዜጎችን ለኢትዮጵያ ሀገራችን የማስረከብ ዓላማ ስላለን ያን ዓላማችንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያን እንድናግዛት ለመጠቆምም ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለውን እምቅ ኃይል በመጠቀም ጤነኛና ብቁ ትውልድን በማፍራት የሀገራችንን የኢትዮጵያን የወደፊት እድገት የማገዝ ሃሳብንም የያዘ ነው። ስለሆነም የድርጅቱ ስያሜ ሴቶችን፣ ወጣቶችን በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ከማገዝ ፍላጎታችንና ዓላማችን የመነጨ ነው›› በማለት ታብራራለች፡፡

‹‹ይህን እንድንሰራ ምክንያት የሆኑን በአካባቢያችን ያየናቸውና ጥልቅ ሃዘን የፈጠሩብን ክስተቶች ናቸው፡፡ በርካታ ወጣቶች በሱስ ተጠምደው፣ ትምህርት ትተው፣ የአእምሮ ህመም ተጠቂ ሆነው መመልከታችን በእጅጉ አሳዝኖናል። በአንዳንድ ከተሞች ችግሩ የተለመደና ባህል እስከሚመስል ድረስ ተንሰራፍቷል፡፡ በእኛ ቤተሰብ ውስጥም የችግሩ ሰላባ ሆኖ የተገኘ ሰው መመልከታችን በውስጣችን ትልቅ ህመም ፈጠረ›› በማለት ሥራውን ለመስራት ያነሳሳቸው የአደንዛዥ እፅ ሱሰኝነት በማኅበረሰቡ ውስጥ የፈጠረው አደገኛ ቀውስ እንደሆነ ታስታውሳለች፡፡

የማኅበሩ መስራቾችም ‹‹ይህ ችግር ከዚህ የባሰ ጥፋት ሳያደርስ መቆም አለበት፡፡ እኛም ችግሩን ለማቃለል አንድ ርምጃ መራመድ አለብን›› ብለው እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ ባደጉበት አካባቢ ላይ በተደጋጋሚ አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት መጥቶ ሥራ ይጀምራል፡፡ ግን ዘላቂ የሆነ ሥራ ማከናወንም ሆነ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፤ የግንዛቤ ለውጥም ሊመጣ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ይህን ሥራ ሀገራዊ ፕሮጀክት አድርገው ለመስራት ለተለያዩ ተቋማት (የሴቶችና ወጣቶች፣ የጤና ጥበቃ… መሥሪያ ቤቶች) ጥያቄዎችን ማቅረባቸውንም ትናገራለች፡፡

ወይዘሪት ጽዮን እንደምትለው፣ የ‹‹ላግዛት›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ዋና ዓላማዎች ወጣቶች በሱስ እንዳይጠቁ ግንዛቤ በመፍጠር የሱስ ተጋላጭነትን መከላከልና በማገገሚያ ማዕከላት ውስጥ እንክብካቤ በማድረግ ከሱስ እንዲላቀቁ ማገዝ፤ ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ቋሚ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ እንዲገኙ እገዛ ማድረግ፤ ወጣት ሴቶች በማኅበራዊ፣ በሙያዊ፣ በትምህርትና በትዳር ሕይወታቸው ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ማገዝ፤ ኅብረተሰቡን መሰረት ያደረገ ወጣት አመራር ማፍራት፤ በጎ ፈቃደኝነት የኅብረተሰቡ ባህል እንዲሆን ግንዛቤ መፍጠርና ኅብረተሰቡ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ በበጎ ፈቃድ እንዲሳተፍ መሥራት እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ አስተዋጽኦ ማድረግ ናቸው፡፡

ከድርጅቱ ዓላማዎች መካከል አንዱ በአደንዛዥ እፅ ሱስ ምንነትና አስከፊነት ላይ አተኩሮ መሥራት ሲሆን ይህ ዓላማ ግንዛቤ መፍጠር እና ከአደንዛዥ እፅ ሱስ ማገገሚያ ማዕከል (Rehabilitation Center) ማቋቋም በሚሉ ሁለት የፕሮጀክት ደረጃዎች ይከፈላል፡፡ ግንዛቤ የመፍጠሩ ደረጃ ለተማሪዎች፣ ለመምህራን፣ ለሌሎች ሠራተኞችና ለወላጆች ስለችግሩ ማስገንዘብን፤ ቀለል ባለ የሱስ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ከሱስ እንዲላቀቁ ማገዝን እንዲሁም የፀረ-አደንዛዥ ሱስ እንቅስቃሴ በቋሚነት የትምህርት ቤቶች ባህል ሆኖ እንዲጎለብት ማድረግን ያካትታል፡፡

ይህን ለመተግበርም ድርጅቱ ዋና ትኩረቱን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በድርጅቱ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ለአደንዛዥ እፅ ሱስ ተጋላጭ በሚሆኑበት የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ በመሆናቸውና የአደንዛዥ እፅ ሱስ በእነዚህ ተማሪዎች በስፋት እየተዘወተረ በመሆኑ ነው፡፡ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ስለአደንዛዥ እፅ አስከፊነት ግንዛቤ መፍጠር የወደፊቱን አምራችና ሀገር ተረካቢ የኅብረተሰብ ክፍል ጤናማ፣ ከሱስ የፀዳና በሙሉ አቅሙ የሚያመርት እንዲሆን ለማድረግ ያግዛል፡፡

‹‹ላግዛት›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ከሱስ የፀዳ ትውልድ የማፍራት ሥራውን ሲያከናውን አቅሙ በፈቀደ መጠን የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶችን ለማዳረስ ጥረት የሚያደርግ ሲሆን፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 14 በሚገኝ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚማሩ 400 ተማሪዎች ስለአደንዛዥ እፅ ሱስ አስከፊነት ግንዛቤ በመፍጠር ጀምሯል። በሱስ የተያዙ ዜጎች እንክብካቤ የሚያገኙበት እና ከሱስ አገግመው የተሻሉ አምራች ዜጎች ሆነው የሚወጡበት የማገገሚያ ማዕከል መገንባት ከድርጅቱ የረጅም ጊዜ እቅዶች መካከል አንዱ እንደሆነ ወይዘሪት ጽዮን ትናገራለች፡፡

‹‹ላግዛት›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ተቋማት መካከል የግል ትምህርት ቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹በግል ትምህርት ቤቶች የሚታየው የአደንዛዥ እፅ ሱሰኛነት አሳሳቢ ነው›› የምትለው ወይዘሪት ጽዮን፣ ድርጅቱ የፀረ-አደንዛዥ እፅ ክበባትን በማቋቋም ተማሪዎች ስለአደንዛዥ እፅ ጎጂነት በነፃነት የአቻ ለአቻ ውይይት እንዲያደርጉ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እንደሰጠ ትገልፃለች፡፡ መሰል ስልጠናዎች ተማሪዎች የፍርሃትና የሃፍረት ስሜታቸውን አስወግደው በክፍት መድረኮች እንዲወያዩ እንደሚያስችሉና ከዚህ የሚገኙ ግብዓቶችም ለሌሎች ተማሪዎች ልምድ ለማካፈል እንደሚጠቅሙም ትናገራለች፡፡

‹‹የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች የሚገኙበት የእድሜ ክልል ተማሪዎች ከቤተሰብ ጋር የሚኖሩበት ነው፤ እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ የችግሩ ሰለባዎች ከመሆናቸው በፊት ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን አስቀድሞ ችግሩን መከላከል ውጤታማ ያደርጋል ብለን እናምናለን። ወላጆች ስለልጆቻቸውና ስለአደንዛዥ እፅ ምን ያህል ያውቃሉ? ልጆች አደንዛዥ እፅ ቢጠቀሙ ምን ዓይነት የባህርይ ለውጦችን ያመጣሉ? ስለዚህ ምን ያህል ያውቃሉ? ልጆቻቸው የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚ ስለመሆናቸው/አለመሆናቸው በትክክል ያውቃሉ? ልጆቻቸው ከትምህርታቸው ውጭ ስላላቸው እንቅስቃሴ በቂ መረጃ አላቸው? መምህራን ስለተማሪዎቻቸው ያላቸው መረጃ ምን ያህል ነው? መምህራን ከተማሪዎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን ዓይነት ነው? ከተማሪዎቻቸው ጋር የሚግባቡት እንዴት ነው? ስለሚሉት ጉዳዮች በግልፅ መነጋገር ያስፈልጋል›› በማለት ፕሮጀክቱ ቤተሰብን፣ መምህራንንና የበጎ አድራጎት ማኅበሩን ያማከለ እንደሆነ ታስረዳለች፡፡

ስለችግሩ ከክፍለ ከተሞች ጋር ባደረጉት ውይይት በጋራ ለመስራት የሚያስችል መግባባት ላይ ስለመድረሳቸውና ችግሩን ለመፍታት በመንግሥት በኩል ትልቅ ፍላጎት እንዳለና ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ስለመገንዘባቸው ጠቁማለች፡፡

እንደ ወይዘሪት ጽዮን ገለፃ፣ ‹‹ላግዛት›› የበጎ አድራጎት ድርጅት ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ የተለየ እሴት አለው ብሎ የሚያምን ሲሆን ሰዎች እነዚህን እሴቶቻቸውን አውጥተው እንዳይጠቀሙ እና ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው፣ ለማህበረሰባቸው እና ለሀገራቸው ብሎም ለዓለማችን አስተዋጽኦ እንዳያደርጉ እና መልካም አበርክቶ እንዳይኖራቸው የሚያደርጓቸውን እንደ አደንዛዥ እፅ ሱስ ያሉ ተግዳሮቶችን በማስወገድ ሰዎች ዕሴቶቻቸውን ተጠቅመው ንቁ እና አምራች ዜጎች እንዲሆኑ ጠንክሮ ይሰራል፡፡

ችግሩ እጅግ አንገብጋቢ ቢሆንም ትኩረት አለማግኘቱ፤ የሕግ ተቋማት የሚሰሩት ሥራ በቂ አለመሆኑ፤ የሱስ ተጠቂዎች ለሥራ አጥነት፣ ለተስፋ ቢስነት፣ ለወንጀል ተጋልጠው መመልከት እንዲሁም የአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ሕግጋት የፀረ-አደንዛዥ እፅ ክበባትን ለማቋቋም መሰናክል ሆነው መታየታቸው በድርጅቱ የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ እክል የፈጠሩ ችግሮች እንደሆኑም ወይዘሪት ጽዮን ታስረዳለች፡፡

ይህን ሥራ አጠንክሮ በመሥራት በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ተማሪዎች የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረግ፤ ከአደንዛዥ እፅ ሱስ ለመውጣት የማገገሚያ ማዕከል ማቋቋም እንዲሁም ከማገገሚያ ማዕከል የሚወጡ ሰዎች ከማዕከሉ ወጥተው በሥራ አጥነትና በተስፋ መቁረጥ ተመልሰው ወደ ሱስ እንዳይገቡ የሥራ ክህሎት ማስተማር የ‹‹ላግዛት›› የበጎ አድራጎት ድርጅት የወደፊት እቅዶች እንደሆኑ ወይዘሪት ጽዮን ትገልፃለች፡፡

‹‹ሁሉም ተቋም የየራሱ ድርሻ አለው፡፡ እኛም እንደተቋም ትኩረት የምናደርገው ተማሪዎች ላይ ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ለተመረቁና በሥራ ላይ ለሚገኙ በሱስ የተጠቁ ወጣቶች ስለችግሩ መናገር ሥራውን ከባድና ምናልባትም ውጤት አልባ ሊያደርገው ስለሚችል፣ መሥራት የሚገባን ታዳጊዎች ላይ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ታዳጊዎቹ ወደዚያ እንዳይገቡ ፈጥኖ መከታተልና መያዝ ትውልዱን ለመታደግ ይረዳል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሕግ ተቋማት እገዛ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡›› የምትለው ወይዘሪት ጽዮን፣ ‹‹ላግዛት›› አሁን የጀመረውን ሥራ በቀጣይም ወደ ሌሎች ትምህርት ቤቶች የማስፋት እቅድ እንዳለው አስታውቃለች፡፡ ‹‹ተማሪዎች የሀገር ተረካቢ ዜጎች ስለሆኑ ጤናማ ዜጎችን ለሀገር ማስረከብና ጤናማ ዜጎች ሀገር እንዲረከቡ ማድረግ እንፈልጋለን›› በማለት የ‹‹ላግዛት››ን ከሱስ የፀዳ ትውልድ የማፍራትና ለሀገር የማስረከብ ዓላማ ትናገራለች፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *