‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ››

ሚዛን

መቼም ማኅበራዊ ሚዲያ የማያሳየው ጉድ የለም። ለብዙዎች የነፃ ንግግር መብታቸው እንዲከበር ያደረገውን ያህል በዚያኑ ልክ የብዙዎቹ ድብቅ አሉታዊ ባህሪ ጎልቶ እንዲወጣም አድርጎታል። ከሁሉ በላይ ግን ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገው በሁላችንም ውስጥ የተደበቀውን አምባገነንነት ባህሪ ነው። ይህን ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም። ለረጅም ጊዜ የማኅበራዊ ሚዲያ ውይይታችንን አስተውዬ ነው።

እኔ የምደግፈውን ካልደገፍክ፣ የምቃወመውን ካልተቃወምክ ብሎ የሚበሻሸቀው ሰው ቁጥር አንድና ሁለት አይደለም። ሕዝባችን ይሳደበዋል አይገልጸውም። የስድቡ እና የእርግማኑ ዓይነት እጅን በአፍ ያስጭናል። ልብ አድርጉ መቃወም መብት ነው። መቃወም እና መሳደብ መሀከል ግን ሰፊ ልዩነት አለ። የብዙዎች ተቃውሞ ሳይሆን ስድብ ነው። ስድቡ ደግሞ አጸያፊ ከመሆኑ የተነሳ ይሄ ስድብ ሃይማኖተኛ ነው ከሚባል ሕዝብ የሚወጣ አይመስልም። ያሳፍራል። የበለጠ አሳፋሪው ነገር ደግሞ አንድን ሰው ሆን ብሎ ለመጉዳት ቤተሰብ ላይ ሳይቀር የሚወርደው ስድብ ዘግናኝ ነው። የሞተ ዘመድ አዝማድ ሳይቀር ይሰደባል። ይህ ጸያፍና ነውር ነው። ይህ ክብረ ነክ ነው።

የሚገርመው ነገር ሕዝባችን ስለ በነፃነት ሀሳብን መግለጽ ሲሟገት በጣም ኃይለኛ ነው። ሁሌም መንግሥትን የሚተቸው በዚህ ነው። እገሌ ብዕር ብቻ ነው የያዘው፤ ብዕር የያዘን ሰው ማሰር ፍርሀት ነው ምናምን ይልሀል። ነገር ግን የመናገር ነፃነትን በመቀማት ከመንግሥት ይልቅ ማኅበረሰብ ራሱ ይቀድማል። ሁሉም ሰው የመናገር ነፃነት መከበር አለበት ብሎ የሚያምነው እሱ ሲናገር ወይም እሱ ሊናገር የፈለገውን ሌላ ሰው ሲናገርለት ነው። ከዚያ ውጪ የመናገር ነፃነት እሱ መስማት ለማይፈልገውም ሀሳብ እንደሚሠራ አይገነዘብም ወይም ሆን ብሎ ይክዳል። ይሄ የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴያችን ያጋለጠው ሀቅ ነው።

ዴሞክራሲ በባህሪው ከስር እየተገነባ የሚሄድ እንጂ ከላይ የሚሰጥ አይደለም። እኛ ግን ከቤታችን ያላሳደግነውን ዴሞክራሲ ነው ከመንግሥት ቢሮ የምንፈልገው። ቤቱ እየተኮረኮመ ያደገ ሰው ቢሮ ሄዶ በነፃ ሀሳብ የሚያምን ይሆናል ማለት ዘበት ነው። ሕዝብ እርስ በርሱ አንዱ ሌላውን በሀሳብ እየሞገተ ሲያድግ ዴሞክራሲ ያብባል አልያም ግን አንዱ ሌላውን እየጠለፈ እና እያሸማቀቀ የሚቀጥል ከሆነ ዴሞክራሲ እንኳን ሊያብብ እንዲያውም ለአምባገነን መንግሥት መፈጠር በር ሊከፍት ይችላል።

እርግጥ እንደ ሕዝብ ካሉብን ችግሮች መሀከል እኛ ሊኖረን የሚገባውን ነገር በሙሉ ከመንግሥት መጠበቅ አንዱ ነው። ለምሳሌ ያህል የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል እንፈልጋለን። ነገር ግን የልጃችንን ደብተር ለማየት፤ የቤት ሥራ ለማሠራት፤ ለማስጠናት ፍላጎት የለንም። የትምህርት ጥራት ግን የብዙ ነገር ድምር ውጤት ነው። ካላስጠናን፤ የቤት ሥራ ካላሠራን፤ አጋዥ መጽሐፍትን ካላቀረብን፤ እንዳይርባቸው ካላደረግን፤ አእምሮአቸው ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩር ካላገዝን፤ ውሎአቸውን ካልተከታተልን ልጆች ትምህርት ቤተ ውስጥ ብቻ በሚደረግ ሥራ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም። ያን ሳናደርግ ግን ስለ ትምህርት ጥራት ብናወራ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ የሚለው ተረት በእኛ ላይ ይፈጸማል።

ሁላችንም ፍትህ እንዲሰፍን እንፈልጋለን። ፍርድ ቤት እኛ በምናውቃቸው ሰዎች ላይ የሚወስነውን እያንዳንዱን ውሳኔ እንከታተላለን፤ የፖሊስን ችግር እንነቅሳለን፤ አቃቤ ሕግ ብዙ ችግር እንዳለበት እንዘረዝራለን። እኛ ያለ ጥፋታቸው ታስረዋል ለምንላቸው ሰዎች እንዲህ ስንሟገት ላየን ሰው ስለ ፍትህ ያለን ተቆርቋሪነት በጣም ከፍተኛ ሊመስለው ይችላል። ነገር ግን በዚያው ልክ ባለሥልጣን ዘመድ ካለን ተማምነን ኢ ፍትሀዊ ነገር ስናደርግ ቀዳሚዎቹ እኛ ነን። ለፖሊስ እና ለአቃቤ ሕግ ጉቦ ሰጥተን ክስ ስናዘጋም ማንም አይበልጠንም። ሌላም ሌላም። እኛ በግላችን ጉዳይ የማናደርገውን ነገር መንግሥት ግን ወንጀል ፈጽመዋል በሚላቸው ሰዎች ላይ እንዲፈጽም እንጠብቃለን።

የብዙዎቻችን ስድቦችም ተቀባይነት የላቸውም። ደግሞ በጣም አስነዋሪ ነገር አንድን ሰው ለሠራው ሥራ ቤተሰቡን አብሮ የመውቀስ አዲስ ባህል ነው። በጣም አስነዋሪ ነው። ልጅን በአባቱ ጥፋት መውቀስ፤ ሚስትን በባሏ ጉዳይ መተቸት፤ እህትን በወንድሟ ጉዳይ ማንጓጠጥ በጣም ጸያፍ ልማድ ነው። ይሄ ኢትዮጵያዊ ባህሪ አይደለም። እንኳን በዚህ ዓለም በሕይወት የሌለችን ቀርቶ በሕይወት ያለውንም ቢሆን እሱ በሌለበት ባላረገው ጉዳይ ስሙን ማንሳት አስነዋሪ ባህሪ ነው።

ልብ አድርጉ፤ የምናወራው በሕዝብ ደረጃ እያዳበርነው ስለመጣነው አምባገነንነት ነው። ይህ አዲስ ባህል አደገኛ ነው። አምባገነን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት አይኖረውም። በፌስቡክ ላይ የሌለውን ዴሞክራሲያዊ ውይይት በምክር ቤት ልናገኘው አንችልም። ይህ የሚያመለክተን ነገር ቢኖር እኛ ራሳችን በነፃነት ሀሳብን የመግለጽ መብትን እያፈንን መንግሥት ግን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር እንደምንፈልግ ነውና እያስተዋልን ያለነው።

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 10/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *