የኪነጥበብ ሥራዎች ሀሳቦችን በአልባሳት ዲዛይን ላይ የመግለጽ ጥበብ

 ባህላዊ አልባሳትን ዲዛይን በማድረግ ትታወቃለች። ወደ ዲዛይኒንግ ሙያን የገባችው ከሁለት ዓመት በፊት ነው። የዲዛይኒንግ ሙያ የልጅነት ፍላጎቷ ነው። ዲዛይነር ሌሊሴ ሙሉጌታ። ሌሊሴ በትምህርቷ ገፍታ በጤናው ዘርፍ በነርሲንግ ሙያ ተምራ ብትመረቅም፣ ውስጣዊ ፍላጎቷ አይሎ የዲዛይኒንግ ሙያ ምርጫዋ ሆኖ በዲዛይኒንግ ሙያ ውስጧን እየገለጸች ትገኛለች።

‹‹ዲዛይኒንግ ሙያን እንድመርጥ ያደረገኝ የውስጤን ሀሳብ በዲዛይን መግለጽ ስለምችል ነው፤ የምወደው ሙያ ስለሆነ ነው» የምትለው ዲዛይነር ሌሊሴ፣ የዲዛይኒንግ ሙያ ፍላጎት በውስጧ ያደረው በልጅነቷ እናቷ የሚሠሯቸውን የእጅ ሥራዎች በመመልከቷ መሆኑን ትገልጻለች። እሳቸውን እየተመለከተች በማደጓ ሙያው እንዴት ሊሻሻልና ሊያድግ ይችላል የሚል ሀሳብ ይዛ መነሳቷን ትገልጻለች።

ባህላዊ አልባሳት ባህላዊነታቸውን ሳይለቁ በተሻለ መንገድ ተሠርተው በቀላሉ ለተጠቃሚ እንዲቀርቡ ማድረግ ይቻላል የምትለው ዲዛይነር ሌሊሴ፣ የዲዛይኒንግ ሙያዋን ተጠቅሞ ባህላዊ አልባሳት ሁሉም ሰው ሊለብሳቸው በሚችል መልኩ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ተሠርተው እንዲለበሱ ለማድረግ ጥረት እያደረገች መሆኑን ትናገራለች።

አሁን ላይ በዲዛይኒንግ ሙያ ገና ጀማሪ ነኝ የምትለው ዲዛይነር ሌሊሴ፣ የዲዛይን ችሎታዋን ተጠቅማ ውስጧ ያለውን ሀሳብ በአልባሳት በመግለጽ ውብና ማራኪ አልባሳትን እየሠራች ትገኛለች። የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ዘመናዊና ፋሽንን የተላበሱ እንዲሆኑ አድርጋ ትሠራለች።

ዲዛይነሯ የባህላዊ አልባሳት ኮሌክሽንን ወደ ፋሽን ተቀይሮ ሊለበሱ እንዲችሉ ዲዛይን ማድረግ እንደምትችል ነው የምትናገረው። ባህላዊ አልባሳቱ መጀመሪያ ላይ ባህላዊነታቸውን ሳይለቁ በኮሌክሽን መልክ ተሠርተው እንዲለበሱ እንደምታደርግ ጠቅሳ፤ የተለያዩ አካባቢዎችን የባህል አልባሳት ኮሌክሽን በመውሰድ ባህላዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ፋሽን ሆነው እንዲወጡ አድርጋ እንደምትሠራቸው ነው የምትገልጸው።

ባህላዊ ኮሌክሽኖች ሁለገብ ሆነው ለሁሉም ሰዎች በሚሆን መልኩ ሊሠሩ እንደሚችሉ፣ ለሙዚቃ፣ ለፊልም እና ለተለያዩ ዝግጅቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ትናገራለች። በተለይ ለሙዚቃ፣ ለፊልም እና ለትላልቅ ዝግጅቶች በሚያስፈልጉ አልባሳት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሠራ ዲዛይነር ሌሊሴ የምትገልጸው።

ዲዛይነሯ፤ ዘፈን ሲሠራ በዘፈኑ ውስጥ የተነሱ ሀሳቦችን በአልባሳት መግለጽ ይቻላል ባይም ናት። ዘፈኑ ውስጥ የተገለጸውን አካባቢ አኗኗር፣ አለባበስና አመጋገብ ካጠናች በኋላ ሀሳቡን ዲዛይን በማድረግ ያንን አካባቢ ሊገልጹ የሚችሉ አልባሳት ትሠራለች። የአልባሳቱን ኮሌክሽን ሰዎች ሲመለከቱ ይህ ልብስ የዚህ አካባቢ ነው ለማለት እንዲችሉ አድርጋ እንደምትሠራ ጠቅሳ፤ ዘፈኑ ውስጥ የተገለጸውን መልዕክት አልባሳቱ እንዲናገሩ ለማድረግ ጥረት ታደርጋለች።

‹‹በዘፈን፣ በመዝሙር፣ በፊልም እና በተለያዩ በዓላት ላይ የሚለበሱትን አልባሳት በሙሉ እሠራለሁ›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ እስካሁን በብዛት የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ላይ አተኩራ እንደምትሠራ ትገልጻለች። የሌሎች አካባቢዎችን አልባሳት እንደምትሠራ ጠቁማለች። በኪነጥበብ ዘርፍ ለዘፈን፣ ለመዝሙር እና ለፊልም የሚሆኑ አልባሳት ስትሠራ እያንዳንዳቸውን ሥራዎች ካዳመጠች በኋላ በሥራዎቹ ውስጥ የተገለጹ ሀሳቦች ወደ ራሷ ሀሳብ በማምጣት ሀሳቡን ወደ ዲዛይን በመቀየር በአልባሳቱ እንደምትገልጽ ትናገራለች።

አሁን ላይ በቋሚነት ከተለያዩ መዝናኛ /ኢንተርቴይንመንት/ አዘጋጆች ጋር በመሆን ሥራዎቿን እንደምትሠራ የምትገልጸው ዲዛይነሯ፤ በዚህም ብዙ ዘፈኖችና መዝሙሮች መሥራቷን ነው የጠቀሰችው። ለአብነትም የኦሮሞ ታዋቂ የኪነጥበብ ሥራዎችን ከሠሩት አርቲስቶች የሌንጮ ገመቹ፣ የዲንቂሳ ደበላ፣ ፈልመታ ከበደ የዘፈን ሥራዎችን በአልባሳት ዲዛይን ማድረጓን ትናገራለች። በፊልሙ ረገድ በሀገሪቱ በተካሄዱ የኪነጥበቡ ዘርፍ ሽልማቶች (አዋርዶች) ላይ የተወሰኑ ሰዎች አልባሳትን ዲዛይን መድረጓንም ጠቅሳለች።

ዲዛይነሯ እንዳለችው፤ የምትሠራቸው አልባሳት ዋጋ እንደዲዛይኑ ዓይነት ይለያያል፤ አልባሳቱ መልዕክት እንዲኖራቸው (መናገር እንዲችሉ) ትኩረት ተደርጎባቸው የሚሠሩ ስለሆነ ዲዛይን በማድረግ በኩል አንድ ቀን እና ከዚያም በላይ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ፤ ዋጋው የሚቀመጠው እንደሚሠራው ዲዛይንና እንደሚወስደው ጊዜ ነው። በቀላሉ የሚሠራና የተለመደ ልብስ ሲሆን፣ ዋጋውም ተመጣጣኝ ሆኖ ሁሉም ሰው ሊገዛው የሚችል ዓይነት ይሆናል።

አብዛኛው የምትሠራቸው የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት በመሆናቸው ለኢሬቻ፣ ለዘመን መለወጫ፣ ለፋሲካ እና ለመሳሰሉት በዓላት እንዲሁም ለተለያዩ ዝግጅቶች ተፈላጊ ናቸው። በተለይ የኢሬቻ በዓል ማድመቂያ በመሆናቸው ለኢሬቻ በዓል ተፈላጊነታቸው ይጨምራል፤ በዚህ ወቅት ከሁለት ወር በፊት ቀደም ብላ ትዕዛዝ በመቀበል በርካታ አልባሳትን ትሠራለች።

‹‹አሁን ላይ በዓለም ደረጃ በአልባሳት ላይ ያለውን ዲዛይን እየተመለከትኩ ተወዳዳሪ ሊያደርጉኝ የሚችሉ ሥራዎችን እየሠራሁ፤ ሥራዎቼን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በማቅረብ እይታን እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እያደረኩ ነው›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ በአሁኑ ወቅትም በሀገር ውስጥ በሚዘጋጁ ትርኢቶች (ሾዎች) ላይ በመሳተፍ ሥራዎቿን እያቀረበች መሆኑን ትገልጻለች። በቀጣይ እነዚህ ዲዛይኖች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲያገኙ ለማድረግም ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

አሁን ላይ ለስድስት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠሯን ጠቅሳ፤ ለቀጣይም ሥራዎቿን ስታስፋፋ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደምትችል ትናገራለች።

በሰፊው ሥራዎችን አስፋፍቶ ለመሥራት የሚያስችሉ ቁሳቁስና መስሪያ ቦታዎች ያስፈልጋሉ የምትለው ዲዛይነሯ፤ እነዚህ ነገሮች በተገቢ ሁኔታ ተሟልተው ሥራው ቢሠራ ብዙ አልባሳትን ማምረት እንደሚቻልም ነው ያመለከተችው፤ ሁሉም ሰው ባህላዊ አልባሳትን በሚፈልገው መጠን ገዝቶ መጠቀም ይችላል ትላለች።

በዚህ ሙያ ችሎታ እያላቸው፤ የሥራ ላይ ልምድ እያላቸው መሥራት የሚችሉ ሰዎች በመሥሪያ ቦታ እጦትና በቁሳቁስ ረገድ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር እንዳይቀይሩ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ነው የምትገልጸው። ሰፊ የመሥሪያ ቦታና ቁሳቁስ ማግኘት አቅምን እንደሚጠይቅ ጠቅሳ፣ በዚህ በኩል የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ትኩረት ሰጥተው ቢሠሩ የተሻለ መሥራት ይቻላል ብላለች።

የፋሽን ኢንዱስትሪው እንደሀገር እንዲያድግ ከተፈለገ የመጀመሪያው የአልባሳቱ ተጠቃሚ ኅብረተሰብ የሚሠራውን ዲዛይን ተቀበሎ በጎ ምላሽ መስጠት እንደሚኖርበት አስገንዝባ፣ ኅብረተሰቡ ይህን ማድረግ ከቻለ ዲዛይኑን ለሚሠራው ዲዛይነር አቅምና ጎልበት ሊሆን እንደሚችልና ተሰጥኦና ችሎታውን ተጠቅሞ ሌሎችንም ሥራዎች እንዲሠራ እንደሚያበረታተው አመልክታለች።

‹‹የአልባሳቱ ተጠቃሚ የሚሰጠኝ ማበረታቻ ትልቅ ኃይልና ጉልበት ስለሆነኝ ነው ችሎታዬን ተጠቅሜ ብዙ ነገሮች ለመሥራት የቻልኩት›› የምትለው ዲዛይነሯ፤ በተለይ በራሳቸው ጥረት የፋሽን ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እየተጉ ያሉ ሰዎችን በማበረታታት ረገድ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አስታውቃለች። ይህ ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻልም ነው የገለጸችው።

 ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 10/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *