ማርታ ወንዱ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በጂንካ ከተማ ነው፡፡ በ2010 ዓ.ም ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቋንቋ ‹ፎክሎር› ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝታለች፡፡ የተማረችው ትምህርት በባህል ዘርፍ ተቀጥራ ለመስራት የሚያስችላት በመሆኑ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ካልሆነም በዞኑ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ውስጥ ተቀጥራ ለመስራት ፍላጎት ነበራት፡፡ ይሁን እንጂ እንዳሰበችው ፍላጎትዋን ማሳካት አልቻለችም፡ ፡
ከተመረቀች አንድ ዓመት ሊሞላት ጥቂት ወራት ብቻ የቀሯት ሲሆን፣ እስካሁን ስራ አላገኘችም፡፡ ማርታ ተወልዳ ባደገችበት አካባቢ ስራ ባለማግኘቷ አዲስ አበባ ከተማ መጥታ ስራ በመፈለግ ላይ ትገኛለች፡፡ ማርታ እስካሁን ሥራ ላለማግኘቷ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ስለ ተመረቀችበት የትምህርት ዘርፍ ያላቸው እውቀት አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ትናገራለች፡፡ እርስዋ በተማረችበት የትምህርት ዘርፍ በፌዴራል፣ በክልል ወይም በዞን ደረጃ የሚወጣ ክፍት የስራ ቦታ አለመኖሩን ታነሳለች፡፡ በአካል ሄዳ የጠየቀቻቸው ተቋማትም የትምህርት ዘርፉን እንደማያውቁ ገልጸውላታል።
አልፎ አልፎ የሚወጣው የሥራ ማስታወቂያም ቢሆን ልምድ ላላቸው ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከርሷ በፊትና ከርሷ ጋር የተመረቁ በርካቶች ስራ አጥ ለመሆን መገደዳቸውን ትናገራለች፡፡ እንደ ማርታ ማብራሪያ እያንዳንዱ መስሪያ ቤት ሳይንሱን ለሚያውቁትና በዘርፉ ለተመረቁት ቅድሚያ መስጠት ይገባ ነበር፡፡ በተለይ የመንግስት ተቋማት በተለምዷዊ አሰራሮች በመጠመዳቸው ሳይንሱን ለሚያውቁ ሰዎች ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ በዘርፉ ሙያው የሌላቸውን ሰዎች በሌሎች መስፈርቶች እንዲቀጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ሳይንሱን ለተማሩት አዳዲስ ምሩቃን የመቀጠር እድል እንዳይኖር እያደረገ ነው፡፡ የሙያ ዘርፎች አለመታወቃቸው ተመራቂዎች ስራ እንዳያገኙ ምክንያት እየሆነ ነው በማለት የማርታን ሃሳብ የሚያጠናክረው ደግሞ በአማራ ክልል የአዊ ዞን ነዋሪ ወጣት ዘለቀ አብዬ ነው።
ዘለቀ በ2009 ዓ.ም ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በ‹ፐብሊክ ሪሌሽንና አድቨርታይዝመንት› ወይም በህዝብ ግንኙነትና ማስታወቂያ የትምህርት ዘርፍ ተመርቋል፡፡ እስካሁን ድረስ በተማረው ትምህርት ስራ አላገኘም። የትምህርት ዘርፉ በድርጅቶችና በግለሰቦች ዘንድ አለመታወቁ ስራ ላለማግኘቱ ምክንያት እንደሆነ ይናገራል፡፡ እርሱ እንዳለው በፌዴራልና በክልል ከተሞች አካባቢ ስለ የህዝብ ግንኙነት ያለው ግንዛቤ የተሻለ ነው፡፡ በታችኛው እርከን ላይ ግን ለሙያው ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው። በፌዴራልና በክልል ከተሞች አካባቢ ተዘዋውሮ ስራ እንዳያፈላልግ ደግሞ ለትራንስፖርትና ለተለያየ ወጪ የሚሆን የገንዘብ ችግር አለበት፡፡
በዚህም ምክንያት ሥራ ማግኘት አልቻለም፡፡ ዘለቀ ከጓደኞቹ ጋር ተደራጅቶ በ‹ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ› ዘርፍ የግል ስራ ጀምሮ ነበር፡፡ በወቅቱ ስራውን ለመጀመር ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል፡፡ ውጣ ውረዶችን አልፎ ስራ ቢጀምርም እንኳ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በስራው ስኬታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ ተደራጅተው ስራ ላይ ከገቡ በኋላ አብረው ይሰሩ የነበሩ የአይሲቲ ተቋማት በራሳቸው ፍላጎት ውል በማቋረጣቸው ነው ውጤታማ ሊሆን ያልቻለው፡፡ አዳዲስ ስራዎችን ለመጀመር ሙከራ ቢያደርግም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ አልቻለም፡፡ድጋፍ የሚያደርግ አካል አለመኖሩም ሌላው ተግዳሮት እንደሆነ ይናገራል፡፡
በ2009 ዓ.ም ከወሎ ደሴ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ልቦና ‹ሳይኮሎጂ› የተመረቀው መካሽ ወንድሰው ነዋሪነቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ነው፡፡ እርሱ ደግሞ ሥራ ላለማግኘቱ የትምህርት ዘርፉ ባለመታወቁ ብቻ ሳይሆን፣ የቅጥር መስፈርቱም መፈተሽ እንዳለበት ይናገራል፡፡ በጉቦ መስፈርት አድርገው የሚቀጥሩ ተቋማት መኖራቸውንና በዚህ ምክንያትም የተማሩና ችሎታ ያላቸው የሥራ ዕድል የማያገኙበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳል፡ ፡ እርሱ በሚኖርበት መተከል አካባቢ ክፍት የስራ ቦታ ማስታውቂያ ሲወጣ አለማየቱንም ተናግሯል።
አሰራሩ ለእርሱና ትምህርታቸውን ጨርሰው ሥራ ለሚፈልጉ ምቹ ባለመሆኑ ሥራ ለማግኘት እንዳላስቻላቸው ያስረዳል፡፡ በክልሉ የተለያየ ምርት በማምረት የሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ቢኖሩም ኩባንያዎቹ ለአካባቢው ነዋሪ ሳይሆን፣ የራሳቸውን ሰራተኞች ይዘው ነው ወደ አካባቢው የሚመጡት። ይህ ደግሞ መሬታቸውን ለልማት የሰጡትንም ተጠቃሚ እያደረጋቸው እንዳልሆነ ይናገራል። መሬታቸውን ለልማት የሰጡ ልጆቻቸው በኩባንያዎቹ ውስጥ ተቀጥረው መጠቀም ሲኖርባቸው ግን አልሆነም፡፡ መካሻ በአካባቢው ሥራ አጥ ወጣቶች እያሉ ከሌላ ቦታ ሰራተኞችን ማምጣት ተገቢነት አለው ብሎ አያምንም፡፡ ተገቢነት የጎደለው አሰራር ነው ይላል፡፡
እንደ መካሽ ማብራሪያ፤ ተደራጅቶ ለመስራት ፍላጎት ቢኖረውም ስራ ለመጀመር የሚያስችል ገንዘብ ሊያገኝ ባለመቻሉ ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባት አልቻለም፡፡ በምህንድስና የተመርቁ አንዳንድ ጓደኞቹ ሥራ ባለማግኘታቸው በንግድ ስራ ለመሰማራት ነበር እንደ አማራጭ የወሰዱት። ግን ለሥራ መነሻ የሚሆን የገንዘብ ብድር ባለማግኘታቸው የትም መድረስ አልቻሉም፡፡ በተመሳሳይ ብድር የጠየቁ ሌሎች ጓደኞቹም በቂ የሆነ የገንዘብ ብድር ስላልተፈቀደላቸው ሥራ መፍጠር ባለመቻላቸው ከቤተሰባቸው ጋር ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡
ማርታ እንደምትለው ከሆነ፤ የምሩቃን እንግልትን ለመቀነስ በማህበረሰብ ደረጃ የትምህርት ዘርፎችን ወይም አይነቶችን ማስተዋወቅ ባይቻል እንኳ የመንግስት ተቋማት በዩኒቨርሲቲዎች ስላሉት የትምህርት ክፍሎች ወይም ዲፓርትመንቶች መረጃው እንዲኖራቸው ሊደረግ ይገባል። ዩኒቨርሲቲዎች በራሪ ወረቀቶች አዘጋጅተው የሚያስተምሩትን የትምህርት አይነቶች ማስተዋወቅ አለባቸው፡፡ ይህ ቢደረግ እያንዳንዱ ተቋማት በዩኒቨርሲቲዎች ስላሉ የትምህርት ክፍሎች መረጃው ይኖራቸዋል፡፡ ግንዛቤው ሲፈጠር በተገቢው ቦታ ተገቢውን ባለሙያ ቅጥር ይከናወናል፡፡ያለስራ የሚቀመጡም አይኖሩም፡፡ የሚማረው የሰው ኃይልና ገቢው እንዲጣጣምም ከዩኒቨርሲቲዎች ብዙ ይጠበቃል፡፡
ጥናትን መሰረት አድርገው የሰው ኃይል ቢያመርቱ የተማረው ኃይል ያለሥራ እንዳይቀመጥ ይረዳል ስትል ማርታ አስተያየት ሰጥታለች፡፡ የአዊው ዘለቀ በበኩሉ፤ ለስራ አጦች ከብድር፣ ከመስሪያና ማምረቻ ቦታ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች ሊቀረፉ ይገባል፡፡ መንግስት ወጣቶችን አደራጅቶ ወደ ስራ ከማስገባት ባሻገር ተደራጅተው ሥራ የጀመሩ ወጣቶች በሥራ ላይ የሚያጋጥማቸውን ችግሮች በየጊዜው ተከታትሎ ችግሮችን በመፍታትና በመደገፍ ማገዝ እንደሚጠበቅ ተናግሯል፡፡ ሁሉም በሚኖርበት አካባቢ ያለ አድልኦ ተወዳድሮ የሚሰራበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል የሚለው ደግሞ መካሽ ነው፡፡ ‹‹ሥራ ለመቀጠር ሃይማኖት፣ ብሄር ወይም ጎሳ መስፈርት መሆን የለበትም፡፡
ችሎታው ነው መስፈርት መሆን ያለበት›› የሚለው መካሻ ተቋማት ግልጽ ማስታውቂያ በማውጣት ሙያተኞችን በችሎታቸው መቅጠር እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ አድሎና የህግ ጥሰት የሚፈጽሙ አካላትም በህግ መጠየቅ አለባቸው ብሏል፡፡ በተለያየ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የኩባንያ ባለቤቶችም ቅድሚያ ፋብሪካቸውን ላቋቋሙበት አካባቢ እንዲሰጡ መደረግ እንዳለበትም ተናግሯል፡፡ በተለይም ኩባንያዎቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ለአካባቢው ወጣቶች ሥራ እንደሚፈጥሩ ከመንግሥት ጋር ውል የሚገቡበት ሁኔታ ቢፈጠር ጥሩ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ 45 ዩኒቨርሲቲዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ የትምህርት ተቋማት በየአመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ ይመረቃል፡፡ የተማረው ኃይል ወደ ሥራ ካልገባ ደግሞ በኢኮኖሚና በማህበራዊ የሚያስከትለው ቀውስ ቀላል እንደማይሆን መገመት አያዳግትም፡፡ በመሆኑም ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ መፍትሄው ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑም ባለድርሻ አካላትም የመፍትሄው አካል መሆን ይጠቅባቸዋል፡፡ የትምህርት ተቋማትም ከገበያው ጋር የሚጣጣም ትምህርት መስጠታቸውን መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በመላኩ ኤሮሴ