በሞያቸው የእንስሳት እርባታ ዓለም አቀፍ ተመራማሪ ናቸው። በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለ28 ዓመታት ሲያስተምሩ ቆይተዋል። የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲን ለማቋቋም የዩኒቨርሲቲው መሥራች ፕሬዚዳንት ሆነው ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል። በዩኒቨርሲቲዎች ለበርካታ አመታት ከሠሩ በኋላ ዓለምአቀፍ የምርምር ፈቃድ ተሰጥቷቸው ከሞያው ጋር ተያያዥ ከሆነ ከዓለምአቀፍ የቆላማ አካባቢዎች የግብርና ምርምር ሥራ ማዕከል (ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር አግሪካልቸራል ሪሰርች ኢን ድራይ ኤሪያ) ጋር ምርምር በማካሔድ ላይ ናቸው።
የዓለምአቀፍ ተመራማሪው የተወለዱት በድሮ ጎጃም ክፍለ አገር በአሁኑ አዊ ዞን ጓትሳ ሺጉዳድ ወረዳ ዛላ ቀበሌ ነው። ነጋዴ አባታቸው ቲሊሊ አካባቢ ወሰደዋቸው በቲሊሊ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የመካከለኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዊ ዞን ግምጃቤት ተምረዋል። የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር በነበረው በቀድሞ አጠራሩ የዓለምማያ እርሻ ኮሌጅ ገብተው በእንስሳት ሳይንስ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ለሁለት ዓመታት በአምቦ አካባቢ ግብርና ላይ ሲሠሩ ቆይተው፤ የኖርዌ መንግሥት ወጪያቸውን ሸፍኖላቸው በታንዛኒያ ሶኬኔ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዳጠናቀቁ ጅማ እርሻ ኮሌጅ በመምህርነት የተቀጠሩ ሲሆን፤ ከመምህርነት በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት ኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ሲሠሩ ቆይተዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ክፍል ኃላፊ፣ የኮሌጅ ምክትል ዲን፣ የግብርና ኮሌጅ ዲን ሆነው ካገለገሉ በኋላ ወደ ሕንድ በማቅናት በሕንዱ ናሽናል ዲዬሪይ ሪሰርች የሦስተኛ ዲግሪያቸውን በዚሁ በእንስሳት እርባታ ላይ ሠርተዋል።ከሕንድ ተመልሰው ወደ ጅማ በማቅናት የማኅበረሰብ አቀፍ እና የድህረ ምረቃ ከፍተኛ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። የጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማኅበረሰብ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ እያሉ፤ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ መስራች ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል።
ዩኒቨርሲቲውን ከማስገንባት ጀምረው ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንዲጀምር በማስቻል ከፍተኛውን ሚና መጫወታቸው ይነገራል። ከእኚሁ ጉምቱ ተመራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላይ ጋር ዩኒቨርሲቲው የተገነባበትን ሁኔታ፣ በሙያቸው የእንስሳት እርባታ ላይ እና አጠቃላይ ምርምርን በተመለከተ ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- የነጋዴ ልጅ እንዴት የእንስሳት እርባታ ተማሪ እና ተመራማሪ ሆነ? ከሚለው እንጀምር፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡– የአባቴ አባት በጣሊያን ወረራ ጊዜ ነው የሞቱት።በዚህ ጊዜ አባቴ 10 አመቱ ነበር። አባቴ በእንጀራ አባት ሲያድግ የተማረው ድቁናን እንጂ ዘመናዊ ትምህርት አልነበረም።አባት ያላቸው የእርሱ ጓደኞች ዘመናዊ ትምህርት ሲማሩ፤ እርሱ ግን መማር እየፈለገ ለመማር አልታደለም። ስለዚህ ከግብርናው በመቀጠል ወደ ንግድ ገባ። መማር እየፈለገ ሲነግድ ኖረ። ስለዚህ እርሱ ያጣውን ትምህርት ልጆቹ እንዲያገኙ ይፈልግ ነበር።
ወደ አስመራ እና ወደ አዲስ አበባ በመኪና 110 ኩንታል ዕህል ሲጭን በመመዘን እና ገንዘብ በመቁጠር ለማገዝ እሞክር ነበር። ጓደኞቼ ወደ ንግድ ሲገቡ፤ እኔም ወደ ንግድ ለመግባት ስሞክር ነበር፤ ነገር ግን አባቴ ፊት አይሰጠኝም ነበር። ክረምት ላይ ንግዱን ሳግዘው እርሱ ግን አይፈልግም ነበር።በመጨረሻ ፍላጎቴን እያየ እስከ መራገም ደረሰ። ‹‹ለሰው ልጅ መልካሙ ነገር ንግድ ሳይሆን ትምህርት ነው።ንግድም ቢሆን የሚያምረው ሲማሩ ነው›› እያለ በትጋት እንድማር ይገፋኝ ነበር።በዚያ ምክንያት እኔም ወደ ትምህርቱ አዘነበልኩ፤ በኋላ አባቴም በጣም ደስተኛ ሆነ።
በጊዜው አጠቃላይ ብሔራዊ ፈተናን 300 እና 400 ልጅ ተፈትኖ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት 7 እና 8 ልጆች ብቻ ነበሩ። እኔም ከ7ቱ መካከል አንዱ በመሆኔ በጣም ተደሰተ። እኔም በትምህርቴ መደሰት ጀመርኩኝ። አባቴ ሦስተኛ ዲግሪዬን እስከምጨርስ በሕይወት ኖሮ አይቷል፤ ከዓለም ድካም አርፏል። በዚህ ምክንያት የነጋዴ ልጅ ብሆንም ወደ ትምህርቱ አዘንብያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እሺ አሁን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንግባ፤ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች በተለይ የአንደኛው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ነባሮቹ ከኮሌጅ ተነስተው ያደጉ ናቸው።እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ግን በአንድ ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ከሆኑ የአራተኛው ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንደኛው ነው።እስኪ አመሠራረቱ እንዴት ነበር?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- አዎ! የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የምሥረታ ሂደት በተለያየ ፈርጅ ይታያል። የመጀመሪያ ትውልድ የሚባሉት እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህርዳር እና ጅማ ዩኒቨርሲቲ የተመሠረቱት ከእርሾ ነው። ለምሳሌ ጅማ እርሻ ኮሌጅ ነበር። የጅማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅም ነበር። በዲፕሎማ እና በዲግሪ የሚያስመርቁ ሁለት ኮሌጆችን አንድላይ በማድረግ የመጀመሪያ ትውልድ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተቋቋመ።
የሁለተኛ ትውልድ፣ የሦስተኛ ትውልድ እና የአራተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ግን በአብዛኛው የተመሠረቱት ከምንም ነው። ምንም እርሾ በሌለበት ማኅበረሰቡ ወይም የአካባቢው አስተዳደር ብቻ መሬት ያዘጋጃል። በጊዜው ለዩኒቨርሲቲዎች እስከ 200 እና ከዚያ በላይ ሄክታር መሬት ይሠጥ እና ዩኒቨርሲቲ ይገነባ ነበር።በወቅቱ በየአካባቢው ተደጋጋሚ የዩኒቨርሲቲ ይገንባልን የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ።መንግሥት ደግሞ ጥያቄውን ተቀብሎ ዞኖችን አወዳድሮ በአዋጅ ዩኒቨርሲቲ እንዲቋቋም ውሳኔ ያስተላልፋል።
የዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ከተመደበ በኋላ ቦርዱ ፕሬዚዳንት መልምሎ ይመድባል። በዚህ ሂደት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ተቀጣሪ እና መስራች ፕሬዚዳንት ሆኜ ሥራ ጀመርኩ። በቅድሚያ 200 ሄክታር መሬት ከተረከብኩ በኋላ፤ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የአስተዳደር ፕሬዚዳንቶችን እንዲሁም የሰው ሀብት፣ የግዢ፣ የፋይናንስ እና የተማሪዎች አገልግሎትን የመሳሰሉትን የመቅጠር ኃላፊነት ተሰጠኝ።
የመጀመሪያው ሥራ ከሲቪል ሰርቪስ ጋር በመገናኘት መዋቅር እንዲፀድቅ ማድረግ ነበር። በጊዜው ብቻዬን ብሆንም የሌሎች ዩኒቨርሲቲ ሰዎችን እና ቦርዱን በመጠቀም መዋቅሩን አስፀደቅኩኝ። በመቀጠል ምክትል ፕሬዚዳንቶችን እና ሌሎችም የኃላፊነት ቦታ የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ላይ ሰዎች ከተቀጠሩ በኋላ፤ ቅጥሩን እያሰፋን ቀጠልን። ለምሳሌ በቅድሚያ 50 እና 100 ሰው በወር እና በሁለት ወር ቀጥረን ከሆነ፤ ትንሽ አረፍ ብለን በድጋሚ እየቀጠርን ቀጠልን።
ሁለተኛው ሥራ የተሰጠንን መሬት ሕጋዊ አድርጎ ማጠር ነው።ቦታው ሰፊ ሲሆን በሃሳብ ይህን ያህል ነው ከማለት ውጪ፤ የተከለለ አልነበረም። ስለዚህ ምልክቶችን በማድረግ የዩኒቨርሲቲው መሬት መሆኑን ማረጋገጥ ስለሚያስፈልግ መሬት ከተገኘ በኋላ ወደ መሠረተ ልማት ተገባ።መሠረተ ልማት ሲባል የተማሪ መማሪያ፣ ማደሪያ እና መመገበያ እንዲሁም ቤተመጽሐፍትን የመሳሰሉ ሕንፃዎችን ከመገንባት ጀምሮ መሥራት ተጀመረ።
ሕንፃው ብቻ ሳይሆን ዋናው ትልቁ ነገር መንገድ፣ ውሃ እና መብራትን እንዲሁም ቴሌኮሙኒኬሽንን የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች እየተሰላሰሉ ይቀጥላሉ። ይህ በእውነቱ በኢትዮጵያ የቢሮክራሲ ሂደት እነዚህን ነገሮች ማሳካት ቀላል አልነበረም። ሕንፃዎችን ማስገንባትም በተመለከተ በመጀመሪያው ዙር ወደ 12 ተቋራጮች ነበሩ። የሠራተኛ ቅጥርን በተመለከተም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር አብረን ስንሠራ ቆይተናል። ሠራተኛው ተቀጥሮ ግንባታ ተካሒዶ፤ መብራት፣ ውሃ እና ኢንተርኔትን ጨምሮ ለማስተማር ብቁ መሆናችን ሲረጋገጥ በ2010 ዓ.ም ተማሪ መቀበል ጀመርን።
አዲስ ዘመን፡-እንዴት በሁለት ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ቻላችሁ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ሁሉንም ነገር በሙሉ ጥርት አድርገን በሁለት ዓመት ውስጥ ማጠናቀቅ ችለናል። ምክንያቱም ተቋራጮቹ አስራ ሁለት ነበሩ። አንዱ አንድ ትንሽ እና ትልቅ ሕንፃ ሲይዝ፤ ሌላኛው ውሃ አስገብቶ ይዘረጋል። ሌላኛው ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ይረባረባል።ሁሉም ተከፋፍሎ ወደ ሥራ ገብቷል።
አዲስ ዘመን፡- ተማሪን ለመቀበል በሁለት ዓመት ውስጥ ስንት ሕንፃ ገነባችሁ? የኅብረተሰቡ አቀባበል ምን ይመስል ነበር?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡– መኝታው፣ መማሪያው እና ቤተመጽሐፉ በአጠቃላይ ወደ 18 ሕንፃዎች ተገንብተው ነበር። ከዚህ ሁሉ በኋላ በ2010 ዓ.ም ታኅሣሥ ላይ ወደ አንድ ሺህ 500 ተማሪዎች ተቀብለን ማስተማር ጀመርን። ለአንድ ወር ካስተማርን በኋላ ዩኒቨርሲቲው ሥራ መጀመሩን በተመለከተ እና የተማሪዎች አቀባበል በሚል ማኅበረሰቡ ጥር 12 ቀን ትልቅ ፕሮግራም አዘጋጀ።
ለበዓሉ የከተማዋ ባለሀብቶች በሬ ገዝተው ሰጡ። ወጣቶች ተደራጅተው ሕዝቡን አስተባብረው ገንዘብ በማምጣት፣ በግ እና በሬ በማቅረብ ተሳትፈዋል።እድሮችም ለዩኒቨርሲቲው ምርቃት ብለው በበኩላቸው በሬ አቅርበዋል። በጣም የሚገርመው በዚያ ጊዜ በመንግሥት አቅም አጥር ለማጠር በመቸገራችን ‹‹ዩኒቨርሲቲ እንዴት ያለአጥር ይታያል?›› ብለው የመጀመሪያውን ወደ ስምንት ኪሎ ሜትር የሽቦ አጥር የሠሩት በመዋጮ የአካባቢው ማህበረሰብ ነው።
በበዓሉ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የወቅቱ አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ እና ብዙ ሚኒስትሮች፣ የክልል አመራሮች እና በሙሉ ባለሥልጣናት እንጅባራ ነበሩ። ኅብረተሰቡ የፈረስ ጉግስ ባህሉ በመሆኑ የፈረስ ጉግስ በማቅረብ በዓሉ ያማረ እና የደመቀ ሆኖ ተጠናቋል። ኅብረተሰቡ በሙሉ ልቡ የዩኒቨርሲቲው መገንባት አስደስቶት ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ስትጀምሩ ኮሌጆቹ እና የትምህርት ክፍሎቹ ምን ያህል ነበሩ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ፡- መነሻችን አራት ኮሌጆች ናቸው። ተፈጥሮ ሳይንስ፣ የማህበራዊ ሳይንስ፣ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ነበሩ። አንዳንዱ ሦስት አንዳንዱ አራት በአጠቃላይ ወደ 16 እና 17 አካባቢ የትምህርት ክፍሎችን በማዘጋጀት ተማሪዎችን ከፋፍለን ማስተማር ጀመርን።
አዲስ ዘመን፡- ከሕንፃ ግንባታው ባሻገር በአዲስ ዩኒቨርሲቲ ከዜሮ ጀምሮ መምህራንን ጨምሮ አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችን መቅጠር ፈተና እንደሚኖረው አያጠያይቅም። እዚህ ላይ እንዴት እንደነበር ያብራሩልን።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ትክክል ነው። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሁለት የሠራተኛ ዓይነት አለ። አንደኛው የአስተዳደር ሠራተኛ ሲሆን፤ ሌላኛው መምህር ነው።የአስተዳደር ሠራተኞችን በማስታወቂያ ቀጠርን። ዩኒቨርሲቲ ስሙም ጥሩ በመሆኑ በአካባቢው ከዞን እና ከሌሎች የመንግሥት ተቋማት ልምድ ያላቸው ተወዳድረው እና የቅጥር መስፈርቱን አሟልተው ወደ ዩኒቨርሲቲው ተቀላቀሉ።
የመምህራን ጉዳይ የመጀመሪያው መምህር ራሴ ነበርኩኝ። ምክትል ፕሬዚዳንቶቹም ያስተምሩ ነበር።በመቀጠል ግን መምህራኑን ያሟላነው በሁለት መንገድ ነው። የትምህርት ሚኒስቴር ቀድሞ ዕቅድ ስለነበረው ከሁለት ዓመት በፊት ቀድሞ በመጀመሪያ ዲግሪ ጥሩ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲማሩ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው ሥራ ሲጀምር ከ100 በላይ የሚሆኑትን መምህራኖች የትምህርት ሚኒስቴር ለዩኒቨርሲቲው አቀረበ። ነገር ግን ተመራቂዎቹ ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖራቸው ከትምህርት ቤት በቀጥታ የመጡ ናቸው። የሥራ ዓለም ልምድ አልነበራቸውም። ይህ ቀላል ችግር አልነበረም።
ሁለተኛው እነርሱ በቂ ስላልነበሩ ማስታወቂያ በማውጣት መምህራን እንዲፈተኑ እና ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ የትምህርት ክፍል ፍላጎቶችን ለማሟላት ችለናል። ፈተናውን በተመለከተ ለየት ያደረግነው፤ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የካበተ ልምድ ያላቸውን መምህራን በፈታኝነት እንጋብዝ ነበር። ለምሳሌ አምስት የአካውንቲንግ መምህር ከተፈለገ ከጎንደር፣ ከባህርዳር፣ ከደብረማርቆስ፣ ከጅማ እና ከሌሎችም ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ መምህራን ይፈትኑ ነበር።
ፈተናው አንደኛ ቃለመጠይቅ ሲሆን፤ ሌላው የአስተማሪነት ብቃትን ለማወቅ አንድ የትምህርት ክፍል ወስደው በፋይናንስ ከሆነ ተፈታኞች ፈታኞችን እንደተማሪ በማሰብ ትምህርቱን እንዲያስተምሩ በማድረግ በመስፈርቱ ነጥብ ተሰጥቷቸው ይመዘናሉ፤ ይለያሉ።ሌላው የሁለተኛ ዲግሪያቸው ላይ ወይም የቆዩ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከነበሩ የሠሯቸው ምርምሮች ይኖራሉ፤ ስለዚህ ምርምራቸውን ያቀርባሉ።በመጨረሻም በማስተማር ስልታቸው፤ በቃለመጠይቅ እና በምርምር ምርጥ የሆኑት ይቀጠራሉ። ስለዚህ በአጠቃላይ ከትምህርት ሚኒስቴር በተገኙት መምህራን እና በቅጥር የመለመልናቸውን አጣምረን ወደ ማስተማር ገብተናል።
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ የገጠማችሁ ፈተና ምን ነበር?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ይህንን ስናደርግ አንዱ ፈተና ዩኒቨርሲቲው ሲመሠረት ከቦታው የተነሱ ገበሬዎች ነበሩ። መጀመሪያ ከነበረው መሬት በተጨማሪ እኔ ሞያዬም ከእርሻ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ቀድሞ ከነበረው 200 ሔክታር በተጨማሪ ተራራውን ጨምሮ 125 ሔክታር መሬት እንዲካተት አድርጌያለሁ። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲው በ325 ሔክታር ላይ የተቋቋመ ሲሆን፤ በዚህም ብዙ የልማት ተነሺ ገበሬዎች ነበሩ።
ገበሬዎቹ መሬታቸውን አስረክበውናል። ነገር ግን የተሠጣቸው ካሳ በጣም ትንሽ በመሆኑ ማድረግ ያለብንን ተወያይተን ለተነሺዎቹ ልዩ ድጋፍ ተመቻቸ። አንደኛው ራሳቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው በዩኒቨርሲቲው ሥራ ውስጥ መግባት እንዳለባቸው ወሰንን።በዚህ ምክንያትም ወደ 260 የልማት ተነሺ ሲሆን፤ ቢያንስ ከየቤተሰቡ አንዳንድ ሰው ወደ ሥራ እንዲገባ አድርገናል። ለምሳሌ በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው በዩኒቨርሲቲው የአረንጓዴ ልማት ላይ ይሰማራሉ። እነዚህ ሰላሳ እና አርባ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሌላው ዩኒቨርሲቲው የምግብ ግብዓት ያዘጋጃል፤ እነርሱ ደግሞ ሥራ ይሠራሉ። ማብሰል እና ፅዳት እንዲሁም ጥበቃ እና ሌሎችም የተለዩ ወደ ሰባት የሚደርሱ የሥራ ዘርፎች ላይ እነኚህ ወደ 260 የተጠጉ አርሶ አደሮች በልዩ ሁኔታ ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዲቀላቀሉ አድርገናል። ይህ ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰቡ ተቀባይነት እንዲኖረው እና እንዲወደድ አድርጓል። ይህ የሆነው ዩኒቨርሲቲው ከኋላ በመፈጠሩ እና የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን ተሞክሮ በማየታችን ነው።
እኔ ሥራውን ስጀምር ከእኔ በፊት የነበሩትን የሦስተኛ እና የአራተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎችን በሙሉ ያጋጠማቸውን አጥንቼ ነበር። ቅጥር ላይ እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር እንዲሁም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እንዴት እንደሚሠሩ አጠቃላይ የነበረባቸውን ግንኙነት በደንብ አጥንቼ ስለነበር ያንን ማወቄ በጣም ረድቶኛል።
ሁለተኛው በአካባቢው ገበሬው ከወጣ በኋላ ሳር ነበር። በጊዜው በዩኒቨርሲቲው ከብት እርባታ አልነበረንም። ስለዚህ ሳሩን ለሁለት እና ለሦስት ዓመት በነፃ እንዲጠቀሙ አድርገናል። ይህ በጣም ትልቅ ነገር ነው።ሌላው የገበሬዎች ልጆች ሆነው የመማሪያ መስፈርቱን የሚያሟሉ ከሆነ ያለምንም ክፍያ ወጪያቸው ተሸፍኖላቸው የማታ እንዲማሩ ይደረግ ነበር። የድሃ ድሃ የሚባሉት የእነዚያው የገበሬዎች ልጆችን በዶሮ እርባታ በማደራጀት ራሳቸውን እንዲችሉ ጥረት ተደርጓል።አሁንም የዶሮ እርባታው ቀጥሏል።በዚህ ምክንያት አንድም ቀን በዩኒቨርሲቲው እና በአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል ግጭት እና ቁርሾ አልነበረም።
ይህንን አካሔድ በመከተላችን በጊዜው አጥር የሌለው ዩኒቨርሲቲ ምንም ዓይነት ሌብነት አላጋጠመውም። በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ያጋጠመው ችግር እንጅባራ ዩኒቨርሲቲን አላጋጠመውም። እንዲያውም የአካባቢው ማኅበረሰብ በየዓመቱ ድግስ እየደገሰ ይጠራናል። የእኛ ድርሻ ልብስ ለብሶ መቅረብ ነው። ይህ እጅግ የሚያኮራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዩኒቨርሲቲው ምስረታ ወጣ ብለን ወደ ምርምር እንግባ። በእርግጥ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምሮችን ያካሒዳሉ።ነገር ግን የሚያካሂዷቸው ምርምሮች ወርደው የማኅበረሰብን ሕይወት ከመቀየር አንፃር ክፍተት አለባቸው በሚል በተደጋጋሚ ወቀሳ ይሰነዘራል።እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡– በኢትዮጵያ ደረጃ እንደዩኒቨርሲቲዎቻችን ብዛት፣ እንደሕዝባችን ቁጥር፣ በአቅማችን ቢሆንም እንደሚመደበው በጀት ብዙ ህትመት የለም። ከአውሮፓ ቀርቶ ከኬንያን እና ከደቡብ አፍሪካ አንፃር ስናየው በቂ አይደለም። ያም ሆኖ ደግሞ በመምህራን እና በተመራማሪዎች በኩል በግብርና ሚኒስትርም ሆነ በዩኒቨርሲቲዎች ህትመት አለ።
ህትመቶች በመኖራቸው በጣም ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም አንደኛ ህትመቱ በሀገራችን ሁኔታ የሁለተኛ ዲግሪም ሆነ አንደኛ ዲግሪ የሚማሩ እንደአቅማቸው ምርምር ሲያካሂዱ የታተመውን ምንጭ ሊደርጉት ይችላሉ። ያ ባይኖር ኖሮ የሕንድን ወይም የአሜሪካን ወይም የጃፓንን ያጣቅሱ ነበር። ይህ ማለት በእኛ ሀገር ተቀባይነቱ እና ተፈላጊነቱ እስከዚህም ይሆናል። ስለዚህ ምርምሩ የወደቀ አይደለም። ነገር ግን ይህ በቂ አይደለም። ከምርምሮቹ ውስጥ ወደ ማኅበረሰቡ መሔድ ያለባቸው አሉ። ሁሉም ግን ወደ ማኅበረሰቡ መሄድ አለበት ማለት አይደለም።
150 የምርምር ህተመቶች ቢኖሩ ሁሉም ቴክኖሎጂ ወይም ሁሉም አሠራርን የሚቀይሩ አይደሉም። ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ አሠራርን ወይም ፖሊሲን የሚቀይሩ ከሆነ ለምሳሌ የግብርናን ምርት እና ምርታማነት ከፍ ለማድረግ የሚጠቅም ከሆነ መልካም ነው።ነገር ግን በዚህ ረገድም ሲታይ ውስንነት አለባቸው። ለምሳሌ ዘርን ብንወስደው የምርምር ውጤት ነው። የማዳበሪያ አጠቃቀም የምርምር ውጤት ነው።እንስሳትን መቀለብ የምርምር ውጤት ነው። በዚያ ረገድ ጥረቶች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም። ነገር ግን እያንዳንዱ የሚያሳትመው ሰው አንዷን እንኳን መሬት ላይ ሳያደርስ ከቀረ ይህ በጣም አደገኛ ነው። 150ውን መሬት ያድርስ አይደለም፤ ቢያንስ አንድ ሁለቱን ምርምር የኅብረተሰቡን ምርት እና ምርታማነት ከፍ እንዲያደርግ አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት።በዚህ ረገድ የተሳካላቸው ጥቂት ሰዎች አሉ። በአብዛኛው የተሳካላቸው አይደሉም። ስለዚህ ይህንን ለማድረግ በትክክልም ምርምሩ ሲሠራ ከመጀመሪያው አንስቶ ከማኅረሰብ አንፃር መታቀድ አለበት።
ተመራማሪዎች ምርምሩን ሲያካሂዱ ከማሳተም ባሻገር በተግባር ፖሊሲ የሚያስቀይር፤ የገበሬውን ምርታማነት የሚያሻሽል፣ የጤና ሁኔታን የሚያሳድግ ተብሎ መጀመሪያ መታቀድ አለበት። እንዳልኩት በዚህ ረገድ የተሳካላቸው አሉ። ያልተሳካላቸውም አሉ። ምርምርን ሼልፍ ማድረግ በየትኛውም ዓለም አለ። በጣም የሚያሳዝነው ግን ጭራሽ ለሼልፍም ያልበቃው ነው። መረጃ ተሰብስቦ ገንዘብ ወጥቶለት ወደ ህትመት የማይደርስ እና ለተማሪዎች እንኳን ማጣቀሻ የማይሆን አለ። መረጃው እያለ ሳይተነተን የጨነገፈ አለ።የሚያሳዝነው ይህኛው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዩኒቨርሲቲም ሆነ በምርምር ተቋማት የተመራማሪው ቁጥር ከፍተኛ ነው። ነገር ግን ምን ያህሉ በምርምር የማኅበረሰብን ሕይወት ቀይሯል? የሚለው አጠያያቂ ነው። ይህ የሆነው በምን ምክንያት ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡– የመጀመሪያው ምርምር ፈንድ በሚደረግበት ጊዜ የማኅበረሰብ ተጠቃሚነት በዕቅድ ውስጥ መግባት አለበት። ህትመት(ፐብልኬሽን) አንዱ መለኪያ ይህንን ገንዘብ ሰጥቼሃለሁ አምስት ህትመት ማምጣት አለብህ ይባላል። ለምሳሌ ሦስተኛ ዲግሪ ስናሰለጥን ህትመት ማሳተም አለበት እንላለን።አምስት የሚታተም ከሆነ አንዱ ማኅበረሰቡን የሚጠቅም መሆን አለበት ተብሎ መጀመሪያውኑ መታቀድ አለበት።
ሁለተኛው ችግር የሚሆነው አንድ ቴክሎጂ ወይም አሠራር ቢወጣም፤ ያንን ተጠቃሚ የሚሆን ለምሳሌ ከግብርና አንፃር ብንወስደው ምርምሩ እና የልማት ባለሞያው መናበብ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ምርምር አለ። የምርምር ውጤት እና ቴክኖሎጂ አለ። የአሠራር ስልት አለ። ይህንን የአሠራር ስልት ደግሞ ተቀብሎ መሬት ላይ የሚያወርድ የልማት ባለሞያው ወይም የግል ዘርፉ በቁርኝት ደረጃ መተግበር አለበት።
ሁለተኛው ሰው መበረታታት ይፈልጋል። አሳትሞ የቆመው ሰው እና አሳትሞ ወደ መሬት ያወረደው ሰው መካከል ልዩነት መኖር አለበት። መሬት ያወረደው ሰው ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል። ዕውቅና በማመስገን ሊሆን ይችላል፤ በገንዘብ ሊሆን ይችላል። ወይም ሌላ አካባቢ ሄዶ እንዲያይ የመሳሰሉ ማበረታቻዎች መኖር አለባቸው።
የኢንዱስትሪ እና የዩኒቨርሲቲዎች ትስስር አናሳ መሆንም ምርምር የማኅበረሰቡን ሕይወት እንዳይቀይር ያደርጋል። በሌሎች ሀገሮች ኢንዱስትሪው ችግር ይዞ ይመጣል። ይህንን ፍታልኝ ብሎ ለዩኒቨርሲቲው ገንዘብ ይከፍላል። ኢንዱስትሪው እንዲታከም ዩኒቨርሲቲው መድኃኒቱን በምርምር ያገኛል። ስለዚህ ቅንጅት ያስፈልጋል የሚል ሃሳብ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ምርምር ብዙ ጊዜ እና ከፍተኛ ጉልበት የተለየ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል።ከዚህ አንፃር ሰልጥነዋል ተብለው የሚጠቀሱ ሀገራት ለምርምር በጀት ከመመደብ አንስቶ የሚሰጡት ትኩረት ከፍተኛ ነው።ምንም እንኳ የሀገሪቱ የዓቅም ሁኔታ ቢታወቅም በትክክል ለምርምር የሚሰጠው በጀት በቂ ነው ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- እዚህ ላይ እኔ በተገላቢጦሽ የምርምር ገንዘብ የሚገኘው ከመንግሥት ብቻ ነው? የሚል ጥያቄን ማንሳት እችላለሁ። የምርምር ገንዘብ የሚገኘው ከመንግሥት ብቻ አይደለም። የሌሎች ሀገሮችም ተሞክሮ ይህንን አያሳይም። የምርምር ገንዘብን ከሦስት አቅጣጫ ማግኘት ይቻላል። አንደኛው እና ትልቁ ከመንግሥት ነው።ሁለተኛው ከልማት አጋሮች ነው። ይህ በውድድር የሚገኝ ሲሆን፤ ፕሮፌሰሮች እና ተመራማሪዎች ከሌሎች ሀገሮች ጋር ተወዳድረው የሚያገኙት ገንዘብ አለ።ሦስተኛው የገንዘብ ምንጭ ኢንዱስትሪው ነው።ከላይ እንደገለፅኩት የኢንዱስትሪውም በትስስር የሚገኝ ነው።
እነዚህን ሦስት ነገሮች አጣጥመን መሔድ አለብን። በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ በሦስቱም መልክ ውስንነት አለብን። መንግሥት በቂ ገንዘብ መመደብ ብቻ ሳይሆን፤ ይህንን ገንዘብ የምመድበው ይህንን ውጤት እንድታመጣ ነው የሚል ተጨባጭ ነገር የመጠየቅ ውስንነት አለበት። ሁለተኛው የባለሙያው ልምድ እና ተወዳዳሪነት ነው። ከእነኚህ ከልማት አጋሮች ጋር ተነጋገሮ ለማምጣት ውስንነት አለ። በሦስተኛ ደረጃ የኢንዱስትሪ ትስስሩ አናሳ ነው። ስለዚህ ሁሉም ድርሻ አለው፤ ችግሩ ሁሉን አቀፍ ነው፤ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ደግሞ በተለየ መልኩ በእርሶ ዘርፍ ያለውን ጉዳይ በተመለከተ እንነጋገር።ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ግንባር ቀደም ከሆኑ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር ተጠቃሽ ሀገር ናት።በተቃራኒው በዚህ ሀብቷ ተገቢውን ጥቅም እያገኘች ስላለመሆኑ እና ብዙዎች በዚህ እንደሚቆጩ ይነሳሉ።ለዚህ ምላሾት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- እርግጥ ከቁጥር አንፃር ከሆነ ኢትዮጵያ ትልቅ ቁጥር ያለው የእንስሳት ክምችት አላት።ይህ በትንበያ ነው። ትንበያውን እንውሰድና በሁሉም የእንስሳት ዓይነቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንስሳት አለን፤ እንበል።ነገር ግን ምርት እና ምርታማነታቸው ከዚህ በላይ መሆን አለባቸው ብለን ስናይ ብዙ ጊዜ የምንሳሳተው በወተት፣ በስጋ እና በእንቁላል ብቻ ስለምንመዝን ነው። የእኛን ሀገር ከውጭው ለየት የሚያደርገው እርሱ ነው።
እርሻው ዘርፍ ላይ ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚሆን አርሶ የሚያበላው በሬ ነው። ይህ መታወቅ እና መደነቅ አለበት።ብዙ ጊዜ የእንስሳት ምርት እና ምርታማነት ላይ ይህ ስሌት ውስጥ አይገባም። በዕቅድም ላይም ወተት እና ስጋ ብቻ ይጠቀሳል። ሁለተኛው ገበሬው በጣም የሚጠቀምበት ከስጋ፣ ከወተት በተጨማሪ እንስሳት ገንዘብ ናቸው። ለምሳሌ በግ እና ፍየልን ማንሳት ይቻላል። እነዚህ ለትንንሽ አርሶ አደሮች ልክ እንደ ኤቲ ኤም ናቸው። ሲቸግራቸው በአስቸኳይ ይሸጧቸዋል።
የስጋ፣ የወተት፣ የእርሻ፣ የፈጣን ገንዘብ ማግኛ ሆነው ግን የእንስሳትን ሀብት ጥቅም በትክክል እየተመዘነ አይደለም።ይህ በመንግሥት ደረጃም የታየ ነው።በዚህ ምክንያት ለዚያ የምንሰጠው ትኩረት ከሰብል ያነሰ ነው። እንደእኔ መላምት እነዚህ ሁሉ ነገሮች አንድላይ መጥተው ጥናት ቢካሔድ በቂ ትኩረት ባያገኝም ለእዚህች ሀገር የእንስሳት አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛ ነው። ነገር ግን በዚህ ደረጃ አልታየም።ትኩረት ባለመስጠታችን እየተንጠላጠልን ያለነው የውጭ ዝርያ በማምጣት ያለመዱትን አካባቢ በግድ እንዲለምዱ እያደረግን ነው።
የውጭ ላሞች ሀገራቸው ላይ 30 እና 40 ሊትር ወተት ያመርታሉ ይባላል። ከቻይና የመጣ ወፍጮ ቻይናም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ 50 ኩንታል ሊፈጭ ይችላል። ከእንስሳት አንፃር ግን የሀገሩን በሬ በሀገሩ ሰርዶ እንደሚባለው ነው። እንስሳቱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ማሽን ባለመሆናቸው ውጤቱ ተመሳሳይ አይሆንም።ስለዚህ እዚሁ ያሉ እንስሳትን በመምረጥ እና በማሻሻል፣ የእንስሳት መኖን በማዘጋጀት እና የገበያ ትስስር በመፍጠር የእንስሳትን ምርት እና ምርታማነት ከፍ ማድረግ ይቻላል።
አሁን እየሠራሁበት ያለው መስሪያ ቤት ከዓለምአቀፍ የቆላማ አካባቢዎች የግብርና ምርምር ሥራ ማዕከል (ኢንተርናሽናል ሴንተር ፎር አግሪካልቸራል ሪሰርች ኢን ድራይ ኤሪያ) ትልቁ አላማው የሀገር በግ እና ፍየልን እዚያው ቤታቸው ላይ እያሉ ማሻሻል ነው። ላለፉት አስር ዓመታት ይህ ፕሮግራም እየተካሔደ ነው።ወደ ሁለት መቶ መንደሮች እና ቀበሌ ገበሬ ማህበራት አሉ። አንድ መንደር 100 ገበሬዎችን ይይዛል። ይህንን ሥራ ስናከናውን ሦስት መሻሻሎች ታይተዋል። አንደኛ በዚህ የዝርያ ማሻሻል የታቀፉ ገበሬዎች ካልታቀፉት 20 በመቶ ገቢያቸው አድጓል። አንድ በግ ብቻ ያርድ የነበረ ገበሬ ሦስት በግ ማረድ ችሏል። አንደኛ ገቢ ነው። ሁለተኛ የምግብ ዋስትና ነው።ፋሲካ ወይም መውሊድ ላይ አንድ በግ ሲያርድ የነበረው ገበሬ አሁን ላይ ሦስት በግ ማረድ ችሏል። ይህ የዛሬ አምስት ዓመት የተጠና ጥናት ነው። እዚህ ላይ ከሥራ ፈጠራ ጋር በማቀናጀት መኖን ብናዘጋጅ የእኛን እንስሳት ማሻሻል እንችላለን።
ገበሬው የምትፈልገው የስንዴ ማሳህን ነው ወይስ በሬህን የሚል አማራጭ ቢቀርብለት፤ መልሱ ሁለቱንም እፈልገዋሁ የሚል ነው። ባለሞያው ግን የሚሻልህ ስንዴ ነው ይለዋል። ነገር ግን እውነቱን ለመናገር በሰብልም ያን ያህል አልተሻሻልንም። ከውጭ የምናስመጣው ወተት ብቻ አይደለም። ስንዴንም ሆነ ሩዝን ከውጭ እናስመጣለን። ጤፍን የምናስመጣበት አጥተን እንጂ እናስመጣ ነበር። ስለዚህ ግብርናው በእንስሳት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሁሉን አቀፍ ችግር አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ችግር መኖሩን ካመንን መፍትሔው ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡– የመጀመሪያው መፍትሔ የመሬት ስሪታችን መታየት አለበት። መሬት የመንግሥት እና የሕዝብ ነው ይላል።ይህንን በደንብ ማየት ይፈልጋል።ሁለተኛው ከላይ እንደጠቀስነው ምርምሩ ቴክኖሎጂን አፍልቆ ጥሩ ዝርያ እንዲያመርት መሥራት ያስፈልጋል። ከዚያም ምርታማነቱ ሲጨምር በተለያየ መንገድ አግሮ ፕሮሰሲንግን በመደገፍ ኢንዱስትሪ ማስፋትን ይጠይቃል። ትልቁ ነገር ግብርና ዕውቀት ይፈልጋል። አያቶቻችን እና አባቶቻችን ሀገር በቀል ልምድ አላቸው።ያ የሚናቅ አይደለም፤ ነገር ግን በተጨማሪ ግብርና እውቀት ይፈልጋል።ግብርና ዕውቀት የሌለው ሰው ሥራ መሆን የለበትም፡፡
ገበሬው በደረጃው ዕውቀት ያስፈልገዋል፤ የግብርና ልማት ባለሙያውም ሆነ ተመራማሪው እንዲሁም አግሮ ፕሮሰሰሩ ዕውቀት ያስፈልገዋል። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ዛሬ የልማት ሠራተኛው ገበሬውን የማማከር ብቃቱ አነስተኛ ነው።ይህንን አትረስ፤ በዚህ ሰዓት ጥመድ፤ በዚህ ሰዓት ፍታ ማለት ዕውቀት አይደለም።የገበያ ትስስርም አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከዕውቀት ችግር ባሻገር ግን የልማት ባለሞያው ደሞዙን ብቻ አስቦ ሳይሆን በተጨባጭ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመለወጥ እንዲሠራ ምን መደረግ አለበት?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡– ገበሬው ዕውቀቱን እና ጉልበቱን አጣምሮ በመሬቱ ላይ ውጤታማ እንዲሆን ዕውቀት ያስፈልገዋል። ገበሬውን ደግሞ የሚያሰለጥነው የግብርና ባለሞያ ዕውቀት ያስፈልገዋል። ባለሞያውን የሚያሰለጥነው መምህር ዘመኑን በዋጀ መንገድ የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ዕውቀት ያስፈልገዋል። የሕንድ ዕውቀት አይደለም። የአገራችን ዕውቀት ያስፈልገዋል። ይህንን ደግሞ የሚመራ ተቋም ግብርና ሚኒስቴር፣ ግብርና ምርምርም ሆነ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ሥራ በአግባቡ መምራት አለበት። በአግባቡ መምራት ማለት የበጀት ፣ የገበያ ፣ የሚሰለጥኑ ሰዎችን ማበረታታት ከሁሉም በላይ ደግሞ የብድር ሁኔታ ተገቢውን ትኩረት ማግኘት አለባቸው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግብርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የተሸከመ ቢሆንም ኢንቨስት የሚደረግበት ግን በጣም አነስተኛ ነው። ከትራንስፖርት፣ ከኢንዱስትሪ ጋር ሲወዳደር በጣም ትንሽ ነው። አንድን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ ኢንቨስት የሚደረግበት መጠን ወሳኝነት አለው። የግብርና አነስተኛ ነው። ለሆቴል ግንባታ ብድር ይገኛል።ለግብርና ብድር ለማግኘት ጣጣው ብዙ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይሔንን ቀደም ብለው ከጠቀሱት ከመሬት ሥሪት ጋር ማያያዝ ይቻላል?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- ትንሽ ለየት ይላል።
አዲስ ዘመን፡- ነገር ግን አንድ አርሶ አደር የመሬት ባለቤት ከሆነ መሬቱን አስይዞ መበደር ይችላል፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- አዎ! ዋናው ጉዳይ ግን በየትኛውም ሁኔታ ብድር መገኘት አለበት። ግብርና የተረሳ ሥራ ነው። ለምሳሌ በደጋም ሆነ ቆላም ወደ አፋር፣ ወደ ጋምቤላ፣ ወደ አማራ ክልል ሲኬድ ብዙ መሬቶች አሉ። እነዚህን በግል ዘርፍ መልማት አለባቸው። ደጋው ላይ ብቻ አንድና ሁለት እርሻ ስላለ ግብርናው አያድግም።የግል ዘርፉ ብድር በደንብ ተሰጥቶት ቁጥጥር እና ግምገማ እየተካሄደ አጭበርባሪውን በደንብ ለመግታት መሥራት ይገባል።
ለምሳሌ በ1960ዎቹ በግብርና ሞያ ላይ ያለው ዩኒቨርሲቲ ዓለምማያ ነበር።በግብርና ዲግሪ የጨረሰ ኢንተርፕርነር መሆን የፈለገ ብሔራዊ ባንክ ዲግሪውን አስይዞ መበደር ይችል ነበር።በዚህ ምክንያት እነሁመራ፤ መካከለኛው አዋሽ ፣ ተንዳሆን የመሳሰሉት የለሙት በዚያ ጊዜ ነው።ወደ ሻሸመኔ ቦለቄ እና አኩሪ አተር የተመረተው በዚያ መልኩ ነው።ነገር ግን በ1966 ዓ.ም አብዮቱ ሲፈነዳ እነዛ በጣም ሃብታም እየሆኑ የነበሩት ብላቴናዎች መሬቱ ተወሰደባቸው ብድሩንም አልከፈሉም።
በኋላም ወደ አሜሪካን እና ወደ ሌሎችም ሀገሮች ተሰደዱ።ስለዚህ ግብርና ላይ ውጤታማ መሆን ከተፈለገ ዘርፉን ወደ ፕራይቬታይዜሽን ማዞር ነው።በሆነ መንገድ የግል ዘርፉ ወደ ግብርና ካልገባ በስተቀር የሀገሪቱ ምርት እና ምርታማነት ከፍ አይልም።እንስሳት ብናረባ መዓት ውጤት ማግኘት ይቻላል፤ ስንዴን ብናመርት በጣም ብዙ ዕድል አለ።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ በዋናነት በእንስሳት ዘርፉ ላይ መሠራት አለበት የሚሉት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- የውጭ ዝርያዎችን ማስመጣት የጀመርነው በ1950ዎቹ ነው። በጥቁር እና ነጭ ላሞች ማለት ነው።ነገር ግን የውጭ ዝርያ ያላቸው ከብቶች ዝርያ አሁንም ከአንድ እና ከሁለት በመቶ አላለፉም።ስለዚህ መሆን ያለበት የእኛን የሀገራችንን ዝርያ ማሻሻል ያስፈልጋል። አቅም ያለው እና የአውሮፓን የአሠራር ሥርዓት መተግበር የሚችል ፕራይቬት እንዲሠማራ ማድረግ ነው።እነሳውዲ አረቢያ እና እነእስራኤል በጣም ሞቃት ሀገሮች ቢሆኑም፤ አሁን በወተት ምርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ናቸው። የሚያደርጉት በቤት ውስጥ የአየር ሁኔታውን ከብቶቹን ካመጡባቸው አካባቢዎች የአየር ሁኔታ ጋር አመሳስለው የሚፈለገውን መኖ በማቅረብ ከአሜሪካ እና ከአውስትራሊያ ወተት ማምጣት አቁመው የራሳቸው ምርት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ስለዚህ የእኛን ምርታማነት ማሻሻል ይቻላል።
ሁለተኛ የተመረተው ምርት ላይም ብዙ ነገር አለ። ለምሳሌ ከበግ አንፃር እንመልከት ከተባለ ሐረርም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች ገበሬው አምርቶ መሸጥ አይችልም።ዋጋ የሚቆርጠው ደላላው ነው። ገበሬው በለፋው ልክ አያገኝም፤ ደላላው ሸጦ ብዙ ያተርፋል።ይሔ ደግሞ አያበረታታም።ስለዚህ የገበያም ችግር አለ። መፍትሔው ግን ምርትን ማብዛት ብቻ ሳይሆን የገበያ ትስስር ላይም መሥራት ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2015