አስፈሪው የሌሊቱ ጨለማ ቦታውን ለብርሃን ለቋል። ታዲያ ንጋቱ በወፎች ጫጫታ ሲበሰር ዘወትር በጠዋት ተነስታ አምላኳን የማመስገን ልማድ ያላት ወይዘሮ ጨረቃ ሽፈራው፤ እንደ ሁልጊዜው በጠዋት በጸሎት ቤቷ ተንበርክካ አምላኳን እየተማጸነች ነበር። ጸሎት እያደረገች እያለ ከወትሮው በተለየ መልኩ የግቢያቸው በር በኃይል ተንኳኳ። ይህንን ተከትሎ ቤት ውስጥ ያሉ ውሾች ጩኸታቸው አየለ። ይሄኔ የንጋት ጣፋጭ የእንቅልፍ ዓለም ውስጥ የነበረው ባለቤቷ አቶ ፍፁም ሐጎስ፤ ከእንቅልፉ ባኖ በውስጡ “በጠዋት የምን መርዶ ነጋሪ መጣብኝ እያለ” እያብሰለሰለ የሌሊት ልብሱን እንደለበሰ ወደ ግቢው በር ተንደረደረ። እሱም ወደ በሩ ጠጋ ብሎ በሩን ሳይከፍት “ማን ልበል”? አለ። በሩን በኃይል ሲያንኳኩ የነበሩ አካላትም “ፖሊሶች ነን፣ ጥቆማ ደርሶን ነው፣ ለፍተሻ ይተባበሩን” የሚል ድምጽ አሰሙ። እርሱም “የሕግ አካል ከሆኑማ” ብሎ የገቢውን በር ወለል አድርጎ ይከፍትላቸዋል።
በሩ ሲከፍት ሦስት ሲቪል የለበሱና ዘጠኝ አዲሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የደንብ ልብስ የለበሱ በድምሩ 12 ሰዎች የግቢውን በር አጥረው በተጠንቀቅ ቁመዋል። ከነዚህ ውስጥ አንዷ ሲቪል የለበሰች ሴት ነበረች። አራቱ ደግሞ ክላሽንኮፍ መሳሪያ ታጥቀዋል። አንዱ ደግሞ የወገቡ ቀበቶ ላይ ካቴና ሸብ አድርጓል። የቤቱ አባወራ ይህንን አቋማቸውንና አለባበሳቸውን ሲያይ የሕግ አካላት እንደሆኑ በሙሉ ልቡ ተማመነ። ወደ ቤት ገብተው እንዲፈትሹም ፈቃደኝነቱን ገለጸላቸው።
ይሄኔ 12ቱም ተንጋግተው ወደ ግቢው ይገባሉ። መሳሪያ ከያዙት አንደኛው ውጭ ላይ የቤቱን ጥበቃ ይዞ ቆመ። ሌሎቹ በጓሮ በር በኩል ተንጋግተው ወደ ቤት ገቡ። አንደኛው ሲቪል የለበሰና መሳሪያ የያዘ ግለሰብ አቶ ፍፁም ሐጎስን ወደ መኝታ ቤት አስገብቶ እንዳይንቀሳቀሱ መሳሪያ ይደግንባቸዋል። እርሳቸውን እንዳይንቀሳቀሱ አንድ ክፍል ቤት ካገቱ በኋላ ቀሪዎቹ ተከፋፍለው የተለያየ የቤቱን ክፍሎች መበርበር ጀመሩ። ሲቪል ከለበሱት አንደኛው ግለሰብ “ቶሎ ቶሎ በደንብ አድርጋቹህ ፈትሹ” እያለ በሳሎን ቤት ከወዲያ ወዲህ እየተንጎራደደ ትዕዛዝ ይሰጣል።
አቶ ፍፁም ላይ መሳሪያ የደገነባቸው ግለሰብ “ተጠቁመን ነው፣ ዶላር አምጣ” ይላቸዋል። እርሳቸውም “የደበቅሁት ዶላር የለኝም፣ ሕጋዊ ነጋዴ ነኝ” ይሉታል። ሌላኛው ግብር አበር ደግሞ አይኑን አፍጥጦ ወደ እርሳቸው ተጠጋና “አውቀህ ነው የደበቅከውን አውጣው” ብሎ ጎሮሯቸውን አንቆ መተንፈሻ ያሳጣቸዋል። “የደበቅሁት ነገር የለኝም መፈተሽ ትችላላቹህ” ብለው የቤቱ አባውራ መልስ ይሰጣሉ። የተወሰኑት ግብረአበሮች የቤቱን አባወራ በመኝታ ቤታቸው ጉሮሯቸውን አንቀው እያፋጠጡ በተመሳሳይ ደግሞ ባለቤታቸውን ወይዘሮ ጨረቃ ሽፈራውን፤ መሳሪያ ከያዙት አንደኛው ግለሰብ “የደበቅሽው መሳሪያና ዶላር የት እንዳለ ካስቀመጥሽው ንገሪኝ” ብሎ አፋጦ ይይዛታል። እሷም “እኔ እንኳን የጦር መሳሪያ ለመያዝ ይቅርና ሳየውም እፈራለሁ። ምንም ነገር የለም። ፖሊስ ከሆናቹህ መፈተሽ ትችላላቹህ” ትላቸዋለች።
እነርሱም ሽርኩቻ ሳይቀራቸው ሁሉንም የቤቱን ክፍሎች በርብረው ቤቱን ግልብጥብጡን አውጥተውት በጓሮ በር እየተጣደፉ ወጥተው ይሄዳሉ። ከወጡ በኋላም ነጭ ሚኒባስ መኪና አስነስተው ወደ አያት አቅጣጫ እየከነፉ ሲሄዱ ባልና ሚስት ተደናግጠው የቤታቸው በረንዳ ላይ ቆመው ወዴት አቅጣጫ እንደሚሄዱ እያዩአቸው እያለ ልጃቸው ሰሎሜ ከመኝታ ቤቷ በራ ወላጆቿ ወዳሉበት በመሄድ “ከልጆች መኝታ ቤት የነበሩ ሁለት ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን እንደወሰዱ” ለእናት እና አባቷ ትነግራቸዋለች።
ልጃቸው ይሄንን ዜና እስክትነግራቸው ድረስ ባልና ሚስት የተፈጸመው ድርጊት የዘረፋ ወንጀል መሆኑን አልጠረጠሩም ነበር። ይህንን መርዶ ከሰሙ በኋላ ባልና ሚስት ወደ ቤት ገብተው ምን ምን ንብረት እንደተዘረፉ ሲያረጋግጡ፤ ከመኝታ ቤት ኮመዲኖ ውስጥ የነበረ ባለ 18 ካራት 23 ግራም ወርቅ ግምቱ 50 ሺ ብር የሚያወጣ፤ የልጃቸው የመስመር ስልክ የሌለው አንድ ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ ናይን (Samsung galaxy s9) የእጅ ስልክ ግምታዊ ዋጋው 15 ሺ ብር የሚያወጣ እንዲሁም አንደኛ ፎቅ የልጆች መኝታ ክፍል ኮመዲኖ ላይ የነበሩ ሁለት ዴል (dell) ላፕቶፕ ኮምፒተሮች እያንዳንዳቸው 30 ሺ ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው፤ በአጠቃላይ 125 ሺ ብር የሚያወጣ ንብረት በ22/04/2014 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 12:30 ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ክልል ልዩ ቦታው አያት መንደር ዞን አምስት ፤ መንገድ ዘጠኝ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የግል ተበዳይ በሆነ ባለ አንድ ወለል መኖሪያ ቤት ውስጥ የተደራጁ የወንበዴ ቡድን በመግባት በጦር መሳሪያ የታገዘ ዘረፋ አካሂደው ይሰወራሉ።
ከዘረፋው በኋላ አቶ ፍፁም ቀጥታ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አቅንተው በእለቱ በቤታቸው በመሳሪያ ታጅቦ የተፈጸመውን የውንብድና ወንጀል ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጋሉ። ፖሊስም ወንጀሉ የፈጸሙ አካላት መልካቸው፣ ቁመናቸው፣ አለባበሳቸው፣ ቋንቋቸው፣ ወዘተ. ምን እንደሚመስል ከተበ ዳይና ከአይን ምስክሮች ቃላቸውን ተቀብሎ ወንጀለኞችን ማፈላለጉን ተያያዘው። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ከሶስት ወር ውጣ ውረድ በኋላ ወንጀሉን ፈጽመው ከተሰወሩት ውስጥ አንደኛዋን ተጠርጣሪ በ02/07/2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር አዋለ። ተጠርጣሪዋ ፅጌ ሸለመ ኃይሉ የምትባል ስትሆን፤ ፖሊስ የሰው ምስክሮች ከተጠርጣሪዎች መካከል በፎቶ እንዲለዩ ካቀረበላቸው ምስሎች ውስጥ ይቺ ተጠርጣሪ ወንጀሉን እንደፈፀመች በመጠቆማቸውና የምስክር ቃላቸውን በመስ ጠታቸው ነው።
የተጠርጣሪ የእምነት ክህደት ቃል
ተጠርጣሪ ፅጌ ሸለመ በቅጽል ስሟ ብርክቲ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አሞባ ጉደር ከተማ ውስጥ ከአቶ ሸለመ ኃይሉ እና ከወይዘሮ ጌጤ ገለታ ከተባሉ እናትና አባቷ በ1979 ዓ.ም ተወለደች። እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ከአንደኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል በመዲናዋ ትምህርቷን ተከታትላለች። በ2000 ዓ.ም ትምህርቷን አቋርጣ በጽዳት ሠራተኝነት በተለያዩ ሆቴሎች ስትሠራ እንደነበር ትናገራለች።
ወንጀሉ በተፈጸመበት ቀን ዮናስ ወይም ሚኪ የተባለው ያልተያዘ የወንጀሉ ፈጻሚ ግለሰብ የሚዘረፍ ቤት እንዳለ በስልክ ደውሎ ያሳውቃታል። እሷም ወንጀሉን ለመፈጸም ተስማምታ ባልቻ ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት ተገናኝተው ከሌሎች ያልተያዙ የወንጀሉ ፈጻሚዎች ጋር በአንድ መኪና ወደ ግል ተበዳይ ቤት ያቀናሉ። በግል ተበዳይ ቤት እንደደረሱ “ፖሊሶች ነን” ብለው የገቢ በር ካስከፈቱ በኋላ ወላይታው የተባለው ያልተያዘው የወንጀሉ ፈጻሚ ግለሰብ ተበዳይን በቦክስ ትክሻው ላይ ደጋግሞ በቦክስ በመምታት እንዲፈራ ያደርጋል።
ከዛ ተበዳይ እንዲፈራ ከተደረገ በኋላ ቤቱን በመበርበር “ሌሎች ተጠርጣሪዎች ሞባይልና የአንገት የወርቅ ሀብል ሲወስዱ ባላይም፤ በቁጥር ሁለት አይነታቸው ዴል (dell) ሲልቨር አልሙኒየም ከለር ያላቸው የዋጋ ግምታቸው ብር 60 ሺ የሆኑ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን አንደኛ ፎቅ መኝታ ቤት ውስጥ ስበረብር ሳገኛቸው ሁለቱንም ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች አንስቼ ቦርሳዬ ውስጥ ከትቻለሁ። ከግቢው እንደወጣን ሚኪያስ ወይም ዮናስ የተባለው ግለሰብ ላፕቶፖቹን ተቀብሎኛል።
ላፕቶፖቹ በ07/05/2014 ዓ.ም በግምት 3:00 ሰዓት አካባቢ የካ ክፍለ ከተማ የተባበሩት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተሽጠው፤ ሚኪ ወይም ዮናስ በመባል የሚጠራው የወንጀሉ ፈጻሚ ግለሰብ ሁለት ሺ ብር እንደሰጣት” ትናገራለች። እሷም የዘረፋ ወንጀሉን መፈፀሟን አምና ጥፋተኛ ነኝ ስትል ለፖሊስ የእምነት ክህደት ቃሏን ሰጥታለች። ፖሊስም የተጠር ጣሪዋን የእምነት ክህደት ቃል፣ የምስክሮችን እና የተበዳይን ቃል አደራጅቶ ዐቃቢ ሕግ ክስ እንዲመሰርትባት መረጃውን አቅርቧል።
ዐቃቢ ሕግ
የ1996 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ) እና 671 (1) (ሀ) እና (ለ) የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሽ ፅጌ ሸለመ በጦር መሳሪያ በመታገዝ በሰው ወይም በንብረት ላይ ወንጀል ለመፈጸም የተደራጀ የወንበዴ ቡድን ጋር በመሆን የማይገባትን ብልጽግና ለራሷ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ከላይ በተጠቀሰው ቀንና ቦታ አራት ክልሽንኮቭ መሳሪያ ከያዙ፣ ዘጠኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ደንብ ልብስ የለበሱና ሁለት የሲቪል ሰው አለባበስ የለበሱ በድምሩ 11 ሰዎች ጋር በመሆን የግል ተበዳይ በሆነው በአቶ ፍፁም ሐጎስ ቤት በመሄድና በር በማንኳኳት በሩ እንዲከፈት ያደርጋሉ። በሩ ከተከፈተ በኋላ “ፖሊሶች ነን፣ ተጠቁመን ነው፣ ቤቱን እንፈትሻለን” በማለት ያልተያዘ ግብረአበሯ “ተበዳይን መሳሪያና ዶላር አምጣ” በማለት የያዘውን መሳሪያ ተበዳይ ላይ በመደገን አንገቱን አንቆ በመያዝ ተከሳሿና ሌሎች ያልተያዙት የወንጀሉ ፈጻሚዎች የተበዳይን ቤት በርብረዋል።
በብርበራውም ተከሳሿ ፅጌ ሸለመ በቁጥር ሁለት አይነታቸው ዴል (dell) የዋጋ ግምታቸው ብር 60 ሺ የሆኑ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን በማንሳት ይዛው በነበረው ቦርሳ በመክተት ስትወስድ፤ ሌሎች ግብራበሮቿ የዋጋ ግምቱ 50 ሺ ብር የሆነ ባላ 18 ካራት 23 ግራም ወርቅ እና 15 ሺ ብር የሚገመት ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ ናይን (Samsung galaxy s9) የእጅ ስልክ በድምሩ 125 ሺ ብር የሚያወጡ ንብረቶችን በመውሰድ መኪና ውስጥ በመግባት የተሰወሩ በመሆኑ ተከሳሽ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀመችው የከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ተመስርቶባታል።
ዐቃቢ ሕግም ሰባት የሰው ማስረጃ፣ ምስክሮች ተከሳሽን ከሌሎች ተጠርጣሪ ግለሰቦች መካከል ሲመርጡ የሚያሳዩ ምስሎችንና ተከሳሽ በወ/መ/ስ/ህ/ቁ 27(2) መሰረት ለፖሊስ የሰጠችውን የእምነት ክህደት ቃል በማስረጃነት አያይዞ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። ዐቃቢ ሕግ የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቦ በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ በተከሳሿ ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል።
ውሳኔ
የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ፅጌ ሸለመ ኃይሉ ክስ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ተከሳሽ በ12 (በአሥራ ሁለት) ዓመት ጽኑ እስራትና ከማናቸውም ሕዝባዊ መብቷ እንድትታገድ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2015