ውልደቱና እድገቱ በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ነው፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በዚያው በአስመራ የተማረ ሲሆን፣ ከደርግ ውድቀት በኋላ ግን ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ቀሪ ቤተሰቦቹ ወዳሉበት ወደ ትግራይ በ1987 ዓ.ም መጣ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተማረው በዓደዋ ንግሥተ ሳባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡
በወቅቱ የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤቱ ለኮሌጅ የሚያበቃና በጊዜው ደግሞ አዲስ የተከፈተ የተምቤን የትምህርት ኮሌጅ ቢኖርም ወደኮሌጅ ገብቶ መማርን አልተመኘም፡፡ ይልቁኑ በወቅቱ የኢትዮ-ኤርትራ (የባድሜ) ጦርነት ስለነበር ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን ለመቆም ወሰነ፤ ብቁ የሚያደርገውንም ሥልጠና ወስዶ መከላከያን ተቀላቀለ፡፡ በጦር ግንባርም በመዋል ጦርነቱ በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ በዚያው ቆየ፡፡
ጦርነቱ እንዳበቃ በመከላከያ ቤት ብዙም አልቆየም፡፡ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አዲስ ኑሮ መኖር ጀመረ፡፡ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ የኮሌጅ ትምህርቱን ተማረ፡፡ በዚያው በተማረው ዘርፍም ተቀጥሮ እየሠራ ሳለ የዲቪ ሎተሪ ስለደረሰው ወደ ሀገረ አሜሪካ ተጓዘ፡፡ በዚያም ለ13 ዓመት ያህል የቆየ ሲሆን፣ ዛሬም እየኖረ ያለው በዚያው ነው፡፡ ይህ የዛሬ የዘመን እንግዳችን የማኅበረሰብ አንቂ ናትናኤል አስመላሽ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ተገድዳ የገባችበትን የጦርነት ወቅት በጊዜው የነበረውን የሕወሓትን ሥርዓት በመቃወም ብቻውን ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል፡፡ ከዚህ እንግዳ ጋር አዲስ ዘመን ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርቧል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ናትናኤል ሰላምን የሚረ ዳው እንዴት ነው? ከሚለው ጭውውታችንን ልጀምር?
አቶ ናትናኤል፡- መልካም ነው፤ ለእኔ ሰላም ትልቅ ትርጉም አለው፤ እንዳልኩሽ ተወልጄ ያደግሁት በሀገረ ኤርትራ ነው። ከዚያም በደርግ ውድቀት ምክንያት ወደ ትግራይ ብመጣም ብዙም ሳይቆይ ሀገራችን ወደጦርነት በመግባቷ ሰላምን ማጣጣም አልተቻለም ነበር።
ምንም እንኳ በደርግ ዘመነ መንግሥት ልጅ ብሆንም ሕወሓት ወደሥልጣን ከመጣ በኋላ ቢያንስ በኢትዮጵያ ወደሦስት ያህል ጊዜ ጦርነትን ለማየት ተገድጃለሁ። ከዚህም የተነሳ ጦርነት ባለበት ሰላም አይታሰብምና ሕይወት ማለፉ፣ መፈናቀሉና መጎሳቀሉ የማይቀር ጉዳይ ነው። በተለይም እኔ የብዙ ጊዜ ጥያቄዬ ትግራይ ለምን ድሃ ሆነች የሚል ነበር። ይሁንና በዚያን ጊዜ በልጅ አዕምሮዬ ለጥያቄዬ ምላሽ የሚሰጠኝ ባይኖርም አሁን ግን ምላሹን አግኝቸዋለሁ፤ እሱም ጦርነት ያመጣው ጣጣ ነው ብዬ ደምድሜያለሁ። እንደ እኔ እምነት ትግራይ ወይም አንዱ የሀገራችን ክፍል ድሃ ሆነ ማለት ኢትዮጵያ ድሃ ሆነች ማለት ነው። ስለዚህ ሰላምን የምመርጥበት ዋናው ምክንያት በጦርነት የተነሳ በትግራይ ከበፊቱም ጀምሮ የሚፈናቀል ሕዝብ በማየቴ ነው።
ትግራይ ገጠራማው አካባቢ ያለውን የአኗኗር ዘይቤ ዛሬም አልተቀየረም። ዘመዶቼ የዛሬ 30 እና 40 ዓመት በሁለት በሬ ያርሱ ነበር፤ ዛሬም እንደዚያው ነው። ዛሬም ቢሆን በነበረው ጦርነት ሳቢያ ምን ያህል እንደተጎዱ አስተውያለሁ። ስለዚህ ለእኔ ሰላም ማለት ሕይወት ላለው ፍጥረት ሁሉ በተለይ ደግሞ ለሰው ልጅ የመጀመሪያው ምርጫ ነው ብዬ እንዳስብ የሚያደርገኝ ነው። በተለይ ደግሞ ትግራይ አካባቢ ተወልዶ ላደገ ሰው፣ የጦርነት አስከፊነት በደንብ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንተ የትግራይ ፖለቲካ መለወጥ አለበት ከሚሉት ጎራ ነህ፤ መለወጥ ካለበት ደግሞ ወጣቱም ጭምር ነው የሚሉ አካላት አሉና ወጣቱ መለወጥ ያለበት እንዴት ነው ትላለህ?
አቶ ናትናኤል፡- በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል እያስተዳደረ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ነው፤ ስለዚህ ይህን ጊዜያዊ አስተዳደር ወደድንም ጠላንም መደገፍ አለብን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ምክንያቱም አሁን በጊዜያዊነት ክልሉን እየመሩ ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ ከነበሩ አመራሮች ከሙስናም ከወንጀልም የጸዳ ነው ብዬ አምናለሁ።
አሁን ባለው የትግራይ ፖለቲካ ከድሮው ሥርዓት ተላቅቆ በጊዜያዊ አስተዳደር የተሻለ የክልል መንግሥት ለውጥ ያመጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ከሳምንታት በፊት አቶ ጌታቸው በአማራ ክልል ተገኝተው የአማራን ክልል ጎብኝተዋል። ይህ አካሄዳቸው በራሱ የአማራ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ ጠላት እንዳልሆነና የትግራይ ሕዝብም ለአማራ ሕዝብ ጠላት አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። ስለዚህ ብቸኛው ምርጫ የአቶ ጌታቸው አስተዳደርን መደገፍና ቢያንስ በቀጣዮቹ አምስትና አስር ዓመታት ውስጥ ትግራይ በአዲሱ ትውልድ የምትመራበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። ያለን አማራጭ ይህ ነው።
እንዲያም ሆኖ ግን አቶ ጌታቸው ብዙ ተግዳሮቶች አሉባቸው። ባለፉት 27 ዓመታት በትግራይ ውስጥ የነበረው ፖለቲካ አሳሪ እና ቋጠሮ የበዛበት ነበር። ስለዚህም ይህን ቋጠሮ ለመፍታት አቶ ጌታቸው ትልቅ ሥራ ይጠብቃቸዋል። ለዚህ ታላቅ ሥራ ደግሞ የትግራይ አዲሱ ትውልድ አቶ ጌታቸውን ለመደገፍ መነሳሳት ይጠበቅበታል። ለውጥ መምጣት የሚችለው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ መጓዝ ከቻልን ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንተም እንደጠቀስከው ቀደም ሲልም በአማራ እና በትግራይ ሕዝብ መካከል ጠላትነት የለም፤ ከዚህስ በኋላ በአማራና በትግራይ ብሎም በሌላውም ሕዝብ መካከል ያለው ተግባቦት ምን መሆን አለበት ትላለህ?
አቶ ናትናኤል፡- አንደኛ ነገር ምናልባት ሌላው ኢትዮጵያዊ የማይገባው፤ እኛ የትግራይ ተወላጆች የምንረዳው አንድ ነገር አለ። በትግራይ ውስጥ ይህን ሰላም የሚፈልግ በተለይ በትግራይና በኢትዮጵያውያን መካከል ዘላለማዊ የሆነ ጦርነት እንዲኖር የሚፈልግ ቡድን አለ። አቶ ጌታቸው ወደአመራርነቱ ስፍራ ከመጡ በኋላ ቀደም ሲል የነበሩትን የድሮ ሚዲያዎችን ተጠቅመው አቶ ጌታቸው የሚመራውን መንግሥት ጥላሸት ለመቀባት የሚጥር ቡድን አለ። ይህ ቡድን በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የማይፈልግ ነው። ይህ ቡድን መሠረቱ የሕዝብ ጥላቻ ነው። በተለይ ደግሞ አማራን እንደጠላት የሚቆጥር ቡድን ነው።
ቀንቶት ሥልጣን እንኳን ቢያዝ ቂሙን መውጣት የሚፈልገው በአማራ ሕዝብ ላይ ነው። ይህ ቡድን ፍላጎቱና ሲሰብከውም የነበረው ነገር ወጣቱ የትግራይ ተወላጅ ሁሌም አማራን እንዲጠላ ነው።
እንደሚታወቀው ሕዝብ ከሕዝብ ጋር አይጣላም። አንድ ሕዝብ የሌላ አንድ ሕዝብ ጠላቱ ሆኖም አያውቅም። ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የነበረው ቡድን አሁንም መደበቅ የሚፈልገው ለትግራይ ሕዝብ ጠላት ለመፍጠር ነው።
እኔ እንደ አንድ የትግራይ ተወላጅ የማስበው አማራ ለትግራይ ሕዝብ መቼም ጠላት ሆኖ አለማወቁን ነው። ለምሳሌ መጀመሪያ ከአሜሪካ በመጣሁ ጊዜ ወደጎጃም አቅንቼ ነበር። እናም ባህርዳርንም ደብረማርቆስንም በደንብ አይቻለሁ። ውስጥ ለውስጥ ተዘዋውሬም ነበርና ሕዝቡ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ምንም ልዩነት እንደሌለው ተመልክቻለሁ። ያለው ልዩነት የቋንቋ ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ ኃይማኖቱም፣ አለባበሱም ሆነ የአኗኗር ዘይቤው ብዙ የሚለያዩ አይደለም። ያንን ሁኔታ ባየሁ ጊዜ እውን ይህን ሕዝብ ነው
የትግራይ ጠላት ነው ተብሎ ሲነገረን የነበረው በማለት ራሴን ስጠይቅ ነበር። በዚሁ አጋጣሚ መናገር የምፈልገው ነገር የአማራ ሕዝብ ጠላት አለመሆኑን ነው።
በሌላ በኩል መናገር የምፈልገው በአማራው አክቲቪስት በኩል የማየው ነገር ልክ በትግራይ እንዳለው አንድ ቡድን ዓይነት ነው። በእርግጥ እነዚህ አክቲቪስቶች ጥቂት ናቸው። እነርሱም መጥተው የትግራይን ሕዝብ አኗኗር ቢያዩና ቢፈርዱ ደስ ይለኛል። ስለዚህ ሕዝቡ በጠላትነት እንዲፈራረጅ ጥረት የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- የሰላም ስምምነት መፈረሙ ያመጣው ለውጥ አለ ብለህ ታምናለህ?
አቶ ናትናኤል፡- አንደኛ የሰላም ስምምነቱ የሚጠቅመው ለትግራይ ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ስለዚህ ለእኔ የሰላም ስምምነቱ ቢያንስ በየአስር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ጦርነት ከዚህ በኋላ ዳግም እንዳይከሰት አድርጓል ብዬ አምናለሁ።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ብዙ ነገር አይተናል። ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ግን የትግራይ ወጣት ከፍራቻ ወጥቶ ጥያቄ መጠየቅ ጀምሮ አይተናል። ለወደፊቱ የትግራይ ወጣት በዚህ መልኩ ጠያቂ ከሆነ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የትግራይ ፖለቲካ ተስፋ የሚሰጥ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በትግራይ ክልል በጦርነቱ ሳቢያ ለችግር የተዳረጉ አካላት ድጋፍ የሚሹ ናቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ የተራድኦ ድርጅቶች ድጋፉ በአግባቡ አይደርስም በሚል ሰበብ ድጋፍ ማቋረጣቸው ይታወሳል፤ እዚህ ላይ የአንተ አመለካከት ምንድን ነው?
አቶ ናትናኤል፡- መንግሥታት የየራሳቸው ተልዕኮ አላቸው። ለምሳሌ የዛሬ ሦስት ዓመት ድጋፍ አድራጊው አካል የራሱን አላማ ማራመድ እንጂ የትግራይ ሕዝብን የመርዳት አይደለም። እኔ የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ በትግራይ ውስጥ ነበርኩ፤ እናም እንቅስቃሴያቸውን እመለከት ነበር። በወቅቱ ይጠቀሙበት የነበረው ቴክኖሎጂ ሁሉ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሚያደርግላቸው ድጋፍ ነበር።
እንደሚታወቀው ደግሞ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በየሀገሩ የየራሳቸው ተልዕኮ ያላቸው ናቸው። የዛሬ ሦስት ዓመት ለትግራይ የመጣው እርዳታ እየተሸጠ የሚገኘው ገበያ ላይ ነበር። በወቅቱ አብዛኛው እርዳታ ፈላጊ የትግራይ ተወላጅ ሊያገኘው አልቻለም።
ላለፉት ስድስት ወራት ምንም እርዳታ ያልተቀበለ በየገጠሩ የሚገኝ በርካታ የትግራይ ተወላጅ አለ። በተለይ ደግሞ ልጆቻቸውን ወደጦር ግንባር የላኩ እናቶች እርዳታ እንኳ በቅጡ አላገኙም።
የውጭ መንግሥታት ሲኮንኑ የነበረው የኢትዮጵያን መንግሥት ነበር፤ ሆኖም በጦርነቱ ወቅት መንግሥት በማይቆጣጠራቸው አካባቢዎች የእርዳታ እህል በትግራይ ገበያ ሲቸበቸብ ነበር። ምናልባት የውጭ መንግሥታት አሁን ጉዳዩን የተረዱት ይመስለኛል። ያም ቢሆን እየተጎዳ ያለው ሕዝብ ነው።
ከዚህ አንጻር ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብዙ ተግዳሮቶች ያሉበት ነው። ስለዚህ ካልሆነ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱን ራሱ ወስዶ እርዳታውን ለትግራይ ቢያከፋፍለው መልካም ነው። ይህ ካልሆነ ከዚህ በኋላም የሚመጣው እርዳታ ለሕዝቡ በአግባቡ ይደርሳል የሚል እምነት ይኖረኛል። ከዚህ በፊት ሲወነጀል የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ግን አሁን ነፃ ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡- በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ዛሬም ቢሆን ድጋፍ ሊደረግ ይገ ባል የሚሉ አሉ፤ በተለይ ለትግራይ ሕዝብ፤ ከዚህ አኳያ በዳያስፖራው ዘንድ የታሰበ ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ ናትናኤል፡- አብዛኛው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በትግ ራይ ሕዝብ ላይ ጥላቻ ያለው አይመስለኝም። ምክን ያቱም እኔ የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ይዤ የመጣሁት ወደ 45 ሺ ዶላር ነው። እሱንም ትግራይ ሔጄ አከፋፍያለሁ። አብዛኛውን ርዳታ የሰጠው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። ስለዚህ በጦርነቱ ጊዜም ይሁን አሁንም በውጭ ሀገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ በትግራይ ሕዝብ ላይ መጥፎ አመለካከት የለበትም።
በዚሁ አጋጣሚ ከሳም ንታት በፊት አስመራ ስለነበርኩ የኤርትራ ወታደርም ሆነ ሕዝቡ ለትግራይ ሕዝብ የሚያዝኑ ሆነው ነው ያገኘኋቸው።
አሁን ከጦርነቱ በኋላ የምናያቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። ደግሞም በውጭ ሀገር የሚኖር የትግራይ ተወላጅ እያንዳንዱ ዋጋ ከፍሏል፤ ወይ አባቱ፣ ወይ እህቱ፣ አሊያም ወንድሙ ሞቷል።
ከዚህም በተጨማሪ በፋይናንስ በኩል ተጎድቷል። በጦርነቱ ወቅት እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ በነፍስ ወከፍ እስከ ስድስት ሺ ዶላር ድረስ ሲያዋጣ ነበር። በአሜሪካ፣ አውሮፓና ካናዳ የሚኖር እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ በዚያ ልክ ሲያዋጣው የነበረው ዶላር አሁን የት እንደደረሰ አይታወቅም። ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ የት እንደገባ አይታወቅም።
በሌላ በኩል ደግሞ በአሜሪካ፣ አውሮፓና ካናዳ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አሁንም ዝምታን መርጠዋል። መጨረሻም ላይ የተነገረውና የሆነው ለየቅል በመሆኑ የትግራይ ዳያስፖራ በትንሹም ቢሆን ጥያቄ እንዲያነሳ ሆኗል።
የትግራይ ዳያስፖራ በአሁኑ ወቅት ትንሽ የተማረው ነገር ቢኖር ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ወደሀገሩ መምጣት መጀመሩን ነው። ትግራይ ድረስ መሄድ ጀምሯል። በተወለደበት አካባቢ በመገኘትም በጦርነቱ የተጎዳው ማን እንደሆነ በመጠኑም ቢሆን አውቋል። የነበረው ፕሮፓጋንዳና ያየው እውነታን ሲያነጻጽር የሚጋጭ ሆኖ አግኝቶታል። ከዚህ የተነሳ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት አይቶታል።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል የመከላከያ ሠራዊት አባል እንደነበርክ ይታወቃል፤ የሀገር መከላከያን እንዴት ትገልጸዋለህ?
አቶ ናትናኤል፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ቀደም ሲል ስለነበርኩበት በደንብ አውቀዋለሁ። እንዲያውም እኔ መከላከያ ውስጥ ባልገባ ኖሮ ጠባብ ሰው የምሆን ይመስለኝ ነበር። ኢትዮጵያዊነትን በቅጡ ያስተማረኝ መከላከያ ነው ብዬ አምናለሁ።
በነገራችን ላይ መከላከያ በትግራይ ሕዝብ ላይ ምንም ዓይነት ጥላቻ የለውም፤ መከላከያ ላለፉት 20 ዓመታት 80 በመቶ ያህሉ በሚያስብል ደረጃ የነበረው በትግራይ ነው። ስለዚህ ለትግራይ ሕዝብ ጥላቻ የለውም።
ባለፈው በጦርነቱ ወቅት አብዛኛው የትግራይ ነዋሪ በተለይ እኔ ሃይስኩል የተማርኩበት አካባቢ አክሱምንም ሽሬንም በደንብ አውቀዋለሁ። በእነዚህ አካባቢዎች መከላከያ የሚመለስልን መቼ ነው በማለት ላይ ነው። ቀደም ሲል የመጣውን እርዳታ መከላከያ ለሕዝቡ ሲያከፋፍል እንደነበር ሕዝብ በደንብ ያውቀዋል።
ሌላው በአሁኑ ወቅት በትግራይ በተለያየ ቀበሌ ላይ አመሽቶ መግባት ከባድ ሆኗል። ጦርነቱ ባመጣው ጦስ ሥራ አጥ ወጣት በርክቷል። ሰፍኗል። ይህን ጉዳይ አቶ ጌታቸውም በቅርቡ ሲናገሩት ነበር። እነዚህ ነገሮች ስላሉ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ መከላከያ ይመለስልን እያለ ነው።
መከላከያ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሆነ መልካም ጊዜም ስለሚመጣ በዚህ አጋጣሚ የትግራይ ወጣቶች እንዲቀላቀሉት ጥሪዬን አቀርባለሁ። ምክንያቱም አይተነዋል፤ መከላከያ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም። እኔ ባለኝ መረጃ መከላከያ ለሕገ መንግሥቱና ለዚህች ሀገር የቆመ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነትን አጠና ክሮ ከመሄድ አኳያ ምን መሠራት አለበት ትላለሀ?
አቶ ናትናኤል፡- አሁን ኢትዮጵያዊነትን በቶሎ ለማምጣት የሚከብድ ይመስለኛል። ያለፈው ትውልድ በተለይ ከ27 ዓመታት በፊት የነበረው በብሔሩ፣ በመንደሩና በጎጡ የሚያምን ትውልድ ነው። የአሁኑ መንግሥት ዕዳ ነው ብዬ የማስበው ያለፈው መንግሥት አንድ ያወረሰው ነገር ቢኖር በዘሩና በብሔሩ ብሎም በወሰኑ የሚያምንን ትውልድ ነው። የዚህን ትውልድ አስተሳሰብ ለመቀየር ሌላ ትውልድ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ስለዚህ እንደእኔ አመለካከት መንግሥት ሥራ መሥራት አለበት ብዬ የማስበው ከ15 ዓመት በታች ባለው ትውልድ ላይ ነው።
እናም በአንድ ጊዜ ኢትዮጵያዊነት አሁን በዚህ ሁኔታ እያለ ማምጣት ከባድ ነው። አንዱ አማራ ሌላው ኦሮሞ፣ ሌላው ቤኒሻንጉል እያለ የሚሄድ ሆኗል። ሰው ከኢትዮጵያዊነት ወጥቶ ስለራሱ ጎጥ ብቻ የሚያስብ ሆኗል። እኔ በሃሳቤ ይህኛ ያኛው ብሔሬ ነው ማለት አልሻም፤ ሲጀመርም ብሔር የለኝም። ስለዚህ ይህ የእኔ ወሰን ነው፤ ያኛው የእኔ ብሔር ነው ማለቱን መተው አለብን።
እንዲያው በጥቅሉ ማለት የምፈልገው ነገር ቢኖር አሁን የተጀመረው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ከጎለበተ ኢትዮጵያ ትድናለች። ፖለቲካው ጤነኛ ከሆነ ኢትዮጵያም ጤነኛ ትሆናለች ብዬ አስባለሁ። እዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ የገባነው ሚዛናዊ ባልሆነ ፖለቲካ ምክንያት ነው። ለአብነት ብናነሳ በትግራይ አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በጣም የተሻለ ነው። ስለዚህ የትግራይ ፖለቲካን የበለጠ የተሻለ ለማድረግ አሁን የአቶ ጌታቸው ረዳ አመራርን ወጣቱ ሊደግፈው ይገባል።
ከዚህ በፊት የነበረው ፍራቻ ሰብሮ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ተጠቅሞ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የመቃወምም የመደገፍም መብቱን ራሱ ማረጋገጥ መቻል አለበት። ለውጥ ከየትኛውም ክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት መጠበቅ የለበትም። ምክንያቱም ትግራይ ከዚህ በኋላ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ መመራት የለባትም። ብዙ የተማረ ሰው አለ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩም ጥሩ ነው፤ ከፌዴራል መንግሥትም ጥሩ የሆነ ድጋፍ አለ። ስለዚህ ወጣቱ ለዚህ ተባባሪ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ናትናኤል፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2015