”በጎነት መልሶ ይከፍላል‘ የሚለው አባባል በማህበረሰቡ ውስጥ ያለ ጠንካራ እምነት ነው። ከዚህ መነሻ ኢትዮጵያውያን አቅመ ደካማን፣ የተቸገረን፣ ጤናው ተጓድሎ እጁ ያጠረበትን ሁሉ በንፁህ ልብና መራራት ይደግፋሉ። ‹‹ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ›› እንዲሉ መረዳዳትና በአንድነት መቆም የኢትዮጵያውያን አንዱ ባህል ነው። አብሮ መብላት ብቻ ሳይሆን “በደቦ” አብሮ መስራት፤ በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሃዘንም ማፅናናት የማህበረሰቡ መገለጫና መልክ ነው። ይህ ድርጊት ቀድሞውንም የነበረ አሁንም በልዩ ልዩ መልክ የቀጠለ ነው።
እጁ ያጠረበትንና ሌማቱ የነጠፈበትን በፍፁም ወገናዊ ስሜት ከመደገፍ ባሻገር መተኪያ የሌለው ጤና ሲጎድል በህብረት የመቆም ባህላችን ከየትኛውም ዓለም በተለየ ልዩና የሚያስደንቅ ነው። ግላዊነት በሰፈነበት፣ ሰው በዲጂታሉ ዓለም እራሱን አግልሎ የግሉን ሩጫ በሚኳትንበት በዚህ ጊዜ የቆየውን የመረዳዳትና አብሮ የመቆም ባህል ዛሬም እንዳይሸረሸር በልዩ ልዩ ማህበራዊ መንገዶች የግል ጥረት የሚያደርጉ ዜጎች እልፍ ናቸው። በተለይ ተወዳጅ የሆኑ አርቲስቶች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች እና ታዋቂ ሰዎች ይህ ባህላችን ሳይበረዝ እንዲቆይ በተለያየ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ እንመለከታለን።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በልብና በኩላሊት ህመም የሚሰቃዩ ዜጎችን የሚደግፉ በጎ ምግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎችን በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረ ገፅ እየተመለከትን ነው። ከዚህ ቀደም ህመማቸውን ደብቀው፣ ደጋፊ አጥተው ለህልፈተ ሕይወት የተዳረጉ አያሌ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። በኢትዮጵያ ውስጥ ታክሞ ለመዳን አዳጋች የሆኑ የልብ፣ የኩላሊት፣ የካንሰርና ሌሎችም በሽታዎች ከግለሰቡ አቅም በላይ ስለሚሆኑ በቀላሉ እጅ ይሰጡ ነበር። ቤተሰብ ጥሪቱን አሟጦ፣ ወዳጅ ዘመድ የቻለውን አድርጎ የጤና መታወክ የገጠመውን ሰው ለማዳን የሚጥር ቢሆንም በቀላል ወጪ ፈውስ የሚያገኙ የህመም አይነቶች ባለመሆናቸው ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ጥረቶቹ አይሳኩም ነበር።
በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ሙያዊ ብቃትና የህክምና ቁሳቁስ የሚሹትን እነዚህን የህክምና አይነቶች መስጠት እንዲቻል መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን በበጎ ፍቃደኝነት የሚሳተፉ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞችና ተፅእኖ ፈጣሪዎች ህሙማኑን ውጭ ድረስ ሄደው ፈውስን እንዲያገኙ የተለያየ ጥረት ያደርጋሉ። ከሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚኖሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጭምር ገንዘብ አሰባስበው የትራንስፖርት ወጪያቸውን በመሸፈን በመላክ ያሳክማሉ። አሁን አሁን ደግሞ በቋሚነት በርካታ የኩላሊት፣ የልብና ሌሎች ከፍተኛ አቅምን የሚጠይቁ ህመሞችን በሀገር ውስጥ ሙያተኛና እዚሁ ባለ የህክምና ተቋም ለመስጠት በግል ጥረታቸው ብዙ እርቀትን እየተጓዙ የሚገኙ ልበ ቀና ተፅእኖ ፈጣሪዎች እያየን ነው። የዝግጅት ክፍላችንም በዛሬው “ሀገረኛ” አምድ ላይ እነዚህን በጎ አምባሳደሮች በምሳሌነት ለማንሳት ወድደናል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበጎ ምግባር እና አምባሳደርነቱ እየታወቀ የመጣው ተወዳጁ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ነው። ይህ አርቲስት በበርካታ ፊልሞች፣ ተከታታይ ድራማዎችና መሰል የኪነ ጥበብ ስራዎቹ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ስፍራ ያለው ነው። ከዓመታት ወዲህ ደግሞ ከሚሰራቸው የጥበብ ስራዎቹ ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበትን “በጎነት” እና “አለሁ ባይነት” ተላብሶ የብዙሃን ፊት ላይ ፈገግታን ማጫር የቻለ ሰው ነው። በኩላሊት ህመም ተይዘው ለዓመታት ይገቡት የጠፋቸው አቅመ ደካሞች፣ ህፃናት፣ እናቶችና የአገሩ ልጆችን ከፈተና የታደገና “ምስጋናን” እንዲቸረው ያስቻለ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ይህ አርቲስት ሕይወትን ለማዳን የግል መኪናውን እስከ መሸጥ የደረሰና ለዚህ አላማም ብዙዎችን በአንድ ጣሪያ ስር ያሰባሰበ ነው። አሁን ደግሞ የግል ጥረቱን አስፍቶና ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አያሌ ደጋፊዎችን አሰባስቦ በኢትዮጵያ የኩላሊት ህክምናን መስጠት የሚያስችል ሪፈራል ሆስፒታል ለማስገንባት ደፋ ቀና እያለ ነው።
ጥረቱን ህሙማንን ወደ ውጭ በመላክና በማሳከም የጀመረው የአርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ፋውንዴሽን ለሆስፒታል መገንቢያ በኦሮሚያ መሬት በመረከብ ትልቅ ስኬትን ማግኘት ችሏል። ከ6 ዓመት በፊት በአርቲስት ሰለሞን ቦጋለ እና ጓደኞቹ የተመሰረተው ሕብረት ለበጎ ፋውንዴሽን በዋንኛነት በኩላሊት ሕመም ለሚሰቃዩ ወገኖች መርጃ የሚሆን ሪፈራል ሆስፒታል ለመገንባት 60 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ነበር በለገዳዲ ከተማ የወሰደው።
በኩላሊት ሕመም ታመው ሲሰቃዩ የነበሩ በርካታ ወገኖቻችንን ወደ ውጭ በመላክ እያሳከመ ቢቆይም ይህ ብቻ በቂ ሆኖ አላገኘውም። ይልቁንም የኢትዮጵያውያን የበጎ አድራጎት ድርጅት በኩላሊት ህመም የሚሰቃዩ ወገኖቻችን በቀላል ወጪ በሀገራቸው እንዲታከሙ ለማስቻል ግዙፍ ሆስፒታል ለመገንባት አስቦ ጥረቱን ጀመረ። በውጤቱም ከመንግስትና ከአገር ወዳድ ዜጎች ይሁንታን አግኝቶ ብዙዎች ላይ ፈገግታን ለመጫርና ከጭንቀታቸው እንዲገላገሉ የሚያስችል ጉዞውን ተያያዘው።
ጥረቱን ቀጥሎም ሕብረት የበጎ አድራጎት ድርጅት ከለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ የተረከበው አራት ሄክታር መሬት በቅርቡ የሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ ሊጀመር መሆኑን ባሳለፍነው ከሳምንታት በፊት ይፋ አደረገ። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ለሚያስገነባው የሪፈራል ሆስፒታል የቅድመ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይም ህሙማንን የማዳን፣ በጎ ምግባር አንዴ አሊያም ሁለት ጊዜ ተደርጎ የሚቆም ሳይሆን የማይቆምና በትውልድ ቅብብሎሽም ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ምግባር መሆኑን አስመሰከረ። አራት ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ በሚታሰበው በዚህ የሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ ቀን የጨለመባቸውና እጃቸው ያጠረባቸው የኩላሊት ህመምተኞች አዲስ ተስፋን የሚሰንቁበትና በቀላሉ ህክምና የሚያገኙበት እንደሚሆን ተስፋ ተጥሎበታል። ድርጅቱ ከተመሰረተ ስምንት ዓመታት እንደሆነው የሚገልጸው አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ በርካታ የተቸገሩ ኢትዮጵያዊያንን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉን ተናግሯል። ይህ ሆስፒታል ተገንብቶ ወደ ስራ ሲገባም ከዚህ በተሻለ አማራጭ እንደሚሰራ ነው ለመገናኛ ብዙሃን ያሳወቀው።
ብዙዎች “ልበ ብርቱ” በማለት ይጠሯታል። ጋዜጠኛ ነች። ልክ እንደ አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ሁሉ በልብ ህመም ለሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ በማሰባሰብና በጎ ምግባር ላይ በመሳተፍ ትታወቃለች። በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ አብዛኛዎቻችን እናውቃታለን። ድንገት ከተፍ ብላም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያወጡ የህክምና ቁሳቁስ ትለግሳለች። በምትኖርበት ሀገረ አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን በማስተባበርም ይሳካ ላታል። ይህቺ ሴት ጋዜጠኛ ሕይወት ታደሰ ነዋሪነቷ በሰሜን አሜሪካ ነው።
ከአራት ዓመታት ወዲህ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ አላማ በሚል መሪ ቃል ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መረጃ ገቢ በማሰባሰብ በተለያዩ ጊዜያት ህፃናቱን ስታሳክም ቆይታለች። ከሰሞኑ በተሰማው ዜናም ግምቱ ከሃምሳ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የህክምና ቁሳቁስ ለልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል አስረክባለች:: ሕይወት ታደሰ ይሄንን የበጎ አድራጎት ስራ ለማጠናከር ” ላይፍ ፎር አፍሪካ ” የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአሜሪካን ሀገር አቋቁማለች። በዚህም በአሜሪካን ሀገር ለሀገር ብሎም ለማህበረሰብ በጎ የሰሩ ሰዎች የሚሸለሙበት “ቤስት ሰርቪስ አዋርድ ” እጩ ሆና ቀርባ እንደነበር ይታወሳል።
ሕይወት ታደሰ በተለይም ሶሻል ሚዲያን ልባቸው ተሰብሮ ወረፋ እየተጠባበቁ ላሉ ምስኪን ህፃናት ሕይወታቸው እንዳያልፍ በተለይም በርካታ ተከታይ ያለን ታዋቂ ሰዎች ልክ ፈጥነን ልንደርስላቸው ይገባል የሚል ቁርጠኛ አቋም አላት።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ማዕከሉ ከ3000 በላይ ህጻናት እንዲታከሙ ሲያደርግ ያለምንም ክፍያ ከተለያዩ ልበ ቀና ከሆኑ ግለሰቦች እና ሀገር በቀል እንዲሁም ከሀገር ውጭ ካሉ ድርጅቶች በሚያደርገው እርዳታ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ከተከሰተው የዓለም አቀፍ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም በሀገራችን ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የሚገኘው እርዳታ በተወሰነ መልኩ መቀዝቀዝ አሳይቶ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ የአላቂ እቃዎች አቅርቦት በዓለም አቀፍ ደረጃ መቀነስ የራሱ አሉታዊ አስተዋጽኦ ኖሮታል።
በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ሚዲያ ሰፊ ተቀባይነትን እያገኙ ከመጡና በአቅም ማጣት ምክንያት የህክምና ወጪያቸውን መሸፈን ለተሳናቸው ህሙማን ድጋፍ ከሚያደርጉ አርቲስቶች መካከል መሰረት መብራቴ ትጠቀሳለች። በርካታ አመታት በኪነ ጥበብ ስራዎቿ ብዙዎችን ስታስደምም ቆይታ አሁን ደግሞ የልብ ህሙማንን ለማከም በሚደረግ ጥረት ላይ በበጎ ፍቃድ ከፊት ተሰልፋለች። የልብ ህሙማን ማእከሉም አርቲስቷን የበጎ ፍቃድ አምባሳደር አድርጎ መርጧታል።
አርቲስት መሰረት መብራቴ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን በማዘጋጀትና በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ጋር በመሆን ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችሉ የገቢ ማሰባሰቢያ ተግባራትን እንዲሁም ስለልብ ህክምና ማዕከሉ በሰው ዘንድ ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር ጥረት ታደርጋለች። በዚህም ባለፉት ጊዜያት ስኬታማ ውጤቶች እያስመዘገበች መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከሶስት ዓመት በፊት ነው ቦርዱ አጽድቆ የበጎ ፍቃድ አምባሳደር ካደረጋት በኋላ ስራውን በደስተኝነት እና ሙሉ ፍቃደኝነት የተቀበለችው አርቲስቷ ማእከሉን በቅርበት ሆና ለማየት እንድትችል እድል የሰጣት ነበር። በአንድ ወቅት በመገናኛ በዙሃን ጥያቄ ቀርቦላት ምላሽ የሰጠችው መሰረት መብራቴ “የህጻናቱና የወላጆቻቸውን ስቃይ እና ሰቀቀን ስመለከት እዚያው ቦታ ላይ ቆሜ ነው በእግዚአብሔርም በሰው ፊት ቃል የገባሁት” በማለት ለዚህ በጎ ምግባር እንዴት በቁርጠኝነት ለመስራት እንደወሰነች ተናግራ ነበር።
በምትችለው ሁሉ፣ ካላት ጊዜ ላይ በመውሰድ፣ ጉልበትና ተሰጦ ሁሉ ማድረግ የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብታ ስኬታማ ጊዜያታትን እያሳለፈች ትገኛለች።
መሰረት “በዙሪያችን ብዙ ችግሮች አሉ፣ ልንሸፍናቸው የሚገቡ ብዙ ጉድለቶች ስላሉ ሁላችንም የራሳችንን ጠጠር መጣል ይገባናል” የሚል አመለካከት አላት። ሁሉም ጋር ደርሰን መቅረፍ ባይቻልም ኢትዮጵያውያን በአቅማቸው አበርክቶ ሊኖራቸው እንደሚገባ ትመክራለች።
እንደ መውጫ
በጎ ማድረግ የተቸገረውን ግለሰብ ከመደገፍ ባሻገር ለረጂው አሊያም ድጋፍ ላደረገው አካል ትልቅ የህሊና እርካታን የሚሰጥ ነው። ዛሬ የዋልነው ውለታም ነገ ይከፍለናል። ከሁሉ በላይ ከፍ ባለ ደረጃ ኢትዮጵያዊነትን ለማጉላት፣ አንድነትን ለማፅናት፣ ችግርን በጋራ ለመወጣት ያለንን ችሎታና ተሰጦ ልንጠቀምበት ይገባል። መልካም ስምን ለዚህ መሰሉ በጎ ምግባር ማዋል ብዙሃንን ከሞት ደጃፍ እንደመመለስ ይቆጠራል። አለፍ ሲልም አርዓያነትን የሚያጎላና ለብዙዎች ምሳሌ የሚሆን ድንቅ ሥራ መሆኑን ተገንዝበን ሁሌም ቢሆን የራሳችንን ጡብ ለመጣል እንሞክር። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2015