በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሰባት ማሰልጠኛ ማዕከላት አንዱ ነው፡፡ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ሙሉ የትጥቅ ድጋፍን ጨምሮ ለአትሌቶች የላብ መተኪያ እና ለአሰልጣኞች የደመወዝ ክፍያ ከፌዴሬሽኑ ያገኛል። ይህ መቀመጫውን በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ያደረገ ማሰልጠኛ ማዕከል ከተለያዩ የፕሮጀክቶችና የክልል ውድድሮች ታዳጊ አትሌቶችን መልምሎ በማሰልጠን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የማሰልጠኛ ማዕከሉ አትሌቶች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጃቸው የውድድር መድረኮች ላይ ከዓመት ዓመት በሚያደርጉት ተሳትፎ ተስፋ ሰጪ ውጤትን እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ በተካሄደው የማሰልጠኛ ማዕከላት አትሌቲክስ ቻምፒዮና ይህንኑ የስኬት ጎዳና በማስቀጠል በሁሉም ውድድሮች የበላይ የሆኑበትን ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡
ተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ በቻምፒዮናው በሴቶች 183 እና በወንዶች 376 ነጥቦችን በመሰብሰብ የአጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ በመሆን ጨርሷል፡፡ ማዕከሉ ከተመሠረተ የሦስት ዓመታት ዕድሜ ብቻ ቢያስቆጥርም በሀገር ውስጥ ተሳትፎ ከሚያስመዘግበው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በመወክል ውጤታማ የሆኑ ወጣት አትሌቶችን በማበርከት ከዕድሜው በላይ ስኬታማ እየሆነ ይገኛል።
ማሰልጠኛ ማዕከሉ ያፈራቸውና ትልቅ ደረጃ የደረሱ ውጤታማ አትሌቶች ጥቂት አይደሉም። የኢትዮጵያን ስም ማስጠራት ከቻሉት የማዕከሉ ፍሬዎች መካከል አትሌት ጀማል ይመር፣ አትሌት ሶፊያ አሰፋና አትሌት ዘይነባ ይመር በትልቁ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር እና ከተንታ ወረዳ አስተዳደር ጋር የሦስትዮሽ ስምምነት በመፈራረም ከታኅሣሥ 9 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከልን በፕሮጀክት ደረጃ ተረክቦ ሲያስተዳደር ቆይቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው 2.5 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ በአትሌቲክስ ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣትና የአትሌቶችን የምልመላና መረጣ ሂደት ሳይንሳዊ በማድረግ በጥናት የተደገፈ አሠራርን ዘርግቶ ለመጀመሪያ ጊዜ 40 አትሌቶችን በማቀፍ ነበር በ4 ዓመት ስልጠና ወደ ሥራ የገባው።
ማዕከሉን የምርምርና የተተኪ አትሌቶች ማፍሪያ ለማድረግ በ2013 ዓ.ም በጀቱን ወደ 39 ሚሊዮን ብር ያደገ ሲሆን፣ 50 አትሌቶችን በአጭር፣ በመካከለኛ፣ በረጅም ርቀትና በሜዳ ተግባራት ለማሰልጠን ወደ ሥራ ገብቷል። በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ አትሌቶችን አቅፎ በማሰልጠንም ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ማዕከሉ በጦርነት ተደጋጋሚ ጉዳት ቢደርስበትም ዛሬ ላይ በማገገም ውጤታማነቱን አስቀጥሎ እየተጓዘ ይገኛል፡፡
በ3ኛው የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ቻምፒዮና ማዕከሉን በመወከል የ10ሺ ሜትር አሸናፊ የሆነው አቤል በቀለ ማሰልጠኛ ማዕከሉን ከተቀላቀለ ሦስት ዓመት ሆኖታል፡፡ አትሌቱ ማሰልጠኛ ማዕከሉን በመወከል በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ውድድሮች ተሳትፎ በውጤታማነቱ ቀጥሏል፡፡ ለውጤቱ ማማር በማዕከሉ የሚሰጣቸው ጥሩ ስልጠናና የአየር ንብረቱ አስተዋጽኦ እንዳለው ያስረዳል፡፡ ደመወዝን ጨምሮ ለስልጠና የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ወሎ ዩኒቨርሲቲ እንደሚያደርግላቸው ጥቅሶም አትሌቶች የሚያገኙት እንክብካቤ እንደሚያስመሰግን ተናግሯል፡፡ አትሌቱ ከአሰልጣኝ ሁሴን ሼቦ ጋር በመሆን ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ በዓለም ቻምፒዮናና ኦሊምፒክ ለሀገሩ ውጤት የማምጣት እቅድ ይዞ እየሠራም ይገኛል።
የርዝመት ዝላይ አሸናፊ የማዕከሉ አትሌት መሠረት መኮንን ወደ ማሰልጠኛው ከገባች አንድ አመት ከስምንት ወር አስቆጥራለች። መጀመሪያ አሰልጣኝ እንዳልነበራቸውና እርስበርስ በመተጋገዝ ሲሠሩ እንደነበር የምታስታውሰው ወጣት አትሌት፣ አሰልጣኝ ከተቀጠረላቸው በኋላ ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ታስረዳለች። ጂምናዚየም አለመኖሩ ግን የማዕከሉ አትሌቶች ፈተና መሆኑን አልሸሸገችም፡፡
የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠና ማዕከል ቡድን መሪ አቶ መሃመድ አለባቸው፣ ማዕከሉ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚሰጡትን መመሪያና ሕጎችን መሠረት በማድረግ ሁሉም የስልጠና መርሐ ግብሮች እንደሚሰጡ ይናገራሉ። እንደ ቡድን መሪው ገለፃ፣ ማዕከሉ የአትሌቶች ምልመላና መረጣን ሲያደርግ ከፕሮጀክት የመጡትን አትሌቶች በመቀበል አጎልብቶ ወደ ቀጣይ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ አልሞ ነው፡፡ በምልመላ ወቅትም አትሌቱ ለየትኛው ርቀትና ተግባር ይሆናል የሚለውን በሳይንሳዊ መንገድን ከለየ በኋላ የአራት አመት ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋል።
ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሳይንስ ክፍል ጋር በመሆን ለምልመላና መረጣ የተዘጋጀ ቴክኒካል ኮሚቴም በሳይንሳዊ መንገድን ምልመላውን ያደርጋል። በቀጣይ ማዕከሉን የአትሌቲክስ ክለብ ለማድረግ እንደታሰበም ቡድን መሪው ጠቁመዋል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት በዓለምና በአፍሪካ ደረጃ በተደረጉ ውድድሮች የማዕከሉ አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸው ከተመሠረተ አጭር ጊዜ ቢያስቆጥርም ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል፡፡ ይህንንም ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ያምሆኖ ማዕከሉ በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ የመገልገያ መሣሪያዎቹን ለመተካት ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ አልተቀረፈም፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሸፈንም ማንኛውም አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ቡድን መሪውና የማዕከሉ አትሌቶች ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ በቀጣይ ለስልጠና የሚስፈልጉ መሣሪያዎችን ጨምሮ የጂምናዚየምና የመም(ትራክ) ሥራን ለመከወን አቅዷል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2015