ኢትዮጵያ በዓለም ታላላቅ የስፖርት ውድድር መድረኮች ውጤታማ ሆና ሰንደቅ ዓላማዋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደረገው አትሌቲክስ ነው። ይህ ስፖርት በዓለም አትሌቶች አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች (በዶፒንግ) ተጠቃሚነት ምክንያት አደጋ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል። ይህ አደጋ ካንዣበባቸው ሀገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች። ኢትዮጵያ ይህን በስፖርቱ ላይ የተቃጣ አደጋ ለመታገል ባለፉት ዓመታት አበረታች ሥራዎችን መስራቷ የሚታወቅ ሲሆን አሁንም ከአደጋው ስጋት ነፃ አልወጣችም።
የዶፒንግ ጉዳይ ለኢትዮጵያ አሁንም አሳሳቢ መሆኑን ተከትሎ ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ በመድረሱ ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተጠቁሟል። ከችግሩ ስፋትና ክብደት አንጻር ከባለድርሻ አካላት ጋር አፋጣኝ ውይይትና ለችግሩ መፍትሔ መፈለግ ብቸኛ መንገድ መሆኑም ገልጿል። የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በአበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ቁጥጥርና መከላከል ላይ ያተኮረ “ችግሩን እንዴት እንዋጋ” የሚል የምክክር መድረክ ሰኔ 17 2015 ዓ.ም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተከናውኗል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የምክክር መድረክ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ቁጥጥር ባለስልጣን አማካኝነት የአበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶችን ስጋት የሚዳስሱ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በቀረቡት የመነሻ ጽሑፎችም አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች (ዶፒንግ) አትሌቲክስ ከሁሉም ስፖርቶች በበለጠ ቀዳሚው ተጋላጭ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ የመነሻ ጽሑፎቹ ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላም የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል፡፡
በስፖርቱ የተከለከሉ ወደ 10 የሚደርሱ ቅመሞችና መድኃኒቶች ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ ለውይይት በቀረቡት ፅሁፎች የተጠቆመ ሲሆን፣ ”ይሄንን ሸንጎ የጠራነው ጎረቤታችን ኬንያ ለቅሶ ላይ ስለሆነች ነው” ሲሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ የህክምና ባለሙያ ዶክተር አያሌው ጥላሁን ለውይይት ባቀረቡት ጽሑፍ ወቅት ተናግረዋል።
ዶክተር አያሌው በአትሌቲክስ የማይነጥፍ ውጤት እየተመዘገበ ቢሆንም የአበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ከፍተኛ ስጋት በመሆናቸው አደጋውን ለመቀልበስ የባለድርሻ አካላትን ሰፊ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። መድኃኒቶቹን በመሸጥና አትሌቶች እንዲጠቀሙ በማድረግ ከስፖርተኞችና ማናጀሮች በተጨማሪ የሙያ ሥነ-ምግባራቸውን የማያከብሩ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የህክምና ተቋማት ትልቁን ድርሻ መያዛቸው ችግሩ ውስብስብና አስቸጋሪ እንዳደረገውም ዶክተር አያሌው አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያውን ማናጀሮች ባሻገር የውጭ ሀገር ዜጎች በነጻነትና መድኃኒቶችን እያዘዋወሩ አትሌቶችን በማታለል እንዲጠቀሙ በማድረግ ግንባር ቀደም ተዋናዮች በመሆናቸው የባለድርሻ አካላት በዚህ ላይ ቁጥጥር በማድረግ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተጠቁሟል።
ተጨማሪ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ጸረ- አበረታች ቅመሞች ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል፣ አበረታች ቅመም (ዶፒንግ) “በዜጎቻችን ላይ የስነልቦና ችግርን እያስከተ ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡ ባለስልጣኑ የአበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር በዓለም አቀፍ በጣም እየተጠናከረ በመምጣቱ በቁጥጥሩ ላይ ሰፊ ሥራዎችን እየሰራ እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡ የዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች መድኃኒቶች ቁጥጥር ባለስልጣን ኢትዮጵያ ቁጥጥሯን ማጠናከር እንደሚኖርባት ማሳሰቢያ መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡ አትሌቶች እየተቀጡ ብዙ ርቀት መሄድ ስለማይቻልም የምርመራ ስራው ሊቀጥልና ባለድርሻ አካላት ሊተባበሩ እንደሚገባ ማሳሰቡን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት ባለስልጣኑ 34 የሚሆኑ መድረኮችን በማዘጋጀት አጫጭር እና የገጽ ለገጽ ሥልጠናዎችን በመስጠት 3425 የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ በሚሊዮን ለሚቆጠር ማህበረሰብ ግንዛቤ መፍጠር እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በበጀት ዓመቱ 657 ለሚሆኑ ስፖርተኞች ምርመራ ያደረገ ሲሆን የተጋላጭነት ዳሰሳ ጥናትም ሰርተል። የዳሰሳ ጥናቱ የአትሌቲክስ ስፖርት የመጀመሪያው የዶፒንግ ተጋላጭ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ በተደረገው ምርመራም 7 የሕግ ጥሰት የፈጸሙና አበረታች ቅመሞች ተጠቅመው የተገኙ አትሌቶች እንዳሉ ታውቋል፡፡ ምርመራው ተጠናቆ ሕጋዊ ሂደቱን ከጨረሰ በኋላ የአትሌቶቹ ዝርዝር ይፋ እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡ የሕግ ጥሰት ከፈጸሙት አትሌቶች ውስጥ ሰባ በመቶ የሚሆኑት ቻይና ላይ በተደረጉ ውድድሮች የተያዙ መሆናቸውም ተጠቁማል፡፡ አበረታች ቅመሞችን ተጠቅመው የተገኙ ስፖርተኞች ከአስተዳደራዊ እርምጃ በተጨማሪ በወንጀል ሊጠየቁ እንደሚችሉም ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመሆን ያደረገው የጸረ ዶፒንግ የምክክር መድረክ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ በመስጠት ተጠናቋል፡፡ በዚህም መሰረት ባለድርሻ አካላት በጋራ በመሆን በርብርብ መስራት፤ በሕገ ወጥ የዶፒንግ መድኃኒቶችና ንጥረ ነገሮችን የሚሸጡና አትሌቶችን እንዲጠቀሙ የሚያደርጉ ሕገ ወጦችን በጋራ መቃወም፣ ለሕግም እንዲቀርቡ ማድረግ፣ አትሌቶችን በሕጋዊ መንገድ ከኢትዮጵያ በመውሰድና በልዩ ልዩ የዓለም መድረኮች በውድድር እንዲሳተፉ በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የአትሌት ተወካዮችን ማበረታታትና ከዚህ ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ ሀገርን የሚጎዳ ተግባር የሚፈጽሙ ተወካዮችን ማጋለጥ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአትሌቲክስ ልማቱን በተሻለ አሰራርና ዕቅድ እንዲፈጽም፣ የኢትዮጵያ ጸረ አበረታች ቅመሞችና መድኃኒቶች ባለስልጣን ምርመራውንና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ ጫና በማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2015