የኦሮሚያ ክልል በርካታ ግብር ከፋዩች ያለው ክልል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህንን በርካታ ቁጥር ያለው የግብር ከፋይ ለማስተናገድ ተዘርግቶ ስራ ላይ የዋለው አሠራር ግብር ከፋዩን ህብረተሰብ ለተለያዩ እንግልትና አላስፈላጊ ወጪ በመዳረግ የግብር ከፋዩን ቅሬታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ክልሉ በግብር ከፋዩ ሲነሱ የነበሩትን ቅሬታዎች ለመፍታት የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህ የግብር አሰባሰብ ሂደቱን በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግና በማዘመን ለግብር ከፋዩ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ለማድረግ ሥራ እየሰራ ነው፡፡ ለዚህም በቅርቡ የግብር አሰባሰብ ሂደቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲፋጠን ለማድረግ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተፈራርሟል፡፡
የክልሉን ወጪ በክልሉ ገቢ ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት የክልሉ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ግብር በብቃት ለመሰብሰብ የክልሉ ገቢ ሰብሳቢ አካል በሰለጠነ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ሰፊ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ከክልሉ የከሚሰበሰበው ግብር አሰባሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፤ ከክልሉ የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በ2010 በጀት ዓመት የተሰበሰበው የገቢ ግብር ብር 16 ቢሊዮን ሲሆን፣ ይህም በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር በ2015 በጀት ዓመት ብር 71 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ክልሉ በቀጣዩ ዓመት በ2016 በጀት ዓመት የሚሰበስበውን የግብር ገቢ አሰባሰቡን በማዘመን 130 ቢሊዮን ብር ለማድረስ አቅዷል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም ደበበ እንደሚሉት፤ ክልሉ የታክስ አሰባሰቡን አሁን ካለው አሠራር ይበልጥ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ ይገኛል፡፡
ለዜጎች ምቹ የሆነች አገርን ለመገንባት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ግብርና ታክስ መሰብሰብ ተገቢ ነው የሚሉት ወይዘሮ መስከረም፤ ለዚህም የግብር አሰባሰብ ሥርዓትን ማዘመን አማራጭ የሌለው ተግባር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከቴሌ ብር ጋር የአሠራር ሥርዓቱን በማቀናጀት የገቢ አሰባሰቡን ወደ ዲጂታሉ ዓለም በመቀላቀል የገቢ ዘርፉን ለማዘመን መሥራት ደግሞ በእጅጉ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የዲጅታል ቴክኖሎጂ የክፍያ ሥርዓቱ ለገቢ አሰባሰብ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ነው ወይዘሮ መስከረም የሚገልጹት፡፡ ግብር ከፋዩ ሥራው ቦታ ሆኖ እየሰራ ግብር መክፈል ከቻለ ግብር ለመክፈል የሚያመጣውን ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት ይቀንስለታል፤ ጊዜውን በአግባቡ እንዲጠቀም በሥራው ውጤታማ እንዲሆን ያደርጋል፤ ግብር ለመክፈል ወደ ግብር መክፈያ ማዕከላት ሲመጣ በሚደርስበት ውጣ ውረድ፣ እንግልት፣ በአግባቡ አለመስተናገድና በመሳሰሉት ሳቢያ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመቀነስ እንደሚያስችል ነው ያብራሩት፡፡
የግብር አሰባሰቡ አሰራር ምልልሶች የበዙበት ሆኖ ቆይቷል የሚሉት ኃላፊዋ፤ ግብር ከፋዩ ወደ ግብር መክፈያ ማዕከሉ ሄዶ የሚከፈለውን የግበር መጠን ካወቀ በኋላ ባንክ ከፍሎ እንደገና ተመልሶ ወደ ግብር መክፈያ ማዕከሉ መምጣት እንደሚጠበቅበት ያስረዳሉ፡፡ አሁን ላይ የተዘረጋው ዲጂታል የግብር አከፋፈል ዘዴ ስራ ላይ የቆየውን አሰራር ሙሉ ለሙሉ እንደሚያስቀር ጠቅሰው፣ አልፎ አልፎ ሲታዩ የነበሩ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችንም ያስቀራል ተብሎ እንደሚታመን ይገልጻሉ፡፡ ግብርን በቴሌብር የመክፈል አሠራር ሂደት የግብር ከፋዩን ውጣ ውረድ የሚቀንስ ቀላል፣ ምቹ፣ ወጪ ቆጣቢ የግብር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ እስካሁን በክልሉ አራት ዞኖች ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በቴሌብር ታክስና ቀረጥ የመሰብሰብ ሥራ ተጀምሯል። እነዚህ ዞኖች 39 ሺ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች ያሏቸው ሲሆን፤ ከ40ሚሊዮን ብር በላይ በቴሌ ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ በተጨማሪም በሸገር ከተማ፣ በአዳማና በቢሾፍቱ እንዲሁም በዋናው መስሪያ ቤት ባሉ ትልልቅ ግብር ከፋዮች በኢብር፣ የኢታክስ እና የኢፋይሊንግ አገልግሎት ተከትሎ የ‹‹ሀ›› እና‹‹ ለ›› ግብር ከፋዩች ስልጠና ወስደው ታክሳቸው በቴሌብር የማሳወቅ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
‹‹አሁን ላይ ከኢትዮቴሌኮም ጋር የተፈራረምነው ስምምነት በዋናነት ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ሰፊውን የግብር ከፋይ የምናገኝበትና በአዲስ በጀት ዓመት የሚሰበሰበው ግብር ተግባራዊ የሚደረግበት ነው›› የሚሉት ኃላፊዋ፤ ግብር ከፋዩ ወደ ሲስተሙ ሲገባ እንዳይቸገር ለማድረግ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመሆን በየቅርንጫፎቻችን ለሚገኙ ሠራተኞች ግብር ከፋዩ በቴሌ ብር በመጠቀም ግብሩን መክፍል እንዳይቸገር ለማድረግ የሚያስችል ስልጠና እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡ እስከ ሐምሌ አንድ ለግብር ከፋዩ ህብረተሰቡ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች በመጠቀም በቴሌ ብር ግብሩን እንዲከፍል ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫና የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራም ይገልጻሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ክልሉ ከ480 ሺ በላይ የሆኑ ግብር ከፋዮች አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ከሐምሌ አንድ እስከ ታህሳስ 30 ድረስ ግብር የሚሰበሰብበት የ‹‹ሐ›› የግብር ከፋዮች ናቸው፡፡ የግብር አከፋፈል ሂደቱ ሁሉንም ሊያካትት በሚችል መልኩ በየምዕራፍ በመከፋፈል ይካሄዳል፡፡
ዘንድሮ ከተሞች ላይ ሙሉ በሙሉ የግብር መሰብሰብ ሂደቱ በቴሌብር ይፈጸማል፡፡ ከከተሞች በታች ባሉ ወረዳዎች ላይ ግን ግብር የሚሰበሰበው በቴሌብር የሚስተናገዱ ሲሆን፣ ነገር ግን ግብር ከፋዩ ወደ ግብር መክፈያ ማዕከላቱ መጥቶ በኪውአርኮድ እስካን በማድረግ የሚጠበቅበትን የግብር ክፍያ አውቆ በቴሌብር እንዲከፍል በማድረግ ነው የሚፈጸመው፡፡ ይህ አሠራር በሁሉም ዘንድ በተመሳሳይ መልኩ ይሰራበታል ብለዋል፡፡
የሀገራችንን የፋይናንስ ስርዓት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመደገፍ የታሰበውን ሀገራዊ ብልጽግና ለማሳካት የሚደረገውን ርብርብ ጠንካራና አስተማማኝ መሠረት ላይ ለማድረስ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊዋ፤ የክልሉ የግብር ከፋዮችና ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ግብር በቴሌ ብር አማራጭ /ፕላትፎርም/ በመጠቀም በቤታቸውና በሥራ ቦታቸው ሆነው ለመክፈል እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ የሞባይል መኒ ኦፊሰር አቶ ብሩክ አድሀና እንዳሉት፤ ግብር ለሀገር፤ ለእድገት ወሳኝ ሚናን ይጫወታል፡፡ ግብር አከፋፈሉ ደግሞ በቴሌ ብር በጣም ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ በሆነ መልኩ የሚፈጸም መሆኑ ሲጨመርበት የግብር አሰባሰቡ ሂደት የበለጠ ይፋጠናል፤ ከፍተኛ ውጤት ይመጣበታል፡፡ ከኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ ጋር ግብርን በቴሌብር በመሰብሰብ የግብር አሰባሰብ ስራውን ለማሳለጥ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል፡፡
ቴሌ ብር ሁሉን አቀፍ በመሆኑ አገልግሎቱን ለመጠቀም በኤስኤምኤስ፣ በሞባይል መተግበሪያ፣ በተለያዩ ቦታዎች ባሉ ኤጀንቶች እንዲሁም ኮኮብ መቶ ሃያ ሰባት መሰላል (*127#) በመጠቀም ምንም አይነት ቀፎ ሳይመርጥ ዘመናዊ ቀፎ ያለውንም ሆነ የሌለውን ደንበኛ በእኩል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላል። በሌላ በኩል በቴሌኮም በኩል ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ወደ ጥሪ ማዕከል በመደወል፣ በዌብ ሳይት እና ዌብ ቻት እና በመሳሰሉት አማራጮች በመጠቀም ድጋፍ ማግኘት የሚቻልበት ምቹ ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡
ደንበኞች ግብር በቴሌብር ሲከፍሉ ከላይ የተጠቀሱትን የቴክኖሎጂ አማራጮች ሁሉ ተጠቅመን ድጋፍ የምንሰጥበት ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረናል የሚሉት አቶ ብሩክ፤ በዚህም በአምስት አይነት ቋንቋዎች በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ፣ በሶማሊኛ እና በእንግሊዘኛ በቀላሉ መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል። እሳቸው እንደሚሉት፤ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ወደ 409 የግብር መሰብሰቢያ ማዕከላት አሉት፡፡ ክልሉ 23 ከተማዎች፣ 42 ክፍለ ከተማዎች፣ 21 ዞኖችና 323 ወረዳዎች አሉት፡፡ ኢትዮቴሌኮም በእነዚህ ሁሉ አካባቢዎች ከሚገኘው ግብር ከፋይ ግብር ለመሰብሰብ የሚያስችል ሥርዓት እየዘረጋ ይገኛል፡፡ በተለይ በ2016 በጀት ዓመት ለመሰብሰብ የታቀደውን 130 ቢሊዮን ብር ግብር ለመሰብሰብ በቴሌ ብር በማሳለጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
በተጨማሪም በኬላዎች ላይ የሚሰበሰበውን ቀረጥ በቴሌ ብር ለመሰብሰብ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ብሩክ ጠቁመዋል፡፡ በምስራቅ አርሲ ሻሸመኔ፤ በምስራቅ ሐረርጌ ቦርደዴ፤ በምዕራብ ሐረርጌ ጎዴ፣ ባቢሊ፣ ደንገጎና ጉሩሱም፤ በደቡብ ምስራቅ ሸዋ ተጂ ኬላዎች ላይ የሚከፈለው የእቃ ቀረጥ በቴሌ ብር እንዲከፈል መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከ39ሺ በላይ የሚሆኑ ቀረጥ ከፋዮች በቴሌብር አማካይነት የቀረጥ ክፍያቸውን መክፈላቸውንና ከቀረጥ ክፍያው ከ44ሚሊዮን ብር በላይ በቴሌብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ የታክስ‹‹ሀ ››ግብር ከፋዮች ቁጥር 24ሺ፤‹‹ ለ ››ግብር ከፋዮች 18ሺ ያህል ሲሆኑ ‹‹ሐ›› የግብር ከፋዮች 456ሺ ግብር ከፋዮች አሉት፡፡ እነዚህ ግብር ከፋዮች ደንበኞች ግብራቸውን በቴሌብር እንዲከፍሉ ተደራሽ ለማድረግ የአጭር የጽሐፍ መልዕክት በመላክ ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ዲጂታላያዜሽን እንዲመጡ ለማድረግ ከገቢዎች ቢሮ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ የግብር ክፍያን በዲጂታል ዘዴ በቴሌ ብር መክፈል የሚያስገኘው ጠቀሜታ ጊዜን፤ ወጪን ይቆጥባል፡፡ ግብር ከፋዩ ጊዜና ሰዓት ሳይገድበውና ባለበት ሆኖ አገልግሎቱን ማግኘት ያስችለዋል፡፡ ቴሌ ብር ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የክፍያ ደረሰኝ ማጭበርበርን ለማስወገድና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያስችላል። ዜጎች በቀላሉ የቴሌ ብር የሞባይል መተግበሪያ ወይም *127# አጭር ቁጥርን በመጠቀም ግብርን በመክፈል የክፍያ ማረጋገጫ ደረሰኝ ወዲያውኑ ለማግኘት እንደሚያስችል ገልጸዋል። ቴሌብርን በጣም ቀላል በሆነ መንገድ መጠቀም የሚቻል በመሆኑ አስተማማኝ ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ገቢዎች ቢሮ በአሠራር ሥርዓቱ (በሲስተሙ) አማካይነት ግብር መከፈሉን ወዲያወኑ የሚያወቅባቸው ሁኔታዎች የተቀመጡለት መሆኑን ጠቁመው፤ የግብር አሰባሰብ ሥርዓቱን በቴሌብር የተደገፈ በማድረግ የግብር አሰባሰብ ሥርዓት ማዘመን የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በቴሌ ብር ግብር ከመሰብሰቡ አንጻር በዲጂታል ዘርፉ ቀዳሚና ውጤታማ መሆን ያስችለዋል የሚሉት አቶ ብሩክ፤ የግብር ከፋዮችን በዲጂታላይዜሽን ላይ ያላቸውን እውቀት በማሳደግ ግብርን በጊዜውና በወቅቱ በቀላል ዘዴ ለመሰብሰብ የሚያስችል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ ብሩክ ማብራሪያ፤ አሁን ላይ ወደ ዲጂታል ክፍያ ሥርዓት የመግባቱን ሂደት በመጀመር 69 የሚሆኑት የግብር መክፍያ ማዕከላት በቴሌብር ግብር ለመሰብሰብ እንዲችሉ ተደርገዋል፡፡ ለገቢዎች ቢሮ ሠራተኞች ስልጠናዎች የመስጠት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ 285 የሚሆኑ የ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮችን የማሰልጠን ሥራዎች እየሰሩ ናቸው፡፡ በቀጣይ ኢትዮ ቴሌኮም ስልጠናዎች በመስጠት፤ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ግንዛቤዎች የመፍጠር ሥራዎችን በመስራት፣ ከገቢዎች ቢሮ ጋር በመሆን በማገዝና በመደገፍ አብሮ እንደሚሰራ ነው የሚናገሩት፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንደሚሉት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ተግባራዊ የተደረገው ቴሌ ብር እስካሁን 34 ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራት ችሏል። ቴሌ ብር በክልሉ የሚገኙ ግብር ከፋዮች ከየትኛውም ቦታ ሆነው በቀላሉ በቴሌ ብር ግብራቸውን ለመክፈል ያስችላል፡፡ ዜጎች ካሉበት ቦታ የገቢ ግብርንም ሆነ የቀረጥ ክፍያቸውን ቀላል፣ ፈጣንና አስተማማኝ በሆነው ቴሌ ብር ቢከፍሉ ጊዜያቸውን ለመቆጠብ ይችላሉ፡፡
ኢትዮቴሌኮም የዲጂታል ሥርዓት በመዘርጋት ሂደት ችግሮች ሲያጋጥሙም መፍትሔ በመስጠት ከተቋማት ጋር ይሰራል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፤ ኢትዮ ቴሌኮም አስቻይ ሆኖ ተቋማት በሙሉ ተወዳዳሪና ውጤታማ ሆነው ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንድትሆን የአስቻይነትን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2015