ዓለም ሳትሰለጥን ጀምሮ የዘረኝነት መንፈስ የተጣባቸው ሰዎች ጥቁሮች ላይ የሚፈፅሙት ፀያፍ ተግባር ዛሬም ዓለም ሰልጥኖ ለጥቃቅን እንሰሳት መብት በሚሟገትበት ዘመን እንኳን መቅረት አልቻለም። የጥቁሮችን ስኬት ለመቀበል የሚተናነቃቸው ዛሬም በእግር ኳሱ ዓለም በየስቴድየሞቹ ዘረኛ ደጋፊዎች ድንገት በሚረጩት የዘረኝነት መርዝ ጥቁር ከዋክብት በቆዳ ቀለማቸው ብቻ ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል።
አስገራሚው ነገር ሰልጥነናል በሚሉ ነጮች ጥቁር ተጫዋቾች ለክለባቸው ሲጫወቱ ብቻ አይደለም በቆዳ ቀለማቸው መጥቆር ከሰው ዝቅ ተደርገው የስድብ ናዳና ትንኮሳ የሚወርድባቸው። መነሻቸው አፍሪካ ሆኖ ለአውሮፓ ብሔራዊ ቡድኖች ታላላቅ ክብርን ያጎናፀፉ ጥቁር ከዋክብት ዛሬም በዘረኛ ደጋፊዎች መዘለፋቸው ነው። ይህ የውብ እግር ኳስ አስቀያሚ ገፅታ ከወር በፊት በቫሌንሲያ ማስቴላ ስቴድየም ብራዚላዊው አፍሮ ኤሽያን ኮከብ ቪኒሺየስ ጁኒየር ላይ ከተፈጸመ በኋላ ብዙዎችን አስቆጥቷል።
በስፔን ስቴድየሞች የተለያዩ ክለብ ደጋፊዎች በጥቁር ተጫዋቾች ላይ የዘረኝነት ጥቃት ሲፈጸም ቪኒሺየስ የመጀመሪያ አይደለም። በእርግጥ ከስፔን በተጨማሪ ሌሎች የአውሮፓ ሊጎችም የዚህ ደዌ ተጠቂ ናቸው። ጣሊያን ከዚህ ችግር ለረጅም ዓመታት መላቀቅ ያልቻለች አገር ናት። የሩቁን ትተን ከጥቂት ወራት በፊት በኢንተር ሚላኑ አጥቂ ሮሜሮ ሉካኩ ላይ የዘረኝነት ጥቃት የፈፀሙ 171 የዩቬንትስ ደጋፊዎች ስቴድየም እንዳይገቡ መታገዳቸውን ማስታወስ ይቻላል። በዚህም ምክንያት የጣሊያን ባለስልጣናት በቂ እርምጃ አልወሰዱም ተብለው ዋንጫን የሚያህል ክብር አጎናፅፈው ዳግም በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ቢያበቁም በአርጀንቲና በመሸነፋቸው የቡድኑን እንቁ ተጫዋች ኪሊያን ምባፔን ጨምሮ ሌሎች ኮከቦች ወደ ፓሪስ ሲመለሱ ሙገሳ ሳይሆን ፀያፍ የዘረኝነት ስድብ ነው በሶሻል ሚዲያው የጠበቃቸው። የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ከዋክብት ማርከስ ራሽፎርድና ባካዮ ሳካም በ2020 አውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ የመለያ ምት በመሳታቸው በቆዳ ቀለማቸው ተብጠልጥለዋል።
በስፔን ስቴድየሞች የሚንፀባረቀው የደጋፊዎች ዘረኝነት ግን ከሁሉም የተለየ ሆኖ በተለያዩ ዘመናት የመታየቱ እንቆቅልሽ አልተፈታም። 2000 ላይ የማላጋው ዩራጋዊ ተጫዋች ዳሪዮ ሲልቫ ለአንድ የኦቪዶ ክለብ ደጋፊ የአድናቆት ፊርማ አላኖርም በማለቱ የዘረኝነት ስድብ ተሰንዝሮበት ወደ ፀብ ያመራበት አጋጣሚ ዛሬም አይረሳም።
2004 ላይ ስፔን ከእንግሊዝ ባደረገችው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ አንዲ ኮል፣ ሪዮ ፈርዲናንድ፣ ጀርሚን ሄናስ፣ ጀርሚን ዴፎይን የመሳሰሉ ጥቁር ከዋክብት በቤርናቦ ስቴድየም ደጋፊዎች የዝንጀሮ ድምፅ እያሰሙ ሊያሸማቅቋቸው ሞክረዋል። ፊፋም በዚህ የደጋፊዎች ፀያፍ ተግባር የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ የ112 ሺ ዶላር በላይ ቅጣት ብቻ ጥሎ አለፈ። በስፔን ሊጎች ፅንፈኛ ደጋፊዎች 2004 ላይ ካሜሩናዊው የባርሴሎና ኮከብ ሳሙኤል ኤቶ ላይ የፈፀሙት የዘረኝነት በደል መቼም የሚረሳ አይደለም። የሄታፌ ደጋፊዎች ኤቶ ላይ የዝንጀሮ ድምፅ እያሰሙ በቆዳ ቀለሙ መጥቆር ሊያሸማቅቁት ሞክረዋል። እሱም ስሜታዊ ሆኖ ኳስ አንስቶ ወደ ፀነፉት ደጋፊዎች በመምታት የቢጫ ካርድ ሰለባ ሆኗል። ኤቶ 2006 ላይም በሪያል ዛራጎዛ ላ ርማሬዳ ስቴድየም ተጨማሪ የዘረኝነት ስድብ ከደጋፊዎች ማስተናገድ አልቀረለትም ነበር። በዚህ ወቅት ግን ኤቶ ትእግስቱ ተሟጦ ልክ ሰሞኑን ቪኒሺየስ ሜዳውን ለቆ ለመውጣት ተቃርቦ ነበር። የባርሳና ተጫዋቾችና ሌሎችም አፅናንተውና አግባብተው ጨዋታውን ጨርሶ እንዲወጣ አደረጉት እንጂ። ለዚህ ጥፋት ክለቡ የጠበቀው ግን የ9ሺ ዩሮ ቅጣት ብቻ ነው።
2014 የባርሴሎናው ተከላካይ ዳኒ አልቬስ በቪላሪያል ስቴድየም የማእዘን ምት ለመምታት በሚዘጋጅበት ወቅት ሙዝ ተወርውሮበት አንስቶ የበላበት አጋጣሚ ብዙዎች የተገረሙበት ነው። ይህን ድርጊት ፈፅሟል የተባለ የ26 ዓመት ግለሰብ ኋላ ላይ በሰብአዊ መብት ጥሰት ተከሶ በቁጥጥር ስር በመዋል የ6ሺ ብር ቅጣት እንዲከፍል ተደርጓል። ቪያሪያልም ደጋፊው በፈፀመው ጥፋት በ12ሺ ዩሮ ቅጣት ታልፏል።
እነዚህ በስፔን እግር ኳስ በጥቁር ተጫዋቾች ላይ ከተፈፀሙ የዘረኝነት ጥቃቶች የማይረሱ ተብለው ይጠቀሱ እንጂ በስፔን ስቴድየሞች ደጋፊዎች በራሳቸው ክለብ ተጫዋች ጭምር ተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃት ያላደረሱበትን ጥቁር ተጫዋች ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው።
ብራዚላዊው ኮከብ ቪኒሺየስ በማስቴላ ስቴድየም የደረሰበት በደል የመጀመሪያ አይደለም። ከዚህ ቀደም ሌሎች ተጫዋቾች ከደረሰባቸው ተመሳሳይ የዘረኝነት ጥቃት አንፃር ግን እዚህ ወጣት ኮከብ ላይ እየደረሰበት ያለው ነገር የበዛ ነው። ባለፈው ጥር የአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎች በሪያል ማድሪድ ላይ ያላቸውን ጥላቻ ለመግለፅ በልምምድ ሜዳ ሳይቀር ቪኒሺየስን መጠቀሚያ ሊያደርጉት ሞክረዋል። የስፔን ፖሊስ ጉዳዩን ከወንጀል ጋር አያይዞ ምርመራ እያደረገበት እንደሚገኝ በወቅቱ ቢገልፅም የወሰደው እርምጃ ተድበስብሶ ቀርቷል።
ቪኒሺየስ በአንድ ወር ልዩነት የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ በሪያል ማዮርካ ደጋፊዎች ዳግም በቆዳ ቀለሙ መጥቆር ተተንኩሷል። ክለቡም ይህን ፈፅሟል ያለውን ግለሰብ ከደጋፊ አባልነት ለሶስት ዓመት አግዶታል። ሪያል ማድሪድ ከቫሌንሲያ ጋር በነበረው ጨዋታ በደጋፊዎች የዘረኝነት ስድብ ሲያስተናግድ በጥቂት ወራት ልዩነት ሶስተኛ ጊዜው ነው። ይህ ጥቃት ግን እንዳለፉት ጊዜያት ተድበስብሶ የሚቀርና በቀላሉ የሚረሳ አይመስልም፣ ብዙ እሳት ቆስቁሷልና። በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ከዋክብቶች ብራዚላዊው ኮከብ ላይ የደረሰውን በደል በማውገዝ ከጎኑ መሆናቸውን አሳይተዋል። በወቅቱ በርካታ ብራዚላውያን በስፔን ኤምባሲ በር ላይ ተሰባስበው ጥቃቱን አውግዘዋል። የስፔን መንግስት ቃል አቀባይ ኢዛቤል ሮድሪጌዝም ስፔን ይህን አይነቱን ያልተገባ የዘረኝነት ባህሪ ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው ቪኒሺየስ ላይ በደረሰው ጥቃት ማዘናቸውን ገልፀው ነበር። የስፔን መንግስትም ይህን የውብ እግር ኳስ ገፅታ የሚያጎድፍ የዘረኝነት በሽታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ከምንጊዜውም በላይ ጫና አድሮበታል።
በዚህም ጉዳዩ በስፔን ፖሊስ ክትትል እየተደረገበት አራት የቫሌንሲያ ደጋፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል። ወትሮም በዘረኛ ደጋፊዎች መጨከንና መረር ያለ ቅጣት መጣል የማይሆንለት የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ለዘረኝነት የመራራት አባዜው የለቀቀው አይመስልም።
የዘረኝነት ስድብ ሲሰነዘር የነበረበት የቫሌንሲያ ሜስታላ ስቴድየም በስተደቡብ የሚገኘው የደጋፊዎች መቀመጫ ለአምስት ጨዋታዎች እንዲዘጋ ያስተላለፈውን ውሳኔ ቀልብሶ ለሶስት ጨዋታዎች ብቻ ፈርዶበታል። በተጨማሪም ቫሌንሲያ ላይ የጣለውን የ45 ሺ ዩሮ ቅጣት ወደ 25 ሺ ዩሮ አውርዶታል። ይህም በበርካቶች ዘንድ ላሊጋው ዘረኝነትን ከስፔን እግር ኳስ የማስወገድ አፒታይት እንደሌለው ማሳያ ተደርጎ ለሰላ ትችት ዳርጎታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2015