ልጆች እንደምን ከረማችሁ? ደህና ናችሁ አይደል? ጥሩ ነው ሰሞኑን የፈተና ጊዜ ነበርና ፈተና እንዴት ነበር? እርግጠኛ ነኝ በደንብ ስላጠናችሁ ብዙዎቻችሁ ውጤታችሁ ጥሩ ይሆናል ⵆ እኔም መልካም የትምህርት ውጤት እንዲገጥማችሁ እመኝላችኋለሁⵆ ነገር ግን በዚህ የፈተና ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ሳታጠኑ ጥሩ ውጤት ያላመጣችሁም ለቀጣይ ሰርቼ ከዚህ በበለጠ አመጣለሁ ብላችሁ የክረምት ጊዜውንም በጥናት ማሳለፍ እንዳለባችሁ ማወቅ ያስፈልጋልⵆ
ልጆች ዛሬ ከፈተና ድካም አረፍ የምትሉበት ብሎም የነገ ራዕያችሁን የምታዩበትና ከተለያዩ ባለሙያዎች የህክምና መሳሪያዎች ጋር የምትተዋወቁበትን አጋጣሚ የፈጠረ አውደ ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም መከፈቱን ልነግራችሁ ነውⵆ
ይህ አውደ ርዕይ በጤና ሚኒስቴርና በሌሎች ተቋማት የተዘጋጀ ሲሆን ለእናንተ ለህጻናት ተብሎ የተለየ “የህጻናት ዞን” አለ ⵆ በዞኑ ውስጥ ደግሞ ዶክተር ሳይንቲስት መሆን የሚፈልጉ ህጻናት አልባሳቱን ለብሰው መሳሪያዎቹን አድርገው የተለያዩ ተግባራትን በባለሙያ እየተደገፉ እንዲያከናውኑ ተፈቅዶላቸዋልⵆ ባለሙያዎችን በመጠየቅ እውቀታቸውን እንዲያሰፉ እድል ተሰጥቷቸዋልⵆ እኔም በስፍራው በተገኘሁበት ወቅት ህጻናት ” በህጻናት ዞኑ” ውስጥ ቁጭ ብለው የተለያዩ ነገሮችን ሲያደርጉ ተመለክቻለሁⵆ
ተማሪ ሄቨን ኢሳያስ የብስራተገብርኤል ትምህርት ቤት የመሰናዶ (ፕሪፕ ) ተማሪ ስትሆን ከፍተኛ የሆነ ሳይንቲስት የመሆን ፍላጎት አላት ⵆ በሳይንስ ሙዚየሙ የተዘጋጀው አውደ ርዕይ ላይ ተገኝታለችⵆ
ሁልጊዜ የምትፈልገውን ነገር እንድትሆን ቤተሰቦቿ እንደሚያበረታቷትና የተለይም ሳይንቲስት የመሆን ፍላጎቷ እንዲሳካ አባቷ የተለያየ ቦታዎች እንደሚወስዳት ገልጻ፣ አሁን በሳይንስ ሙዚየም መጥታ የሳይንቲስት የስራ ልብስ ለብሳ መሳሪያዎችን ይዛ መነካካት መቻሏ በጣም እንዳስደሰታትም ትናገራለችⵆ
ልጆችም የሚፈልጉትን ነገር ለመሆን በርትተው እንዲያጠኑና የሚፈልጉትን ነገር ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን አስፈቅደው ማየት እንደሚችሉ ትናገራለችⵆ
ሌላው በቦታው ላይ የነበረው ተማሪ እራሱን የሚጠራው ዶክተር ሁሴን አህመድ በማለት ነውⵆ ምንም እንኳን ገና የስድስት ዓመት ህጻን ልጅ ቢሆንም ነገ ተምሮ ዶክተር መሆን እንደሚችል እርግጠኛ ስለሆነ ከአሁኑ ለራሱ ዶክተር የሚለውን የሙያ ማዕረግ ሰጥቷልⵆ እኔም ዶክተር እያልኩ ነው ያዋራሁት ⵆ
ዶክተር ሁሴን በግሪክ ትምህርት ቤት የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን በትምህርቱም በጣም ጎበዝ እንደሆነ ይናገራልⵆ ሲያድግም ዶክተር በመሆን ሰዎችን መርዳትና ማከምም በጥብቅ ይፈልጋልⵆ
” ዛሬ አባቴ ወደሳይንስ ሙዚየም አምጥቶኝ እንደ ዶክተር ለብሼና የጆሮ ማዳመጫ አድርጌ ሰዎችን እያከምኩ ነው፤ በዚህም በጣም ደስ ብሎኛልⵆእንደ እኔ ዶክተር የመሆን ፍላጎት ያላቸው ልጆችም ወደሳይንስ ሙዚየም በመምጣት ዶክተር መሆን ይችላሉ “በማለት ተናግሯልⵆ
ተማሪ በእምነት የኔነህ የ11 ዓመት ታዳጊ ሲሆን የስኩል ኦቭ ቱሞሮ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነውⵆ ተማሪ በእምነት የሳይንስ ትምህርት በጣም እንደሚወድና ጥሩ ውጤትም እንደሚያመጣበት ይናገራል ⵆ በሳይንስ ሙዚየምም በመምጣቱ ብዙ አዳዲስ የህክምና መሳሪያዎችን ከማየቱም በላይ እንዴት ተደርጎ ጥቅም ላይ እንደሚውልም መመልከት መቻሉ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረበት ይናገራልⵆ
በተለይም የላብራቶሪ ማሽኖች የሰዎችን ደምና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ወስደው በመመርመር ያለውን ችግር የሚያሳዩበት መንገድ በጣም እንደማረከው የሚናገረው በእምነት ይህም ከእሱ የህክምና ባለሙያ የመሆን ህልም ጋር ስለተገናኘለት በጣም መደሰቱን ያብራራልⵆ
” ዶክተር ለመሆን መጀመሪያ ፍላጎት ከዛ ደግሞ ጠንክሮ መማር ያስፈልጋልⵆ እኔ በሳይንስ ትምህርት በጣም ጎበዝ ነኝⵆ ይህንንም አጠናክሬ እቀጥላለሁ ⵆ እንደ እኔ ዶክተር ለመሆን የምትፈልጉ ልጆች ደግሞ በመጀመሪያ ሙያውን መውደድና አለመውደዳቸውን እርግጠኛ መሆንና በትምህርት ጎበዝ መሆን ከዛ አልፎ ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የማታውቁትን ነገር መጠየቅ አለባችሁ “ብሏል ተማሪ በእምነትⵆ
ልጆች እናንተም እንደልጆቹ መጀመሪያ መሆን በምትፈልጉት ነገር ላይ እርግጠኛ ከሆናችሁና ትምህርታችሁን በአግባቡ ካጠናችሁ ዶክተርም ሳይንቲስትም መሆን ትችላላችሁⵆ ሌላው ደግሞ ለአንድ ወር ያህል የሚቆየውን የጤና ኤግዚቢሽን ከእናትና አባታችሁ ጋር ሆናችሁ በመጎብኘት የተለያዩ እውቀቶችን ማግኘት ትችላላችሁ እሺ ልጆችⵆ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2015