‹‹ሰኔ እና ሰኞ›› እንዳንለው ሁለቱም ክስተቶች በዕለተ ቅዳሜ የተከሰቱ ናቸው። የታሪክ ግጥምጥሞሽ አንዳንዴ እንዲህ ነው! በግንቦት ወር ውስጥ የኢህአዴግና የደርግን የታሪክ ግጥምጥሞሽ ስናስታውስ ነበር። እነሆ በሰኔ ወር ውስጥ ደግሞ የብልጽግና የታሪክ አጋጣሚዎች ተከስተዋል። ተከታታይ ቀናት (ሰኔ 15 እና 16) ተከታታይ ዓመታት (2010 ዓ.ም እና 2011 ዓ.ም) ክስተቶች ናቸው። በዓመተ ምህረታቸውና በክስተታቸው ቅደም ተከተል እንሂድ!
የሰኔ 16 የዶክተር ዐቢይ የድጋፍ ሰልፍ
ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተመረጡ በሦስተኛው ወር አካባቢ የድጋፍ ሰልፍ ተዘጋጀ። ዕለተ ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፉ እንደሚደረግ አስተባባሪ ኮሚቴው አሳወቀ።
በተባለው ቀንና ቦታ የጠጠር መጣያ እስከሚጠፋ ድረስ ከአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ በመጡ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች መስቀል አደባባይ ተጥለቀለቀ።
በዚያ ክስተት ውስጥ ዓመቱን ሙሉ መነጋገሪያ ሆኖ የከረመውና በታሪክም የሚመዘገበው አስደንጋጭ ክስተት ግን ተከሰተ። ክስተቱን እናስታውስ።
ዶክተር ዐቢይ ንግግር አድርገው ጨረሱ። መድረክ መሪው ማይኩን ከዶክተር ዐቢይ ተቀብሎ በአማርኛ የተናገረውን በእንግሊዝኛ እየደገመ ሳለ፤ በቀጥታ ሥርጭት ለሚከታተሉ ብዙም ያልተሰማ፣ በጭብጨባና ጩኸት ለታጀበው ታዳሚ እምብዛም ጉልህ ያልሆነ የፍንዳታ ድምጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች ባለስልጣኖች ካሉበት መድረክ አቅራቢያ ተሰማ። ዳሩ ግን በዚያው ቅጽበት ፍንዳታው ቦንብ መሆኑን ያወቁት በመድረኩ ላይና እዚው አቅራቢያ የነበሩት ብቻ ናቸው።
የፍንዳታው ድምጽ ወደተሰማበት አቅጣጫ ለመመልከት ጠቅላይ ሚኒስትሩና በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው የነበረ ሲሆን በዚያው ቅጽበትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠባቂዎች ዶክተር ዐቢይን ዙሪያቸውን በመክበብ እያጣደፉ ከመድረክ ይዘዋቸው በመውረድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቀኑ።
ቦንቡ በፈነዳበት የመድረኩ አቅራቢያ ትርምስ በመፈጠሩ የጸጥታ ሰራተኞች ተሰማርተው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት ጥረት ያደርጉ ነበር። ይህም ሆኖ ከመድረኩ እርቀው የነበሩ የሰልፉ ታዳሚዎችና በቴሌቪዥን በቀጥታ ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎች ግን ምን እንደተከሰተ አላወቁም ነበር።
በመድረኩ ላይ ይካሄድ የነበረውን ሥነ ሥርዓት በቀጥታ ሲያስተላልፉ ከነበሩት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መካከል ቀዳሚው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የነበረ ሲሆን ከፍንዳታው መከሰት በኋላ ያቀርባቸው የነበሩት ምስሎች ከመድረኩ የራቁትን ብቻ ነበር።
የፍንዳታው ክስተት በማህበራዊ ሚዲያዎችና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን በኩል ከተገለጸ በኋላ በአጠቃላይ በሕዝቡ ላይ በተለይ ደግሞ በአደባባዩ ታድመው በነበሩ ሰዎች ላይ ድንጋጤና ቁጣን ቀሰቀሰ። አንዳንዶችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጉዳት የደረሰ ስለመሰላቸው ስሜታዊ እስከመሆን ደርሰው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጽህፈት ቤታቸው በተመለሱ በደቂቃዎች ውስጥ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ደህና መሆናቸውንና በቦንብ ጥቃቱ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን በማሳወቃቸው ወዳልታወቀ አቅጣጫ ሊያመራ ይችላል ተብሎ የተሰጋው ቁጣ ረገብ ማለት ችሏል። ቢሆንም ግን በታዳሚው መካከል የተወሰኑት ከጥቃቱ ጋር ሊገናኙ ይችላሉ ባሏቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቧል።
በክስተቱ የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በመስቀል አደባባይና በአካባቢው ተቋርጦ ነበር። በዚህም ምክንያት በዕለቱ የስልክ ግንኙነት ማድረግም አዳጋች ሆኖ ነበር።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሁነቱን ከመስቀል አደባባይ ከተለያዩ ስፍራዎች ምስሎችን እያሳየ የነበረ ሲሆን ከፍንዳታው በኋላ ግን የተወሰኑ ካሜራዎቹ ምስል ማስተላለፍ እንዳልቻሉ በስፍራው የነበረ የጣቢያው ባልደረባ እንደነገረው ቢቢሲ በወቅቱ ዘግቧል። ምክንያቱም የካሜራዎች ገመዶች ባልታወቁ ሰዎች በመቆረጣቸው እና በካሜራዎች ላይ ጉዳት በመድረሱ ነበር።
ከፍንዳታው ዕለት ከሰዓት በኋላ አንስቶ ባሉት ተከታይ ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሆስፒታል በመሄድ ጠይቀዋል፤ በተጨማሪም የደም ልገሳ አድርገዋል።
በተከታታይ ቀናትም ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፤ በድርጊቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ የፖሊስና የደኅንነት ኃላፊዎችና ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው መነገር ጀመረ።
የአገር ውስጥ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት የሚያደርጉትን ምርመራ ለማገዝ አሜሪካ ውስጥ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር የታወቀው የኤፍ ቢ አይ ባለሙያዎችም ተልከዋል።
በወቅቱ በትንሹ ለሁለት ሰዎች መሞትና ለበርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት ምክንያት ለሆነውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጉዳት ቢደርስ ኖሮ ከባድ ምስቅልቅልን ሊያስከትል ይችል በነበረው የሰኔ 16ቱ የቦንብ ጥቃት በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል። እነሆ ያ ክስተት ታሪክ ሆኖ ሲታወስ ይኖራል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኔ 18/2015