የታሪካዊውን አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰብያ የሆነው የማራቶን ውድድር በነገው ለ39ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ውድድሩ ነገ ከጠዋት 12፡00 ጀምሮ መነሻውንና መድረሻውን ሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ አካባቢ በማድረግ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሰጠው መግለጫ አሳታውቋል።
ውድድሩ ለከተማ አስተዳደር፣ ለክለቦችና ለግል ተወዳዳሪ አትሌቶች የአገር ውስጥ የውድድር ዕድል ለመፍጠርና ተተኪ የማራቶን አትሌቶችን ለማፍራት ታስቦ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል። በተጨማሪም በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች መካከል በስፖርቱ ፉክክርን ለመፍጠርና ውድድሩን የሚያሸንፉ አትሌቶችን በሽልማት ለማበረታታት እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
ፌዴሬሽኑ ውድድሩን በጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ ስም የሚያካሂደው ጀግናውን አትሌት ለመዘከርና ውጤታማ የማራቶን አትሌቶችን በዘላቂነት ለማፍራት ትልቅ መነቃቃት ይፈጥራል ብሎ ሲሆን፣ በማራቶን ውድድር ትልቅ ስም ያላቸው 12 ክለቦች፣ 2 ክልሎችና 1ከተማ አስተዳደሮ እንደሚሳተፉ ጠቁሟል። በውድድሩ አንጋፋ(ቬተራን) አትሌቶችና የግል ተወዳዳሪ አትሌቶችም የሚሳተፉ ይሆናል።
የአበበ ቢቂላ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ 51 አትሌቶች በማፎካከር የተጀመረ ሲሆን ውድድሩን ያጠናቀቁት 27 ብቻ ነበሩ። ውድድሩንም አንደኛ በመውጣት ያሸነፈው አትሌት ሻምበል ከበደ ባልቻ ሆኖ ይታወሳል። 42 ኪሎ ሜትሩን ያጠናቀቀውም በ2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ነበር። በዘንድሮ ውድድር 92 ሴትና 262 ወንድ በድምሩ 354 አትሌቶች በውድድሩ እንደሚሳተፉ የተገለፀ ሲሆን፣ 11 ታዋቂ አትሌቶች የሚያደርጉት ፉክክርም ይጠበቃል።
በሴቶች ዘርፍ ከሚካፈሉት ውጤታማ አትሌቶች አንዷ የሆነችው የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ደጊቱ አዝመራው ትጠቀሳለች። ይቺ የማራቶን ውጤታማ አትሌት እአአ በ2019 በሞሮኮ ራባት በተካሄደው መላው አፍሪካ ጨዋታዎች የብርና በተመሳሳይ ዓመት በኔዘርላንድ በተካሄደ የማራቶን ውድድር 1ኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳለያ ባለቤት መሆኗ ይታወሳል። ደጊቱ በ2021 የለንደን ማራቶን 2ኛ ሆና ያጠናቀቀች አትሌት እንደመሆኗ የነገው ውድድር ድምቀት ትሆናለች ተብሎ ይጠበቃል። ወጣቷ አትሌት ጽዮን አበበ፣ብዙአገር አደራው፣ ማሚቱ ባልቻ በነገው ውድድር ጎልተው ከሚጠቀሱ ታዋቂ አትሌቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድር ወጣቱ ኃይለማርያም ኪሮች ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የማሸነፍ ቅድመ ግምት የተሰጠው አትሌት ሲሆን ጽዳት አበጀና ልመንህ ጌታቸውን የመሳሰሉ የርቀቱ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ይጠበቃሉ።
ለውድድሩ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ፌዴሬሽኑ የገለፀ ሲሆን 1.2 ሚሊዮን ብር ለሽልማትና ሌሎች ወጪዎች በጀት መመደቡም ታውቋል።
በሁለተም ጾታ ከ1ኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለሚወጡ አትሌቶች የወርቅ፣ ብርና የነሐስ ሜዳሊያዎችን ከመሸለም በተጨማሪ እንደየደረጃቸው የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል። በሁለቱም ፆታ ከ1ኛ-8ኛ በመውጣት የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በተቀመጠው የሽልማት መጠን እያንዳንዳቸው ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል።
ፌዴሬሽኑ ለሽልማት 400ሺ ብር ያዘጋጀ ሲሆን 1ኛ 50ሺ፣ 2ኛ 25ሺና 3ኛ 20ሺ ብር ሽልማት የሚያገኝ ይሆናል። 8ኛ ደረጃን ይዞ የሚያጠናቅቅ አትሌት ደግሞ ዝቅተኛ የተባለውን የ10ሺ ብር ሽልማት የሚወስድ ይሆናል። የገንዘብ ሽልማቱ ለአንጋፋ አትሌቶችም የተዘጋጀ ሲሆን ከ1ኛ-6ኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን ለሚያጠናቅቁ የሚሰጥ ይሆናል። በዚህም 1ኛ ለሚወጡት 12ሺ ብር፣ 2ኛ ለሚወጡት 6ሺ ብርና 3ኛ ለሚወጡት 5ሺ ብር ይበረከታል። በሁለቱም ጾታ በቡድን አሸናፊ ለሚሆኑ ደግሞ የዋንጫ ሽልማት እንደሚሰጥ ተገልጿል። ውድድሩን የሚመሩ በአለም አትሌቲክስ ደረጃ የሰለጠኑ 80 ዳኞች ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል።
የሻምበል አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ውድድር በ1974 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረ ሲሆን፤ በየዓመቱ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተካሄደ አሁን 39ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል። በመጀመሪያው ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት አገራት ማለትም ጅቡቲና ሶቪየት ተካፍለዋል። እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ የአበበ ቢቂላ ዓለም አቀፍ ማራቶን ውድድር የሚል ስያሜን በመያዝ የውጭ አገራት አትሌቶችን ተሳታፊ ሲያደርግ ቢቆይም ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ግን ውድድሩ አገራዊ መልክ እንዲይዝና ስያሜውም የሻምበል አበበ ቢቂላ ማራቶን ውድድር በሚል ተሰይሞ እየተካሄደ ዛሬ ላይ ደርሷል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2015