ከአቶ መኮንን ኃይሉ እና ከወይዘሮ ፅጌ ገመቹ ከተባሉ አባትና እናቷ በ1995 ዓ.ም በኦሮሚያ ልዩ ዞን ሰንዳፋ ቀበሌ ልዩ ቦታው 44 ማዞሪያ ሥላሴ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይችን ዓለም ተቀላቀለች። ቤተሰቦቿ ልጆቻቸውን እንደማንኛውም ወላጆች እርሳስ፣ እስክርቢቶ፣ ደብተር ገዝቶ ለማስተማር ይቅርና በቀን አንዴ መግቦ ለማስተዳደር ኑሮው ዳገት ሆኖባቸዋል። ከእጅ ወደ አፍ ያለፈ ተቀማጭ ጥሪትም አልነበራቸውም።
ልጃቸው ሕይወት መኮንን እደሜዋ ለትምህርት ቢደርስም ቤተሰቦቿ ለማስተማር አቅማቸው አልፈቀደም። መቼም በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አይደለም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና አፍንጫ ስር ይቅርና እልም ያለ ገጠር ውስጥ የሚኖር አርሶ አደር ስለ ትምህርት ጥቅም ጠንቅቆ ያውቃል ቢባል ማጋነን አይሆንም። አርሶ አደሩ ትናንት የትምህርት ጥቅሙንና እድሉን አውቆና አግኝቶ ሳይማር መቅረቱ “የእግር እሳት” ሆኖበት ዛሬ ላይ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካልገጠመው በስተቀር ልጁን ትምህርት ቤት የማይልክ ወላጅ አለ ብሎ መገመት ያዳግታል። ነገሩ “ማጣት ከሰማይ ይርቃል” እንዲሉ ሆኖ የሕይወት ቤተሰቦች ግን ልጃቸውን እንደኩዮቿ ቀለም እንድትቀስም ትምህርት ቤት ለመላክ አልቻሉም። በዚህም እኩዮቿ ደብተር ይዘው ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱና ሲማሩ ውለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ዘወትር ቤተሰቦቿ ሲያዩ የልጃቸውን እድል እንደሰበሩት፤ የነገ ተስፋዋን እንዳጨለሙት፤ ከእኩዮቿ በታች እንዳደረጓት እየተሰማቸው ቅስማቸው ይሰበራል። ልባቸው ያዝናል።
በተመሳሳይ ሕይወትም እኩዮቿ ጠዋት ማልደው እየቦረቁ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ፤ ከትምህርት ገበታቸው ውለው በአንድ ላይ ሰብሰብ ብለው የቆጥ የባጡን እያወሩ፣ እየተጫወቱ፣ እንደእምቦሳ ጥጃ እየዘለሉ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ስታይ እሷም እንደእኩዮቿ ትምህርት ቤት ባለመዋሏ ታዝናላች፣ ታለቅሳለች። የትምህርት ጣሙንና ጥቅሙን ለይታ የማታውቅበት የእድሜ ደረጃ ላይ ብትሆንም ቅሉ እንደእኩዮቿ ትምህርት ቤት ውሎ መምጣት እንደውሃ ይጠማት፤ እንደእንጀራ ይርባት ነበር። እኩዮቿ ጋር ጠዋት ማልዳ ወደ ትምህርት ቤት እየቦረቀች መሄድ፤ ከትምህርት ገበታዋ ውላ ከእኩዮቿ ጋር እየተጫወተች ወደ ቤቷ መመለስ በአይኗ ይዞር ነበር። ነገር ግን ትምህርት ቤት ለመግባት እና እንደኩዮቿ ለመማር ግን አልታደለችም።
“ዓለም ለአንዱ እንቁላል ለሌላው ኩስ ትጥላላች” እንዲሉ ሕይወት እንደእኩዮቿ ትምህርት ቤት ገብቶ መማሩ ቀርቶባት ክፉና ደጉን መለየት እስከምትችልበት ዕድሜ ድረስ የቤተሰቦቿን ፍቅር አግኝታ ማደግ አልቻለችም። የሰባት ዓመት ልጅ እያለች እናቷ ለቤት ሠራተኝነት አሳልፋ ለባዳ ሰጠቻት። እስከ 12 ዓመቷ ድረስም በተለያየ ሰው ቤት በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ በለጋ እድሜዋ የሰው ፊት እየገረፋት ያገኘችውን የወር ደሞወዝ ለቤተሰቦቿ ትረዳ ነበር። በሰው ቤት ተቀጥራ እየሠራች ክፉውንም ደጉንም ገና በጨቅላ እድሜዎ አይታለች።
በሰው ቤት ተቀጥራ እየሠራች እያለ የተዋወቀቻት አንድ ጓደኛዋ ጋር ተያይዘው የተሻለ እንጀራ ፍለጋ ወደ አማራ ክልል ደብረ ማርቆስ ከተማ ይኮበልላሉ። ሕይወት ከቤተሰቦቿ እርቃ ወንዝ ተሻግራ ወደ ደብረ ማርቆስ መሄዷን ለቤተሰቦቿ ሳትናገር እዛው ደብረ ማርቆስ ከተማ ቀበሌ 04 አንድ ግለሰብ ቤት ውስጥ በቤት ሠራተኝነት ጓድኛ አማቾቹ ይቀጠራሉ። በዚህ ግለሰብ ቤት ለአንድ ዓመት ያህል ከሠሩ በኋላ “ያልተገላበጠ ያራል እንዲሉ” ሌላ የተሻለ ሥራ ፍለጋ በሀዲስ አለማየሁ በፍቅር እስከ መቃብር መጽሃፍ ላይ ጎልቶ ስሟ ወደ ምትታወቀው ማንኩሳ ከተማ ጎራ ይላሉ። ባልንጀሮቹ በማንኩሳ ከተማ በአንድ መለስተኛ ምግብ ቤት ውስጥ በምግብ አብሳይነት ተቀጥረው ለአራት ዓመት ያህል አብረው አንድ ቤት ሠርተዋል። ክፉውንም ደጉንም፣ ማግኘት ማጣቱንም በጋራ አሳልፈዋል። አንዱ ሲከፋው ሌላኛው እያጽናና፣ አንዱ ሲደሰት ሌላኛው ቢከፋውም አብሮ እየተደሰተ አራት ዓመት እንደአራት ቀን ሳይታወቃቸው እንደዋዛ አለፈ።
ጓደኝነታቸው ልክ “ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው” በችግርና ፈተና ውስጥ ጸንተው በፍቅር ዓመታትን አብረው አንድ ላይ ዘልቀዋል። ፍቅራቸው እየጠነከረ ከመምጣቱ የተነሳ ልክ እንደስጋ እህትማማች ይተያዩ ነበር። ከመዋደዳቸው የተነሳም ለምን አንድ ላይ ቤት ተከራይተን አንኖርም ይሉና ማንኩሳ ከተማን ተሰናብተው ወደ ፍኖተ ሰላም ከተማ አቀኑ። በዛም በጋራ መኖሪያ ቤት ተከራይተው አንድ ላይ መኖር ይጀምራሉ። በፍኖተ ሰላም ከተማም ምግብ ቤት ውስጥ ተቀጥረው እየሠሩ በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን እየደጎሙ ለሁለት ዓመታት ክፉውና ደጉን አሳልፈዋል። ሁለት ዓመታትን በአንድ ጣሪያ ስር ሲኖሩ አንዱ እሳት ሲሆን አንዱ ውሃ፤ አንዱ ሲያጠፋ ሌላኛው መካሪ እየሆነ በፍቅር በደስታ ኖረዋል።
የሰው ልጅ በሆነ አጋጣሚ እንደተገናኘ ሁሉ በተቃራኒው መለያየቱ አይቀሬ ነው። ጓደኛ አማቾቹም በአንድ አጋጣሚ ተዋውቀው ጎደኝነት መስርተው ለዓመታት አብረው ኖረዋል። በአንጻሩ ደግሞ ለዓመታት ከዘለቀው ያማረና የሠመረ የጓደኝነትና የአብሮነት ጉዞ በኋላ ሊለያዩ ግድ ሆነ። በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሲካሄድ በነበረው የህልውና ዘመቻ መንግሥት ህብረተሰቡ የአገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል ያቀረበውን ጥሪ ተቀብላ ጎደኛዋ የአገር መከላከያ ሠራዊትን ተቀላቀለች። ሕይወትና ጓደኛዋ ዳግም ለአይነ ስጋ ያብቃን ብለው እየተላቀሱ ተለያዩ። ይሄኔ ሕይወት የሆዷን የምትነግረው፣ ችግሯን የምታዋየው ጓደኛዋን ከጎኗ ስታጣ የቀን ጨለማ ዋጣት። በፍኖተ ሰላም ከተማ ያለጓደኛዋ መኖር በምድረ በዳ እንደመኖር ሆነባት። በዚህም ሰኔ መጨረሻ 2014 ዓ.ም ፍኖተ ሠላም ከተማን ለቃ ወደ አዲስ አበባ አመራች።
አዲስ አበባ …
ሕይወት ከፍኖተ ሠላም ወደ አዲስ አበባ እንደመጣች ሳትወጣ ሳትወርድ ቀጥታ ሥራ እንድትገባ ደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኝ አንድ ደላላ ሥራ ያመቻችላታል። በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው አራብሣ ኮንዶሚንየም (የጋራ መኖሪያ ቤት) ብሎክ 151 4ኛ ፎቅ የቤት ቁጥር ቢ151/30 በሆነ የአቶ መላኩ ታረቀኝ እና የወይዘሮ መሰረት የሻነው መኖሪያ ቤት ውስጥ በቤት ሠራተኝነት ትቀጠራላች።
በዚህ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥራ እየሠራች እያለ አሠሪዋ ወይዘሮ መሰረት አንዳንዴ ስትጠራት ሳትሰማት ቀርታ አቤት ሳትላት ስትቀር “ለምንድ ነው አቤት የማትይው” ከሚል ምክር አዘል ንግግር ባሻገር የከረረ ንግግር እንኳን ተነጋግረው አያውቁም። ጸብም ጭቅጭቅም በመካከላቸው አልነበረም። በተመሳሳይ ከአቶ መላኩ ጋርም ምንም አይነት ፀብም ሆነ የከፋ ንግግር ተነጋግርው አያውቁም። እንድትንከባከብ እና እንድትጠብቅ አደራ የተሰጣትን ህጻን ጊዮናዊት መላኩና ክርስቲና መላኩን ወላጆቻቸው ጠዋት ወደ ሥራ ወጥተው ማታ ወደ ቤት እስኪመለሱ ድረስ በሥነስርዓቱ ምግባቸውን አብልታ፣ ልብሳቸውን አልብሳ፣ ሲቆሽሹ አጥባ፣ ወዘተ. አደራዋን በአግባቡ ስትወጣ ቆይታለች። ከልጆቹ ጋር ካላት ቅርበት የተነሳ ሁለቱንም ህጻናት “ማሚ” ብላ ትጠራቸው ነበር። በነ አቶ መላኩና ወይዘሮ መሰረት ቤት ሁለት ወር ሊሞላት በጣት የሚቆጠሩ ቀናት እስኪቀራት ድረስ በሰላም ሥራዋን ሥትሠራ ቆይታለች።
ነሃሴ 26 ቀን 2014 ዓ.ም
በዚህ ጥቁር ቀን በአዲስ አበባ ሰማይ ሥር የተሰማው አስደንጋጭ ዜና በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘን የሚገኘውን ህዝብ በእንባ ያራጨ፣ በዓለም ላይ ከዚህ ቀደም ተሠርቷል ለማለት የሚከብድ ነበር።
ሕይወት አሠሪዋ አቶ መላኩ ታረቀኝ ባልትና ሱቅ እከፍትልሻለሁ ብሎ ቃል እንደገባላት ለፖሊስ በሰጠችው የእምነት ክደት ቃል ትናገራለች። እሷም ሱቅ ከፍታ ነግዳ ከራሷ አልፋ ቤተሰቦቿን ለመርዳት ቋመጠች። ነገ ላይ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ጓጓች። ይህንን ህልሟ ሠምሮ ለማየት ካላት ጉጉት የተነሳ አሠሪዋ የገባላትን ቃል እንዲፈጽምላት በተደጋጋሚ ትጠይቀዋለች። እርሱም የገባውን ቃል ለመፈጸም አቅም አጥሮት ይሁን ወይም ልቡ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ ቃሉን ሳይፈጽምላት ቀናቶች ተቆጠሩ። እሷ ግን ጠዋት ሲወጣ ማታ ሲገባ “የገባህልኝን ቃል ፈጽምልኝ እንጂ” እያለች ትወተውተዋለች። ይህ ሥራ ክፈትልኝ የሚለው ውትወታ አቶ መላኩ ሲበዛበት “አይመለከተኝም” የሚል ምላሽ ይሰጣታል። እሷም ተስፋ ሳትቆርጥ “ሥራ እከፍትልሻለሁ” ብለህ ቃል ገብተህልኛል፤ ክፈትልኝ እያለች ነጋ ጠባ ትጠይቀዋለች። እሱም በምላሹ “አይመለከተኝም” የሚል ምላሽ ደጋግሞ ይሰጣታል።
“የገባልኝን ቃል አልፈጸመለኝም” በሚል ቂም በቀል አቶ መላኩን ለመበቀል ወሰነች። ሕይወት ይህንን ቂም በቀል በመያዝ አቶ መላኩን በምን እንደምትበቀለው ማሰላሰል፣ ማውጣት፣ ማውረድ ጀመረች። እሱን በተኛበት በቢላ ለመውጋት አሰበች፤ ነገር ግን ‹‹ልወጋው ወደ አጠገቡ ቢላ ይዤ ስጠጋ ቢነቃና ቢይዘኝ›› ብላ ፈራች። ይህ አያዋጣም ብላ አሰበች። አቶ መላኩን እርር ድብን የምታደርግበት አንድ ክፉ ሃሳብ በአዕምሮዋ መጣ። ይህንንም ቆርጣ ለመፈጸም ወሰነች።
በዚሁ ቀን እማወራዋ ወይዘሮ መሰረት ከሁሉም ቀድማ በጥዋት ተነስታ “ይሄን ይሄን ሥሪ፣ ይሄን ብሉ” ብላ በጥዋት ወደ ሥራ ወጣች። በተመሳሳይ አቶ መላኩ ባለቤቱ ወደ ሥራ እንደወጣች እሱም እግር በእግር ተከታትሏት ወደ ሥራ ወጣ። ይህኔ አቶ መላኩን ለመበቀል አስባ ለመፈጸም ያቀደችውን ክፉ ሃሳብ የሚያስቆማት አንዳች ነገር እንደሌለ ሕይወት አረጋገጠች።
እንድትንከባከብና እንድትጠበቅ አደራ የተሰጣትን ሁለት ህጻናት በመግደል አቶ መላኩን ለመበቀል ወሰነች። በግምት ከጠዋቱ 3: 30 ገደማ ህጻናቱ አገር ሰላም ብለው ወደ ተኙበት መኝታ ክፍላቸው ገባች። መጀመሪያ መስማትና መናገር የማትችል የሶስት ዓመት እድሜ ያላትን ህጻን ጊዮናዊት መላኩን በትራስ አፏንና አፍንጫዋን አፈነቻት። ህጻኗ ትንፋሽ አጥሯት አይኗ ፈጦ እይተንፈራገጠች ስታያት በሕይወት እንድትቀጠል ልቧ ባለመራራቱ አንገቷን በቢላ በማረድ ህይወቷ እንዲያልፍ አደረገች። ይህ ብቻ ቂም በቀሏን ስላላረካላት ቀጥላ እድሜዋ ሁለት ዓመት ያልሟላትን እንቦቃቅላ ህጻን ክርስቲና መላኩን በተኛችበት አፏንና አፍንጫዋን በማፈን ሕይወቷ እንዲያልፍ ታደርጋለች። ይህንን ድርጊት ከፈጸመች በኋላ ለልጆቹ አባት ደውላ “ቤት አይደለሁም፤ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየሄድሁ ነው” ብላ ትነግረዋለች። እሱም መልሶ መላልሶ ሲደውልላት ስልኩን ዘጋችበት። ወደ ቤት በሮ ሲሄድ ልጆቹን ዳግም ላያገኛቸው እስከወዲያኛው አሸልበዋል።
የፖሊስ ምርመራ
ሕይወት እንድትንከባከብና እንድትጠብቅ አደራ የተሰጣትን እህታማቾቹን በነውረኝነትና ፍጹም ጨካኝነት በሚያሳይ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ካደረገች በኋላ ቀጥታ ፖሊስ ጣቢያ ሂዳ “ሰው ገድያለሁ” ብላ እጇን ሰጠች። ለፖሊስም “አባታቸው ቢያናድደኝም፣ ምንም የማያውቁትን ህጻናቱን በመግደሌ ተፀጽቻለሁ፣ ምን ብናደድም ህጻናቱን መግደል አልነበረብኝም፣ በሚቀርብብኝ የሰው መግደል ወንጀል ጥፋተኛ ነኝ፣ ተጸጽቻለሁ” ብላ የእምነት ክህደታ ቃሏን ሰጥታለች። ፖሊስም የተከሳሽን የእምነት ክደት ቃል እና ማስረጃዎችን አጠናቅሮ ክሱን ለዐቃቤ ሕግ አሳልፏል።
ውሳኔ
ህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ሕይወት መኮንን ኃይሉ ክስ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት ተሰይሟል። ፍርድ ቤቱም በዚህ ቀን በዋለው ችሎት ተከሳሽ በሞት እንድትቀጣ ሲል ውሳኔ አሳልፏል።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2015