3ኛው የኢትዮጵያ ማሠልጠኛ ማዕከላት የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከትላንት በስትያ ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል። ውድድሩ ሦስተኛ ቀኑን ያስቆጠረ ሲሆን በነገው ዕለት ይጠናቀቃል።
ሻምፒዮናው በማሠልጠኛ ማዕከላት ውስጥ ሥልጠናቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዋናነት ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራትና በማዕከላቱ የሚገኙ አትሌቶች በሚወስዱት ሥልጠና ምን ደረጃ እንዳሉ አቋማቸውን የሚለኩበትም ነው።
በሻምፒዮናው ስድስት የማሠልጠኛ ማዕከላት በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች እየተሳተፉ ሲሆን በርካታ የማጣሪያና የፍፃሜ ፍልሚያዎችን እያስተናገዱ ይገኛሉ። ሀገረ ሰላም፣ ደብረብርሃን፣ ተንታ፣ ቦሬ፣ በቆጂ በሻምፒዮናው እየተሳተፉ የሚገኙ ማሠልጠኛ ማዕከላት ናቸው። ከነዚህ ማሠልጠኛ ማዕከላት የተወጣጡ 160 ወንድና 129 ሴት በድምሩ 289 ታዳጊ አትሌቶች የውድድሩ ተካፋይ ሆነዋል። አትሌቶቹ በአጭር ርቀት፣ መካከለኛ ርቀት፣ ረጅም ርቀትንና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ፉክክር ያደርጋሉ።
በውድድሩ መክፈቻ ዕለት በሁለት ውድድሮች አራት የፍጻሜ ፉክክሮች ተካሂደዋል። እነዚህም የ10ሺ ሜትር ወንድና ሴት እንዲሁም ርዝመት ዝላይ ወንድና ሴት ናቸው። በሁለቱም ፍፃሜዎች ጥሩ ፉክክሮች የተደረጉ ሲሆን የወደፊት ተተኪ አትሌቶችም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይተዋል።
በ10ሺ ሜትር ወንዶች አቤል በቀለ ከተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ 29፡09፡48 በመግባት የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን፣ ኃይሌ ጥጋቡ ከደብረብርሃን 29፡40፡11 በመግባት የብር ሜዳሊያ ወስዷል። አንዳርጋቸው አዳሙ ከተመሳሳይ ማዕከል በ29፡53፡77 የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችሏል። በሴቶችም አበበች ተመስገን ከደብረብርሃን፣ አሳመነች ማሙሽ ከቦሬና ኤደን አንተናየሁ ከደብረብርሃን ማሠልጠኛ ከ1ኛ-3ኛ በመውጣት የወርቅ፣ ብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችለዋል።
በርዝመት ዝላይ የወንዶች ፍጻሜ ውድድር በጥሶ ቱሞቻ ከሃገረ ሰላም 7 ሜትር በመዝለል አሸናፊ ሲሆን፣ ንጋቱ ዋቶ ከቦሬ ማሰልጠኛ 6.66 ሜትር በመዝለል ሁለተኛ ሆኖ ፈፅሟል። ወንድማገኝ ደገፋ ከተንታ ማሰልጠኛ 6.52 ሜትር በመዝለል የወርቅ የብርና የነሐስ ሜዳለያ ተሸላሚ መሆን ችሏል። ጠንካራ ፉክክርን ያስተናገደው የሴቶች ርዝመት ዝላይ ውድድር በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተንታ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ አትሌቶች ከ1ኛ-3ኛ በመውጣት ውድድሩን በበላይነት አጠናቀዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ፣ ፌዴሬሽኑ ከ160ሺ ብር በላይ በጅቶ አትሌቶችን ለማበረታታት ውድድሩን እንደሚያካሂድ ገልፀዋል። አቶ አስፋው በኢትዮጵያ ደረጃ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ የሚደገፉ ሰባት የአትሌቲክስ ማሠልጠኛ ማዕከላት እንዳሉ ጠቁመው፣ በውድድሩ ስድስት ማሠልጠኛ ማዕከላት ብቻ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በውድድሩ ያልተሳተፈው ብቸኛው ማሠልጠኛ ማዕከል በትግራይ ክልል የሚገኘው የማይጨው ማሠልጠኛ ማዕከል ሲሆን በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰበት በመሆኑ በውድድሩ ሳይካፈል ቀርቷል። ማዕከሉ እራሱን መልሶ በማደራጀትና ሥልጠናዎችን በመጀመር ላይ በመሆኑ የዘንድሮ ውድድር ሊያልፈው መቻሉን አቶ አስፋው ገልፀዋል።
“ወጣት አትሌቶች በማሠልጠኛ ማዕከላት በተገቢው ዕድሜ ተገቢውን ሥልጠና ማግኘት ከቻሉ በአትሌቲክሱ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራትና አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል” ያሉት አቶ አስፋው፣ የእድሜ ጉዳይ መጀመር ያለበት ማዕከላት ላይ ሳይሆን ፕሮጀክት ላይ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት የፕሮጀክት ሰንሰለቱ ተያይዞ ሲሄድ የዕድሜ ማጭበርበር ችግሮች ሊቀረፉ ይችላሉ ባይ ናቸው። ማሠልጠኛ ማዕከላት ላይም ተመሳሳይ ሥራ የሚሠራ ቢሆንም ዋና መሠረቱ ፕሮጀክት በመሆኑ በትኩረት በመሠራት ላይ ይገኛል። ማሠልጠኛ ማዕከላትም የወጣት አትሌቶች መፍለቂያ ናቸው ተብሎ የሚታሰብ በመሆኑ ዕድሜ ላይ የተለመደው ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚሠራ አቶ አስፋው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለነዚህ ማሠልጠኛ ማዕከላት ሙሉ የትጥቅ ድጋፍን ጨምሮ ለአትሌቶች የላብ መተኪያ እና ለአሠልጣኞች የደሞዝ ክፍያን ይፈፅማል። ማሠልጠኛ ማዕከላቱ ከተለያዩ የፕሮጀክቶችና የክልል ውድድሮች ታዳጊ አትሌቶችን መልምለው በማሠልጠን ለውድድሩ ያቀርባሉ።
ታዳጊ አትሌቶቹ በተለያዩ መድረኮች ውድድሮችን (የኢትዮጵያ ሻምፒዮናና በወጣቶች አቋም መለኪያ) የሚካፈሉ ሲሆን አሁን አሁን ደግሞ ማሠልጠኛ ማዕከላት እርስ በርሳቸው አቋማቸውን የሚለካኩበት ውድድር ተዘጋጅቶላቸው ለ3ኛ ጊዜ በመፎካከር ላይ ናቸው። ይህም የልምድ ልውውጥ በማድረግ ከሌሎች ማዕከላት የሚበልጡበትንና መሥራት ያለባቸውን የቤት ሥራ ለመውሰድ ይረዳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2015