የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን የጠረጴዛ ቴኒስና የእጅ ኳስ ቻምፒዮናን በበጀት እጥረት ማካሄድ እንዳልቻለ አስታወቀ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ለክልሎች ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ላይ እንደሚሠራም ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን የሚዘጋጁ ውድድሮች ዓላማቸው መስማት የተሳናቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በስፖርቱ በማሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ የተሻሉ ስፖርተኞችን በመምረጥ በዓለም አቀፍ ውድድሮች አገርን ወክሎ ውጤት ማምጣት እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ ለ2015 ዓ.ም ሦስት ውድድሮችን ለማካሄድ ያቀደ ቢሆንም የበጀት እጥረት ገጥሞታል። ፌዴሬሽኑ ሊያካሂድ ካቀዳቸው ውድድሮች ማሳካት የቻለውም የአትሌቲክስ ውድድርን ብቻ ነው፡፡
መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን የገጠመውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ የደጋፊ አካላት እና የመንግሥት ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ውድድር ለመዘጋጀት ተቸግሯል። ይህም ብዙ ውድድሮች እንዲሰረዙ አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት መስማት የተሳናቸው ስፖርተኞች ስፖርት ውስጥ የመሳተፍ ዕድላቸው አነስተኛ እንዲሆን አድርጓል፡፡
ፌዴሬሽኑ የጠረጴዛ ቴኒስ እና የእጅ ኳስ ቻምፒዮናን ለማካሄድ አዘጋጅ ክልል መርጦና የውድድር ቀን ቆርጦ የነበረ ሲሆን ክልሎች በበጀት እጥረት ምክንያት መሳተፍ እንደማይችሉ መግለጻቸውን አሳውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን ከእጅ ኳስ ፌዴሬሽንና ከጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጋር ውድድሮቹን ለማዘጋጀት ዝግጅቱን ቢጨርስም ክልሎች አለመሳተፋቸውን ተከትሎ ውድድሮቹን ለመሰረዝ ተገዷል።
ውድድሩን ለማስተናገድ ድሬዳዋ ከተማ በዝግጅት ላይ የነበረ ቢሆንም በዚሁ ምክንያት ሊሰረዝ ችሏል፡፡ ለዚህም ፌዴሬሽኑ በደብዳቤ ለሚመለከታቸው አካላት ማስታወቁን ገልጿል፡፡
የስፖርት ኢንዱስትሪ ውስጥ መስማት ለተሳናቸው ስፖርተኞች ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠ የተጠቆመ ሲሆን፣ ከፋይናንስ እጥረት ባሻገር በዚህ ስፖርት ዘርፍ በቂ ግንዛቤና ዕውቅና አለመኖሩ ምክንያት ተደርጓል። መስማት የተሳናቸው ስፖርተኞች እራሳቸውን የሚያሳዩበት ይህ መድረክ ልዩ ትኩረትና ድጋፍ ከሚሹ ዘርፎች መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑም ተጠቁሟል።
በዚህም መስማት የተሳናቸው ስፖርተኞች በቂ ትኩረትና ድጋፍ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመሥራት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ ወደ ክልሎች ወርዶ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች በስፋት መሥራትም ታስቧል። በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ ከኦሊምፒክ ኮሚቴና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ጥምረት ፈጥሮ መሥራትን እንደ አማራጭ ይዟል፡፡ እያንዳንዱን የውድድር ዓይነት ከየፌዴሬሽኑ ጋር አስተሳስሮ እገዛ እንዲያደርጉ በማድረግ የስፖርተኞቹን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ለማድረግም እንደሚሠራ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች ፌዴሬሽን ባለሙያ አቶ ኃይለማርያም ታረቀኝ በኅዳር ወር በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ውድድሮችን ጥርና የካቲት ለማድረግ ቢታቀድም የበጀት ድጎማው በወቅቱ ባለመለቀቁ ውድድሮቹ እየተሸጋሸጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ የበጀት ድጎማው ሲለቀቅ ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ለክልሎች ቢያሳውቅም ክልሎች በጀታቸው እያለቀ በመምጣቱ እጥረት ሊያጋጥማቸው ችሏል፡፡ በዚህም ምክንያት በውድድሩ መሳተፍ እንደማይችሉ ማሳወቃቸውን ባለሙያው አስረድተዋል።
«በቀጣይ ሁለት ወራት ክልሎች ጋር ወርደን ክትትልና ድጋፍ አድርገን ለምን በጀት እንደልተመደበና ትኩረት አልተሰጠውም የሚለው ጉዳይ ላይ ከክልሎች ጋር መግባባት ለመፍጠር ይሠራል» ያሉት ባለሙያው፣ ፌዴሬሽኑ ስለ መስማት የተሳናቸው ስፖርቶች አስፈላጊነት እና የተሳትፎ ፋይዳ ለክልሎች ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት እቅድ መያዙን አብራርተዋል። ይህም ተሳትፎውን ለማሳደግና ለማነቃቃት ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል። ግንዛቤን ከመፍጠር በተጨማሪ መስማት ለተሳናቸው ስፖርተኞች የተሳትፎ እድገት ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ተጨማሪ ድጋፍ ሰጪዎችን ለመሳብ ይረዳል ተብሎም ይጠበቃል።
ፌዴሬሽኑ ስፖርቱ መስማት ለተሳናቸው ስፖርተኞች ብቻ አለመሆኑን በመጠቆም በዚህ ረገድ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለመለወጥ ጥረት እያደረገ ይገኛል። መስማት የተሳናቸው ስፖርተኞች ልክ እንደማንኛውም ሰው ያሰቡትን ሁሉ ማሳካት እንደሚችሉ ለሌላው ማኅበረሰብ ለማሳየት ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጿል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015