‹‹ጤፍ፤ ገብስ፤ ማሽላ፤ ሳመርት ማንም ከቁብ ያልቆጠረኝ ምነው ስንዴ ስዘራ ሁሉም ፊቱን አጠቆረብኝ፡፡ ምነው ምቀኛዬ በዛ፤ ወዳጄ የነበረው ሁሉ ምን ነክቶት ነው በአንድ ጊዜ ጠላት የሆነብኝ›› እያለ አርሶ አደር ጣሰው በለሆሳስ ይናገራል፡፡ ታታሪው አርሶ አደር ጣሰው ክንደ ብርቱ ወዳጅ ይመስሉ የነበሩ ሁሉ ስንዴ በማምረቱ በክፉ ዓይናቸው ማየት እንደጀመሩት ቀልቡ ነግሮታል፡፡
ይህ ጉዳይ በአርሶ አደር ጣሰው ላይ ብቻ የተፈጸመ አይደለም፡፡ ከግለሰብም አልፎ አገርም የታመመችበት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስንዴ ማምረቷና ወደ ጎረቤት አገር መላኳ የከነከናቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ ለወትሮ ወዳጅ የሚመስሉት ሁሉ ዛሬ በጠላትነት መገለጥ ጀምረዋል፡፡ ምስጢሩ ደግሞ ይሄ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት ያህል ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ብትሆንም በምግብ ሰብል እራሷን ባለመቻሏ ነፃነቷን በሚገባ ሳታጣጥም ኖራለች። በዓድዋ የተገኘው ድል በቅኝ ገዢዎች የፈረጠመ ኢኮኖሚ ሲጠመዘዝ ኖሯል፡፡ የኢትዮጵያ ኩራትና ድል በስንዴ ልመና ኮስሶ ቆይቷል፡፡ ዛሬ ግን የዓድዋ ድል በተገቢው ቦታው ላይ እንዲነግስ የሚያስችል አኩሪ ታሪክ መጻፍ ጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያ ዳግም ነፃነቷን በስንዴ ማወጅ ቀጥላለች፡፡ ከስንዴ ጠባቂነት ወደ ስንዴ ላኪነት ተሸጋግራለች፡፡
ስንዴ ከሩዝ ቀጥሎ በዓለማችን በስፋት የሚመረት የሰብል ዓይነት ነው፡፡ በዓለም ላይ ከሚታረሰው የመሬት መጠንም 15 በመቶ የሚሸፈነው በስንዴ ነው። ስንዴ በባህላዊ መንገድ ተፈጭቶ ለቂጣ፤ ለገንፎ፤ ለተለያዩ መጠጦች መሥሪያ ከማዋሉም ባሻገር በፋብሪካ ተቀነባብሮ ለፓስታ፤ ለማካሮኒ፤ ለብስኩትና ለተለያዩ መድኃኒቶች መሥሪያ ይውላል፡፡
ስንዴ በዓለማችን ላይ በድሃም ሆነ በሀብታም አገራት እጅግ ተፈላጊ የሆነ ሰብል ነው፡፡ ከምግብነቱ ባሻገርም እንደነዳጅ ሁሉ ከፍተኛ ገንዘብ አምጪ የሆነ ሀብት ነው፡፡ በስንዴ ምርት ውጤታማ የሆነ አገር አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ ከመፍጠሩም ባሻገር ነፃነቱን እንዳረጋገጠ ይቆጠራል፡፡ ከተረጂነት ነፃ የመሆንና እራስን የመቻል ተምሳሌት ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል በርካታ አገራት ስንዴን ከምግብም በላይ የሆነ ግምት የሚሠጡት፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ስንዴ ሸማች ከሆኑ አገራት ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምትታወቅ አገር ነበረች፡፡ በየአመቱም እስከ 107 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማስገባት 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ትገፈግፍ ነበር፡፡ ሆኖም ባለፉት አራት አመታት መንግሥት ለስንዴ ምርት በሰጠው ትኩረትም ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ከማቆሟም ባሻገር ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች፡፡ ይህ ጥረቷም በዓለም ላይ ስንዴ በማምረት ተጠቃሽ ከሆኑ 18 አገራት ተርታ አሰልፏታል፡፡ ኢትዮጵያ ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት እራሷን በመለወጥም ታሪክ ሠርታለች፤ለቀጣናው አገራትም ኩራት ሆናለች፡፡
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ሁልጌዜ ተመጽዋች ሆና እንድትቀጥል ለሚፈልጉ ወገኖች የሚዋጥላቸው አልሆነም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ዓድዋው ድልሁሉ በስንዴ ላይ ድልን ከተቀዳጀች ዳግም ነፃነቷን እንዳወጀች የሚቆጠር ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ግስጋሴ ምጽዋትን ለፖለቲካ ጥቅማቸው በማዋል አገራትን ማንበርከክ ለሚፈልጉ አገራት ደግሞ የመርዶ ያህል አስደንጋጭ ነው። በዚህ የደነገጡ አገራት ደግሞ ከአምና ጅምሮ በርካታ ጻያፍ ተግባራትን ሲከውኑ ከርመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ስንዴ አምርታ ወደ ኬንያ እንደምትልክ ባስታወቀች ማግስት ኬንያ በዘመኗ አይታ የማታውቀውን የስንዴ እርዳታ እንዲጎርፍላት ተደርጓል፡፡ በግብረሰናይ ስም የገቡ ለጋሽ ነን የሚሉ አገራት ተላላኪዎችም ስፍር ቁጥር የሌለው ገንዘብ እየረጩ አርሶአደሩ ስንዴ ለመንግሥት እንዳይሸጥ በርካታ አፍራሽ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በአጠቃላይ ከጅምሩ ጀምሮ ‹‹ኢትዮጵያ ስንዴን እንኳን ለውጭ ገበያ ልታቀርብ ቀርቶ እራሷም በርሃብ ውስጥ ነች ያለችው፤ ስንዴ አምርታ ወደ ውጭ መላክ አይሳካላትም›› የሚሉ ሀሰተኛ ዜናዎችን በማሰራጨት መንግሥት የጀመረውን ጥረት ለማኮላሸት ረጅም ርቀት ተጉዘዋል፡፡
መንግሥት የጀመረውን የስንዴ ልማት ለማደናቀፍና አሁንም ኢትዮጵያ እርዳታ ጠባቂ አገር ናት ለማስባልም የማይፈነቀል ድንጋይ የለም፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የእርዳታ ስንዴ ተሰርቋል በሚል ሰበብም በኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ይቀርብ የነበረው ዕርዳታ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ሰበብም በርካታ ንጹሃን ዜጎች ማግኘት የሚገባቸውን እርዳታ በወቅቱ እንዳያገኙ ከማድረጉም ባሻገር በቀጣይ ከፍተኛ የሆነ እርሃብ እንዳይከሰት ስጋት ደቅኗል፡፡ በተለይም ደግሞ እርዳታ የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ለሁለት አመታት ያህል በዘለቀ የሰሜኑ ጦርነት ውስጥ የነበሩና አሁንም ጦርነቱ ካስከተለባቸው ሥነልቦና ያልተላቀቁ መሆኑ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡
እርዳታና ፖለቲካ በተደበላለቀበት የምዕራቡ ዓለም ዜጎች ሲቸገሩ እየታየ በፖለቲካ መነጽር ብቻ በመመልከት እርዳታን መንፈግ ከሰብዓዊነትም በታች ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድንጋጌ መሠረት ሰው ሰራሽም ሆነ ሰው ሰራሽ ባልሆነ ምክንያት የተፈናቀሉና ለችግር የተጋለጡ ሰዎች ሰብአዊ እርዳታ የማግኘት መብት እንዳላቸው ቢደነገግም ይህንኑ ድንጋጌ በመተላለፍ የፖለቲካ እሳቤም ሆነ ድርጊት ውስጥ ምንም ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ሲቀጡ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡
ሆኖም ግመሎቹም ይጓዛሉ፤ውሻዎችም ይጮሃሉ እንደሚለው ተረት ኢትዮጵያ አርሶ አደሩን ከመሬቱ ጋር በማስማማት ማሳውን በሙሉ በስንዴ መሸፈን ችላለች፡፡ አርሶ አደሩም የስንዴን ጠቀሜታ እየተረዳ በመምጣቱም ከሌሎች ሰብሎች በተለየ ለስንዴ ትኩረት ሰጥቶ መሬቱን በማረስ ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በምግብ እህል ራሷን መቻል አቅቷት ቢሊዮን ዶላር አውጥታ ከውጭ ከማስገባት በዘለለ፣ ለዕርዳታ የብዙዎችን በር ስታንኳኳም ሰንብታለች። አንዳንድ ጊዜም ረጂ አገራት ስንዴን እንደመያዣ አድርገው የሚፈልጉትን ሁሉ ለመጫን ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ ሆኖም ይህ ታሪክ ያበቃ ይመስላል፡፡
በተያዘው አመት ኢትዮጵያ 129 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የስንዴ ምርት ታመርታለች፡፡ 97 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ሲሆን 32 ሚሊዮን የሚጠጋው ወደ ውጭ ተልኮ ዶላር የሚያስገኝ ነው፡፡ ለዚህም ዘንድሮ ሱዳንና ኬንያን ጨምሮ ስንዴ የመግዛት ፍላጎት ያላቸው ስድስት አገራት ጋር የ3 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት ተፈርሟል። የረድኤትና ሌሎች የአገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ የሚገዙትን በአገር ውስጥ እንዲተኩ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነት በመፈረም ላይ መሆናቸው ተነግሯል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ከ200ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንደምታገኝ ይገመታል፡፡
ይህ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባሻገር የጎረቤት አገራት ከአውሮፓ፤ ከአሜሪካና ካናዳ ደጅ ጠንተው የሚገዙትን ስንዴ ከደጃቸው በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካን አካባቢም ከግጭትና ሁከት በማውጣት አገራቱን በልማት እንዲተሳሰሩ በር ይከፍታል፡፡
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የስንዴ ምርት ግስጋሴ ቀጥሏል፡፡ ዓምናና ዘንድሮ 2.8 ሚሊዮን ሔክታር በስንዴ ማሳ የተሸፈነ ሲሆን በበጋ ወቅት ይመረታል ተብሎ የታሰበ 50 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴን ሳይጨምር ከ108 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ ይታሰባል፡፡
በዓለም ላይ እጅግ ውድ እና ተፈላጊ የሆነውን አዝርዕት ኢትዮጵያ ከማምረትም አልፋ ለውጭ ገበያ እነሆ ብላለች፡፡ ስንዴ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ቁልፍ የምግብ ዘርፍ ሲሆን የአምራች አርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግ፤ የሥራ ዕድልን በመፍጠርና አገራዊ ገቢን በማሳደግ የማይተካ ሚና አለው፡፡
ስንዴ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች እንዲነቃቁ የሚያስችል ሞተር ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩትም፤ የስንዴ ልማቱ በአገር ውስጥ ላሉ ከ440 በላይ ኢንዱስትሪዎች ግብዓትን ሙሉ በሙሉ በአገር አቅም መሸፈን የሚያስችል ነው።
ኢትዮጵያ ለስንዴ ምርት የሚሆን ምቹ የአየር ጸባይና ለም አፈር አላት፡፡ ይህንኑ አቅሟን በመጠቀምና ቴክኖሎጂን ከክላስተር የእርሻ አስተራረስ ዘዴ ጋር በማቀናጀት በተሠራው ሥራ ኢትዮጵያን ከስንዴ ተቀባይነት ወደ ስንዴ ላኪነት አሸጋግሯታል፡፡ ስንዴ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል የሚመረት ቢሆንም በዋናነት ግን በኦሮሚያና በአማራ በስፋት ይመረታል፡፡ በአገሪቱ ከሚመረተው የስንዴ ምርት ውስጥ 54 ነጥብ 4 በመቶ ከኦሮሚያ የሚገኝ ሲሆን 27 በመቶ ከአማራ፤ 8ነጥብ 7 በመቶ ከደቡብ ሕዝቦች እንዲሁም 6ነጥብ 2 በመቶ ከትግራይ የሚገኝ ነው፡፡
በቀጣይም መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረትም የሶማሌ፤ የቤኒሻንጉል፤ አፋር፤ ጋምቤላ፤ ሲዳማን የመሳሰሉት ክልሎች ኃይላቸውን አስተባብረው ስንዴን ማምረት ጀምረዋል፡፡ የእነዚህ አካባቢዎች ምርታማነት ሲጨምርም ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ላይ ያላት ስንዴን የማምረት ታሪክ በእጅጉ የሚቀይረው ይሆናል፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ እንኳን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ሁለተኛዋ ስንዴ አምራች አገር ለመሆን አብቅቷታል፡፡ የአፍሪካ አገራት ስንዴን ከውጭ በመቀበል የሚታወቁ ናቸው፡፡ ስንዴንም ለማግኘት በርካታ ውጣውረዶችን ማለፍ ይገባቸዋል፡፡ በዩክሬንና በራሽያ ጦርነትም በግልጽ እንደታየው በዓለም ላይ በሚነሱ መስተጓጎሎች የቅድሚያ ተጠቂዎቹ የአፍሪካ አገራት ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በዩክሬንና በራሽያ ጦርነትም በተከሰተው የስንዴ እጥረት እስከ 300 ሚሊዮን የአፍሪካ ሕዝብ ለርሃብ እንደሚጋለጥ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግዙፍ ሚዲያዎቻቸው ጭምር በስፋት የዘገቡት ነው፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያ ስንዴ አምራችና ላኪ አገር መሆኗ በስጋት ውስጥ ላሉት የአፍሪካ አገራት ትልቅ እፎይታን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ ይህንኑ ሃቅ መሠረት በማድረግም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ250 ሚሊዮን በላይ እርዳታ ፈላጊዎች መኖራቸውን በመጥቀስ «ኢትዮጵያን ኤይድ» በሚል ስንዴ ለመለገስ ተግተን እንሠራለን ነው ያሉት። በዓለም ላይ የተፈጠረውን የስንዴ ገበያ ችግር ለማቃለልም ኢትዮጵያ የበኩሏን እንደምትወጣ ገልጸዋል።
Index box market intelligence የተሰኘ የመረጃ መረብ ይፋ እንዳደረገውም የአፍሪካ አገራት የስንዴ ፍላጎት እየጨመረ ነው፡፡ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2012 ብቻ የአፍሪካውያን የስንዴ ፍላጎት በ1 ነጥብ 3 በመቶ ጨምሯል፡፡ ይህ አሃዝ በቀጣዮቹ አመታት እንደሚጨምር የመረጃ መረቡ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡ ይህ ደግሞ እንደኢትዮጵያ ላሉ ስንዴ አምራችና ላኪ አገራት ጥሩ ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው፡፡
ወደ አፍሪካ ከሚገባው ስንዴ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን ምርት የሚወስዱት ናይጄሪያ፤ አልጄሪያና ግብጽ ሲሆኑ የጎረቤታችን ኬንያ ፍላጎትም በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዘንድሮም ኢትዮጵያ ኬንያን ጨምሮ ወደ ስድስት አገራት የስንዴ ምርቷን ለመላክ ዝግጅቷን ጨርሳለች፡፡
ላለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ ብትቆይም ከጦርነቱ ጎን ለጎን ስንዴን፤ አረንጓዴ ዐሻራ፤ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችንና የህዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ግዙፍ የኃይል ፕሮጀክቶችን በመገንባት አይበገሬነቷን አሳይታለች፡፡ እንደበርካቶች እምነትም ጦርነቱ በሚፈጥረው ቁርሾ አገር ትበታተናለች፤ ኢትዮጵያ የሚባለው ስምም ከመቃብር በታች ይወርዳል ብለው ቢያልሙም በተቃራኒው ኢትዮጵያውያን ችግራቸውን በራሳቸው ባህልና ወግ ፈትተው ለአፍሪካ ምሳሌ ለመሆን በቅተዋል፡፡ በጦርነት ውስጥ የነበሩትም የትግራይ፤ የአማራ እና አፋር አካባቢዎች ሰላም ሰፍኖባቸዋል፡፡ ፊታቸውንም ወደ ልማት አዙረዋል፡፡
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015