የኢትዮጵያን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል ተብለው ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች (Industrial Parks) ልማት አንዱ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የመሳብ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን የማስፋት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የማድረግ ዋና ዋና መሠረታዊ ተልዕኮዎች አሏቸው። ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ሥራ በመፍጠርና ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለአገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሠረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ዋጋ የሚከፈልባቸውን የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት፣ የብድር አቅርቦት፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡
በእርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ (Manufacturing Hub) እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ አበርክተዋል። በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገኙ ሲሆን በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
በተለይም የግብርና ውጤቶችን እሴት በመጨመር በብዛትና በጥራት ተወዳዳሪ የማድረግ አቅም እንዳላቸው የታመነባቸው የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ((Integrated Agro-Industry Parks)፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ያሳካሉ ከተባሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ የአግሮ- ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአርሶ አደሮች የግብይት ሰንሰለቱን ቀላል በማድረግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ፡፡ ባለሀብቶች የግብርና ግብዓቶችን ከአርሶ አደሮች እንዲቀበሉ በማድረግ አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል እንዲጠቀሙ አወንታዊ አስተዋፅዖ ያበረክታሉ፡፡ መንግሥት አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት እስካሁን ድረስ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንና ይህ ወጪ ባለሀብቶች በፓርኮቹ ውስጥ ገብተው በምርት ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ አዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ፣ ከባቱ ከተማ በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የ‹‹ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ›› በአገሪቱ ከተገነቡ የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል አንዱ ነው። ፓርኩ በሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተመረቀ ሲሆን፤ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት፣ የማር፣ የስጋና የእንቁላል ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አምራቾች የሚሰማሩበት የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው፡፡ የፓርኩ የመጀመሪያ ዙር ግንባታ በ271 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ እስከ አንድ ሺ ሄክታር መሬት መሸፈን የሚችሉ ቀጣይ ዙር ግንባታዎች ሊከናወኑለት እንደሚችል የፓርኩ የአዋጭነት ጥናት ያሳያል፤ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ከ70ሺ እስከ 100ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ጌታሁን አዱኛ እንደሚናገሩት፣ የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ባከናወናቸው ተግባራት አንዳንድ አምራች ኩባንያዎች ወደ ፓርኩ ገብተው በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችሏቸውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ፤ በማር ምርት ማቀነባበር ላይ የተሰማራ አንድ አምራች ድርጅት ደግሞ ምርቶቹን ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ ጀምሯል፡፡ ድርጅቱ በቀጣይ ምርቱን በስፋት በማምረት ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅድ አለው፡፡
‹‹24 አምራቾች በፓርኩ ውስጥ ገብተው ለመሥራት በተለያዩ የሥራ ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ፡፡ ኢንቨስተሮቹን ተቀብለን የውል ስምምነት ፈፅመናል፡፡ አምራቾቹ ከባንክና ሌሎች ዘርፎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በመጨረስ ላይ ይገኛሉ፤ ሼድ በመገንባት እና ማሽኖችን በመትከል ላይ የሚገኙ አምራቾችም አሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጨርሰው ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡ ባለሀብቶቹ የሚሰማሩባቸው የአግሮ-ፕሮሰሲንግ (ግብርና ማቀነባበር) ዘርፎች የማርና ሰም፣ የምግብ ዘይት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ (ቲማቲም፣ ድንች፣ ጭማቂ…)፣ የቡና፣ የአቮካዶ ዘይት፣ የስጋ፣ የወተት፣ የእንስሳት መኖ፣ የፓስታና ማካሮኒ፣ የሕፃናት ምግቦች ማምረትና ማቀነባበር ሥራዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አምራቾች ያስመዘገቡት አጠቃላይ የካፒታል መጠን 19 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ወደ ሥራ ሲገቡ ከ10ሺ እስከ 20ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል›› ብለዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ተግባራት ማኅበረሰቡን በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በገበያ ዕድል ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡ የተቀናጁ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮችም በተገነቡባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በልዩ ልዩ መንገዶች ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
አቶ ጌታሁን እንዳሉት፤ የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርውን ዘርፍ ለማሳደግ ታልሞ የተገነባ በመሆኑ የአገር ውስጥ የግብርና ምርቶችን በግብዓትነት ይጠቀማል፡፡ በፓርኩ አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ አርሶ አደር እንደመሆኑ የፓርኩ አምራቾች የሚጠቀሙት ጥሬ ዕቃ የአካባቢውን የግብርና ምርት ነው፡፡
አርሶ አደሩ ግብርናውን በማዘመንና አምራችነቱን በመጨመር ለምግብና ለገበያ ከሚያውለው ምርት በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ትርፍ ምርት እንዲያመርት እየተሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ውስጥ ሥራ የጀመረው የማር ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በመሆኑ በክልሉ ከሚገኙ ብዙ የማር አምራች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር የገበያ ትስስር ፈጥሯል፡፡ በቀጣይ ተጨማሪ አምራቾች በስጋ፣ በዶሮ፣ በወተት፣ በጥራጥሬ፣ በዘይትና በሌሎች ዘርፎች ወደ ሥራ ሲገቡ አርሶ አደሩ ይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት የአካባቢው ኅብረተሰብ የገበያ ዕድል እንዲያገኝ ያደርጋል በማለት ፓርኩ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እያበረከተ ያለውን ፋይዳ አስረድተዋል፡፡
እንደአቶ ጌታሁን ገለፃ፣ ከፓርኩ ጋር ትስስር ያላቸውና ግንባታቸው የተጠናቀቀ ስድስት የገጠር ሽግግር ማዕከላት ያሉ ሲሆን፤ የማዕከላቱ ዋና ተግባር የአርሶ አደሩን ምርት በጥራትና በብዛት ሰብስቦ ለፓርኩ አምራቾች ማቅረብ ነው፡፡ ወደ ፓርኩ የሚገቡት ባለሀብቶች ከሽግግር ማዕከላቱ ጋር በሚፈጥሩት ትስስር አርሶ አደሩን ጨምሮ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡
በሲዳማ ክልል የሚገኘው የ‹‹ይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ››ም የግብርና ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አምራቾች የሚሰማሩበት የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው፡፡ የፓርኩ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው በ2013 ዓ.ም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ እንደጀመረ ይታወሳል፡፡
በአገሪቱ ከሚገኙ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ቀድሞ ወደ ሥራ የገባው ይህ ፓርክ፣ 152 ሼዶችን መያዝ የሚችል የለማ መሬት የተዘጋጀለት ነው። ግንባታው በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚከናወነው ፓርኩ በ294 ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ አርፏል። ፓርኩ (በሲዳማ ክልል ሦስት እና በጌዴኦ ዞን ሦስት) በድምሩ ስድስት የገጠር ሽግግር ማዕከላት አሉት፡፡
በሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቢዝነስ ልማትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጴጥሮስ ማርቆስ እንደሚናገሩት፤ በይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡና ወደ ሥራ የገቡ አራት አምራቾች አሉ፡፡ ሁለቱ በአቮካዶ፣ አንዱ በወተት እንዲሁም አንዱ በማር ምርትና ማቀነባበር ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች በተጨማሪ በቡና፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ማቀነባበር እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚሰማሩ ሌሎች 26 ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ለመግባት የሚያስችላቸውን ስምምነት ፈርመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ሁለት በቡና ማቀነባበር ተግባር ላይ የሚሰማሩ ድርጅቶች ማሽኖቻቸውን በመትከል ላይ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ ምርት የጀመሩትና ስምምነት የፈረሙት የፓርኩ አምራቾች ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አላቸው፡፡ በፓርኩ ውስጥ ገብተው ሥራ የጀመሩ አምራቾች ከሰባት ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ወደ ፓርኩ ለመግባት ስምምነት የተፈራረሙ አምራቾች ሥራ ሲጀምሩ ከ58 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች (ስምንት ሺ ቋሚ እና ከ50 ሺ በላይ ጊዜያዊ) የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ፡፡
የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ብዙ ጥቅሞችን እያስገኘ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጴጥሮስ፤ ከዚህ ቀደም አርሶ አደሮች አቮካዶ ለነጋዴዎች ሲሸጡ በዝቅተኛ ዋጋ ያቀርቡ እንደነበር አስታውሰው፣ ግብዓቱን በቀጥታ ለፓርኩ አምራቾች ሲያቀርቡ ግን የተሻለ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ነው ያስረዱት፡፡ ከገበያ ዕድል በተጨማሪ የአካባቢው ኅብረተሰብ በሥራ ዕድል ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ እና አምራቾቹም ለአካባቢው ኅብረተሰብ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡
የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ተጠቃሽ የሆነ አግሮ- ኢንዱትሪ ፓርክ ነው የሚሉት አቶ ጴጥሮስ ‹‹በፓርኩ ውስጥ ተመርተው ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንም አመላክተዋል፡፡ ኩባንያዎቹ አምርተው ለገበያ ያዘጋጁት ምርት ለገበያ ሲቀርብ ደግሞ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና ዕድሎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት አገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ስለሆነም መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሻሻል ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ኢንዱስትሪ መር ምጣኔ ሀብትን ለመገንባት ጠንካራ ግብዓት ለሚሆኑት የተቀናጁ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ላቅ ያለ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ትኩረትም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የመሠረተ ልማት ግብዓቶች፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015