“የመቀንጨርን ችግር ለመቅረፍ ማህበረሰቡን ማዕከል ያደረጉ ተግባራትን ማስፋፋት ያስፈልጋል” – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፡- መቀንጨርንና ሌሎችንም የሥርዓተ ምግብ ችግሮችን ለመቅረፍ ማህበረሰቡን ማእከል ያደረጉ ተግባራትን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ፣ የሰቆጣ ቃልኪዳን እና የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ትናንት ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር፤ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት መሳካት የሚያስችል አምራች ኃይል ለመገንባት የተለያዩ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተቀርጸው እየተተገበሩ ነው። መቀንጨርንና ሌሎች የሥርዓተ ምግብ ችግሮችን ለመቅረፍ ማህበረሰቡን ማእከል ያደረጉ ተግባራትን ማስፋፋት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የራስን ችግር በራስ አቅም መፍታት በሚያስችል መልኩ ለምንተገብራቸው ሀገር በቀል ፕሮግራሞች አመራሩ ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፤ ይህም ሀገራችን ምግብና ሥርዓተ ምግብ ችግርን ለመፍታት ያስቀመጠቻቸውን ግቦች ለማሳካት ሀገር በቀል መፍትሔዎች ያላቸውን ፋይዳ የሚያሳይ እንደሆነ አመልክተዋል።

የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ ፣ የሰቆጣ ቃልኪዳን የ15 ዓመታት ፍኖተ ካርታ እና የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ችግሮችን በሀገር በቀል መፍትሔዎች ለመፍታት ለሚደረገው ርብርብ ተግባራዊነት ማሳያዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን የአመራር ቁርጠኝነት የታየበትና ለሌሎች ፕሮግራሞች ልምድ የሚወሰድበት ሀገራዊ መፍትሔ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ እና ሰቆጣ ቃልኪዳን ያስቀመጥናቸው ግቦች ሊሳኩ የሚችሉት ማህበረሰቡን የችግሩ መፍትሔ ሰጪ ማድረግ ሲቻል እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር በሰቆጣ ቃልኪዳን የማስፋፋት ምዕራፍ ትግበራ ሕዝቡን ባለቤት በማድረግ እና ያለውን ሀብትና ጉልበት በአግባቡ በመጠቀም መፍታት እንዲቻል የማህበረሰብ መማማሪያና ሠርቶ ማሳያ በማስፋፋት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች አንዱ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ዜጎች በፍትሐዊነት ተደራሽ ማድረግ መሆኑን አስታውሰው፤ የከፍተኛ አመራሩ ቁልፍ ተግባር ሆኖ በመሠራቱም በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ሺህ 195 ወረዳዎች ተተግብሮ ከ63 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማጠናከር በክልሎች መካከል የሚታየውን የአፈጻጸም ልዩነት ማጥበብና ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

ጤና ተቋማት የጥራት ደረጃውን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ማቅረብ እንዲችሉ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም ከፍተኛ አመራር ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዳለበት አሳስበው፤ ሥርዓቱን ለማዘመን የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከርም የመረጃ አያያዝን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የምግብና ሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂ፣ ሰቆጣ ቃልኪዳን እና የማህበረሰብ ጤና መድህን ሥራዎችን ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮግራሞች በመሆናቸው ሁሉም ከፍተኛ አመራር ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እዳለበት አመልክተው፤ ፌዴራል መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ በመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት የሚደረጉ የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦቶች ውጤታማ ዜጋ ለማፍራት ትልቅ ሚና ያበረክታሉ ብለዋል።

የምግብና ሥርዓተ ምግብ የ10 ዓመት ስትራቴጂና የሰቆጣ ቃል ኪዳን የማስፋፋት ትግበራ ባለፉት አራት ዓመታት ተስፋ ሰጪ ትግበራ እየተከናወነ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ በ2017 ዓ.ም በ334 ወረዳዎች ሲተገበር ቆይቷል። ከአንድ ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ነፍሰ ጡሮች እና የሚያጠቡ እናቶች፣ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ከሁለት ዓመት በታች ያሉ ህጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲሠራ ቆይቷል። በ2018 ዓ.ም ትግበራውን ወደ 520 ወረዳዎች ለማስፋት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

መቀንጨርን ዜሮ ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ከዚህም በተጨማሪ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ግቦችን ለማሳካትና ጥራቱን የጠበቀ የጤና ሽፋንን ለማሳደግ እየተሠራ ነው።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You