የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) የአፍሪካ ዋንጫ ተስፋ መጨለሙን ተከትሎ ቀሪዎቹ ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች ከመርሃግብር ማሟያና ለክብር ከመፋለም የዘለለ ትርጉም አይኖራቸውም። ዋልያዎቹን በተመለከተ ከማጣሪያ ጨዋታዎቹ ይልቅ አንድ ጉዳይ የስፖርት ቤተሰቡን ቀልብ ስቧል። ይህም ከወር በፊት ቀጠሮ የተያዘለት የዋልያዎቹ የአሜሪካ ጉዞና እንቅፋት የገጠመው የወዳጅነት ጨዋታ ነው።
ዋልያዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ምድር ለመጫወት፣ የጉያና ብሔራዊ ቡድን በበኩሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፍሪካ አገር ጋር ለመጋጠምና በወዳጅነት ጨዋታ ለመፈታተሽ ቀጠሮ መያዛቸው ይታወቃል። ይህ ጨዋታ ሐምሌ 1/2015 ወይም july 8/2023 በፔንሴልቪንያ ግዛት ቸስተር ፊላዴልፊያ በሚገኘውና 18ሺ 500 ተመልካች የመያዝ አቅም ባለው subaru park ስታዲየም ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለታል።
ዋልያዎቹ 25 ተጫዋቾችና 5 የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ያለው ልዑክ ይዘው ወደ ስፍራው ለመጓዝ ታቅዷል። ለ30 ሰው የጉዞ፣ የሆቴል፣ የልምምድ ሜዳ አቅርቦትና ሌሎች ወጪዎች በሙሉ በአዘጋጁ ይሸፈናል ተብሏል። ዋልያዎቹ አሜሪካ ሲደርሱ 5ሺ ዶላር እንደሚያገኙም የተጠቆመ ሲሆን የስታዲየሙ ሙሉ ገቢ ግን የአዘጋጁ ሲጂኤ ኒውማን ኮርትኒ ይሆናል። ፌዴሬሽኑ ከ30 በላይ ልዑክ ይዞ የሚሄድ ከሆነ ግን ተጨማሪውን ወጪ ራሱ ይችላል።
ይህ እቅድ ግን እንቅፋት ሳይገጥመው እንዳልቀረ መረጃዎች ወጥተዋል። ይህም በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለዋልያዎቹ የቪዛ ቀጠሮ የሰጣቸው ለጨዋታው ከተያዘው ዕለት ከሁለት ቀን በኋላ መሆኑ ነው። ፌዴሬሽኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ቀጠሮውን ለማሳጠር ጥረት ማድረግ ከጀመረ የሰነበተ ሲሆን፣ የኤምባሲው ምላሽ እየተጠበቀም ይገኛል። ነገር ግን መልስ አልተገኘም። በዚህም የስቴድየም መግቢያ ትኬት ሽያጭ እንዲቆም አድርጓል። ቦታውና ቀኑ እንዲለወጥ የሚደረገው ግፊት መጨመሩን ተከትሎም የአዘጋጁ ምላሽ እየተጠበቀ ነው። በመሆኑም የዋልያውና የወርቃማ ጃጉዋሮቹ የአሜሪካ የወዳጅነት ጨዋታ በተያዘለት ቀንና ቦታ የመካሄዱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል። በሁለቱ ፌዴሬሽኖችም ሆነ በአዘጋጁ በኩል ግን ስለጨዋታው ቀን መቀየር ወይም መሰረዝ በይፋ የተገለፀ ማረጋገጫ የለም።
ከቪዛው ጉዳይ በተጨማሪ ጨዋታው የሚካሄድበት ቀንና ቦታም ቅሬታ መፍጠሩ ተሰምቷል። ጨዋታው የሚከናወንበት ቀን ሐምሌ 1 ወይም july 8 የሰሜን አሜሪካ የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል በቴክሳስ ዳላስ የሚጠናቀቅበት ዕለት ነው፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊም በዚህ ዝግጅት ላይ ይታደማል፤ የወዳጅነት ጨዋታው በዚህ ቀን መሆኑ ቅሬታን የፈጠረውም በዚህ የተነሳ ነው። በተመሳሳይ ጨዋታው የሚደረግበት ቦታ ፊላዴልፊያም ለምን እንደተመረጠ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በዲሲ፣ ሜሪላንድና ቨርጂኒያ ይኖራል፤ ከእነዚህ አካባቢዎች ፊላዴልፊያ ከሁለት ተኩል እስከ ሦስት ሰዓት የመኪና መንገድ ይፈጃል፤ ይህም ጨዋታው የሚካሄድበት ቀንና ቦታው ወጣ ማለቱ በብዙዎች እንዳይወደድ አድርጎታል።
የስፖርት አፍቃሪው ጥያቄ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች፤ የጨዋታው ዋና አላማ ወዳጅነትና አንድነትን ለማጠንከር እንዲሁም በአሜሪካ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በብዛት ለማግኘት በመሆኑ ብሔራዊ ቡድኑም በአገሩ ደጋፊ መታጀብ እንዳለበት ስለሚታመን ቅሬታውን ተቀብለዋል። ለአዘጋጁም አማራጭ መፍትሄ ካለ በይፋዊ ደብዳቤ ማሳወቃቸው ታውቋል። በዚህም ጨዋታው የሚካሄድበት ቀንና ቦታ የመቀየር ዕድሉ ሰፊ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ጉያና በእግር ኳስ ቀርቶ በሌላም ጉዳይ ስሟ ሲጠራ የሚያውቁ ጥቂቶች ናቸው። ይህም የዋልያዎቹን ክብር ዝቅ ያደርጋል ተብሎ ገና ከጅምሩ ተቃውሞ እንደገጠመው ይታወቃል። ጉያና በደቡብ አሜሪካ አህጉር የምትገኝ በሰሜን በኩል በአትላንቲክ ውቂያኖስ፣ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ በብራዚል፣ በምዕራብ በቬኑዚዌላ እንዲሁም በምሥራቅ በስሪናም የተከበበች 800ሺ ሕዝብ ያላት አገር ነች። አገሪቱ በደቡብ አሜሪካ ብትገኝም የእግርኳስ ተሳትፎዋ ግን በሌላ አህጉር ነው፤ የሰሜን አሜሪካና ካሪቢያን አገራት የእግርኳስ ማህበር አባል ነች። ብሔራዊ ቡድኗ «ወርቃማው ጃጉዋር» የሚል ቅፅል ስም ያለው ሲሆን፤ በ2019 በኮንካፍ ጎልደን ካፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፋ ነበር። አሁንም ማጣሪያ ላይ ትገኛለች። በወቅቱ የፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ 170ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ዋልያዎቹ ደግሞ 142ኛ ላይ ይገኛሉ።
የትሪንዳድ ዜጋ በሆኑት የ59 አመቱ ጀማል ሳባዝ ዋና አሰልጣኝነት የሚመራው የጉያና ብሔራዊ ቡድን በእንግሊዝ ፕሮፌሽናል ያልሆኑ ሊጎች የሚጫወቱ ስምንት ተጫዋቾች ያካተተ ነው። ዘጠኝ ያህል ደግሞ በአገር ውስጥ ሊግ ይጫወታሉ። የብሔራዊ ቡድኑ የቅርብ ጨዋታ ከሞንትስራት ጋር የነበር ሲሆን 0-0 በሆነ ውጤት ነበር የተለያየው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2015