በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሴቶች እግር ኳስ የአፍሪካ ዞን የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ ከቻድ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን (ሊሲዎቹ) ዝግጅታቸውን ቀደም ብለው በአዲስ አበባ ያደርጋሉ፡፡ ለዚህም እንዲረዳው ዋናው አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል።
የ2024 የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ አስተናጋጅነት ሊካሄድ የአንድ ዓመት እድሜ ብቻ ቀርቶታል። ትልቁ የዓለም የስፖርት ድግስ በሁለቱም ፆታዎች ከ40 በላይ ስፖርቶችን አካቶ የሚካሄድ ሲሆን በርካታ ስፖርተኞችን በማሳተፍ ግንባር ቀደሙ መድረክ ነው፡፡ ለዚህም ከአዘጋጅ ሀገር ቅድመ ዝግጅትና ሽር ጉድ ጎን ለጎን በመድረኩ የሚሳተፉት ስፖርተኞችና አገራት የሚለዩባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ከወዲሁ ይካሄዳሉ። በመሆኑም በተለያዩ የስፖርት ዲሲፒሊኖች ማጣሪያዎች በቅርቡ የሚካሄዱ ይሆናል።
አገራት እንደየደረጃቸው ማጣሪያ ከሚያካሄዱባቸው ስፖርቶች ውስጥ እግር ኳስ አንዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በሴቶች እግር ኳስ በኦሊምፒክ ለመሳተፍ በአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች፡፡ የአፍሪካ ሴቶች የእግር ኳስ ማጣሪያ ውድድሩ አራት ዙሮች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ከሐምሌ 3-11 2015 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) የመጀመሪያ ዙር የማጠሪያ ጨዋታቸውን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከቻድ አቻው ጋር የሚያደርጉ ይሆናል። ሉሲዎቹ በዓለም አገራት የእግር ኳስ ደረጃ ከዓለም 125 ደረጃን ይዘው ሲገኙ ተጋጣሚያቸው ቻድ በበኩሏ በዓለም የእግር ኳስ ደረጃ ካልተሰጣቸው አገራት ተርታ ትመደባለች። የሁለቱ አገራት አሸናፊ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያውን ከናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያከናውን ይሆናል፡፡
በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመሩት ሉሲዎች የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታቸውን በተሻለ ብቃት ለማለፍ ጠንካራ ዝግጅትን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። በአፍሪካ ጥሩ እግር ኳስን ይጫወታሉ ከሚባሉት ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ተጠቃሽ የሆኑት ሉሲዎቹ፣ ለተሻለ ዝግጅትና ውጤት ወጣትና ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች በማካተት ዝግጅታቸውን ከዛሬ ይጀምራሉ። ተጫዋቾቹ ትናንት በአዲስ አበባ ጁፒተር ሆቴል ሪፖርት በማድረግ ልምምዳቸውን እንዲጀምሩም ተነግሯቸዋል።
አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ለሉሲዎቹ ጥሪ ሲያቀርቡ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮኑ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከበረኛ እስከ አጥቂ ብዙ ተጫዋቾችን በማስመረጥ ቀዳሚ ሆኗል። በአጠቃላይ ስምንት ተጫዋቾችን ማስመረጡም ታውቋል፡፡ መቻልና ሀዋሳ ከተማ እያንዳንዳቸው አምስት አምስት ተጫዋች በማስመረጥ ይከተላሉ፡፡
ብሔራዊ ቡድኑ አራት ግብ ጠባቂዎችን ያካተተ ሲሆን( ታሪኳ በርገና፣ ፍሬወይኒ ገብሩ፣ ቤተልሔም ዮሐንስና ፅዮን ግርማን) ጥሪ የተደረገላቸው ግብ ጠባቂዎች ሆነዋል። በተከላካይ ስፍራ በርካታ ተጫዋቾች ጥሪ የተደረገላቸው ሲሆን (ብዙአየሁ ታደሰ፣ ናርዶስ ጌትነት፣ ቤተልሔም በቀለ፣ ነፃነት ፀጋዬ፣ ቅድስት ዘለቀ፣ መንደሪን ክንድይሁን፣ ብዙአየሁ አበራ፣ ኤልሳቤት ታምሩ፣ ደመቀች ዳንኤል፣ ትዕግሥት ኃይሌና ድርሻዬ መንዛን) በቡድኑ ተካተዋል።
በአማካይ ስፍራ ዘጠኝ ተጫዋቾችን ያካተተው ጥሪ (ንቦኝ የን፣ መሳይ ተመስገን፣ መዓድን ሳህሉ፣ ፅዮን ፈየራ፣ ሕይወት ዳንጊሶ፣ ንግስት ኃይሉ፣ ራኬብ ዓለማየሁና ንጋት ጌታቸውን) አካቷል፡፡ የአጥቂ ክፍሉ ከተከላካይ ክፍሉ በመቀጠል ብዙ ተጫዋቾች የተካተቱበት ሲሆን አስር ተጫዋቾችን ይዟል፡፡ (ሎዛ አበራ፣አረጋሽ ካልሳ፣ አርያት ኦዶንግ፣ ረድኤት አስረሳኸኝ፣ ቱሪስት ለማ፣ ማርታ ወልዴ፣ ዓለሚቱ ድሪባ፣ ንግስት በቀለ፣ በሬዱ በቀለና እና ሴናፍ ዋቁማ) ጥሪ የተደረገላቸው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ሉሲዎቹ በሁሉም የሜዳ ክፍል ጠንካራና ልምድ ያላቸው ኮከቦችን ያሰባሰቡ ሲሆን የቅድመ ማጣሪያውን የደርሶ መልስ ጨዋታ የማለፍ ግምትም አግኝተዋል። በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ከ5 ጊዜ በላይ የኮከብ ግብ አግቢነቱን መድረክ መቆጣጠር የቻለችውና በብሔራዊ ቡድኑም ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት ሎዛ አበራን ጨምሮ አረጋሽ ካሳ፣ ሴናፍ ዋቁማ፣ አርያት ኦዶንግ፣ ቱሪስት ለማና ታሪኳ በርገና ያላቸውን የዳበረ ልምድ ተጠቅመው ለብሔራዊ ቡድኑ ውጤት የጎላ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2015